ለፀረ-ሰላም ኃይሎች የዘረኝነት ፕሮፖጋንዳ እንዳንጋለጥ…! 

                                                       ቶሎሳ ኡርጌሳ 
ሰሞኑን የወጣው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) መግለጫ አንድ ጉዳይን አስታወሰኝና ብዕሬን ለማንሳት ፈቀድሁ። ይኸውም “…ህዝቡ የውጭም ሆነ የውስጥ ፅንፈኛ ፀረ- ሰላምና ፀረ- ልማት ኃይሎችን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግሉ የገነባውን ስርዓት በቀጣይነት ለማሻሻል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መጠጊያ አድርገው ሁከትና ትርምስን ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ጥረት በፅናት እንዲመክትና በሀገራችን ህዝቦች ብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነትና አብሮነት በአስነዋሪ የዘረኝነት ፕሮፓጋንዳቸው ለማላላት የሚያደረጉትን አፍራሽ እንቅስቃሴ እንዲያመክነው ጥሪያችንን እናቀርባለን” የሚል ነው። 
ይህ ከመግለጫው ቀንጭቤ የወሰድኩት ሃሳብ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኙና በዘረኝነት ላይ በመንተራስ የህዝቡን የጠነከረ አንድነት በማላላት በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተውን ልማታዊና ዴሞክሲያዊ ስርዓት ለመናድ ያለመ በመሆኑ መመከት እንዳለበት የሚያሳይ ነው። እርግጥም እነዚህ ሃይሎች ሀገራችን ውስጥ አንድ ክስተት በተፈጠረ ቁጥር የሚያካሂዱት እንጉርጉሮ የህዝብን አንድነት የሚያላላ ብቻ አይደለም። ከዚህም ተሻግሮ እጅግ ኋላ ቀር በሆነ መንገድ የዘረኝነት አጀንዳቸውንም ለመርጨት ይሞክራሉ። እነዚህን ፅንፈኛና ፀረ-ሰላምና ፀረ-ህዝብ ሃይሎች ህዝቡ በምንም ዓይነት መልኩ ሊሰማቸው የሚገባ አይመስለኝም። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ውስጥ በነባራዊነት ሊፈጠር በሚችል ጊዜያዊ ችግር ምክንያት እነዚህ ሃይሎች ሁከት ቀስቃሽ አሉባልታዎቻቸውን ሰንቀውና የነገር ካራቸውን ስለው በየሚዲያዎቹ ሲያቅራሩ ማየት የተለመደ በመሆኑ ነው። 
እርግጥ በተለይም እነርሱ ውጪ ሆነው በተደላደለ ህይወት እየኖሩ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚካሄዱ ማናቸውም ጉዳዩች የሚጥሟቸው አይደሉም። ስለ ሀገራቸው ከማሳብ ይልቅ በሰው ሀገር ውስጥ ሆነው ህዝባቸውን ለማተራመስ የሚከጅሉ የሴራ ንድፈ-ሃሳብ አራማጆች ናቸው። ለእነዚህ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች “የሰው ወርቅ አያደምቅ” የሚለው ይትብሃል ምናቸውም አይመስለኝም። ሆኖም አባባሉ የራስ ባልሆነ ወርቅና ጨርቅ መድመቅ የማያኮራ፣ የሰው ነገር ሁሌም የሰው፣ እንዲያውም የማታ ማታ የሃፍረት ሸማን ማከናነቡ የማይቀር መሆኑን የሚያመላክት ነው። እንዲያውም እዚህ ሀገር የሚከናወኑ ማናቸውም ተግባራት አንዱን ወገን የሚጠቅምና ሌላውን የሚጎዳ አስመስለው ያቀርባሉ። ሃቁ ግን እዚህ ሀገር የተመሰረተው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ሀገር ቤት ያለው ዜጋ የሚገነዘበው ነው።   
ዛሬ ላይ እነዚህ ፅንፈኞች ባህር ማዶ ቁጭ ብለው የሚያስደምጡን መሪ መፈክርም ማረጋገጫ የሌላቸውን ቅንጭብጫቢ ሃሳቦችን እየገጣጠሙ ማውራት ነው። አንዳንዶቹ በወንጀል የሚፈለጉ አሸባሪዎች ፣ የቀድሞው ስርዓት ናፋቂዎች፣ የሀገራችን ጠላት የሆነው የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች እንዲሁም ከእንቅልፋቸው ብንን ሲሉ ኢትዮጵያ ተበታንና የምትታያቸው ሃይሎች ናቸው። እነርሱ በሚሰበሰቡባት ሀገረ- አሜሪካ አሊያም ሌላ ሀገር ውስጥ ሆነው የሚሰጥዋቸው መሰረተ- ቢስና ዘረኛ አስተያየቶች፤ ቁም ነገር አልባ ከመሆናቸው ባሻገር የኮሜዲያንነት ባህሪይን እየተላበሱ መጥተዋል።
እነዚህ ፖለቲካን የማያውቁ አሊያም ፖለቲካውን ገና ዳዴ እያሉ የሚገኙ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች፡ በሀገረ- አሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ የእምነት ተቋማትንና የንግድ ቦታዎችን በፖለቲካና በዘረኝነት ስም እየፈረጇቸው መሆኑን ብትሰሙ ከቶ ምን ትሉ ይሆን?—አዎ! ወጉን ያጫወተኝ ለሃያ ዓመታት አሜሪካ የኖረ አንድ ወዳጄ ሲሆን፤ የወዳጄን ጨዋታ በብዕሬ እንዲህ እንደወረደ አቀርበዋለሁ።…
…አክራሪ ፖለቲከኞቹ በአንድ የእምነት ተቋም አሊያም የንግድ ቦታ ተቀጣጥረው ለመገናኘት ከፈለጉ፤ በዚሁ ሁናቴ ቀጠሮ መያዛቸው አይቀርም። ታዲያላችሁ እኔም ወዳጄን “በምን መልኩ” ማለቴ አልቀረም። እርሱም ለጠቀና እንዲህ አለኝ።… ይኸውልህ በሀገረ- አሜሪካ አንድ ስቴት ሁለት የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ያለ እንደ ሆነ… ጓድ የት እንገናኝ? የቅንጅቱ ወይስ የኢህአዴግ? በማለት ቀጠሮ ይይዛሉ።
ምን ይህ ብቻ!? ንግድ የሚጧጧፍበት ቦታ ለመገናኘት ከፈለጉም በተመሳሳይ መልኩ ቀጠሮ መያዛቸው አይቀርም። እርግጥም ጉዳዩ ያስገርማል። እነዚህ ወገኖች በሰለጠኑት ዓለም እየኖሩ ኃይማኖትን እና ፖለቲካን ንግድን እና ፖለቲካን ለይተው የማያውቁት አክራሪ ኃይሎች ናቸው። እኔን የደነቀኝ እና ያልገባኝ ጉዳይ ግን የእምነት ተቋማት እና የንግድ ቦታዎች በፖለቲካ ስም መሰየም ያስፈለገበት ምክንያት ነው። ግና እነዚህ ፀንፈኛ ሃይሎች በኃይማኖትን ጨምሮ በእያንዳንዱ ጉዳይ ሽፋን ፖለቲካዊ አጀንዳቸውን ለመፈፀም የማይቀነጥሱት የቅጠል ዓይነት እንደሌለ ስለሚታወቅ ነገረ-ስራቸው እምብዛም እንደማይደንቅ ይኸው ወዳጄ አጫውቶኛል።
ፅንፈኞቹ ለሀገር የሚመኙት ምርጥ እቅድ እና ኘሮግራም፣ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ መንደፍን ሳይሆን ብሔርን እና ኃይማኖትን ከለላ በማድረግ ሁከት እና ብጥብጥ ማስነሳት እንዲሁም በድህነት የምትማቅቅ ሀገርን መፍጠር ነው። እርግጥም እንደ እነርሱ እሮሮ እና እንደ እነርሱ እርግማን ይህቺ ሀገር ድሮ ነበር ሊያበቃላት የሚችለው፡፡ ይሁንና ሀገራችን የህዝብን ኑሮ በተጨባጭ በመለወጥ ላይ የሚገኝ መንግስት የታደለች እንዲሁም ተታልሎና በውሸት ተገፋፍቶ ካልሆነ በስተቀር ባህር ማዶ ቁጭ ብሎ ለሚቀነቀን ተራ ወሬ ጆሮውን የሚያውስ ህዝብ የሌለባት በመሆኗ ፍላጎታቸው በረሃ ላይ እንደተዘራ ዘር መክኖ የሚቀር ይመስለኛል። በተለይም ከሰሞኑ ኢህአዴግ ባወጣው መግለጫ ላይ ህዝቡን የሚያስመርሩ አስፈፃሚዎችን እስከ ታች ድረስ በመውረድ በድርጅትና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ግምገማ እንደሚያካሂድ ቃል በመግባቱ ይህ ቀዳዳ እንደሚደፍን በእርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። 
ማንኛውም ሀገራዊ ችግር መፍትሔ የሚያገኘው ሀገሪቱን በመምራት ላይ በሚገኘው መንግስት እንጂ በእነዚህ ፅንፈኛ ሃይሎች አለመሆኑን የሚገነዘበው የሀገራችን ህዝብ፤ የፀረ-ሰላምና የፀረ-ልማት አጀንዳን የሚያራምዱ ፅንፈኞችን አሉባልታ ካለመስማት ባሻገር በመሃሉ የሚገኙ የእነርሱን የዘረኝነት አጀንዳን ለማስፈፀም የሚሹ ወገኖችንም ማንገዋለል ይኖርበታል። ህዝቡ በተለያዩ ወቅቶች እነዚህ ሃይሎች ሌላው ቢቀር “ኢትዮጵያን አትርዷት” የሚል አጀንዳን ይዘው ሲያወነቅኑ እንደነበር ያውቃቸዋል። ባህር ማዶ የሚገኙና ማንነታቸውን በውል ያልተገነዘቡ ዲያስፖራዎችን የእነርሱ ተከታይ ለማድረግ ብሎም እርጥባን ለመለመን በአምሳያ ሚዲያቸው የማይቀባጥሩት ነገር እንደሌለም ያውቃል።
አዎ! እርግጥም እዛው ባህር ማዶ ተቀምጠው የመንግስትንና የህዝቡን መልካም ስም ለማጉደፍ የማያዥጎደጉዱት የአሉባልታ ጋጋታ የለም። ምን አለፋችሁ! በአሜሪካ ሆሊውድ በተሰኘ የፊልም ኩባንያ ውስጥ የሚፈበረኩ “ሆረር” የተሰኙ አስፈሪ እና እርስ በርስ የመበላላት ድራማዊ ትዕይንትን ከሚያሳዩ ፊልሞች ጋር በቀጥታ በማዛመድ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ስርዓትም ልክ እንደ ፊልሙ ሕዝቡን እርስ በርሱ እንዲበላላ እያደረገ ነው ሲሉ እስከመወትወት ይደርሳሉ። ምን ይህ ብቻ! በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ በአንድ ወቅት አንድ የሩቅ ምስራቅ ሀገር ውስጥ የሚገኝ ፖሊስ ያደረገውን ተግባር የኢትዮጵያ ፈፀመው ብለው ይለጥፉታል። ህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ተግባሩን እየከወነ ያለበትን ከተማ የለለ እንቅስቃሴን በፎቶ በማሳየት ‘የእገሌ ከተማ ህዝብ አድማ መታ’ ብለው ያቀርባሉ። ሌላ…ሌላም። እርግጥም የመወትወታቸው ጉዳይ አስገራሚ እና ሰበካቸውም አስቂኝ ነው። ሆኖም ገና ለገና ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ስለ ሀገሩ በቂ ግንዛቤ የለውም የሚል የእውር ድንብር እሳቤን ይዘው ይቀርባሉ።
ይህን ተግባር የሚፈጽሙት ፅንፈኛና አሸባሪ ፖለቲከኞች ብቻ አይደለም። የግንቦት ሰባት ልሳን እንደሆነው “ኢሳት” እና የአሜሪካ ድምፅ አማርኛው ክፍል ዓይነት በሚዲያ ስም የሚነግዱ የከሰሩ ፖለቲከኞችም “በዲያስፖራ ፋኖነት” የተሰለፉ ናቸው። እርግጥ እነዚህን  “የዲያስፖራ ፋኖዎች” ጋዜጠኞች ናቸው ብሎ ለመጥራት ከሚታወቀው የአሰራር ስርአት እና የስነምግባር ሂደት ውጪ አዲስ የጋዜጠኞች መስክ እና ብያኔ ከሌለ በስተቀር በምን ስም ራሳቸውን ጋዜጠኛ ብለው እንደሾሙ እነሱው ብቻ ናቸው የሚያውቁት። 
እርግጥ ነው— ድንጋይ ለብዙ ዓመታት ውሃ ውስጥ ስለኖረ ብቻ ዋና አይማርም። የበለፀገ የሚዲያ ህግና የአሰራር ስርአት እና ስልጠና እንደ ልብ ባለበት አገር እየኖሩ “የዲያስፖራ ፋኖዎች” ግን ካሉበት ሀገር ሊማሩ የማይችሉ በመሆናቸው ውሃ ውስጥ እየኖረ ዋናን ሊማር ካልቻለው ድንጋይ የሚለያቸው ምንም ነገር ያለ አይመስለኝም። እናም ሀገር ቤት ያለው ዜጋ በእነዚህ ሃይሎች እየተከናወነ ያለውን የዘረኝነት ፕሮፖጋንዳ እንዲሁም የሌለ ነገርን ቆርጦ የመቀጠል ተግባራቸውን በውል ተገንዝቦ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊያደርግ ይገባል። 
ያም ሆነ ይህ ግን ህዝቡ ራሱ በትግሉ የፈጠረውን ስርዓት መጠበቅ ያለበት ራሱ ይመስለኛል። በየማህበራዊ ሚዲያውና በፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች እየተከናወኑ ያሉትን የዘረኝነትና ጥላሸት የሚቀባ አሉባልታዎችን መመከት ይኖርበታል። እዚህ ሀገር ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ልማታዊ ተግባራት እንዲሁም የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን እየተረጋገጠ የሚገኘውን ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል የሚያውቀው ህዝቡ እንደ መሆኑ መጠን፤ ዘረኝነትንና ከእርሱ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ማናቸውም ጉዳዩች በቂ ምላሽ በመስጠት የውጭና የውስጥ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች የሚያናፍሱትን የአሉባልታ ውዥንብር ማዳፈን ይኖርበታል። በመግቢያዬ ላይ ቀንጭቤ የጠቀስኩት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫም ይህንኑ ለማለት የተሰጠ ይመስለኛል።