የስኳር ህመም ህክምና ለእድሜ ልክ ጤና

ስለ ስኳር ህመም መረጃ ለመጠየቅ ስነሳ ዐባይነህ አበራ «ዶክተር ለራሴ» በሚል ያሳተሙት መጽሐፍ ትዝ አለኝ። በመጽሐፉ በውጭው ዓለም በስኳር ህመም የተያዘ ሰው «እንኳን ደስ አለህ!» እንደሚባል ተጽፏል። የዚህ ምክንያቱ የስኳር ህመም ምልክት የታየበት ወይም በህመሙ የተያዘ ሰው ተጠንቅቆ የሚኖር በመሆኑ እንደሆነ ተጽፏል።

የዘመኑ ሰው አኗኗርና አመጋገብ እንቅስቃሴን የረሳ፣ ጣፋጭ ምግቦችንና ሌሎች ለአላስፈላጊ ውፍረት እንዲሁም ለተለያዩ በሽታዎች የሚዳርጉ አመጋገቦችን የሚያዘወትር እየሆነ ሄዷል።

የስኳር ህመም የተከሰተበት ሰው ግን ዕድሜ ልኩን በህክምና ባለሙያ የሚነገረውን እየተገበረ ጤንነቱን ጠብቆ መኖር ይችላል። ይህም ለስኳር ህመሙ ብቻ ሳይሆን ለሙሉ ጤንነቱ ይጠቅመዋል በሚል ነው «እንኳን ደስ ያለህ» የሚባለው።

በዚህ ህመም ዙሪያ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የስኳር ህመም ህክምና ክፍል ነርስ የሆኑት ሲ ስተር ውቢት ኃይሉ ሙሉ መረጃ ሰጥተውኛል። ለሰጡት መረጃና ቃለ ምልልስ ሲስተር ውቢትን እያመሰገንኩ ቃለ ምልልሱን አስከትላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- የስኳር ህመም እንዴት ይገለጻል?

ሲስተር ውቢት፡- አንድ ሰው ከሚመገበው ምግብ ወደ ካርቦሃይድሬት ወይም ኃይል ሰጪነት የተቀየረው ክፍል ቆሽት በሚያመነጨው «ኢንሱሊን» አማካኝነት ለክፍለ አካላት ሁሉ መዳረስ አለበት። ኃይል ሰጪ ምግቦች በኢንሱሊን አማካኝነት ለሰውነት ሁሉ ካልተዳረሱ ስኳር በደም ውስጥ ይጠራቀማል። ስኳር በደም ውስጥ ተጠራቅሞ ሲበዛ ደግሞ ችግር ይፈጥራል። ከዚያም በሰውነት ውስጥ በአንዳንድ አካላት ላይ ችግር ይከሰታል።

አዲስ ዘመን፡- የስኳር ህመም ዓይነት ወይም ደረጃ አለው?

ሲስተር ውቢት፡- የስኳር ህመም በአራት ዓይነት ይከፈላል- በደረጃ ሳይሆን። አንደኛው ዓይነት ሕፃናትን ጨምሮ ከሰላሳ አምስት ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰት ነው። ቆሽት ምንም ኢንሱሊንን ባለማመንጨቱ ምክንያት ይከሰታል። በቆሽት አማካኝነት የሚመነጨውን ኢንሱሊንን ኃይል ሰጪ ምግቦች ካላገኙ ደም ውስጥ ዝም ብለው ይጠራቀማሉ። የስኳር መጠንንም ከፍ ያደርጋሉ። እንዲህ ያለው ችግር ያለባቸው ሰዎች ዕድሜ ልክ ኢንሱሊን እየወሰዱ መኖር ይገባቸዋል፤ ይችላሉም።
ሁለተኛው ዓይነት የስኳር ህመም ከ35 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው አዋቂዎች የሚባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚከሰት ነው። ቆሽት ኢንሱሊን ያመርታል። በቂ ሆኖ ግን የካርቦሃይድሬት ይዘት ያላቸውን ምግቦች «ሊያቃጥል» አይችልም። ወይም የቆሽት ሥራ ደካማ ይሆናል።
የቆሽትን ሥራ ለማነቃቃትና ተግባሩን ለማገዝ በኪኒን መልክ የሚዘጋጅ መድኃኒት ይሰጣል። ይህም ሆኖ ቆሽት ተነቃቅቶ በቂ ኢንሱሊን ካላመነጨ ካርቦሃይድሬትን ለሰውነት ሁሉ ለማዳረስ ወደመርፌ ህክምና ይገባል።

ሦስተኛው ዓይነት የስኳር ህመም ሴቶችን በእርግዝና ጊዜ ብቻ የሚይዘው ነው። ይህም ከእርግዝና በኋላ ዘጠና ሰባት ከመቶው ይወገዳል። ከወሊዱ በኋላ ይጠፋል። በቤተሰብ የስኳር ህመም የተከሰተበት ሰው ከነበረ፣ ከአራት ኪሎ በላይ የሚመዝን ልጅ ተወልዶ ከነበረና የሰውነት ክብደት ከአስፈላጊው በላይ ከፍ ካለ ምናልባት የስኳር ህመሙ ይቀጥል ይሆናል። በእርግዝና ምክንያት ብቻ የተከሰተ ከሆነ ግን በቋሚነት አይቀጥልም።

አራተኛው ዓይነት የስኳር ህመም አዘር ስፔሲፊክ ታይፕ ኦቭ ዲያቤት (other specific type of diabetes) የሚባል ነው። ቆሽት በቀዶ ህክምናና በተመሳሳይ መንገድ ሲጎዳ የሚከሰት ነው። ይህ ዓይነት የስኳር በሽታ በአገራችን የተለመደ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- የስኳር ህመም መንስኤዎች ምን ምን ናቸው?
ሲስተር ውቢት፡- የስኳር ህመም በዘር (በጂን) አማካኝነት ከቤተሰብ የሚመጣ ነው። በጥንቃቄ ጉድለት በንዝህላልነት የሚባል ሳይሆን በተፈጥሮ የሚከሰት ነው።

አዲስ ዘመን፡- የስኳር ህመም ምልክቶች ምን ምን ናቸው?

ሲስተር ውቢት፡- ብዙ መሽናት፣ ብዙ ውሃ መጠጣት፣ ብዙ መመገብ፣ ክብደት መቀነስ፣ ዐይን ብዥ ብዥ ማለት፣ ማዞር፣ ድካምና የመሳሰሉት ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የስኳር ህመም ምን ችግር ያስከትላል?

ሲስተር ውቢት፡- የስኳር ህመም ሳይታወቅና ሳይታከሙ ብዙ ሲቆይ፣ ህክምናው ተጀምሮ መድኃኒት በአግባቡ ሳይወሰድ ሲቀርና ዕድሜም ሲገፋ የአካል ጉድለት ያመጣል። የዐይን ብርሃንን ያሳጣል። በኩላሊት፣ በነርቭና በልብ ላይ ችግር ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን፡- የስኳር ህመም መከላከያ ምንድን ነው?

ሲስተር ውቢት፡-ስኳር ህመም ሳይከሰት ቅድመ ስኳር ህመም መከላከል ማድረግ ይቻላል። አስቀድሞ ምርመራ ማድረግ፣ አላስፈላጊ ክብደትን ማስወገድ፣ ጤነኛ አመጋገብን መከተል ማለትም ቅጠላ ቅጠል የበዛበትን አመጋገብ መከተል፣ የካርቦሃይድሬት ምግቦችን መመጠን፣ ቅባትን መቀነስ፣ እንቅስቃሴ ማድረግ ወዘተ- ከመከላከያ መንገዶች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

አዲስ ዘመን፡- ለስኳር ህሙማን የተከለከሉና የሚፈቀዱ አመጋገቦች አሉ?

ሲስተር ውቢት፡- ለስኳር ህሙማን በገደብ የሚፈቀዱ፣ ያለገደብ የሚወሰዱና በፍጹም የሚከለከሉ የምግብ ዓይነቶች አሉ፡፡ ፓስታ ፣ድንችና ዳቦን የመሳሰሉት ገለባ አልባ የተ ጣሩና ካርቦሃይድሬት ሰጪ ምግቦች በገደብ የሚወሰዱ ናቸው። ያልተፈተጉ እህሎችና አረንጓዴ ተክሎች ያለገደብ ይወሰዳሉ። ስኳር በደም ውስጥ ካላነሰና የስኳር እጥረት ምልክት ካልታየ በቀር ከጣፋጭ ነገር የተሠሩት ሁሉ ክልክል ናቸው።

አዲስ ዘመን – ስኳር በሽታ ስኳር በመጠቀም ይከሰታል?

ሲስተር ውቢት – ስኳር ራሱ የስኳር በሽታን አያመጣም። ቆሽት ኢንሱሊን ሳታመነጭ ወይም በቂ ሳይሆን ሲቀር የሚከሰት በመሆኑ « ስኳር እንዳይዝህ ስኳር አትመገብ » የሚለው ትክክል አይደለም።
አዲስ ዘመን -የስኳር ህመም ህክምና ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል?
ሲስተር ውቢት፡- የስኳር ህመም ህክምና ዘላቂ መድኃኒቱም ዕድሜ ልክ የሚወሰድ ነው። የተከለከሉትን እየተው የተፈቀዱትን እየሠሩ በጤንነት መኖር የሚቻልበት ህክምና ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ጊዜ የስኳር ህሙማን ቁጥር እየበረከተ ነው የሚሉ አሉ። እውነት ከሆነ ምክንያቱ ምንድን ነው?

ሲስተር ውቢት ፡- አዎ የስኳር ህሙማን ቁጥር እየበዛ ነው።
ሆኖም ለቁጥሩ መብዛት በውል የታወቀ ምክንያት የለም። ምክንያቱም ጤነኛ አመጋገብ አለመኖር፣ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ አስፈላጊ ክብደትን አለመቀነስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ የስኳር ህሙማን ቁጥር የበዛበት ምክንያት በውል የታወቀ አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- ለስኳር ሕሙማንና ለኅብረተሰቡ ምን መልዕክት አለዎ ?

ሲስተር ውቢት ፡- የስኳር ህሙማን ብቻ ሳይሆኑ ሌላውም ኅብረተሰብ ጤናውን መጠበቅና ጤንነቱን ማረጋገጥ ይገባዋል። ጤነኛና ቅጠላ ቅጠል ያመዘነበት አመጋገብ መከተል፣ ቅባትን ጨርሶ መቀነስና ቅድመና ድህረ ስኳር ህመም ምርመራ ማድረግ ያስፈ ልጋል። ህመሙ ኖሮ ሳይታወቅ ብዙ ሰው ሊያልፍ ይችላልና። የስኳር ህሙማንም መድኃኒታቸውን በአግባቡ መውሰድ አንዳንዴ የአይናቸውን ጤና መመርመር ያስፈልጋቸዋል። የዕድሜ ልክ ህክምና ማግኘት እንዳለባቸው ተቀብለውና የተከለከሉትን በመተውና የተፈቀደላቸውን በማድረግ ያለ እንከን ዕድሜ ልክ መኖር ይችላሉ። ለስኳር ህሙማን የተለየ የምግብ ማዘጋጀት ሳይሆን አመጣጥኖ መውሰድ ነው ዋናው። « ከየትኛው ምግብ ምን ያህል ? » የሚለው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አዘ አግቧል።