የቡና ገለፈትን ወደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያነት የሚቀይረው የምርምር ፕሮጀክት ተመረቀ

የቡና ገለፈትን በስነህይወታዊ ዘዴ ወደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያነት የሚቀይረው የምርምር ፕሮጀክት ተመረቀ፡፡

በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ድጋፍ በደብረ ብረሃን ዩኒቨርሲቲ የተሰራው ምርምሩ በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን 3 ቀበሌዎች ላይ የተካሄደ ነው።

ምርምሩ የአካባቢው ቡና አምራቾች ለማስወገድ ችግር የሆነባቸውን የቡና ገለፈት በትሎች በማስበላት (በስነህይወታዊ ዘዴ) ወደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያነት መቀየር ያስቻለ ነው ተብሏል።

የቡና ገለፈት ቡና የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ለማስወግድ ችግር ሆኖባቸው የቆየ ከመሆኑም ባሻገር መርዛማት ስላለው አካበቢውን ሲበክል የቆየ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ምርምሩን ያካሄዱት ገዛኸኝ ደግፌ (ዶ/ር) ውሃን በመመረዝ በእንስሳት ላይም ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱንና ምርምሩ ይህንን ችግር እንደፈታ ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያውም ለቡና ማዳበሪያነት ጥቅም ላይ ውሎ በአካባቢው አርብቶ አደሮች መወደዱን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ካሳሁን ተስፋየ (ዶ/ር) ኢንስቲቲዩቱ በውጭ የሚከናወኑ 24 ችግር ፈቺ ምርምሮችን እየደገፈ እንደሆነና በቅርቡ 8ቱ ተመርቀው ወደ ትግበራ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

ተቋማቸው ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን መደገፉን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

የደብረ ብረሃን ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የምርምሩን መተግበሪያ ለሲዳማ ዞን አስረክበዋል። ዞኑም ምርምሩን ወደ ተግባር በማውረድ ለበርካቶች የስራ እድል ይፈጥርበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የቡና ገለፈትን ወደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያነት በሚቀይረው በዚህ ምርምር ስልጥነው የተደራጁ የአካበቢው ነዋሪዎችም የተፈጥሮ ማዳበሪያውን በመሸጥ ተጠቃሚ ሆነዋል ነው የተባለው።

የተራቡ ትሎችን ለአሳና ለዶሮ ምግብነት፣ የዶሮ ኩስን በተመሳሳይ ለአሳ ምግብነት በማዋል የተቀናጀ ግብርናንም ያካተተ ነው።

የምርምር ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የስራ ኃላፊዎች፣ የደብረ ብረሃንና የዲላ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የፋብሪካ ተወካዮች እና የአካባቢው አርብቶ አደሮች በተገኙበት ተመርቆ ርክክብ ተደርጓል። (ምንጭ፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)