የቶኒ ብሌር ኢንስቲቲዩሽን የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ትግበራ እንደሚደግፍ ገለፀ

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር  ጌታሁን መኩሩያ ከቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ጋር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ትግበራውን መደገፍ በሚችሉበት ዙሪያ መክረዋል።

በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ማዘጋጀቷንና  ከአንድ ወር በኋላ ተጠናቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ዶ/ር ኢንጂነር  ጌታሁን መኩሩያ ተናግረዋል።

ስትራቴጂው የበይነ መረብ ግንኙነትን እስከ ቀበሌና ወረዳ ማድረስ፣ ቀላል የንግድ ስራ አሰራር የቱሪዝም ዘርፉን በቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የዲጂታል እውቀትን ማሳደግ፣  የባሉበት ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ እድል ፈጠራ ላይ የሚያተኩር ነው።

ቶኒ ብሌር ኢንስቲቲዩታቸው ትግበራውን በሰው ሃይልና በገንዘብ እንደሚደግፉ ለሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውን ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ድረ ገፅ ያገኘነው መረጃ  ያመለክታል።

የቶኒ ብሌር ኢንስቲቲዩሽን በተለያዩ የአለም ሀገራት በመዘዋወር የመንግስት ድርጅቶችን በተለያየ መልኩ እገዛ የሚያደርግ ድርጅት ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥም ስራ ፈጠራ ኮሚሽን፣  ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣  አይሲቲ ፓርክ አዋሳ፣  የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት፣  የወጪ ንግድ ላይ በማማከርና ጥናት ማድረግ  እገዛ እያደረገ ነው።