ክፍል ሁለትና የመጨረሻ
አባ መላኩ
የአፍሪካ ህብረት፤ አቶ መለስ ዜናዊ ለአፍሪካ ህብረት ዓላማዎች መሳካትና የአፍሪካን ፍላጎቶች በዓለም አቀፍ መድረኮች በማቅረብ ባበረከቱት አስተዋፅኦ ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ አቶ መለስ በተለይ አስፈፃሚ ኮሚቴውን በሊቀመንበርነት የሚመሩት አዲስ የልማት አጋርነት በአፍሪካ (ኔፓድ) ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በአፍሪካ መሪዎችና መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚቴ ውስጥም በብቃትና በቁርጠኝነት ሰርተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በአቶ መለስ ዜናዊ መሪነት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረትና በኢጋድ አማካይነት ለአፍሪካ ሠላምና ፀጥታ ላበረከተችው አስተዋፅኦ አድናቆቱን ይገልፃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረትና ለተባበሩት መንግሥታት ሠላም አስከባሪ ኃይል ጦሯን በቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ አቢዬ ማሰማራቷ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ ለሶማሊያ መንግሥትና በሶማሊያ ለተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ሠላም አስከባሪ ኃይል አሸባሪነትንና አክራሪነትን ድል ለመምታት የሚያደርገውን ጦርነት በማገዝ በአገሪቱ ዘላቂ ሠላምና እርቅ እንዲሰፍን ድጋፍ አድርጋለች፡፡
አቶ መለስ ደቡብ ሱዳን ከሰሜን ሱዳን ተነጥላ የራስዋን መንግሥት ከመሠረተች በኋላ የሠላም ስምምነቱና ድርድሩን ለማቀላጠፍና ተግባራዊ ለማድረግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ጥረት አድርገዋል፡፡ አቶ መለስ አገራቸውን አሁን የምትገኝበት በአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ስኬት እንድትበቃ በማድረግ ረገድ የላቀ ድርሻ ነበራቸው፡፡
በዚህም በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህዳሴ የአዲስ መፃኢ ዘመን የተስፋና የዕድገት ፈር ቀዳጅ በመሆን ወሣኝ ድርሻ ተጫውተዋል፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ ሞት አፍሪካን ከታላላቅ ልጆቿ አንዱን አሳጥቷታል፡፡
ዴቪድ ሺን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩ፤ አብዛኞቹ የአቶ መለስ ዜናዊ የመከላከያ ፖሊሲዎች አይለወጡም ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ በአገር ውስጥ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ለሶማሊያ ጉዳይ የሚሰጠው ትኩረት ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡ በኤርትራ ጉዳይ ላይ የሚወሰደውም አቋም አይለወጥም ብዬ እገምታለሁ፡፡
በኒያሚን ናታኒያሁም የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር፤ መለስ ዜናዊ በአገራቸው ጎበዝና ተወዳጅ መሪ ነበሩ፡፡ እውነተኛ የእሥራኤል ወዳጅም ነበሩ፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን እመኛለሁ፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፤ አቶ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ. በ1990 ዎቹ
3 ነጥብ 8 በመቶ የነበረውን የአገራቸውን የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ አሥር በመቶ ከፍ እንዲል በማድረግ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባሳየው እመርታ የሚደነቁ መሪ ናቸው፡፡
ዶክተር አርነስት ባየ ኮሮማ የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት፤ አቶ መለስ ዜናዊ የአፍሪካ ህብረትን ለማጠናከር የአፍሪካ ፒር ሪቪው ሜካኒዝም (peer review mechanism) ሊቀመንበር ሆነው በሰሩበት ወቅት ላሳዩት ውጤታማ ሥራ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ሠላም እንዲሰፍን ባከናወኑት ተግባር ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ በአህጉሩ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች አገር እንድትሆን አድርገዋል፡፡
ሩቢያህ ባንዳ የቀድሞው የዛምቢያ ፕሬዚዳንት፤ አቶ መለስ ዜናዊ ለአፍሪካ ብልፅግና ያላቸውን ጠንካራ ፍላጎት ያረጋገጡ ብልህና ቅን መሪ ነበሩ፡፡ መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለአፍሪካ በቅንነት ጠንክረው በመሥራት ባበረከቱት አስተዋፅኦ ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡
አህመድ መሐመድ ሲላንዮ የሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንት፤ የአቶ መለስ ዜናዊ ሞት ምሥራቅ አፍሪካን ታላቅ ባለራዕይ መሪ አሳጥቷታል፡፡ በሶማሌ ላንድ ሕዝብና ስም እንዲሁም በግሌ ለኢትዮጰያ ሕዝብና መንግሥት በአቶ ሞት የተሰማኝን ሐዘን እገልፃለሁ፡፡
ቢል ጌትስ አሜሪካዊ ቢሊየነር፤ አቶ መለስ ዜናዊ ደሃ ኢትዮጵያውያን በተጨባጭ ተጠቃሚ ያደረጉ መሪ ነበሩ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ፡፡
የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ፤ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ የእንግሊዝኛ ሥርጭት አንድሪው አስሞአህ የተባሉ የደቡብ አፍሪካ የደህንነት ጥናት ኢኒስቲትዩት ተንታኝን ጠቅሶ የሚከተለውን አስተላልፏል፡፡ “አቶ መለስ ዜናዊ ለአፍሪካ ራዕይ ከቆሙ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ መለስ ይህ ራዕይ ምን እንደሆነ ጠንቅቀው ተገንዝበዋል፡፡ በምን ዓይነት አኳኋን ወደተግባር እንደሚሸጋገርም የተረዱ መሪ ነበሩ፡፡ ምሥራቅ አፍሪካ አንድ የሠላም አቋም አራማጅ የነበሩ ሰው አጥታለች፡፡”
አቶ መለስ ዜናዊ ወደሥልጣን ከመጡ በኋላ በአገር ውስጥ የታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቁ ስኬታቸው ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራና ለአፍሪካ አስፈላጊ አገር እንድትሆን አድርገዋል፡፡
ፋይናንሻል ታይምስ፤ አቶ መለስ ዜናዊ የፖለቲካ መረጋጋት በማስፈንና በደሃ አገራቸው ውስጥ ላስመዘገቡት የኢኮኖሚ ዕድገት ዋጋ ለሚሰጡ ሁሉ አጥተዋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም ደሃ አገራት አንዷ ብትሆንም ባለፉት ዓመታት አማካይ ዓመታዊ አገራዊ ምርት ዕድገት 11 በመቶ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህም ከሰሐራ በታች ካሉ አገራት አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት በላይ ነው፡፡
በርካታ የአፍሪካ አገራት ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ የቻሉት በተፈጥሮ ሐብት ላይ ተመስርተው ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ይህ ነው የሚባል የተፈጥሮ ሀብት ሳይኖራት በአፍሪካ በኢኮኖሚ ዕድገት ቀዳሚዋ አገር ለመሆን በቅታለች፡፡
የሮያል አፍሪካ ሦሳይቲ ዳይሬክተር ሪቻርድ ዶውድን፤ መለስ ዜናዊ አገሪቱን ሲረከቡ ሙሉ ሙሉ ኪሳራ ላይ የነበረች አገርን አሁን ላይ ለዚህ አብቅተዋታል።
ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስትመንት በሯን ከፍታለች፣ አዲስ ያደጉትን ህንድ፣ ቱርክና ቻይና ለመሳሰሉ አገራት ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በሯን ከፍታለች፡፡ የዚያኑ ያህል ከምዕራባዊያን ጋርም መልካም ግንኙነት መሥርታለች፡፡
ዴይሊ ስታር፤ የኢኮኖሚ ዕድገት መሪ የነበሩትና አሸባሪነትን በመዋጋት የምዕራባውያንን አድናቆት ያተረፉት አቶ መለስ ዜናዊ በ57 ዓመታቸው አረፉ፡፡ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ. በ1991 የመንግሥቱ ኃይለማሪያም ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ በአፍሪካ ታዋቂ ፖለቲከኛ ወደመሆን ተሸጋግረዋል፡፡ መለስ በዓለም በድህነቷ የምትታወቀውን አገራቸውን ወደ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሸጋገር በመቻላቸው አድናቆትን አፍርተዋል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ፤ በርካታ የዓለም መሪዎች አቶ መለስ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማንሳታቸውና ለአካባቢው ሠላምና ደህንነት ላበረከቱት አስተዋዕኦ አድንቀዋቸዋል ሲል ዘግቧል፡፡ አያይዞም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ጄህኒ ከርሰን የመለስ ወዳጆችም ሆኑ ተቺዎች አፍሪካ ከታላላቅ ምሁር መሪዎች አንዱን ማጣቷ ላይ ይስማማሉ ማለታቸውን ዘግቧል፡፡
ዘ ጋርዲያን፤ እ.ኤ.አ ከ2000 በኋላ ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ ትልቅ ዕድገት ማስመዝገቧና ይህ ዕድገት በ15 ዓመታት ውስጥ በሦስት እጥፍ የሚያድግ መሆኑ መለስ ዜናዊን ድንቅ መሪ አድርጓቸዋል፡፡ አቶ መለሰ ዜናዊ የሥልጣን ዘመን ኢትተዮጵያ ውስጥ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች በመገንባታቸው በትምህርት ዘርፍ ትልቅ እመርታ ተመዝግቧል፡፡ ሴቶች መብቶቻቸው ተከብረውላቸዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) እ.ኤ.አ በ2008 እንደገለፀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሐራ በታች ከሚገኙ ነዳጅ አምራች አገራት በበለጠ ፍጥነት እያደገ ነው፡፡
እንግዲህ እነዚህ ሁሉ የአገር መሪዎች፣ ታላላቅ ሰዎችና የህትመት ሚዲያዎች ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዲህ ያለ አስደማሚ አድናቆታቸውን የቸሩት እንዲያው ዝም ብለው እንዳልሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው። እንደኔ…እንደኔ ባከናወኗቸው መልካም ሥራዎችና በግል ብቃታቸው እንደ አቶ መለስ አድናቆት የተቸረው አንድም የአገር መሪ አላየሁም።
አቶ መለስ እጅግ አንደበተ ርቱዕ ስለነበሩ በተካፈሉባቸው መድረኮች ሁሉ አድማጭን ማስደመም የሚችሉ ንግግራቸው ሁሉ ለዛ ያለው ሰው ናቸው። እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እንኳን በመድረክ ይቅርና በየቤታችን ቴሌቪዥን መስኮት አቶ መለስ ሲናገሩ በጉጉት የማይከታተል ሰው ነበረን? አቶ መለስ በበርካታ ነገሮች ዙሪያ በቂ እውቀት ያላቸው በመሆኑ የሚሰጧቸው አስተያየቶች ሁሉ እጅግ በሣልና ገንቢ ነበሩ። በተመሳሳይ የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ሁሉ በእውቀት ላይ ተመስርተው በመሆኑ ውጤታማ እንዲሆኑ አስቸሏቸዋል።
አቶ መለስ እስካሁን አገራችን ማስመዘገብ ለቻለችው ውጤት የአንበሣውን ድርሻ ነበራቸው። ይህ ብቻ አይደለም፤ ነገም አገራችን የተሻለ ዕድገት ማስመዝገብ የምትችልበትን መንገድ አመላክተውናል። በመሆኑም አገራችን የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ማስቀጠል የእኛ የቀሪዎቹ ተግባር ይሆናል። ዛሬም ራዕይህ ህያው ነው!!