እስራኤል በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ጉብኝት ወቅት ቃል የገባቻቸው ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ሊገቡ ነው

እስራኤል በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጉብኝት ወቅት ለመደገፍ ቃል የገባቻቸው ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ሊገቡ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ጀማል በከር ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በእስራኤል በነበራቸው ጉብኝት የእስራኤል መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ቃለ የገባቸው ፕሮጀክቶች ወደ ስራ መግባት በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ነው የመከሩት፡፡

በቴክሎጂ የተደገፈ የዓሳ ሃብት ልማት፤ የበረሃማ ቦታዎች ልማት፤ የበይነ መረብ ደህንነትና ለቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን መፍጠር ላይ ነው እስራኤል ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገባቸው፡፡

እስራኤል በበረሃማ ቦታዎች ልማትና በትንሽ ቦታ ሰፊ የዓሳ እርባታን በማከናወን ሰፊ ልምድ ያላት ሀገር በመሆኗ ሰርቶ ማሳያ በማከናወን ለኢትዮጵያ ለማስረከብ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በሰርቶ ማሳያው መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት የማስፋፋቱን ስራ ይሰራል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከር በቴክኖሎጂ የተደገፈ የስራ እድል ለመፍጠር ኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው የእስራኤል መንግስት ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡