በአገራችን ላይ የሻእቢያ ማቆሚያ ያጣ ሽብርና ትንኮሳ መንስኤው ምንድነው?

በሃይሉ ምንተስኖት¬- ከአዲስ አበባ
ግጭትና ብጥብጥ ተለይቶት በማያውቀው የአፍሪካ ቀንድ ካለፉት ሃያ አመታት ወዲህ ሰላምና መረጋጋቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ኢኮኖሚዋ እያደገና በሁሉም መስክ እያንሰራራች ያለች ብቸኛ አገር ብትኖር ኢትዮጵያ መሆኗ አያጠያይቅም። ይህም ኢትዮጵያን በምእራቡም ሆነ በምስራቁ ክፍለ አለም ባሉ የአለም አገራት ዘንድ በአጋርነት እንድትፈለግ አድርጎታል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ለአለምዓቀፉ የፀረ ሽብር ትግል በቁልፍ አጋርነት ያላትን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት  አጠናክራ እየቀጠለች መሆኑን ሲነገር እናዳምጣለን።
በሌላ በኩል ቻይናን ጨምሮ በምስራቁ ክፍለ አለም የሚገኙ አገራት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ትብብርና ወዳጅነት አጠናክረው ለመቀጠል እንዲያስችላቸው የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ በውል በመገንዘባቸው ግኑኝነታቸውን  በየጊዜው ጠበቅ እያደረጉት እንደሆነ በተለይም ከአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ህንፃ ምረቃ ጋር ተያይዘው የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ ፈፅሞ በተቃረነ የፖለቲካል አይዶሎጂ በሚመሩትና በጂኦግራፊካዊ አቀማመጣቸውም ሙሉ በሙሉ ተቃራኒ በሆነ አቅጣጫ በሚገኙት ክፍለ አለማት መንግስታትና ህዝቦች ዘንድ ያላት ተቀባይነትና ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎላ መጥቷል።

የበርካታ ብሄርና ብሄረሰቦች አገር የሆነችው ኢትዮጵያ በውስጧ ሰላምንና መረጋጋትና አስፍናና የህዝቦቿን አንድነት አስጠብቃ እንዲሁም ልማትን የማፋጠን አጀንዳን በዋነኝነት ይዛ መንቀሳቀስ ከጀመረች እነሆ ድፍን ሃያ አመታትን አስቆጥራለች፡፡
በአገራችን በአሁኑ ወቅት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የመጣው መረጋጋት ፈጣን ልማትን በማረጋገጥ ከድህነት ለመውጣት ከሚደረገው የህዝቦቿ ትግልና የመንግስት ጥረት ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ጭምር የሰላም የመረጋጋትና የእድገት ተምሳሌት ለመሆን ችላለች።

በሁሉም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችው መጠነ ሰፊ ለውጥና እድገትም በሌሎች የአፍሪካ አገራት እንደ አርአያ እንድትወሰድ እያደረጋት ነው ።

ለህዝቦች ህልውናና ደህንነት በቅድሚያ በአንድ አገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው በውል የተገነዘበችው አገራችን ከሯሷ አልፋ በግጭትና ጦርነት ውስጥ ባሉ የአፍሪካ አገራትም ተመሳሳይ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ባለፉት አመታት የሰላም አስከባሪ ሃይሏን በመላክ የበኩሏን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ አሁንም በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

እንደ አብነት ላይቤሪያና ሩዋንዳን የመሰሉ የአፍሪካ አገራት ቀደም ሲል የተከሰቱባቸውን የእርስ በእርስ ጦርነቶችና ግጭቶች በህዝቦቻቸውና በአገራቸው ላይ ያደረሱትን አለመረጋጋቶች መፍትሄ ለመስጠት ባደረጉት ጥረት ቅድሚያ የደረሰው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል መሆኑን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል በላይቤሪያና ሩዋንዳን የመሰሉ የአፍሪካ አገራት ለሰላም ማስከበር እገዛ በተሰማራበት ወቅት ከሰላም ማስከበር ተግባሩ በተጨማሪ ችግኞችን መትከልን ጨምሮ በተለያዩ ሰብአዊ ዘርፎች በመሰማራት ለእነዚህ አገራት ህዝቦች ያለውን ወንድማዊ አጋርነት ማስመስከር ችሏል፡፡

ለሠራዊቱ ይህን መሰል መልካም ተግባርም በእነዚህ አገራት የነበሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮች የእውቅና ሽልማት በሰጡበት ወቅት በንግግራቸው አስምረውበታል፡፡ለእነዚህ የአፍሪካ አገራት አገራችን የሰጠችው እገዛም አህጉራዊ አለኝታነቷንና አጋርነቷን ከማረጋገጥ በተጨማሪም አፍሪካዊ ክብርና ሞገስም አላብሷታል፡፡

ይህም የአገራችን መንግስት ሰላምን የማስፈን በጎ ጥረቱና ሰላም ወዳድነቱ በአገሩ ብቻ ሳይወሰን አህጉራዊ ሃላፊነት የተሞላበት መሆኑን አረጋግጧል። ይህ መልካምና በጎ ተግባርም ኢትዮጵያን በአለምዓቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅናንና አድናቆትን እንድታተርፍ አስችሏታል።

ቀደም ባሉት አመታት ቀደም ሲል በተጠቀሱት አገራት ባበረከተችው የሰላም ማስከበር አስተዋፅኦም በቅርቡ በሱዳን አቢዬ ግዛት ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት አሜሪካና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያን ከየትኛውም አገራት ይበልጥ ተመራጭ

እንደሆነች በመግለፅ ወደ ስፍራው የሰላም አስከባሪ ሃይሏ እንዲገባ ያደረጉትን ጥረት ከአለምዓቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ስንከታተለው የነበረ ጉዳይ ነው።
የአሜሪካና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥረትም የሁዋላ ሁዋላ የሌሎች በርካታ የአለም አገራት ድጋፍ ታክሎበት አገራችን የሰላም ማስከበር ጥሪውን ተቀብላ በአሁኑ ወቅት የአቢዬን ግዛት ከሱዳን ህዝብ ጋር ለማረጋጋት የተለመደ ድጋፏን እየሰጠች ነው።

ኢትዮጵያ በአለምዓቀፍ መድረክ ላይ አፍሪካውያን ተቀባይነታቸውና ተደማጭነታቸው ይበልጥ እየጎለበተ እንዲመጣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገች ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቀደም ሲል በአፍሪካና በምእራባውያን መካከል የነበረው የእርዳታ ሰጭነትና የተመፅዋችነት ግኑኝነት ተቀይሮ  አፍሪካ በአለም ዓቀፍ ገበያ ፍትሃዊ የሆነ የንግድ ሚዛን እንዲፈጠርላትና ግኑኝነቱም በመከባበርና በመተማመን ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።

በጠቅላይ ሚኒስትር መለስና በሌሎች የአህጉሩ አገራት ግንባር ቀደም መሪዎች ሲደረግ የቆየው ይህ ጥረትም ፍሬ በማፍራቱ ከቅርብ አመታት ወዲህ አለም በኢኮኖሚ ቀውስ ባለበት ሁኔታ እንኳን በአህጉሩ አበረታች ኢኮኖሚያዊ እድገት እየተመዘገበ ይገኛል።
አገራችን የመላው አፍሪካን ህዝቦችን ወንድማማች በሆነ መንፈስ በማስተሳሰር ረገድ እያበረከተች ካለችው አስተዋፅኦ በተጨማሪም በሯሷ ውስጥ እየተመዘገበ ባለው ዘርፈ ብዙ እድገት አፍሪካውያን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በአሁኑ ወቅት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ህዝቦችን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ አበረታች ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። 
ሆኖም በዚህ ሂደት ግን የአገራችንን ይህንን በጎ ጥረት ለማደናቀፍ ላለፉት አመታት እንቅልፍ አጥቶ ሌት ተቀን ሰላሟን በማናጋት እኩይ ተግባር ላይ ተጠምዶ የቆየው የሻእቢያ መንግስት ለአፍታም ቢሆን የሽብርና የትንኮሳ ተግባሩን ያቆመበት ጊዜ ባለፉት አስራ አራት አመታት ለአንድም ጊዜ አልታዬም።

•    የሻእቢያ የሽብርና ትንኮሳ ስትራቴጂ የተኮላሹ እርምጃዎቹና የተላላኪዎቹ ፍፃሜ

በአገራችን ላይ ሻእቢያ ማቆሚያ የሌለው የሽብርና ትንኮሳ ስትራቴጂ እየተከተለ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህንን እኩይ ተግባሩን ለማሳካት ኢትዮጵያ ውስጥ ኦነግ ኦብነግ ግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባርና የመሳሰሉትን ጨምሮ እሱ ያልተጠቀመበት ፀረ ሰላም ተላላኪ ሃይል አለ ለማለት ያስቸግራል።
እነዚህ ሃይሎች በሻእቢያ የሽብር ስልጠና ተሰጥቷቸው፣ ምክርና የሎጂስቲከስ ድጋፍ ተደርጎላቸው፣ በአገሪቱ የሚካሄድን አለምዓቀፍ ጉባኤ እንዲያጨናግፉ አሊያም ሰላሟን እንዲያደፍርሱ ታዘው ከገቡ በሁዋላ በህዝብና በመንግስት ጥረት ተልእኳቸው ተጨናግፎ እነሱም በቁጥጥር ስር ሲውሉና በሚሰጡት ቃለ ምልልስ ይህንን እኩይ ተግባራቸውን ሲያረጋግጡ ለበርካታ ጊዜያት በሚዲያዎች ተመልክተናል።
እነዚህ የተለያዩ የሽብር ሙከራዎች ለበርካታ በተደጋጋሚ ጊዜያት እየተሞከሩ ይክሸፉ እንጂ ሁኔታውንና መልኩን እየቀያየረ ይህን ጠብ አጫሪና ነውጠኛ የሸብር ተግባሩን ግን ሻእቢያ በአገራችን ላይ ያልቃጣበት ጊዜ አለ ማለት ይቸግራል።
የሻእቢያ መንግስት በነውጥ፣ በጦርነትና በሽብር  አባዜ ተልክፎ  በቀውስ ሁኔታ ውስጥ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ የሚመራት ኤርትራም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች።
ለዚህ አባባል እንደ አብነት The daily maverick የተሰኘ ድረገፅ  ኤርትራን አስመልክቶ በሃምሌ 25 ቀን 2003 ያወጣውን እትም መጥቀስ ይቻላል።ይህ ድረ ገፅ    ኤርትራ ከሶማሊያ ጋር ድንበር የምትጋራ አገር ባትሆንም አልሸባብን የመሳሰሉ አክራሪ እስላማዊ አክራሪዎች በአገሪቱ ውስጥ ላላቸው ስኬት ገንዘብና የጦር መሣሪያ በመርዳት ረገድ ዋነኛ አገር ነች ብሎ ነበር ፡፡ በዚህ ድርጊቷም የተነሳ ኤርትራ በአሁኑ ወቅት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተነጠለች፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከባድ ማዕቀብ ውስጥ የምትገኝና ከኢጋድ የተገለለች አገር ሆናለች ሲል ነበር ያመለከተው ፡፡

The daily maverick አያይዞም በአሁኑ ወቅት በኤርትራ ድህነት ስር የሰደደ ሲሆን ትምህርትና ጤና አገልግሎት የሉም የሚባልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል በዘገባው፡፡ በኤርትራ ያለው አገዛዝ የአፍሪካ ሰሜን ኮሪያ፣ በዓለማቀፍ ማኅበረሰብ

የተገለለና የተንጋደደ የውጭ ፖሊሲ አራማጅ እንዲሁም በአገር ውስጥ አጥፊ መንግሥት ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም ሲልም ነበር ያሰፈረው ይሀው ድረ ገፅ፡፡አሁንም በኤርትራ የሚታየው ሁኔታ ይህ ድረ ገፅ ከገለፀው በበለጠ በተባባሰ ሁኔታ ላይ ቢገኝ እንጂ አንዳች መሻሻል የሚባል ሁኔታ የሚታይበት አይደለም።

ኤርትራ በሻእቢያ መንግስት የቀውስ አመራር ላይ መገኘቷን የሚያረጋግጠው ሌላው አብነት በሻእቢያ አገዛዝ የተማረሩ ኤርትራውያን በየቀኑ ወደአገራችን የሚያደርጉት ስደት ዋነኛው ማሳያ ነው።ለዚያውም ከሻእቢያ ጥብቅ የድንበር ጥበቃና ድንበር ሲያቋርጡ ቢገኙ ሊወሰድባቸው የሚችለውን የግድያ እርምጃ ተቋቁመው አምልጠው ማለት ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ፅህፈት ቤት በሃምሌ ወር አጋማሽ 2003 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ከኤርትራ እየፈለሱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገቡ ኤርትራውያን ስደተኞች አሃዝ እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል።

በዚሁ ወቅት ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ብቻ እንደሚገኙ ያመለከተው የድርጅቱ የስደተኞች ጉዳይ ፅህፈት ቤት 49 ሺ የሚሆኑት ደግሞ ትግራይ ውስጥ ባሉ ሦሰት ካምፓችና አፋር አካባቢ ደግሞ ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው በመኖር ላይ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር።

የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ፅህፈት ቤት በቁጥጥር ስር ቢውሉ በሻእቢያ አመራሮች ሊደርስባቸው የሚችለውን የሻእቢያን የሞትና የእስራት ቅጣት ሳይፈሩ በአማካይ በወር 800 የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡም አመልክቶ ነበር በዚሁ ወቅት ፡፡ይህ የስደተኞች አሀዝ መረጃም አሁን ከሰባት ወር በሁዋላ እንደገና ቢታይ ይብስ ይሆናል እንጂ ሊሻሻል የሚችልበት አንዳች ሁኔታ በኤርትራ አልተፈጠረም።

በዚህም ሳቢያ ሻእቢያ በአገር ውስጥ አመራሩ የፈጠረበትን ቀውስና በህዝቡ ዘንድ ያስከተለው ምሬት የፈጠረበትን አለመረጋጋት ለመሸሽና አጀንዳ ለማስቀየር አንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ሌላ ጊዜ ሶማሊያ፣ ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ኬንያ፣ አልሆን ሲል ደግሞ ጂቡቲ ውስጥ በመግባት የተጠናወተውን የሽብርና ቀውስ የመፍጠር ሱሱን እየተወጣ ይገኛል።

የጤንነት ሁኔታቸው እጅግ አጠራጣሪ የሆነው የሻእቢያ አመራሮች በአመቱ መጀመሪያም ሆነ ነግቶ ሲጠባ እቅድ ነድፈው የሚንቀሳቀሱት በዋነኝነት በኢትዮጵያ ቀጥሎ ደግሞ በሌሎች ጎረቤት አገራት ላይ ስለሚከፍቱት የሽብርና የትንኮሳ ስትራቴጂያካዊ እቅድ በማውጣት ነው። ሁላችንም የምናጭደው የዘራነውን ነውና ኤርትራ ሁሌም ቢሆን በአለምዓቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ሆነ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ በተለያዩ የአለምዓቀፍ ተቋማት በሚወጡ ሪፖርቶች ላይ ስሟ የሚነሳው ጠብ አጫሪ አመራሮቿ አገራቸውን ጨምሮ ከአገራቸው ውጭ በጎረቤት አገራትና አልፎም በአፍሪካ በፈጠሩት ብጥብጥ ሁከትና ሽብር ብዛት ነው።

አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ እነዚህ የሻእቢያ ጠብ አጫሪ አመራሮች የሽብርና የጦርነት  ስትራቴጂ የመንደፍ ክህሎታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጎለበቱ በመሄዳቸው ነው መሰለኝ አገሪቱ በየአመቱ እምርታ የምታሳይበት ዘርፍ ካለ ይሀው የሽብር፣  ጦርነትና የጠብ አጫሪነት ዘርፍ ነው።

እንደሚታወቀው አስተዋይ ባለ ራእይና ለህዝቦቹ መለወጥና እድገት የሚተጋ ብቁ አመራር ያላት ኢትዮጵያ በፈጣንና በተከታታይ ሁኔታ እያስመዘገበች ባለው ኢኮኖሚያዊ እድገት፣  የምእተ አመቱን የልማት ግቦች ከሚያሳኩ ታዳጊ አገራት በቀዳሚነት በመገኘቷና እንዲሁም በውስጧ ባለው ሰላምና መረጋጋት የአለምዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን ትኩረትን መሳቧ ገሃድ እየሆነ መጥቷል። ይህም ብቻ አይደለም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ከምታደርገው ጥረት በተጨማሪም በክፍለ አህጉሩ ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት የጎረቤት አገራት ህዝቦች መጠለያ ፍለጋ የሚሰደዱት ወደ ኢትዮጵያ ነው።

በቅርቡ እንኳ በአፍሪካ ቀንድ በስድሳ አመታት ውስጥ ያልተከሰተ የተባለለት የድርቅ አደጋ ባስከተለው ርሃብ በርካቶች ለችግር ሲዳረጉ በዋነኝነት የጎረቤት ሶማሊያ ዜጎች የፈለሱት ወደ ኢትዮጵያ ነው።ኢትዮጵያ እነዚህን ስደተኞች ለመቀበልና ለማስተናገድም በደቡባዊ ኢትዮጵያ ዶሎ አዶ ላይ ብቻ አራት የመጠለያ ጣቢያዎችን አቋቋማ  እስከ 40 ሺህ ስደተኞችን ተቀብላ ነበር ።
በኬንያም እንዲሁ በድርቅ የተጎዱ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ከመሰደዳቸው በተጨማሪ እጅግ አስገራሚ የሆነው ደግሞ ሰሞኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ይፋ ባደረጉት ዘገባ ላይ እንደተገለፀው በጠረፍ የኬንያ ግዛት የሚኖሩ ኬንያውን በእርስ በእርስ የሚፈጠሩ የጎሳ ግጭቶችን ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ ከተሞች በስደት የመግባታቸው ጉዳይ ነው።
ቀደም ሲል እንደተገለፀው በአገራቸው ያለውን ነውጠኛና ጦረኛ አመራር ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ በስደት የሚገቡ ኤርትራውያን ስደተኞችን አገራችን በእንክብካቤ ከመያዝ አልፎ ሰርተውና ተምረው የሚኖሩበት ምቹ ሁኔታም ተፈጥሮላቸዋል።
የኬንያና ሶማሊያን ጨምሮ በየጊዜው እየፈለሱ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞችም ኢትዮጵያን የሚመርጡት አገራችን ለስደተኞች በምታደርገው እንክብካቤና ለደህንነታቸው የሚያሰጋ ሁኔታ እንደሌለባቸው በመተማመን ነው።
ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዋና ዋና ምክንያቶችን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት አገራችን በአፍሪካም ሆነ በአለም መልካም ስምና ዝና ያላት፣  የእድገት የሰላምና የመረጋጋት ምሳሌ ስትሆን ሻእቢያ ደግሞ በአንፃሩ የሽብርተኝነት፣  የድህነት፣  የብጥብጥና የትርምስ ምሳሌ እየሆነ መምጣቱ በአደባባይ ፀሃይ የሞቀው ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል። 
ይህ እረፍት የነሳቸው የሻእቢያ አመራሮችም ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በተጠቀሰው መልክ እየገነባች ያለችው ገፅታና እያገኘች የመጣችው አለምዓቀፍ እውቅናና አድናቆት  እረፍት እንደነሳቸው ባለፈው አመት ተላላኪዎቻቸውን በመጠቀም በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ለማጨናገፍ ያደረጉት ሙከራ በግልፅ ያመላክታል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሶማሊያና ኤርትራ ክትትል ቡድን የኤርትራ መንግስት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የቦንብ አደጋ ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ እንደነበር ባረጋገጠበት ሪፖርት ላይ የኤርትራ መንግስት የቦንብ ጥቃት

ሴራ ዓላማ የህብረቱን የመሪዎች ጉባኤ ሂደት ማናጋት ነበር ብሏል፡፡ በመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት መሰረት የኤርትራ መንግስት በኡጋንዳ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያና ሶማሊያ ያሰማራቸው የስለላ ሃይሎች በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ላይ ስጋትን በሚፈጥር ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙም ነበር አያይዞ የገለፀው፡፡
የሶማሊያን በርካታ ክፍሎች ከሚቆጣጠረው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ጋርም ኤርትራ ግንኙነቷን እንደቀጠለች መሆኗን በቅርቡ ባወጣው ባለ 400 ገጽ ሪፖርቱ ላይ ነበር ያስታወቀው።
የሻእቢያ አመራሮች ይህንን እኩይ ተግባራቸውን በኢትዮጵያ ለማሳካትም ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የዜግነት መንፈስ የሌላቸውን የአገር ውስጥ ተላላኪ ፀረ ሰላም ሃይሎችን በመሳሪያነት ሲጠቀሙ ቆይተዋል።
እነዚህ ፀረ ሰላም ሃይሎች በኢትዮጵያ ህዝብ ተጠልተው የተተፉ ሲሆኑ ጦረኛውና አምባገነኑ የሻእቢያ መንግስትም ለእኩይ ጦረኛና ፀረ ሰላም ተግባሩ ሲፈልግ ሲጠቀምባቸው ቆይቶ ተላላኪነታቸውን በብቃት አልተወጡም የሚል ስሜት ባደረበት ወቅት ደግሞ አፈሙዙን ወደ እነርሱ ያዞራል።
በዚህም በጅምላ ከጨፈጨፋቸው በሁዋላ በጅምላ እንደሚቀብራቸው ባለፈው አመት በአርበኞች ግንባር በሚል በሚታወቀው የአሸባሪ ቡድን አመራር አባላት ላይ ተፈፀመ በሚል በደጋፊዎቻቸው ድረ ገፅ ላይ ያቀረቡትን ዘገባ ማስታወስ ይበቃል።
•    ተመጣጣኝ አፀፋዊ እርምጃ የሚያስፈልገው የሻእቢያ ጠብ አጫሪ እርምጃ
ቀደም ሲል እንደተገለፀው ኢትዮጵያ በውስጧ የፈጠረችው ሰላምና መረጋጋትና ከዚህ ጋር ተያይዞም ፈጣንና ተከታታይ በሆነ ሁኔታ እያስመዘገበች ያለችው እድገት  ሻእቢያንና አመራሩን እንቅልፍ እንደነሳው ለመገመት ነቢይ መሆንን አይጠይቅም።
ከዚህም በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ፣  በአፍሪካና በአለም ዓቀፍ ደረጃ ያገኘችው እውቅናና ተቀባይነትም በተመሳሳይ በፈጠረበት እረፍት ማጣት ማእቀብ ሲጣልበትና እንዲሁም በአሜሪካና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሸባሪነቱ ሲገልፅም ሆነ ሲረጋገጥ ይህንኑ ስህተቱን አስተካክሎና አርሞ ከመገኘት ይልቅ ሁሌም በተደጋጋሚ ሲያላዝን የሚሰማው “ይህ ሴራ በኢትዮጵያ የተሸረበ ነው” በሚል  ነው።

በኤርትራ የሻእቢያ አመራር በአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ የዜጎቹን የማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ማሻሻል ይቅርና ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በአፍሪካ ቀንድ ከስድሳ አመት ወዲህ ተከስቶ የማያውቀው እጅግ አስከፊ ርሃብና ድርቅ በተከሰተበት ወቅት እንኳን ለጋሾችና ምእራባውያን መንግስታት በከፍተኛ ደረጃ ያስጨንቃቸው የነበረው በድርቅና ርሃብ የተጠቁ ኤርትራውያን ቁጥርና በአገሪቱ የሚያስፈልገውን ያህል እርዳታ በመደበቁ ነበር።
በአለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀያየር ላይ ባለው የአየር ንብረት መቀየር ሳቢያ   በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ርሃብና ድርቅ ከከፋ አገዛዙ ጋር ተዳምሮ በርካታ ኤርትራውያን በርሃብ አለንጋ እየተገረፉ እንደሆነ መረጃ የነበራቸው ለጋሾችና ምእራባውያን ይህንን ሁኔታ ይፋ በማውጣት ዜጎቹን ከርሃብ ለመታደግ የሚያስችል እርዳታ ለአገሪቱ እንዲሰጥ የሻእቢያን አመራሮች ቢጠይቁም እነርሱ ግን ይህን አሀዝ ለመግለፅ ፈቃደኝነቱም ሆነ ፍላጎቱ አልነበራቸውም።

ይባስ ብሎ አሜሪካ የኤርትራ መንግስት ከድርቅ ጋር በተያያዘ በአገሩ ያለውን ሁኔታ እንዲያሳውቅ ለኤርትራ መንግስት ላቀረበችው ጥያቄ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ  አቶ አሊ አብዱ “በኤርትራ በቂ ምግብ አለ፣ አገሪቱ የምግብ ዋስትና ስትራቴጂዋን አረጋግጣለች” በሚል  በችግር ሲሰቃዩ የነበሩ ኤርትራውያንን የሚያደማ የሹፈት ምላሽ ነው ሲሰጡ የተደመጡት ፡፡

ፌዘኛውና በህዝባቸው ችግር ላይ ቀልድ የተካኑት የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር አሊ አብዶ የተጠየቁትን ትተው “አሜሪካ ለኤርትራ ሕዝብ ካሰበች የሚጠበቅባት የኤርትራን የልማት እቅድ መደገፍና በኤርትራ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ማንሳት፣ የኤርትራና የኢትዮጵያ ጥያቄ ወደ ግልፅነት እንዲደርስ ማድረግና የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት ወደ ተገቢው መንገድ እንዲመለስ ማድረግ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የማስታወቂያ ሚኒስትር ተብዬው ፌዘኛ ሰውዬ ፍዬል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ በሆነ መልክ ለአሜሪካ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ እርሳቸውና ሌሎች የቅርብ የሻእቢያ አመራር ጓደኞቻቸው እንኳንስ ህዝብና አገርን መምራት ይቅርና ለተጠየቁት ጥያቄ እንኳን በአግባቡ ምላሽ መስጠት የተሳናቸው ናላቸውና አእምሯቸው ሽብርና ነውጥን በማብሰልሰል የላሸቀ መሆኑን ነው ያሳበቀባቸው፡፡

በተለይም እንደ ኢትዮጵያና ኬንያ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርአት የዘረጉ አገራት  እንዲህ አይነት ያልተገመተና ያልተጠበቀ አየር መዛባት በአገራቸው ሊከሰት መሆኑን አስቀድመው ሲያውቁ ሊከሰት የሚችለውን የድርቅ ስፋትና መጠን ለለጋሾች አስቀድመው ይፋ በማድረግ ያሳውቃሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገራቸው ውስጥ ለአደጋ ጊዜ የተከማቸን የመጠባበቂያ ምግብ ሁኔታ ከተረጂዎች ቁጥር ጋር አጣጥመው የሚያከፋፍሉበትን መንገድ

ይተልማሉ፡፡አስከትለውም ተረጂዎች ከአካባቢያቸው ሳይፈናቀሉ ችግሩን የሚቋቋሙበትን መንገድ በአግባቡ ይቀይሳሉ፡፡
ያልተረጋጉት ጠብ አጫሪዎቹ ግን ቢያንስ ይህን መሰል የተቀናጀና ችግሩ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል የተጠና እርምጃ መውሰድ  ባይጠበቅባቸው እንኳን በግድ የተጎጂዎችን ሁኔታ አገናዝቦ እርዳታ ልስጥ በሚል ገፍቶ የመጣ ለጋሽ  ላይ መሳለቅን በሚመሩት ሀዝብ ጉዳት ላይ ማፌዝንና ማሾፍን ምን አመጣው? ለዚህም ነው ቀደም ሲል የእነዚህ ጦረኛ አመራሮች የጤንነት ሁኔታ በእጅጉ አጠራጣሪ መሆኑን ለመግለፅ የሞከርኩት፡
የሻእቢያ አመራሮች በዜጎቻቸው ላይ የሚያደርሱት በደል ይህ ብቻ አይደለም በቅርቡ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና አገልግሎት ኤርትራን አስመልክቶ ባስተላለፈው ዘገባ  በኤርትራ በግዳጅ የሚካሄደውን የብሄራዊ አገልግሎት ምልመላ በመቃወም በየወሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አገራቸውን ጥለው በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያና ሱዳን በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ገልፆ ነበር፡፡የዜና ምንጩ በአገሪቱ በርካታ ህፃናትም ለውትድርና እየተመለመሉ፣ ትምህርት ቤታቸው እየተዘጋ የውትድርና ማሰልጠኛ እየሆኑ መሆኑን ነበር በዚሁ ዘገባ ያመለከተው ፡፡

ከተለያዩ የጎረቤት አገራትና ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር ያለው የውጭ ግኑኝነት አሸባሪነትን ጦርነትንና ጠብ አጫሪነት መሰረት ያደረገው የሻእቢያ አመራር ለዚሁ ፖለሲው ተግባራዊነት በመንግስትነት ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በግዳጅ ብሄራዊ ውትድርና  ፕሮግራሙ የኤርትራ ወጣቶችን ለጦርነት እያስገደደ ሲማግድ ቆይቷል ፡፡

ይህን እኩይ ተግባሩን አጠናክሮ እየገፋበት ያለው ይህ ሃላፊነት የጎደለው ነውጠኛ አመራር ኤርትራውያን ወጣቶችን በጦርነቱ ከማገደ በሁዋላ ለዚሁ ረብ የለሽ አላማው ወደ ህፃናት እየተሸጋገረ መሆኑን ነው የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያጋለጠው፡፡

የነገ አገር ተረካቢ ህፃናት በትምህርት ታንፀውና ተኮትኩተው ማደግ ሲገባቸው ትምህርት ቤታቸው ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ ተቋምነት የሚቀይር ሻእቢያን መሰል ነውጠኛ አመራር በአምባገንነቱና ጨካኝነቱ ከነሂትለር ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይሆንም፡፡

ይህ ሃላፊነት የጎደለው ጦረኛና ሽብርተኛ መንግስት የሚከተለው ጠብ አጫሪ ስትራቴጂና አመራር በኤርትራ ከተከሰተው ድርቅና ርሃብ ጋር ተዳምሮ በዜጎች ላይ ባስከተለው ከፍተኛ ችግር ሳቢያም በተለይ በቅርቡ በርካታ ኤርትራውያን ከመቼውም በበለጠ ወደ ኢትዮጵያ በስደት እንዲገቡ አድርጓል፡፡

አምባገነኑና ጦረኛው የኤርትራ መንግስትም ይህ ሁኔታ የፈጠረበት ስጋት መልኩን እየቀያየረ በአገራችን ላይ የማያቋርጥ የሽብርና የጦርነት ሙከራ እንዲጭር አስገድዶታል።
ይህ የሽብር ሙከራና ትንኮሳ በመልካም ሁኔታ እየተለወጠና እየተሻሻለ ባለው የአገራችን ገፅታ ላይና እያደገና እያንሰራራ በመጣው የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ማነጣጠሩ በእጅጉ ሊያሳስብ የሚገባው ጉዳይ ነው።
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ አገራችን የአፍሪካ መዲና መሆን የቻለችው በተለይም ባላት የማይናወጥ ሰላምና መረጋጋት መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም።
ሻእቢያ ደግሞ ባለፈው አመት “አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ” በሚል ሊያካሂደው አስቦ በከሸፈበት የሽብር ስትራቴጂ ላይ ተላላኪዎቹ ሲገልፁ እንደነበሩት የሽብር ጥቃቱን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት በመክፈት የአገራችን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ መልእክት ማስተላለፍ ነበር የፈለገው።
ሆኖም በሰላም ወዳድ ህዝባችንና የመንግስታችን የተቀናጀ ጥረት ስንትና ስንት ጊዜና ሃብት አባክኖ የነደፈው የሽብርና የጦርነት እቅድ ሳይሳካ እንደ ጉም በኖ በደመና ላይ ሊቀር ችሏል ።

ባለፈው ሰሞን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጣሪ ቡድን ይፋ የሆነው ሪፖርት፣ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ ክልሉን እያተራመሰና እያሸበረ እንደሚገኝ በማረጋገጡ የኤርትራ ባለስልጣናት በተለያየ መልኩ እውነታውን ቢያስተባብሉትም  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአገሪቱ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጥል አስገድዶታል፡፡
ይህ ሁኔታ ደግሞ ኤርትራን የበለጠ እንድትገለል እንዳደረጋት ሲገለፅ የቆየ ቢሆንም የፖለቲካ ተንታኞች ግን ኤርትራ አሁንም አካባቢውን የማተራመስና የጦርኝነት ተግባሯንና በሶማሊያ ከአልሸባብ ጋር ያላትን የአሸባሪነት ግኑኝነት እስካላቆመች ድረስ ምናልባትም በዓለም አቀፉ የሽብርተኝነት መዝገብ ውስጥ ልትሰፍር የምትችልበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ሲገልፁ ነበር፡፡
የሻእቢያ መንግስት ከአልሸባብ ጋር ያለው ቁርኝትና ወዳጅነት ከሽብር እንቅስቃሴው ጋር ተዳምሮም የመንግሥትነት ዕድሜውን በቅርቡ ሊያሳጥረው ይችላል የሚል ትንታኔም የፖለቲካ ተንታኞች ይፋ እያደረጉ ናቸው፡፡
የሻእቢያው አመራሮች በኤርትራ በመንግስትነት ስልጣን ላይ ከወጣበት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባሉት ጊዜያት በአገሪቱ ይህ ነው የሚባል ፋይዳ ያለው የኢኮኖሚ የማህበራዊና የፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ባለማከናወናቸውና በአምባገነንና ኢ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ጦረኛ አመራራቸው በኤርትራ ዜጎች ለስደት እየተዳረጉ ያሉበት ሁኔታ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪም የሻእቢያ አመራር በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ የተከተለው የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ እንዲጣል ካደረገበት ሁለት ማእቀብ በተጨማሪም በጎረቤት ሀገሮችና በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍተኛ ተሰሚነት ባላቸው ሃያላን ሀገሮች ጭምር ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎታል፤ በዚህም የተነሳ የኤርትራ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ በሚባል ፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ መግባቱ እየተገለፀ ይገኛል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም የኤርትራ መንግስት ከገባበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት ተስፋ የቆረጠ እርምጃ -የማይወስድበት የመከራከሪያ ነጥብ ማስቀመጥ የማይቻል በመሆኑ የኤርትራ መንግስት እንቅስቃሴን የኢትዮጵያ መንግስት በተጠንቀቅ

ማጤን፣ በንቃት መከታተል ይገባዋል ሲሉ በኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ መምከራቸውን አንድ የግል ጋዜጣ በቅርቡ ነበር ያሰፈረው ፡፡
የተፈራው አልቀረምና የሻእቢያ መንግስት ይህ ዘገባ በወጣ ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአገራችን ላይ የሚከተለውን የሽብርና የጠብ አጫሪ ተግባር በመቀጠል በቅርቡ  በአፋር ክልል በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ቱሪስቶች ላይ በመገናኛ ብዙሃን ይፋ የተደረገውን የጥቃት እርምጃ ፈፅሟል፡፡
ምንም እንኳን አገራችን ሰላምን ከምንም በላይ አጥብቃ የምትፈልግ በመሆኗ የተያያዘችውን የልማት ተግባር ለአፍታም ቢሆን ማቋረጥ ባትፈልግም ሻእቢያን መሰል አሸባሪዎችንና ጠብ አጫሪዎች ላይ የማያዳግም የአፀፋ እርምጃ መውሰድ ደግሞ ልማቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል ዋስትና በመሆኑ አገራችን አፋጣኝ በሆነ ሁኔታ በሻእቢያ ላይ መውሰድ ያለባትን ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ በምንም ሁኔታ ለድርድር የማይቀርብ ነው።
በአገራችን እየተመዘገበ ያለው ፈጣንና ተከታታይነት የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት የሚኖረው በአገራችን የሰፈነው ሰላምና መረጋጋት ላይ የሚቃጡ ማንኛውንም አይነት የሽብርና የፀረ ሰከላም እንቅስቃሴ በተገቢው ሁኔታ መመከትና መከላከል ሲቻል ብቻ ነው። 
በአገራችን በሚሊዮኖች መስዋእትነት እውን የሆነው ሰላምና መረጋጋትና ይህን ተከትሎም በልማታዊ መንግስት እቅድ ነዳፊነት አስተባባሪነትና በመላው ዜጎች ንቁ ተሳትፎ በፖለቲካው በኢኮኖሚውና በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች የተገኙ እድገቶችና መሻሻሎች መጠበቅ የመከላከያ ሃይላችንን ጨምሮ የመላው ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን ህዝቡ በአግባቡ የተገነዘበበት ወቅት ላይ እንገኛለን ረጋገጠው ፖለቲካዊ ተጨማሪም በኤርትራ መሽገው የሚገኙ ፀረ ሰላም ተላላኪ ሃይሎች ከምንጫቸው ማድረቅ የሚቻለው ይህንኑ ተመጣጣኝ እርምጃ ኢትዮጵያ በሻእቢያ ላይ መውሰድ ስትችል ነው።
በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በስድስት ወር የመንግስት የስራ አፈፃፀም ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ እንዳስታወቁት የመከላከያ ሃይላችን በጦረኛው የሻእቢያ መንግስት ላይ ተመጣጣኝ አፀፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ካደረገው ዝግጁነት ጋር ተያይዞ በአሸባሪው ላይ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ኢትዮጵያ በትክክለኛው ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡በተመጣጣኝ እርምጃው በኤርትራ የመሸጉ የአገር ውስጥ ፀረ ኢትዮጵያ ተላላኪ ፀረ ሰላም ሃይሎችም ላይ ተገቢውን ዋጋ የሚያገኙበት እንደሚሆን ይታመናል፡፡

ቸር እንሰንብት!