መልካሙ ታደሰ
እናንተዬ!… ለካስ የሀገሬው ሰው “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ብሎ የተረተው ያለ ነገር አይደለም— ሃቅ ኖሮት እንጂ፡፡ …ይህንንም ደግሞ በሚገባ ያረጋገጥኩት ከሰሞኑ ነበር፤ “አርፍድሃል” የሚለኝ ካለም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡
እስኪ ምን አጋጥሞኝ ይህንን ልላችሁ እንደቻልኩ ላውጋችሁ፡፡ አንድ የካፊቴሪያ በረንዳ ተቀምጩ “ፍትህ” በሚል ስያሜው የሚታወቀውን ጋዜጣ እያነበብኩ ነበር– የመስከረም 19 ቀን 2004 ዓ.ም ዕትሙን፡፡ ከፊት ለፊት ገጹ ላይ ከሰፈሩ ጉዳዮች ጀምሬ ሁለተኛውን ፣ ሦስተኛውን ገጽ…ወዘተ እስከሚታክተኝ ድረስ እያገላበጥኩ ማንበቤን ቀጥያለሁ፡፡ ገጽ አራት ላይ ስደርስ ግን አንድ ነገር ያዝ አደረገኝ፡፡ “አስተያየት” በሚለው ቋሚ ዓምድ ስር የሁለት ሰዎች አስተያየቶች ስፍረዋል፡፡ ሁለቱም ደግሞ “ደበበ እሸቱ” ስለተባለውና በአሁኑ ወቅት በሽብር ተግባር ተጠርጥሮ በህግ ጥላ ስር ስለሚገኘው ግለሰብ የተሰጡ አስተያየቶች ነበሩ፡፡
እዚህ ላይ ቀድሞ ትኩረቴን የሳበው ጉዳይ “እስክንድር ነጋ ስለ ደበበ እሸቱ” በሚል የተቀመጠው አስተያየት ነበር፡፡ ምክንያቴ ደግሞ “እስክንድር ነጋ” የተባለው ግለሰብ በዚህ ዓመት መግቢያ አካባቢ በሽብር ሴራ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውሳለሁ፡፡ እናስ ይህ ሰው በህግ ጥላ ስር ሆኖም፣ የአውቃለሁ ባይነት ፖለቲከኛነቱን አላቆመም እንዴ? የሚለው ጥያቄ በህሊናዬ ውስጥ ቀድሞ በማቃጨሉ ስለ ግለሰቡ ቀድሜ ለማንበብ ከጀልኩ፡፡
አስተያየቱን ሳነብ አንድ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ አባባሉ አዲስ አለመሆኑንና ተጠርጣሪው አቶ እስክንድር በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት እንደ ፃፈውና፤ ጋዜጣውም ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ ያቀረበው መሆኑን ነው፡፡ ግና ጳጉሜ 5 ቀን 2003 ዓ.ም ፃፈው በተባለው በዚህ አስተያየት ውስጥ ያገኘሁት ሃሳብ “ጉድ ሳይሰማ…” አባባልን ትክክለኛነት ያረጋገጠልኝ ነበር፡፡
ነገሩም እንዲህ ነው።… “ብዙዎች የሚስማሙበት የሽብርተኝንት ብያኔ እንደሚለው ብዙውን ጊዜ ሽብርተኛ የሚሆነው በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለ፣ ያላገባ…”ይላል ፅሑፉ። …ይህንን አባባል ደግሜ፣ ደጋግሜ አነበብኩት፡፡ እስክንድር ይህንን ‘ትርጓሜ’ ከየትኛው ‘መዝገበ-ቃላት’ እንዳገኘው ባላውቅም፣ ይህንን ማለቱ ግን ከገሃዱ ዓለም እውነታ ጋር ፍጹም የሚጣረስ አመለካከት እንዳለው ለመገንዘብ ብዙም መመራመር አልጠየቀኝም፡፡… እስኪ አስቡት፤የዓለማችን ቁጥር አንድ አሸባሪ ሆኖ የቆየው ኦሳማ ቢን – ላደንን ለማሳያነት ብናነሳ እንኳን፣ የትኛውን የእስክንድርን የአሸባሪነት መስፈርት ሊያሟላ ይችላል?- በሀገራችን የሽብር ዓላማን አንግበው ሲንቀሳቀሱ የተጋለጡና የተፈረጁት እንደ ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት 7 ያሉት አመራሮችና አባሎቻቸውስ ዕድሜያቸው በ20ዎቹ ውስጥ ስለሆነ ነው ወይስ ላጤዎች?
እስክንድር ከዚህ ይልቅ ቢለው እኔንም ሆነ ሌላውን ሰው ሊያሳምን የሚችለው “በሽብርተኝነት ተግባር ላይ የሚሰማሩ ኃይሎች አስተሳሰባቸው ከ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ካለ ሰው እጅግ ያነሱ ናቸው” የሚል ቢሆን ነበር፡፡ አሊያም “ሽብርተኝነትን የሚደግፉና የሚመሩ ኃይሎች ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን ከጀርባ አድርገው በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶችን ወደ እሳት ይማግዳሉ…ወዘተ” ቢል ነው፡፡
እናም ይህ ግለሰብ ያሰፈረው ነገር “ሽብርተኛ ማን ነው?” አይነቱን ጥያቄ የሚመልስ አይደለም፡፡ ይልቁንም በ1997 ዓ.ም ሦስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ህዝብን ለአመጽና ለብጥብጥ ሲቀሰቅሱና ሲያስተባብሩ ተደርሶባቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉና በምህረት ከእስር ተፈተው ከነበሩት የተቃዋሚ ቡድኖች አባላት መካከል የሆነው ደበበ እሸቱ፣ በግንቦት 7 አሸባሪ ቡድን ውስጥ ተሳታፊ በመሆን ተጠርጥሮ በህግ ጥላ ስር መዋሉ አግባብ አለመሆኑን ጥብቅና ለመቆም ያመጣው መሰረተ – ቢስ ማብራሪያ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ግና በህግ የተያዘ ጉዳይ በእስክንድር አስተያየት የሚላላበት ወይም የሚጠብቅበት ሁኔታ ይኖራል የሚል አንዳች ግምት የለኝም፡፡
የእስከንድር አስተያየት በሚል “ፍትህ” ካሰፈረው ሃሳብ ይበልጥ ያስገረመኝ ደግሞ ፤ፕሮፌሰር አስራት ስለ ተጠርጣሪው ደበበ ያሉት ነገር ነው፡፡ ግለሰቡ በዚህ አስተያየታቸው ቀድመው ሊያነሱ የሞከሩት ከደበበ ጋር ስላላቸው እውቅ ነበር፡፡ ምርጫ 97ን ተከትሎ የጎዳና ላይ አመጽና ብጥብጥ እንዲቀሰቀስ ሲያስተባብሩና ሲመሩ በአደባባይ ተገኝተው በህግ ጥላ ስር ከዋሉት የተቃዋሚ ቡድኖች አንዱ አመራር የነበሩት እኚህ ሰው፤ በቃሊቲ ወህኒ ቤት በታሰሩበት ወቅት ጀምሮ ከደበበ ጋር ስለመሰረቱት ወዳጅነት በዝርዝር ያሰፈሩ ከመሆኑም ባሻገር፤ ስለ ግለሰቡ የግል ባህሪ ያሰቡትን ሊሉም ሞክረዋል፡፡ በተጨማሪም ለሰውየው ያላቸውን አድናቆት፣ ግለሰቡም ከእርሳቸው የሚያደርገውን ውለታ ተንትነው ነበር፡፡
…ፕሮፌሰሩ በሰጡት አስተያየት ግራ መጋባት የጀመርኩት ገና ከመግቢያው ጀምሮ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ከደበበ እሸቱ ጋር በቃሊቲ ወህኒ ቤት ውስጥ የመሰረቱት ወዳጅነት አቶ እሸቱ በሽብርተኝነት እንዳይጠረጠር የሚያደርገው መሰረት ምን ሊሆን እንደሚችል ገና አስተያየታቸውን ማንበብ ስጀምር፤ በአእምሮዬ የቋጠርኩትን ጥያቄ እያብሰለሰልኩ ከዓረፍተ ነገር ዓረፍተ ነገር፣ ከአንቀጽ አንቀጽ ብሸጋገርም ምንም ዓይነት ማሳመኛ ግን አልነበራቸውም፡፡ ታዲያ ፕሮፌሰሩ ስለምን የባጥ የቆጡን መዘላመድ አስፈለጋቸው?
እኚህ ሰው ከተጠርጣሪው ደበበ ከእሳቸው ጋር የሚግባቡ ስለሁኑ በሽብርተኝነት ከመጠርጠር የሚታደጉት መስሎ ከታያቸው እጅግ ተሳስተዋል፡፡ ደበበ ከማንም ጋር ሺህ ጊዜ ሊግባባ የሚችል እንዲሁም የፕሮፌሰሩና መሰሎቻቸው ጉዳይ አስፈጻሚ ቢሆን ወዘተም. ከመጠርጠር ነጻ ሊያወጣው የሚችል አይመስለኝም፡፡ ፕሮፌሰሩ አርቆ ማስተዋል ተስኗቸው እንጂ፣ ከሌሎች ጋር በቀላሉ መቀራረብና መግባባት መቻል ከሽብርተኝነት መጽዳት ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜም እኮ ለእንዲህ ዓይነቱ እኩይ ተልዕኮ ይህን መሰሉን ስብእና ያለው ሰው ይፈለጋል። እርሳቸው ግን አስበውት ይሆን?
ፕሮፌሰሩ ግራ ተጋብተው ሌላውን ግራ ለማጋባት ካላሰቡ በስተቀር፤ የእርሳቸው አድናቆት ግለሰቡን ከተጠርጣሪነት የሚያድን አይመስለኝም፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ እርሳቸው ደበበን የሚያደንቁትን ያህል ሌሎች በርከት ያሉ ሰዎችም ሳያደንቁት ቀርተው አይደለም– ምናልባት የእርስዋና የሌሎች አድናቆት መነሻው የተለያየ ሊሆን ይችል ይሆናል እንጂ፡፡
ብዙዎቻችን ደበበን በአርቲስትነቱ እናውቀዋለን ፡፡ ለበርካታ ዓመታት በኪነ – ጥበብ ሙያ ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል፡፡ በዚህ ሙያውም በርከት ያሉ አድናቂዎችን ሊያፈራ እንደሚችል ለመገመት አይከብድም፡፡ ይህ በአንድ ወቅት የተመሰረተ አድናቆት ግን ዘለአለማዊ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ደግሞ ደበበን በኪነ – ጥበባዊ ስራዎቹ ያውቁትና ያደንቁት የነበሩ በርከት ያሉ ሰዎች፤ በምርጫ 97 ሰሞን ፖለቲካ አውቃለሁ ብሎ ሲዘላብድ ባዩት ጊዜ “አይንህን ላፈር” ያሉበት አጋጣሚ መጥቀስ በቂ ይመስለኛል፡፡
ታዲያ ደበበ በነበረው ሙያ አድናቂዎች የነበሩት በመሆኑ ብቻ በሽብር ተግባር ላይ ላለመሰማራቱ ማረጋገጫ ሊሆን ይችላልን? በተለያዩ ቴአትር ቤቶች፣ መድረኮች ወዘተ. ማገልገለሉስ ለዛሬ ማንነቱ ህያው ምስክር ይሆናልን?– እርግጠኛ ሆኜ ልናገር የምችለው ዛሬ ፕሮፌሰር መስፍን ደበበን ሊያደንቁት ፣ ሊክቡት…ወዘተይችላሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ ስለሌላው የኢትዩጵያ ህዝብ ለመናገር መሞከራቸው ግን ከድፍረት ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡
ፕሮፌሰር ሆይ፣ እርግጥ ደበበን “አደንቀዋለሁ” አልያም “ጥሩ ሰው ነው” ብለው መናገርዎ ለራስዎ ስህተት ላይሆን ይችላል፡፡ ደበበ ለእርስዎም ሆነ ለቤተሰብዎ “መልካም ሰው ነው” ቢሉም አልተሳሳቱም፡፡ ነገሩ “ዘመድ ከዘመዱ…” መሆኑስ መች ቀረ?! ለማናችንም ግልጽ ይሆናል ብዬ የማስበው ነገር ቢኖር ግን፤ ደበበ ከእርስዎ ጋር ያለው ቅርርብ በቤተሰብአዊነት ላይ ብቻ የታጠረ አይደለም፡፡ ለአንድ ፖለቲካዊ አላማም በጋራ ተንቀሳቅሳችሁ እንደ ነበር ማንም የሚያውቀው ሃቅ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ወቅት የእርስዎ ፓርቲ ህገ – መንግስቱ ከሚፈቅደው ሰላማዊ የምርጫ ውድድር አፈንግጦ በመውጣት በህዝቡ ውስጥ አመጽና ብጥብጥ ለመቀስቀስ ነበር ጥረት ያደረገው፡፡ ይህ በኃይል ህገ-መንግስቱንና ህገ – መንግስታዊ ሥርዓቱን ለመናድ ያደረጋችሁት ጥረትም ከባድ ወንጀል በመሆኑ በህግ እንድትጠየቁ የተደረገበት አግባብ መፈጠሩን ያስታውሳሉ፡፡
በዚህም ወቅት ደበበ ከእርስዎ ጋር ተመሳሳይ አጀንዳ አንግበው ለጥፋት ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር ከዋሉ መሰሎችዎ መካከል የሚገኝ ነበር፡፡ “ደበበን የተዋወቅኩት በ1998 ዓ.ም በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ነው” ብለው ቢክዱም ማለቴ ነው፡፡ ወንጀለኛ መሆናችሁን አምናችሁ የእስር ውሳኔ በተላለፈባችሁ ወቅትም ቢሆን፤ ይህ ሰው ከእርዎ አጠገብ ነበር– ከዚያም በኋላም ቢሆን፡፡
ታዲያ በዚህ መልኩ ለጥፋት አብራችሁ ስታሴሩ ለነበራችሁ ሰዎች አንዳችሁ ሌላውን “አደንቀዋለሁ” አልያም “ጥሩ ሰው ነው” እያላችሁ ብትሞካከሹ ምን ይደንቅ ይሆን? –ስለ ደበበ “ሠላማዊነት” ሸንጥዎን ገትረው ሊመሰክሩ መሞከርዎ እንጂ፡፡… ግና እርስዎ ማን ሆኑና ነው ስለ ተጠርጣሪው ሠላማዊ መሆን አልያም አለመሆን ከህግ ቀድመው ሊመሰክሩ የደፈሩት?– ከገባዎት እርስዎ ከሌላው ዜጋ የሚለዩበት ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም የህግ ተገዢ እንጂ የበላይ ባለመሆንዎ ነው፡፡ እናም ከህግ ቀድመው “እገሌን አውቀዋለሁ…አደንቀዋለሁ…ስለዚህም ወንጀል ሊፈፅም የማይችል ንፁህ ሰው ነው” እያሉ ፍርድ መስጠት አይችሉም፡፡ ደበበ ተጠርጥሮ በህግ ጥላ ስር የዋለበትን ምክንያት የማጣራት፣ “ነጻ ነው ወይም ወንጀለኛ” ብሎ ውሳኔ የመስጠት ህገ – መንግስታዊ ስልጣን ያለው የህግ አካል ስላለ፤ ከህግ የበላይ ለመሆን የሚያደርጉትን ጥረት ተገቢነት የጎደለው መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
ከፕሮፌሰሩ አስተያየት የገረመኝ ሌላው ጉዳይ “ደበበ በ60ዎች ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኝ፣ በጀርባ ህመም የሚሰቃይ…” እያሉ የደሰኮሩት ነገር ነው፡፡ ምክንያቴ ግን ይህን ለምን አሉ የሚለው አይደለም– በአንድ ሳንባ የመተንፈሳቸው ጉዳይ፣ እንደበቀቀን አንዱ ያለውን ሌላው የማስተጋባቱ ሁኔታ አስገርሞኝ እንጂ፡፡
ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ስለ ደበበ ”ነፃ” መሆን ከህግ ቀድመው ብያኔ ለመስጠት ከደፈሩት ግለሰቦች አንዱ በአሁኑ ወቅት በሽብርተኝነት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የሚገኘው እስክንድር ነጋ ነው፡፡ ይህ ሰው ስለ ደበበ “ንፁህነት” ማረጋገጫ ብሎ ካሰፈራቸው ሃሳቦቹ ዋነኛው ደግሞ ግለሰቡ ዕድሜው የገፋ፣ በጀርባ ህመም እየተሰቃየ ያለ መሆኑን ወዘተ. ነው፡፡ ታዲያ የዚህ አስተያየት ሰጪ አስቂኝ ሃሳብ ገርሞኝ ሳያበቃ ፕሮፌሰሩም ያንኑ ደግመውት እርፍ አሉ፡፡
ይህ ፕሮፌሰሩ የደገሙትን ሃሳብ በሦስት መልኩ ልንገነዘበው የምንችል ይመስለኛል። አንደኛው እነዚህ ዘወትር ለህዝብና ለሀገር ውድቀት ሲማስኑ የኖሩ የጭፍን ፖለቲካ አራማጆች የሚያስቡትና የሚናገሩት ሁሉ ተመሳሳይ መሆኑ ነው። በእስክንድር አስተያየት ውስጥ የታጨቁ አባባሎች (አሳማኝ ባይሆኑም) በፕሮፌሰሩ መደገማቸው በእነዚህ ሰዎች መካከል ያለውን የጠበቀ ቁርኝት ያመለክታል። ይህ ደግሞ ተቃዋሚ ኃይሎች በተደጋጋሚ ስሀተት ሰርተው ትርፋቸው ውርደትና ከህዝብ መገለል ቢሆንም ግና፤ ዛሬም ከስህተታቸው አለመማራቸውን በቀላሉ የሚያስገነዝበን ይመስለኛል።
ሁለተኛው ጉዳይ እነዚህ ወገኖች ስለሽብትኝነት የሚያውቁት የተሻለ ነገር የሌለ መሆኑን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዛሬ ሸብርተኝነት በዓለማችን ሠላምና ፀጥታ ላይ ትልቅ እንቅፋት የሆነበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ግና የዚህ ተዋንያን ሆነው የሚገኙት ግለሰቦች ዕድሜያቸው በ20ዎቹ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው ብለን ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉን አይደሉም– በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሰው በሽብርተኝነት ተግባር ውስጥ ሊሰማራ እንደሚችል በተግባር የታየ ሃቅ ነውና፡፡ ህሊና እንጂ ዕድሜ ሰውን ከዚህ አስነዋሪ ድርጊት ሊያርቀው አይችልም፡፡
በሀገራችንም ሲስተዋሉ የነበሩ የሽብር እንቅስቃሴዎችም ቢሆኑ ዕድሜያቸው ጠና ባሉ ሰዎች ሲመሩና ሲደራጁ የተስተዋሉ መሆናቸው የሚታበል ጉዳይ አይደለም፡፡ ምን አልባትም ለዓላማቸው ማራመጃነት በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙትን በገንዘብና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች አታለው ሊጠቀሙባቸው ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን እነዚህን መሰል ወጣቶች ቀድሞውን የሽብር ድርጊቱ አቀናባሪዎች ናቸው ማለት አይደለም። ዓላማውን ደግፈው ለመፈጸም የሚነሱ ሳይሆኑ ጊዜያዊ ችግሮቻቸውን ለመሸፈን በጥቅም ተታለው እንደሆነ ለሽብር ተግባር ሲንቀሳቀሱ እጅ ከፈንጅ የተያዙ ግለሰቦች የመሰከሩት ጉዳይ ነው፡፡ እናም የደበበ በሽብርተኝነት መጠርጠርን በዚህ መልኩ ለመከላከል የሚቻል አይሆንም፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ፕሮፌሰሩም ሆኑ ሌሎች “የደበበ ዕድሜ በመግፋቱ.. ወዘተ ተጠርጣሪ አያደርጋቸውም” እያሉ የሚቀላቀምዱ ግለሰቦች ለወጣቱ ትውልድ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት ያመላክታል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ሰው ከተጠርጣሪነት ነፃ ለማድረግ ሽብርተኝነትን ከወጣትነት ጋር አቆራኝተው አስተያየት በመስጠታቸው ነው፡፡ ስለሆነም በእኔ እምነት እነዚህ ሰዎች ምክንያታዊ ሳይሆኑ ወጣቱና ከመሬት ተነስተው እየወነጀሉት ያሉ ናቸው፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ የተሳሳተ መሆኑን ፕሮፌሰሩም ሆኑ ቢጤዎቻቸው ልብ ሌሉት የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡
ፕሮፌሰሩ በዚሁ አስተያየታቸው ላይ ያሉት ሌላም ጉዳይ ነበር፡፡ “ደበበ ጠብን፣ ጥላቻን፣ ስቃይን፣ ህመምን የሚጠላ ሰው ነው፡፡ ለእኔ አሸባሪ ማለት የሞት አጋፋሪ ነው፡፡ ይህንን ደበበ እሸቱን የሚያሳዝነውንና የሚያስለቅሰውን፣ የሚዘገንነውንና የሚጠላውን ነገር አውቆ በድፍረት፣ ሳያውቅ በስህተት ይገባበታል ብዬ በጭራሽ አላስብም” ብለዋል፡፡ ሰውዬው እውነታቸውን ይሁን እየቀላመዱ?…
እስኪ ይህን የፕሮፌሰሩን አባባል ዘርዘር አድርጌ ለማስቀመጥ ልሞክር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ግለሰቡ “ደበበ ጠብን፣ ጥላቻን፣ ስቃይን … የሚጠላ” ብለው ገልፀውታል፡፡ እዚህ ላይ ግን ፕሮፌሰሩ የማስታወስ አቅማቸው እጅግ እየተዳከመ መምጣቱን ለመገንዘብ የሚዳግት አልመሰለኝም፡፡ ምክንያቱም ደበበ በእርግጠኝነት ጠብን፣ ጥላቻን፣ ወዘተን. የሚጠላ ሰው ቢሆን ኖሮ፤ በምርጫ 97 ጋር ተያይዞ በነበረው የሁከት ሁኔታ እጁን አያስገባም ነበር፡፡ በወቅቱ ደበበም ሆነ መሰሎቹ ከእርቅ ይልቅ ጠብን፣ ከመፋቀር ይልቅ ጥላቻን፣…ወዘተን አንግበው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ህዝብን ለሁከትና ለትርምስ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ሊቀሰቅሱት የነበረው ለሠላምና ለፍቅር እንዳልሆነ ከማናችንም ህሊና የተፋቀ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ደበበ ጠብን፣ ጥላቻን፣ ወዘተ. የሚጠላ እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያል፡፡
ፕሮፌሰሩ ይህንን በድፍረት ያሉት ስለ ደበበ ማንነት ጠፍቷቸው ነው የሚል ግምት የለኝም።ምክንያቱም ከማናችንም ይልቅ ስለ ደበበ ጓዳ ጎድጓዳ ጠንቅቀው እንደሚያውቁት ነግረውናልና፡፡ ግና ይህንን ሲሉ እያዘናጉን አልያም ራሳቸው እየዘነጉ መሆኑን መገንዘብ አይከብድም፡፡
በሌላም በኩል ደግሞ “ደበበ ህመምን የሚጠላ” እንደሆነ የገለፁት ለምን እንደሆነ ባይገባኝም፤ ግና ፕሮፌሰሩ እየቃዡ ለመሆናቸው መገመት አይከብድም፡፡ ምክንያቱም ሠላማዊም ሆነ አሸባሪ ግለሰብ ህመምን የሚወድ የለም፡፡ ታዲያ የደበበ ህመምን መጥላት እንዴት በሽብርተኝነት እንዳይጠረጠር ሊያደርገው ይችላል?
እዚህ ላይ ፕሮፌሰሩ “ለእኔ አሸባሪ ማለት የሞት አጋፋሪ ነው” ማለትዎን ከምንም በላይ የምደግፈው ነው፡፡ ግን እውነት ፕሮፌሰር አባባሉን ከልብ ያምኑበታል?–እኔ እንጃ።እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሚያምኑበት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም እርስዎም ሆኑ ከእርስዎ ጋር በአንድ ሳንባ የሚተነፍሱት ጀሌዎቻችሁ ይህንን መሰሉን አስተሳሰብ አምርራችሁ እንደምትቃወሙ ስለማውቅ ነው፡፡ ከእርስዎ አጠገብ ተሰልፈው በጎደና ላይ ነውጥ ህገ – መንግስቱን በኃይል ለመናድ ሲፍጨረጨሩ የነበሩ ሰዎች፤ ዛሬ ጭልጥ ወዳለ የአሸባሪነት ጎራ መቀላቀላቸውን እንዴት ተዘንግቶዎት ይሆን?– ‘ግንቦት 7’ በሚል ስያሜ ራሱን በመጥራት የሚንቀሳቀሰው አሸባሪ ቡድን እኮ ትናንት ከእርስዎ አጠገብ የተሰለፈ ቡድን ነበር። እናስ ይህንን እያወቁ “…የሞት አጋፋሪ” እያሉ መደስኮርዎ ምን ይሉት ቅጥፈት ይሆን? ፕሮፌሰር ሆይ፣ በቃላት ጨዋታ ሊያታልሉን እየሞከሩ ከሆነ እጅግ መሳሳትዎን ልነግርዎት እወዳለሁ፡፡
በመጨረሻም “ደበበ እሸቱ የሚያሳዝነውንና የሚያስለቅሰውን፣ የሚዘገንነውንና የሚጠላውን ነገር አውቆ በድፍረት፣ ሳያውቅ በስህተት ይገባብታል ብዬ በጭራሽ አላስብም” ማለትዎ ከራስዎ አልፈው “ስለሌላው አውቃለሁ” ባይነትዎ የሚመነጭ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ለምን ቢሉ፤ እርስዎ ሊናገሩና ሊመሰክሩ የሚችሉት ስለራስዎ ብቻ ነው–ለዚያውም እውነት የመናገር ልምድ ካለዎት። ምናልባት “ጠንቋይ ልሁን” እያሉን ካልሆነ በስተቀር ደበበ በስህተትም ይሁን በድፍረት በእንደዚህ ዓይነቱ ተግባር ላይ ይሳተፍ አልያም አይሳተፍ፤ መርምሮ ትክክለኛ ውሳኔ ማሳለፍ የሚችለው ፍርድ ቤት ብቻ ነው። እናም ስለ ደበበ እውነተኛ ማንነት ህግ መርምሮ የሚያሳውቀን መሆኑን ተገንዝበው፣ ስለሌላው ከመፈትፈት ቢታቀቡ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ደግሞስ ደበበ “የሽብር ተግባር የሚያስለቅሰው…” ምናምን ማለትዎ ምን ለማለት ፈልገው ይሆን? “ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ” የሚለውን ሀገራዊ ብሂልን ዘንግተውት ይሆን እንዴ?– ለምን መሰልዎት፤ በዚህች ሀገር ተደጋጋሚ የሽብር ተግባር ሲፈፀም፣ ንጹሃን በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸውን ሲያጡ፣ ሌላው ሲያነባ… ባለበት ወቅት ሁሉ፣ እርስዎና መሰልዎችዎ ግን በአደባባይ በደስታ ሲፈነጥዙ ነው ያስተዋልናችሁ፡፡ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪዎች እየደረሰ ያለውን ጥፋት ለመከላከል የሚያስችል ህግ ባጸደቀ ጊዜ አምርራችሁ የተቃወማችሁትስ ለምን ሆነና ? –አሜሪካና አውሮፓ ሆነው በህዝብ ላይ ሽብርን የሚያሴሩና የሚመሩ “አጋሮቻችሁ” መፈናፈኛ እንዳያጡ ሰግታችሁም አይደል?! እናም ከእነዚህ አሸባሪዎች ጋር እጅና ጓንት የነበረን ሰው “ሽብርተኝነት የሚያስለቅሰው…” እያሉ ሽፋን ለመስጠት መሞከር ማንን የሚያሞኝ ይመስልዎታል?…
ፕሮፌሰር ሆይ! እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎ፡፡ “ደበበ እሸቱ በሽብር ተግባር ውስጥ አይሰማራም” ብለው ከህግ ቀድመው ፍርድ ሰጥተዋል፡፡ ግን ይህንን ያህል ደፋር አስተያየት ሰጪ ሆነው ሳለ፤ ለምንድነው “ደበበ ከህግ ተሰውሮ የቆየው?” ብለው አንድ ቃል እንኳን ለመተንፈስ ያልሞከሩት? …አዎ! “ደበበን በቅርበት አውቀዋለሁ፣ ንጹህ ሰው ነው… ወዘተ.” እያሉን “ሰውየው ለምን ከህግ ተሸሸጎ ቆየ?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ያጣሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
በእርግጥ እርስዎ በህግ የሚያምኑ እንዳልሆኑ በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይን ጣልቃ በመግባት ማረጋገጥዎን አውቃለሁ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን፤ ማንም ሰው ከህግ በላይ አለመሆኑን ሊያውቁ ይገባል፡፡ ታዲያ በንጽህናው የሚተማመን ሰው ከመሬት ተነስቶ ለመሰወር ይሞክራል ብዬ አልገምትም፡፡ ስለዚህ “ይህ ሰው ነጻ ነው “ እያሉ ባለበት ወቅት “ይህንን ንጽህናውን እያወቀ ለምን ከህግ ለመሰወር ሞከረ?” የሚለውን ምክንያትም አብረው ሊነግሩን በተገባ ነበር፡፡ ዳሩ ግን “ምን ያለበት ዝላይ አይችልም” ብለን እንዳናማው ከሌላው ይልቅ ቀድመው ሊያሳውቁን የሚባዎት ይህን ሆኖ ሳለ፤ እርስዎ ግን “እወደዋለሁ፣ አደንቀዋለሁ” እያሉ በተራ ነገር ሊሸነግሉን ሞከሩ፤ በዚህ ዕድሜዎ ቀጣፊ መሆንዎ እጅግ ያሳዝናል!
ለማንኛውም አንድ ጠቃሚ ነገር ላክልና ሃሳቤን ልቋጭ። ደበበ እሸቱ በአሸባሪነት ተጠርጥሮ ነው በህግ ጥላ ስር ሊውል የቻለው፡፡ ይህን የተጠረጠረበትን ወንጀል የማጣራትና ተገቢውን ውሳኔ የመስጠት ህጋዊ መብት ያላቸው ደግሞ ፕሮፌሰር ምስፍን አይደሉም። ህገ – መንግስታዊ ስልጣን የተሰጠው የፍትህ አካል አለ፡፡ እናም ፕሮፌሰሩም ሆኑ ሌሎቻችን የደበበን ንጹህነት አልያም ጥፋተኛነት ከፍርድ ቤት ብቻ ሰምተን የምናረጋግጠው ይሆናል፡፡
ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ፕሮፌሰርም ሆነ መሰሎቻቸው የራሳቸውን ምሽግ ለማመቻቸት ሲሉ በሌላው ላይ እጃችሁን መቀሰራቸው የሚያስኬዳው አይመስለኝም፡፡ ይህች ሀገር በእነርሱ እየታመሰች መሆኗ ሳያንስ፤ ከእነርሱ ብሶ ሽብርተኝነትን ከወጣትነት ጋር ለማጣመር መሞከራቸው እጅግ የሚያሳፍር ተግባር ነው፡፡ ፕሮፌሰሩም ሆኑ ወዳጅዎቻቸው ቢገባቸው ኖሮ፣ ዛሬ ከ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኘው ወጣት ብሰው እንደ ህጻን ያልተገባ ዕቃ ዕቃ ጨዋታ ውስጥ የገቡት እነርሱ መሆናቸውን ባወቁት ነበር፡፡
እናም ፕሮፌሰር ሆይ፣ በዚህ ዕድሜዎ ከመቀላመድ ቢቆጠቡ ለጤንነትዎም ለሰላምዎም ይበጃል እንደሚበጅ ማወቅ ይኖርብዎታል፡፡ ግና እርስዎ “ደበበ ሰላማዊ፣ የሚወደድ ፣ የሚደነቅ…” እያሉ የባጥ የቆጡን ሲቀባጥሩ ቢውሉ ማንም የሚያምንዎት የለም፣ እርስዎስ ማን እንደሆኑ የሚጠፋን ይመስልዋቷልን?! -በፍፁም። ምክንያቱም የደበበ ምስክርነትዎ “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” የሚለውን አባባል እየደገሙት መሆንዎን በእርግጠኝነት ለመናገር አይከብደኝምና።
ፕሮፌሰር ሆይ፣ ከወጣቱ ላይ እጅዎን ቢያነሱም በጄ ነው፡፡ ዛሬ ወጣቱ ለዚህች ሀገር ዕድገትና ብልጽግና እየለፋ መሆኑን ሊገባዎት ያስፈልጋል፡፡ ከእናንተ ጋር አብሮ ለመዋል እየተገደዱ ያሉት ጥቂት ወጣቶችም ቢሆኑ፤ ስለ እርስዎና መሰልዎችዎ የጭፍን ፖለቲካ ግንዛቤ ኖሯቸው ሳይሆን ባለማወቃቸው ነው፡፡ ይህም ቢሆን እነዚህ ባለማወቅ እየተከተሏችሁ ያሉት ወገኖች፤ ብዙሃኑን ወጣቶች የሚወክሉ አይደሉም፡፡ ስለሆነም አንድ ቀን ትክክልኛውን መንገድ ተረድተው መመለሳቸው አይቀርም።ያም ሆነ ይህ ግን፤ ፕሮፌሰር ሆይ፣በዚህ ዕድሜዎ ባይቀላምዱ ምናለበት?!…