የባለሙያዎችን እጥረት በዘላቂነት የመፍታት ተግባር

አቶ ሰለሞን ከበደ ዓይኑን ለመታከም ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ተመላልሷል። ለመመላለሱ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ስፔሻሊስት ሐኪም አግኝቶ ለመመርመር አለመቻሉ ነው። የህክምና ባለሙያዎች ዓይኑን የቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልገው ነግረውታልና።

አቶ ሰለሞን እንደሚናገረው፤ ህክምናውን ለማግኘት የሁለት ዓመት ቀጠሮ ተሰጥቶታል። « ዓይኔ እንባ እያፈሰሰ ነው። ህመሙ በከፍተኛ ደረጃ ያሰቃየኛል። እስከ ሁለት ዓመት እንዴት እቆያለሁ?» በማለት ይጠይቃል። በግል ሆስፒታል ለመታከም ደግሞ፤ « አቅም የለኝም ፈጣሪ ይርዳኝ እንጂ » ይላል።

አቶ ቶፊቅ መሀመድ በኩላሊት በሽታ የምትሰቃየውን ልጃቸውን ህክምና መከታተል ይችሉ ዘንድ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል «ሪፈራል» ተፅፎላቸዋል። እንደእርሳቸው ገለጻ ሐኪሙ ባለመገኘቱ « ነገ ተነገ ወዲያ » እየተባሉ ለአንድ ሳምንት ተጉላልተዋል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ አስራ ሰባት ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ደጀኔ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ጤና ጣቢያው በየቀኑ በአማካይ አራት መቶ ታካሚዎችን ያስተናግዳል። ሆኖም የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የተገልጋዮችን ፍላጐት ለማሟላት አዳግቷቸዋል።

የየካ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሴም ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው። በጤና ጣቢያው በቀንም ከአምስት መቶ በላይ ደንበኞች ይስተናገዳሉ። የእነዚህን ፍላጐት ለማሟላት ደግሞ « የባለ ሙያዎቻችን የትምህርት ደረጃ አሁን ካሉበት በበለጠ ከፍ ማለት ይኖርበታል» ይላሉ።

የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካህሳይ ገብረመድህን በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በሆስፒታሉ የሚገኙ የስፔሻላይዝድ ትምህርታቸውን ተከታትለው የተመረቁ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ ነው።

በገበያ ላይም አግኝቶ ለመቅጠር አልተቻለም። በአሁኑ ወቅትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ባላቸው ትርፍ ሰዓት አገልግሎት እየሰጡ ናቸው። የሚሰጠው አገልገሎት ከመላው ሀገሪቱ ለሚመጡ ህሙማን በመሆኑ በተፈጠረው የባለሙያ እጥረት ሳቢያ መጉላላት ይስተዋላል። የቀጠሮ ጊዜ አንዳንዴ ይቀየራል። ከዚህ በተጨማሪም እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ ቀጠሮ ሊሰጥም ይችላል። ምንም እንኳን ከባለፉት ዓመታት ችግሮቹ እየቀነሱ ቢመጡም።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፋንቱ ጸጋዬ እንደሚናገሩት፤ የሐኪሞችና ስፔሻሊስት ሐኪሞች ባለሙያዎች በበቂ የሉም። በተለይም የማህጸንና የጽንስ ስፔሻሊስቶች እጥረት አለ። ይህም በህክምና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው።

« መንግሥት ባለሙያዎችን በስፋት እያሰለጠነ ነው። እኛም ከችግሩ ስፋት የተነሳ በየካቲት አስራ ሁለት ሆስፒታል ባለሙያዎች እናሰለጥናለን። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ችግሩ ይፈታል» በማለት አስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ይገልጻሉ።

የትግራይ ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐጐስ ጎዲፋይም የሐኪሞች በተለይም ስፔሻሊስት ሐኪሞች እጥረት መኖሩን ይገልጻሉ። በአስራ ሦስት ወረዳዎች ላይ ያሉ ጤና ጣቢያዎች ወደ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልነት አድገዋል። አስፈላጊ መሣሪያዎችም ተሟልተውላቸዋል። « ሆኖም በሐኪሞች ቁጥር ማነስ ሥራቸውን መጀመር አልቻሉም» ብለዋል።

እንደ አቶ ሐጐስ ገለጻ፤ በክልሉ በሚገኙ ሆስፒታሎች የተከሰተውን የሐኪሞች እጥረት ለማቃለል የመጨረሻ ዓመት የህክምና ተማሪዎችን ካሉት ባለሙያዎች ጋር በማቀናጀት እንዲሰሩ እየተደረገ ነው። ይህም ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ ዕድል ሰጥቷል።

«በሚቀጥሉት ዓመታት ችግሩን ለመፍታት እየሠራን ነው» የሚሉት የቢሮው ኃላፊ፤ በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የሚያ ሰለጥኗቸው ባለሙያዎች በቅርቡ እንደሚመረቁ ይናገራሉ። በሚቀጥለው ዓመት የሚመረቁትን ባለሙያዎች ጨምሮ መንግሥት በቀየሰው አዲስ የሥልጠና መርሐ ግብር መሠረት እድሉን ያገኙ እና ትምህርታቸውን የሚከታተሉት ሲመረቁ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት አላቸው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመድ ኢማኖ እንደሚገልጹት፣ በእርግጥ የስፔሻሊስት ሐኪሞች እጥረት አለ።
« አሁን የምንገኘው አንድ ሐኪም እስከ ሰላሳ ሺ ለሚደርሱ ሰዎች የሚያክምበት ደረጃ ላይ ነን። ኅብረተሰቡን የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት አንድ ሐኪም አስር ሺ የሚደርሱ ሰዎችን የማከም ደረጃ ላይ መድረስ አለበት።»

አቶ አህመድ እንደተናገሩት፤ እስከ አለፈው ዓመት ድረስ በየዓመቱ ሰልጥነው የሚወጡት ሁለት መቶ ሐኪሞች ብቻ ናቸው። እነዚህ ሐኪሞች የተሻለ ደመወዝ ፍለጋ ወደ ውጭ ይወጣሉ።

ይህን በህክምና ዘርፍ የተጋረጠን ተግዳሮት ለመፍታት መንግሥት ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄዎችን ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ነው። የዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅም እንዲያድግ ተደርጓል። « ባለፈው ዓመት አንድ ሺ ሠልጣኞች፣ ዘንድሮ ከሦስት ሺ በላይ ተቀብለናል። ሰልጥነው የሚወጡትም ሀገራቸውንና ህዝባቸውን እያገለገሉ ናቸው» በማለት አቶ አህመድ ይገልፃሉ።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፣ የህክምና ባለሙያዎች የሚበረታቱበት ሥርዓት ተፈጥሯል። በሀገሪቱ ሩቅ አካባቢ የተመደቡ ሐኪሞች ከሁለት ዓመት በኋላ መንግሥት በነፃ የ’ ስፔሻላይዝድ’ ትምህርት እንዲከታተሉ እድል ይሰጣቸዋል።

«መንግሥት ከሚያደርገው እገዛ በላይ ሐኪሞች ኅብረተሰቡን ማገልገል የሚለው አስተሳሰብ በውስጣቸው ሰርጿል። ባለፉት ሦስት ዓመታት የሰለጠኑ ባለሙያዎች ዘጠና ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት ኅብረተሰቡን እያገለገሉ ነው» በማለት አቶ አህመድ የሐኪሞች ኅብረተሰቡን የማገልገል መንፈስ መጨመሩን ይናገራሉ።

መንግሥት ባለሙያዎችን ለማግኘት ዓለም ላይ ያሉ ፈጣን የማሰልጠኛ ስልቶችን በመዘርጋት እየተንቀሳቀሰ ነው። በተፈጥሮ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውን ባለሙያዎች ለአራት ዓመት ተኩል በማሰልጠን በህክምና ሙያ ላይ እንደሚሰሩ ለማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህ ዓመትም አንድ ሺ አንድ መቶ ተማሪዎች ይሰለጥናሉ።

« በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ዓመታት ሐኪሞችና ስፔሻሊስት ሐኪሞች በበቂ ሁኔታ ይኖሩናል» ይላሉ ዳይሬክተሩ አቶ አህመድ፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ደግሞ አምስት ሺ ነርሶች እንደሚሰለጥኑ አመልክተዋል።

አቶ አህመድ እንደሚናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ የስፔሻላይዝድ ስልጠና የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ አይደለም። በሌሎችም ዩኒቨርሲዎች ይሰጣል።

የሐኪሞችን እጥረት በጊዜያዊነት ለመፍታት የውጭ ሀገር ባለሙያዎች በዝቅተኛ ዋጋ ክፍያ እንዲመጡ በማድረግ ለማሰራት ከተለያዩ ሀገሮች ጋር ስምምነትም ተደርጓል።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፤ ሐኪሞች በጤና ተቋም በትርፍ ሰዓት እንዲያገለግሉ ተደርጓል። ይህም ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል። የ« ግል ህክምና መስጫ ክንፍ» ፕራይቬት ዊንግ» አገልግሎት ተጀምሯል።

« እነኚህ መፍትሄዎች ችግሩን በጊዜያዊነትና በዘላቂነት በሚቀጥሉት ዓመታት ለመፍታት ያስችላሉ» ብለዋል።