የጥፋት ሃይሎቹ ሰለባ ላለመሆን ወይስ ለመሆን?

ዮናስ

ላለፉት 15 አመታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጥ ያስመዘገብን መሆናችን እና ከዚህ የዕድገት ለውጥ ጋር ተያይዞ የህብረተሰቡ የመጠቀምና ተጨማሪ ለውጦችን የመፈለግ ፍላጎቶች ጎልተው መውጣታቸው የሚጠበቅና ተፈጥሯዊ ነው። መንገድ፣ የውሃ አቅርቦት የደረሳቸው የተሻለ ጥራት ያለው አቅርቦት መጠየቃቸው፣ የሰዎች ፍላጎት ያልተገደበና ማለቂያ የሌለው ነው (Human wants is unlimited) ከሚለው የምጣኔ ሃብታዊ ሳይንስ ሀሁ የሚመነጭ ነው። ከሁለት አንዱ የተሟላላቸው ሁለቱም እንዲሟላ ይጠይቃሉ። ጨርሶም ያልደረሳቸው ቅሬታ ማንሳታቸው ተገቢና ጤናማ ነው የምንለውም ከላይ ስለተመለከተው አመክንዮ ነው። ስለዚህም እድገቱ እየቀጠለ ሲመጣ ሕብረተሰቡ የተጠቃሚነት እና የተደራሽነት ጥያቄዎችን ያቀርባል። ያም ሆኖ ግን የሁሉንም ፍላጎት በአንድ ጊዜ ለማሟላት ከባድ መሆኑና በዚህ መሃል ክፍተቶች  የመፈጠራቸውን እውነታ አለማጤናችን ሌላ ተልእኮ ካላቸው ሃይሎች ሰበካ ተጠልፎ ዋጋ እያስከፈለን ነው።

ከነዚህ ክፍተቶች እና ዋጋ እንድንከፍልና የተላላኪዎች ሰለባ እንድንሆን ካስቻሉን መካከል በዋናነት ጎልቶ የሚወጣው የወጣቶች ሥራ አጥነት ነው። ይህ ቁጥር ከሌሎች ሀገሮች አጠቃላይ የህዝብ ብዛታቸው አንጻር ሲሰላ ከፍተኛ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ቢወጡም፣ ሁሉንም ማስተናገድ ወይም መሸከም የሚችል የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት በተፈለገው ደረጃ ማድረስ ያለመቻሉን በአግባቡ ያልተገነዘቡ ወይም እንዲገነዘቡ ያልተደረጉ ወጣቶች ቅሬታ ቢያነሱ ተገቢና የዜግነት መብታቸው ነው። ችግሩ በአንዳንድ ዳተኛ አመራሮች እንዝህላልነት የጎደለው ክፍተት በጥፋት ሃይሎች ሰበካ ተጠልፎ ሰሞኑን ለገጠሙን እና ገና ላልተወጣናቸው ምስቅልቅሎች መዳረጉ ነው። ሥራ አጥነቱ ደግሞ በከተማም በገጠርም መኖሩ እና ሌሎችም ችግሮች ተደማምረው ያስከተሉት በመልካም አስተዳደር የሚገለፁ ጉድለቶች ለጥፋት ሃይሎቹ ምቹ መደላድል ፈጥረዋል። እነዚህ ክፍተቶች ላይ የአመጽ ኃይሉ እየሰራ ለመሆኑ ማህበራዊ ሚዲያዎች ለብቻቸው በቂ አስረጅ ናቸው። አስቀድሞ  ወጣ ገባ በሚመስል መልኩ የታዩት ብጥብጦች እና አሁን ደግሞ በስፋት የሚስተዋሉትም በወጣቶቹ ላይ የአመጽ ኃይሉ እየሰራ ስለሚገኝ ነው። የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት የበለጠ ፈጣን እና አስተማማኝ ደረጃ ላይ ካልደረሰ እና በዚያው ልክ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ማረጋገጥ ካልተቻለ ይልቁንም ለዚህ የሚመጥን አመራር እስካልተገነባ   ብጥብጡ የሚቀጥልበት እድል የሰፋ መሆኑንም ማጤን ያስፈልጋል።

ለገባንበት ቀውስ የአዲስ አበባ የማስፋፊያ  ማስተርፕላን  ጥሩ ማሳያ ነው። ይኸውም የዚህ ማስተር ፕላን እቅድ በሶስተኛ ወገኖች ተጠልፎ ለህብረተሰቡ በቀረበበት አግባብ ሳይሆን ከዘላቂ የከተሞች እድገት ጋር ተመጋጋቢ የሆነ የጋራ ልማት ተጠቃሚነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ በአዎንታዊ ፍላጎት የተዘጋጀ መሆኑን የተመለከተው እና የተጠለፈበት አግባብ ነው። አመራሩ ከግንዛቤ ጋር ተያይዞ አንዳች ነገር ባለመስራቱና መድረኮችን ባለመፍጠሩ ከተላላኪዎቹ ዘንድ ሕዝቡ ላይ የተረጨው የተሳሳተ መረጃ ሕብረተሰቡን ወደ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተቱ ለብጥብጥ በር ከፍቷል።  

ከዚሁ ጋር ተያይዞ  ለኦሮሚያ ከተሞች እድገት አይነተኛ ጠቀሜታ ያለው አዋጅ ወጥቶ የነበረ ቢሆንም በዚህ አዋጅም ላይ ከሕብረተሰቡ ጋር የጋራ ግንዛቤ ባለመወሰዱ ጥርጣሬዎችን ማስከተሉ እና የአመጽ ኃይሎች የተጠቀሙበት መሆኑም ሌላኛው የመንግስትን ቀርነቶች እና ሲከፋም ዳተኝነትን የሚያጠይቅ አስረጅ ነው። ስለሆነም ለልማት የተቀረጸ አጀንዳ ተጠልፎ ለአፍራሽ ተልእኮ ጠቀሜታ ሲውል ዳተኝነት ካልተባለ ምን ሊባል ነው?።  

ኢንቨስትመንት የሀገር እድገት ጉዳይ ነው። የሥራ ዕድል የመፍጠር ጉዳይ ነው። የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ጉዳይ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳይ ነው። ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ እድገት ነው። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረግ ሽግግር ነው። በአጠቃላይ ኢንቨስትመን በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለንተናዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ ዘርፍ ነው። የዓለም የእድገት ሽግግር ያለፈበት ሒደት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ እንኳ በሚገባ ግንዛቤ መፍጠር ሲቻል “የአርሶ አደር መፈናቀል” በሚል የተላላኪዎች ፕሮፖጋንዳ ተጠልፎ እስካሁንም ላለተቋጨ መመሳቀል ያበቃን የኢኮኖሚያችንን መወናጨፍ የሚመጥን አመራር በተገቢው ሰአትና ቦታ ባለማስቀመጣችን ወይም ባለመገንባታችን የመሆኑን እውነታ መንግስት ሳያላምጥ ሊውጣት ይገባል። ከነሃሴ 10 እስከ 15 የተካሄደውም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ግምገማ ያመላከተውም ይህንኑ ነው።

ለዚህ፣ ለበሳል አመራር የሚመጥን አቅም ቢገነባ ኖሮ ከአርሶ አደር መፈናቀል ጋር ተያይዞ የተራገበው ዋጋ ባላስከፈለን ነበር። ምክንያቱም የተቀደሰውን እና ከላይ ለተመለከቱት ሃገራዊ አጀንዳዎች ለሚሆኑ መሬቶች  የሚሰጠው የመሬት ካሳ ገበያን ያማከለ እና የገንዘብ የመግዛት አቅምን ያገናዘበ እንዲሆን አስቀድሞ መስራት ስለሚቻል፤ ሁለተኛ ካሳውን አርሶ አደሩ ከተቀበለ በኋላ ምን ላይ እንደሚያውለው? እንዴት ዘላቂነት ወዳለው ሕይወት ካሳውን መለወጥ እንደሚችል የሚያግዝ አሰራር እና ስርአት መዘርጋት ስለሚቻል፤ በለቀቀው መሬት ላይ በሚገነቡ የኢንቨስትመንት እድሎች አርሶ አደሩ ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር በመዘርጋት አርሶ አደሩ እና ልጆቹ የሥራ ዕድሎች የሚያገኙበትን እድሎች በመፍጠር ከአሉባልታ የታቀበ ህብረተሰብ መፍጠር ስለሚቻል።

ከዚህ በተያያዘ የሚነሱት የወረዳ እና የዞን ጥያቄዎች ናቸው። ሰፋፊ ወረዳዎች በመኖራቸው ለአሰራር ቅልጥፍና አመቺ አለመሆናቸው ተነስቶ ነበር። በተለይ በ22 ወረዳዎች አገልግሎት ለማግኘት ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ርቀት የሚጓዝ በመሆኑ ለአሰራር አመቺ በሆነ መልኩ ወረዳዎች ተፈቅደው ችግሩ ተቀርፏል። የዞን ጥያቄዎችም በኢሊባቡር ለረጅም ጊዜ ሲጠይቅ ነበር። በደሌ ላይ ዞን እንዲቋቋም ከሕብረተሰቡ ጋር ተማክረን ፈተነዋል። እንዲሁም ምዕራብ ጉጂ በተመሳሳይ ሁኔታ ቡሌ ቦራ ላይ የተፈቀደበት ሁኔታም አለ። 

ይህ እና ይህን መሰል ስራ ባለመሰራቱ ተላላኪ ሃይሎቹ መንግስት ባልሰራቸው የመልካም አስተዳር ጉድለቶች መነሻ ሕብረተሰቡን ወደ ሚፈልጉት አጀንዳ ለመጠምዘዝ አልከበዳቸውም። አሁን መታወቅ ያለበት እነዚህ ሃይሎች በመልካም አስተዳር ጉድለት ሽፋን ሕብረተሰቡን ማንቀሳቀስ ከቻልን ለምን ብጥብጡን ወደ ስርዓት ለውጥ  አናደርሰውም ብለው እየሰሩ የመሆኑ እውነታ ነው። ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመገርሰስ ወጣቱ ላይ እየሰሩ ናቸው። ስለዚህም የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቀዎች ይዘት በመቀየር ወደ ስርዓት ለውጥ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መንግስትና አመራሩ ተገንዝበው ስራቸውን ህዝባቸውን ከማወያየትና ከማስገንዘብ ሊጀምሩ ይገባል።

ለዚህ ድምዳሜ በቂ ማሳያ የሚሆነው ይህ የጥፋት ኃይል በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰርጎ በመግባት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን የኦነግ ባንዲራና በጨቋኙ ጊዜ የቀረውን ከተቀበሩበት አንስቶ ማውለብለቡ እና የብሄር ብሄረሰቦች ሁሉ አቀፍ መብት የተንጸባረቀበትን ሰንደቅ አላማ ለመተካት ሲሞክሩ መታየታቸው ነው።  ሰልፍ  ማድረግ መብት ቢሆንም ጥያቄው ሰልፉን የጠራው አካል ማን ነው? ሰልፉ ለምን ዓላማ ነው የተጠራው? ሰልፉ የት እና መቼ ነው የሚከናወነው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ የሌለው ሰልፍ የሚሆነው አመጽ ብቻ ነው ።

እንደማንኛውም ግለሰብ በማሕበራዊ ድረ ገፆች የተጠራ ሰልፍ ነው የሚል መላመት ተይዞ ከመንግስት የሚሰጥ ምላሽ መጠበቅም ተገቢ ያልሆነ የዋህነት ነው። መንግስት ለባለቤት አልባ ሰልፎች ከዚህ በፊት ምላሽ የሰጠው ሕብረተሰቡን ከተሳሳተ መረጃ መጠበቅ ካለበት ኃላፊነት መነሻ እንጂ ለሰልፎቹ እውቅና በመስጠት አለመሆኑ መታወቅ አለበት። ሰልፉም የዋለው ለሁከት እና ለብጥብጥ ነው። የዜጎችም ህይወት ጠፍቷል። መሆን ያልነበረባቸው በርካታ ኃላፊነት የጎደላቸው ተግባሮች መፈጸማቸውን ተገንዝቦ ከጥፋት ሃይሎቹ የጠለፋ ዘመቻ መታቀብ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነትና ግዴታ ነው።

በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉ እስረኞችን ለማስፈታት መሞከር፣ የፀጥታ ኃይሎችን መሣሪያ በኃይል የመቀማት፣ የፀጥታ ኃይሎችን በጦር መሳሪያ መግደል፣ እነዚህ ተግባሮች በምንም መመዘኛ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የወለዳቸው ናቸው ብሎ  መውሰድም ምክንያታዊ አይሆንም። በመልካም አስተዳደር ሽፋን በሌሎች ሀገሮች እንደሚደረገው ግልፅ የሆነ የቀለም አብዮት ነው የጥፋት ኃይሉ ለመፈጸም የሞከረው። በየክልሎቹ የተደረጉትን እንቅስቃሴዎች ስንመለከትም የተበታተኑ ሳይሆን ግንባር ፈጥረው የተፈጸሙ ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።

ባጠቃላይ፣ የጥፋት ኃይሎቹ ሕዝባዊ መሰረት ይዘው እየሰሩ አይደለም። እነዚህ ኃይሎች መሰረታቸውን ያደረጉት ባልተሰሩ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች እና በኪራይ ሰብሳቢው ላይ ነው። ስለሆነም ያለው አማራጭ፣ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ሀገር እንዲበትኑ መፍቀድ፣ ወይም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እና የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚን ነቅሎ መጣል ብቻ ነው።