ቻይና ከድምፅ 5 እጥፍ የሚፈጥን ሃይፐርሶኒክ ባሊሲቲክ ሚሳኤል ይፋ አደረገች

የቻይና ህዝብ ኮሙኒስት ሪፐብሊክ 70ኛ የምስረታ በዓልን ለማክበር በተሰናዳው ዝግጅት ላይ የቻይና ጦር እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ይፋ አድርጓል።

ከዚህም ውስጥ ከድምፅ ፍጥነት አምስት እጥፍ በላይ የሚወነጨፍ ሃይፐርሶኒክ የኒዩክሌር ባሊሲቲክ ሚሳኤል ይፋ ሆኗል።

ዲ ኤፍ-17 የተሰኘው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በተሽከርካሪ ላይ ሆኖ ለዕይታ ቀርቧል።

አዲሱ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል በአሜሪካና አጋሮቿ ለስራ ዝግጁ የሆኑ የሚሳኤል መቃወሚያዎችን ዒላማ አልፍ ጥቃት ማድረስ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ቻይና በ30 ደቂቃ ውስጥ አሜሪካ መድረስ የሚችሉ ሚሳኤሎችንም አሳይታለች።

አንዳንድ ተንታኞች የቻይናን ወታደራዊ ትርዒት ለአካባቢው ስጋት ነው ብለዋል።

በተለይም በፍጥንታቸው ከፍተኛ የሆኑ መሳሪያዎችን ማሳየቷ ለቀጣናው ወታደራዊ ደህንነት የመከላከልና የማጥቃት ሚዛን ላይ ጫና እንደሚፈጥር ነው ያነሱት።

ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሉ ከመሬት በዝቅተኛ ርቀት ላይ የሚወነጨፍ መሆኑም ጥቃት ለሚከላከሉ ሀገራት የሚሳኤል መቃወሚያዎች ፈታኝ እንደሚሆን ተገምቷል።

ቻይና 70ኛ ዓመት የኮሙኒስት ሪፐብሊክ ሀገርነቷን ያወጀችበትን ዕለት ዛሬ ቤጂንግ በሚገኘው ግዙፉ የቲያንሜን አደባባይ አክብራለች።

በስነስርዓቱም ዲ ኤፍ-41 ከ12 ሺህ እስከ 15 ሺህ ኪሎሜትር የሚወነጨፈው ድንበር ተሻጋሪ ባሊሲቲክ ሚሳኤል ይፋ ሆኗል።

ጄ ኤል-2 ሚሳኤል፣ የተዋጊ መርከብ መቃወሚያ የሆነው ዋይጄ-18 ሚሳኤል በትርዒቱ ቀርበዋል።

እጅግ ዘመናዊ የተባለ የጄቶች እና ሚሳኤሎች አነፍናፊ መሳሪያ እና ኤችኪው-9ቢ የተሰኘ( HQ-9B) የጥቃት ማክሸፊያ መሳሪያም ይፋ ሆኗል።

በወታደራዊ ትርዒቱ ላይ 160 የጦር አውሮፕላኖች፣ 580 ዓይነት የጦር መሳሪያዎች፣ 15 ሺህ ወታደሮች ሰልፍ አድርገዋል። (ምንጭ፡-አልጀዚራ)