የጸረ ሙስና እርምጃ መጠናከር ለትራንስፎርሜሽኑ ስኬት

ዮናስ

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተዘጋጅቶ ይፋ በሆነበትና ለህዝብ ውይይት በቀረበበት ወቅት አንዳንዶች የማይፈጸም ነው ሲሉ ስጋታቸውን ሲገልጹ እንደበር አይዘነጋም፡፡ የነዚህ ስጋቶች መነሻም የተለያየ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በተለይም የአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና የግሉ ፕሬስ አብዛኞቹ ፀሃፍት መንግስት ዕቅዱን ያወጣው ምንም መሰረታዊ መነሻ ሳይኖረው ህዝቡን ግራ ለማጋባትና ከገባበት ውጥረት “ለማስቀየስ” ነው የሚል አይነት ዕንድምታ ያለው አስተያየት ሰጥተው የነበረ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አይ እቅዱ ጥሩ ነው፣ ነገር ግን የበጀትም ሆነ የሰው ሃይል ብሎም ከእቅዱ ስፋት አንፃር የመንግሥት የማስፈጸም አቅም ውስንነት በመኖሩ የሚሳካ አይሆንም ብለው ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ እቅዱን ለማስፈጸም መሠረታዊ አቅም ሊፈጠር ይችላል የሚል ታሳቢ ቢያዝም ኪራይ ሰብሳቢው ከመንግስት መዋቅር ጀምሮ የተደራጀና መረቡን በስፋት የዘረጋ በመሆኑ ዕንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ነው የሚል አስተያየት ሲሰጡ ነበር፡፡

የኑሮ ውድነቱ፣ የዋጋ ግሽበቱና የንግድ ሥርዓቱም በዜጎች ላይ የሚፈጥረው ጫና እንዲሁ የራሱን ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀሬ ነው ተብሎም ነበር፡፡ ከነዚህ ሁሉ የእቅዱ ስኬት ስጋት መነሻዎች እኔም

እንደ ዜጋ በተለይ በመንግስት መዋቅሩ ያለው የመልካም አስተዳደርና የሙስና ጉዳይ ለእቅዱ ስኬት ፈተና ሊሆን እንደሚችል ያለኝን ስጋት ከተገኙሁባቸው መድረኮች መካከል በአንዱ ላይ መግለጤን አስታውሳለሁ፡፡

መንግስት እቅዱን ወደ ተግባር መለወጥ ከጀመረ ደግሞ እነሆ አንድ ዓመት ከመንፈቅ አካባቢ ሆነ፡፡ በነዚህ ጊዜያት በተለይ በመሰረታዊ ልማት እና ኢንቨስትመንት አካባቢ የተሰራው ሥራ ለስኬቱ የነበረንን ጥርጣሬ ያስወገደ ነው፡፡ በአንድንድ ቦታዎችና ውስን የመንግሥት መዋቅሮች አካባቢ ጥሩ የሚባሉ ስራዎች ሲከናወኑ ብንመለከትም አልፎ አልፎ ዘላቂነት የሌላቸውና የሚዋዥቁ ነበሩ፡፡ እውነትም በአንዳንዶችን ዘንድ ስጋታቸውን ወደ መቀበል ያጋደሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር በግሌ ተረድቻለሁ፡፡

አሁን የተያዘው አቅጣጫና በተለይም በከተሞች አካባቢ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግርና የሙስና ጉዳይ ከምንጩ ለማድረቅ መንግሥት የጀመረው ጥረት የአንድ ወቅት ግርግር ሆኖ የሚቆም እንዳይሆን የሚለውን ስጋት ያስወገደ ይመስለኛል፡፡ ባጠቃላይ ለኢኮኖሚያችን እድገትና በተለይም ለተያያዝነው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማነት፤ለመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓታችን መጎልበትና ለማህበራዊ ለውጦች በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉትን ጥረቶችና ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች ከሰሞኑ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጡት ማብራሪያ መረዳት ይቻላል፡፡

በዚህ ረገድ በተለይም ከመድብለ ፓርቲ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ከተጠያቂነት እንዲሁም ሙስናንና የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብ በመስበር መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር በመንግስት በኩል የታዩትን በጎ እርምጃዎችና ጥረቶች ማየቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ሪፖርት ቀደም ብሎ በነበሩት ሳምንታት በፓርላማው ውስጥ የተቋቋሙት ቋሚ ኮሚቴዎች በየዘርፋቸው የሚገኙ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችን ከሪፖርት በዘለለ እስከ መስክ ጉብኝት የዘለቀ ጥልቀት ያለው ምልከታና ግምገማ አድርገው እንደነበር ከተለያዩ የብዙሃን መገናኛዎች አድምጠናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የበላይ ኃላፊዎች በፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡና ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ በማድረግ ማስተካከል የሚገባቸውንም እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡

ይህን አይነት አሰራር ማስቀጠልም ተጠያቂነትን በማስፈን ደረጃ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ከመሆኑ በላይ “የአንድ ፓርቲ ስብስብ” ሲባል የቆየውን ፓርላማና የ”ድርጅታዊ” አሰራር ስጋት የሚቀርፍ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ይህ የቋሚ ኮሚቴዎች የተጠናከረ ግምገማና የመፍትሄ አቅጣጫም በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ላይ ከወዲሁ ለውጥ እያመጣ መሆኑን መመልከታችንም በመንግስት ላይ ያለንን አመኔታ የጨመረ ሲሆን ዕቅዱ ስለመሳካቱም ተስፋችንን የበለጠ አለምልሞታል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርትና ማብራሪያም በዋናነት ትኩረት ያደረገው መንግስት ያስቀመጠውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ግብ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ይኸውም በአጠቃላይ ኢኮኖሚ፣ የኑሮ ውድነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የውጭ ግንኙነትን የተመለከተና የልማታችን መሠረት ከሆነው ሠላም አንፃር ትኩረት ያደረገ ሪፖርት ነው፡፡

የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠልና የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ባለፉት ስድስት ወራት መንግስት በሰራው ሰፊና የተጠናከረ ስራ ጥሩ የሚባል ውጤት መገኘቱን ያመለከተው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ግብርና ስምንት በመቶ ኢንዱስትሪው 17.9 በመቶና አገልግሎት የ11.5 በመቶ እድገት በአመቱ መጨረሻ እንደሚኖር መተንበዩንም ይገልጻል፡፡

የመንግስትን የበጀት ጉድለት መለስተኛ ለማድረግ መንግስት ከብሄራዊ ባንክ የሚወስደውን ብድር እንዳቆመና ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ቁጥጥር መደረጉን የሚገልጸው ሪፖርት ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር መንግስት ገዝቶ በማከፋፈል የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ያደረገው ጥረት ከሞላ ጎደል የተሳካ እንደነበርም ያትታል፡፡ ከሃገር ውስጥ የተለያዩ ምንጮች 45.2 ቢሊዮን ብር እንደተገኘና ከዚህም ውስጥ 41.2 ቢሊዮን ብር በስራ ላይ እንደዋለና የበጀት ጉድለቱም የ941 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ገልፀው ጥር ላይ የዋጋ ግሽበቱን ወደ 32 በመቶ ማውረድ የተቻለበትን አጋጣሚም ጠቁመዋል፡፡ ከወጪ ንግድ ዘርፍ የተገኘው 1.3 ቢሊዮን ዶላር መንግስት ለዘርፉ ያለውን ትኩረት ያመላከተ ነው፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን ደረጃ በደረጃ ለማድረቅ በተያዘው እቅድ መሠረትም የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን በመሰረታዊነት ወደ ሕጋዊ አሰራር ለማምጣትና የተመለከተው ሪፖርት ከመሬት አስተዳደር ሥርዓቱ ጋር በተያያዘም የሊዝ አዋጁን ወደ ተግባር በመለወጥ በኩል የተሰራው ስራም ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ሪፖርቱ ያብራራል። የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን ቀልጣፋ ለማድረግም በመዋቅሩ ላይ መሰረታዊ የሆነ የአደረጃጀት ለውጥ በቅርብ ጊዜ እንደሚደረግ አመልክቷል፡፡

ባጠቃላይ ልማቱን ከማስቀጠል ሰላማችንን ከመጠበቅና የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን ከማድረቅ አንፃር የቀረበው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ከምክር ቤት አባላቱ የቀረቡ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ከነምላሻቸው የተስተናገደበት ነበር፡፡

ቀደም ሲል ብዙዎቻችን የበይ ተመልካች ሆነን በቆየንባት ሃገራችን በጥቅማጥቅም የተሳሰሩት ሙሰኞች በልጽገው በኛው ላይ ሲያቅራሩ ሌባናችሁ ብለን ደፍረን ለመናገር እንኳ እንዳንችል አድርገው አፋችንን ሸብበውን ቆይተዋል። እገሌ ዘመዴ ነው፤ እገሌ አበልጄ ፤ እገሌ ደግሞ አብሮ አደጌ ሌላም ሌላም እየተባለ ምትክ የለሽ የሕዝብ አንጡራ ሃብት የሆነውን መሬት አየር ባየር ሲቸበቸቡ፣ ሳይለፉና ምንም አይነት እሴት ሳይጨምሩበት ባካበቱት ሃብት ሕገወጦች ሲበለጽጉና ገበያውን ሲያንሩ እንደነበር አንዘነጋም።

መንግስት አሁን ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣትና ሙሰኞች የተሳሰሩበትን የግንኙነት ድር ለመበጣጠስ ጠንካራ አቋም እንደያዘ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ሙሰኞቹ ጡንቻቸው ፈርጣማ ፣ ኪሳቸው የደለበ፣ ጉዳይ አስፈፃሚዎቻቸውም እጃቸው እረጅም እንደመሆኑና የረቀቀ ስልት ፈጥረው ለመንቀሳቀስ የማይታክቱ መሆናቸውን ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ህብረተሰቡ የመንግሥትን ጥረት በመደገፍ ረገድ የራሱን ገንቢ ሚና መጫዎት ይጠበቅበታል፡፡ መሬት የህዝብና የመንግስት ነው። ዜጎች በህግ መሰረት መሬት ቀርቦላቸው ሃብት ሊያፈሩ ይችላሉ፤ መብታቸውም ነው። በተግባር የታየው ግን መሬት በአቋራጭና በሕገ-ወጥ መንገድ መበልፀጊያ ሆኖ መቆየቱን ነው። ልማታዊ ባለሀብቶቻችን አስከፊ በሆነው ዓለም አቀፋዊ የገበያ ውድድር ውስጥ ራሳቸውን በመክተት ተፎካካሪ ለመሆን ሲጥሩና ራሳቸውን ጠቅመው ሃገርንና ሕዝብን ለመጥቀም ሲጥሩ፤ ከዚህ በተጻራሪው አንዳንዶቹ ግን በሕገወጥ የመሬት ሽያጭ ሃብት እያጋበሱ በሕብረተሰቡና ሕጋዊነትን ጠብቆ በሚንቀሳቀሰው ነጋዴ ኪሳራ ሲቆምሩ ቆይተዋል። ይህ አካሄድ በሃገሪቱ የልማትና የብልፅግና ተስፋ ላይ ጥቁር ጥላ የሚያጠላ በመሆኑ “ሳይቃጠል በቅጠል” ሊባል ይገባዋል፡፡ በመንግሥት መዋቅር የተሰገሰገ ኪራይ ሰብሳቢና ቦታ አሻሻጭ የሙሰኛ አቀባባይ ባለበት ሁኔታ ህብረተሰቡን በአግባቡ ማገልገልና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ አይታሰብም። ስለሆነም ይህን ከምንጩ ለማድረቅ የሊዝ አዋጁ አንድ ሁነኛ መነሻ ነው። ሙሰኞችን መዋጋት የሕዝብ ተጠቃሚነትንና የመንግሥትን የማስፈጸም አቅም ለማጎልበት የሚኖረው ድርሻም ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር ለአዋጁ ተግባራዊነት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል፡፡

ልማትን ለማፋጠን ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል። ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ መብራት፣ ውሃ፣ መንገድና መሰል የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለመዘርጋትና ለማስፋፋት ከፍተኛ አቅምን ይጠይቃል፡፡ ቁጥሩ እጅግ የሚልቀው የከተማ ኗሪም የቤት ባለቤት ለመሆን ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ቀደም ብለው ከተመዘገቡት 400 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገሚሱ እንኳን ገና የቤት ባለቤቶች አልሆኑም፡፡ እነዚህን የህዝብ ጥያቄዎች ለማሟላት መሬትን የህዝብና የመንግስት መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ሙሰኞችንና ኪራይ ሰብሳቢዎችን ገለል ማድረግ፤ብሎም ጠበቅ ያለ ሕጋዊ እርምጃ በየጊዜው መውሰድ ያስፈልጋል። በከተሞች አካባቢ ለሚነሳው የመልካም አስተዳደር ችግር ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ሽያጭ አንዱ ዋነኛ መንስኤ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሊዝ አዋጁን በተመለከተ ሌላው መነሻ ነው ሲሉ ያቀረቡት ደግሞ ከስራ እድል መፍጠር ጋር የተያያዘ ነው። መሬት በሕጉ መሰረት የመንግስትና የህዝብ ከሆነ በሚገነቡ ግንባታዎች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ወጣቶች የስራ እድል ይፈጠርላቸዋል። በመሰረቱ በሊዝ አዋጁ ላይ ምንም አዲስ ነገር የለም። መሬት በሊዝ መከራዬት ከጀመረ ሰንብቷልና። አሁን አዲሱ ነገር መሬት ከሙሰኞቹና ከደላሎች እጅ መውጣቱ ብቻ ነው።

ሁለተኛው የሙሰኞች መፈልፈያ እና መናሃሪያ ደግሞ ግብር ነው። ከጅምሩ መንግስት ልማት የሚሰራው ከየትም አምጥቶ ሳይሆን በዋናነት ከዜጎች በሚሰበስበው ግብር ነው። መንግሥት ልማትን ለማስቀጠል የሚያደርገውን ጥረት በማሰናከል ላይ የሚገኘው አንዱ ጋሬጣ የንግድ ምዝገባና የግብር ስርዓቱ ኋላቀር መሆኑና ኪራይ ሰብሳቢዎችንና አገናኝ ደላሎችን ጨምሮ ለሙሰኞች የከፈተው ቀዳዳ ነው። ግብር የመሰብሰብ ስልጣን የተሰጠው ለመንግስት ብቻ ቢሆንም፤ በመሞዳመሞድና በሕገ-ወጥ መንገድ በግብር አሰባሰቡ ሂደት ውስጥ የግል ጥቅማቸውን በጎን ሲያጋብሱ የነበሩት እነኝህ በየደረጃው በመንግሥት ስልጣን የተከለሉና ከመንግሥት መዋቅር ውጪ የሚገኙ አቀባባዮቻቸው ናቸው።

ከጸረ- ሽብርተኝነት አዋጁ ጋር በተያያዘም የፀረ ሽብርተኝነት ህግ የወጣው “ምህዳሩን ለማጥበብ ነው፣ ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው እንቅፋት ለመሆን ነው፣ ተቃዋሚዎችን ለማፈን ነው፣ ፕሬሱን ለመግደል ወዘተ” ነው ሲል “የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነኝ ባዩ ሂውማን ራይትስ ዎች ይደመጣል። በተደጋጋሚ በመንግስት እንደተብራራውም በአዋጁ ውስጥ የሰፈሩ አንቀጾች የዳበረ ዴሞክራሲ አላቸው ከሚባሉት አገሮች ቃል በቃል የተቀዳ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ መመዘኛዎችን ያሟላ እንደሆነ ከማመልከቱና በዚህም ተቀባይነትና አድናቆት የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር ያልሆነ ትችት የሚያስከትል ባልሆነ ነበር፡፡

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ከተደረጉ በኋላ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት በነጻ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ታይቶ የፍርድ ውሳኔ የተሰጣቸውንና ሌሎች ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያሉትን በተመለከተ እየተሰነዘረ ያለው ትችትም ውሃ የማይቋጥር አጉል ክስ ነው፡፡ በሸብርተኝነት ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው ፍርድ ቤት በማስረጃ አረጋግጦና ይህንኑም ተከሳሾች ለመከላከል ሳይችሉ በመቅረታቸው ሕጉ በሚያዘው መሰረት የፍርድ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ይታወቃል፡፡ በሌላም በኩል በጋዜጠኝነት ሽፋን ከኦብነግ ጋር በመሰለፍ የሃገራችንን ድንበር በሕገወጥ መንገድ አቋርጠው በገቡ ስዊድናዊያን ጋዜጠኞች ላይም የተላለፈው የፍርድ ቤት ውሳኔ የሃገርንና የህብረተሰብን ደህንነት ከማስጠበቅ ሉአላዊነትን ከማስከበር አንጻር በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት ያለውና ሕጋዊ ነው፡፡ አንድ ሉአላዊ ሃገርና የሕዝብ ተጠያቂነት ያለው መንግሥት ሊያደርገው የሚችለውም ሆነ ሊከተል የሚገባው ትክክለኛ መርህ ይህ ነው፡፡ ከዚህ በተጻራሪው መቆም እንዴት ሆኖ ነው ለሃገርና ለሕዝብ ጥቅም እንደመቆምና መሟገት ተደርጎ የሚወሰደው?

ታዲያ ይህን ሕጋዊ እርምጃ መቃወም ማለት ለማን ማሰብና ከነማን ጋር ማበር እንደሆነ ለመረዳት ልዩ ምርምር ማድረግን አይጠይቅም፡፡ ነገሩ አበው እንደሚሉት “ዘር ከልጓም ይስባል” ነውና እነዚህ በጭፍን ተቃውሞና በጥላቻ ፖለቲካ የናወዙ ኃይሎች ሰልፋቸው ከነማን ጋር እንደሆነና ምን ዓይነት ዓላማ እንዳስተሳሰራቸው ግልጽ ማሳያ ነውና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዚህ ጊዜ ባለፈበት ማደናገሪያቸው ከቶ የሚዘናጉ አይሆኑም፡፡ ከዚህ ይልቅ መንግሥት በየጊዜው አሰራሩንና አፈጻጸሙን እየገመገመና በዚህም ላይ ተመስርቶ ተገቢውን ወቅታዊ እርምትና ማስተካከያ እያደረገ ልማትን ለማፋጠን የቀየሰውን የትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ያለን ቁርጠኝነት ከምን ጊዜውም ዛሬ የላቀ መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡ የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካትም በህብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎ ርብርቡ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ከድህነት የተላቀቀችና የበለጸገች ኢትዮጵያም ትፈጠራለች፡፡