ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚያስችላትን ተጨማሪ ፕሮቶኮል ፈረመች

ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለማንኛውም አይነት ሰላማዊ አገልግሎቶች ለመጠቀም የሚያስችላትን “የተጨማሪ ፕሮቶኮል” ስምምነት ተፈራርማለች፡፡

በኦስትሪያ ቪዬና በመካሄድ ላይ ባለው 63ኛው የአለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጄንሲ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ከኤጄንሲው ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ኮርኔል ጋር ስምምነቱን ፈርመዋል።

ስምምነቱ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ፕሮግራሞቿን ሁሉ በግልፀኝነት ለማከናውን ፈቃደኝነቷን ያረጋገጠችበት መሆኑም ነው የተገለፀው።

ይህ ፕሮቶኮል ሀገሪቱ ከዚህ በፊት የፈረመቻቸውን ሌሎች ስምምነቶች ለማጠናከር በኤጄንሲው የወጣ ተጨማሪ የግልፀኝነት ግዴታዎችን የሚያስቀምጥ ነውም ተብሏል።

ሚኒስትሩ ሀገራቸው ኒውክለርን በተለይም ለጤና፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ እና የኤሌክትሪክ ሀይልን ለማመንጨት ጭምር ለመጠቀም ዕቅድ እንዳላትና በዚህ ዘርፍ ኤጄንሲው ከሀገራቸው የሚጠብቀውን ግልፀኝነት ለማረጋገጥ እንዲቻል መንግስት የተጨማሪ ፕሮቶኮል ሰነዱ እንዲፈረም መወሰኑን አስታውቀዋል።

የዘላቂ ዕድገት ግቦችን ያለ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ማሳካት አይቻልም ያሉት ሚንስትሩ ይህም የኒውክለር ቴክኖሎጂንም ያካትታል ብለዋል።

በማናቸውም መንገድ አለማችንን ከኒውክለር ስጋት ለማስወገድ ኤጄንሲው ለሚያወጣቸው ማናቸውም ፕሮቶኮሎች ሀገራቸው ኢትዮጵያ ጠንክራ አንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

የተጨማሪ ፕሮቶኮሉ መፈረም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነቷን የሚያረጋግጥላት ስምምነት ነው። (ምንጭ፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)