ስናጣ ከመናፈቅ  ክፉ ልማድ እንላቀቅ !!

ስሜነህ

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንን በመቃወም ከዓመት በፊት በኦሮሚያ በርካታ ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከዓመት በኋላ በድጋሚ በ2008 ዓ.ም. ኅዳር ወር ላይ አገርሽቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ያም ሆኖ የክልሉ መንግሥት ይህንን ማስተር ፕላን በይፋ  ቢያጥፍም በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ግን እስካሁን ሊበርድ አልቻለም፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ከወልቃይት ማንነትና የመሬት ባለቤትነት ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ ከጐንደር ወደ ባህር ዳር፣ ደባርቅ፣ ደብረ ማርቆስ እንዲሁም የተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች በመስፋፋት ለሰው ህይወትና ለበርካታ ንብረት ውድመቶችም ምክንያት ሆኗል። በዚህ መልኩ መልስ የተሰጣቸውን ጥያቄዎች አስቀድሞ እየተስፋፋ የመጣው ተቃውሞ መልኩን እየቀየረና በአዲስ አበባም በመጠኑ እንደታየ ቢስተዋልም በተቃውሞ ሠልፉ ለመሳተፍ የሞከሩት ወጣቶች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዳልሆኑና ከኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች እንደመጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ይህን እና ባለቤት አልባ የሆነውን ተቃውሞ ወደ ሕዝባዊ አብዮት ለመቀየር የሚንደፋደፉ ሃይሎችም ስለመኖራቸው በራሱ ሰልፎቹ ባለቤት አልባ ከመሆናቸው በላይ አስረጅ አይገኝም።  በመሆኑም፣ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚሹ ሃይሎች ወደ ሕዝብ የወረወሩት የተቃውሞ አጀንዳ ነው? ወይስ በትክክል የሕዝብ ተቃውሞ ነው? የሚለውን መርምሮ በመለየት ህዝባዊ አቋም መያዝ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ፍተሻና ምርመራችን  ውጤት ደግሞ ብዙ ርቀት ሳንሄድ በጊንጪ ወይንም በአምቦ የሚገኝ የአንድ ትምህርት ቤት ይዞታ ተነካ በሚል ሰበብ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ተቃውሞ በአንድ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ማስተር ፕላን የመምጣቱ ጉዳይና፤ በተመሳሳይም ከወልቃይት ጥያቄ ወደ መንግሥት ይውረድልን ጥያቄ በአንድ ጊዜ እንዴት ተደረሰ? የሚሉት ጥያቄዎች ሁነኛ መነሻዎች ናቸው፡፡

የጊንጪውም ሆነ የወልቃይቱ ጉዳይ መልካቸውን ይቀይሩ ዘንዳ የመጀመሪያ ምክንያት የሚሆነው የመንግስት ኢምክንያታዊ የሆነ ማፈግፈግ መሆኑን ብዙዎች ይጋራሉ። ይኸውም የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተርፕላን በሕዝብ ተቃውሞ ምክንያት በመንግሥት ሲታጠፍ፣ በአዲስ አበባ የትራፊክ አስተዳደር መመርያ በታክሲ ሾፌሮች አድማ ሲቀለበስ፣ የቅማንት የማንነት ጥያቄ በቅማንት ሕዝብ ተቃውሞ በድጋሚ ሊከለስና የመሳሰሉት ክስተቶችን በተሳሳተ መንገድ መንግሥት ልፍስፍስ እንደሆነ አድርገው የተረዱ ቡድኖች ዕድሉን ለመጠቀም መሞከራቸውን የተመለከተ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግሥት ሕዝባዊነቱን ለማሳየት ውሳኔዎቹን ማጠፉ ሊያስመሰግነው ቢገባም ቀጥሎ የሚመጣውንም ቀዳዳ ማሰብ እንደነበረበት አያጠያይቅም፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ  የተቃውሞ ሠልፎቹ በጥፋት ሃይሎቹ ሴራ በመታገዝ በማኅበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች የሚጠራ እና  ተዋናዮቹ እነማን እንደሆኑና ዓላማቸው ምን እንደሆነ አለመታወቁን ሁሉም ዜጋ ሊያጤነው እና አቋሙን በይፋ ሊገልጽ ይገባል፡፡

በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልሎች የተካሄዱትን የተቃውሞ ሠልፎች እንደወረዱ እንኳ ስንመለከታቸው ሕዝቡ እንዲወጣ ጥሪ የተደረገውና እየተደረገ ያለው በማኅበራዊ ድረ ገጾች ነው፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች  በተመሳሳይ ሰዓትና ቦታ ውስጥ የሌሉ ሰዎች ስሜትን በመጋራት ብቻ የሚቀሰቅሱት እንጂ የሚመሩት አለመሆኑን በመግለጽ አደጋው የከፋ እንደሚሆን የሚያመላክቱትም ስለዚህ ነው፡፡

ስጋቱን የሚያጠነክረው ደግሞ በየማህበራዊ ድረገጾች የምናያቸው ጥሪዎችም ሆኑ ቅስቀሳዎች ስሜታዊ እና ዘረኛ  በሆኑ ንግግሮች የታጨቁ እንጂ ክርክር ተደርጐ በነጠረ ሀቅ ላይ የተመሠረቱ  አለመሆናቸው ነው፡፡ የማኅበረሰቦችና የመንግሥት ህልውና በክልል የተወሰነ ቢሆንም፣ ክስተቶችን ድንበር ዘለል ሆኖ ከመጋራት ባለፈ ለውጥንም ለማምጣት በዚሁ መስመር መንቀሳቀስ ሌላኛው እና የአደጋውን ክብደት የሚያጠይቅ ነው፡፡

የተደራጀ መሪ የሌለው ተቃውሞ መሪ እስኪያገኝ ሊቀጥል እንደሚችል ተመራማሪዎች መግለጻቸውም በተመሳሳይ የስጋታችንን ደረጃ ያብሰዋል፡፡ ተቃውሞው የታቀደ መጨረሻ እንደሌለው  በመገንዘብና የህዝቡን ስጋት ከግምት በመክተት መንግስት በተቃውሞው ግለት ልክ መልስ ሊሰጥ ከሞከረ ደግሞ ከላይ በተመለከተው አግባብ ይዋል ይደር እንጂ አስቀድሞም መልስ የተሰጣቸውን ጥያቄዎች ያነገበ ሃይል የበለጠ ድፍረትና ጉልበት እንዲያገኝ ያስችለዋል። ስለሆነም የመልስ አሰጣጡ መሠረታዊ ችግሮቹ ምንድን ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎችን በሚገባ ያገናዘበና ህዝብን ያሳተፈ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በዚህ መልኩ የሚገኝ መፍትሄ ሰላማችንን የሚያናጋ ቀዳዳ አይኖረውምና።

ከላይ በተመለከተው አግባብ እና በሌሎችም መመዘኛዎች የህዝብን ጥያቄ መሰረት ያላደረጉ መሆናቸው ሲታሰብ እየተፈጠረ ያለው ነገር  በጣም አሥጊነቱ አያጠያይቅም። ስለሆነም መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎችና የፖለቲካ ኃይሎች አስቸኳይ መፍትሔ በመሻት ረገድ ሊተባበሩና ሃገሪቱን ከነዚህ የጥፋት ሃይሎች ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ሁላችንም የችግሩ አካል በመሆናችን ላይ ከተስማማን መፍትሔውም የሚገኘው ከሁላችንም መሆኑ ላይ ልዩነት ሊኖር አይገባም፡፡ አንዱ አካል ችግር ፈጣሪ፣ ሌላው አካል ደግሞ መፍትሔ ፈላጊ መሆን የለበትም፡፡ ተቃውሞ ከተባለም ያየናቸው እንቅስቃሴዎች በተደራጀና ኃላፊነት መውሰድ በሚችል ኃይል እየተመሩ አይደለም፡፡ በአመፅ የሚገለጽ እንቅስቃሴ ደግሞ የሚያመጣውን መፍትሔ ከግብጽና ሊቢያ ተምረናል፡፡ ልክ እንደነሊቢያ ይሄኛውም በአብዛኛው እየተመራ ያለው በፌስቡክ ነው፡፡ ይህ ዓይነት የሕዝብ እንቅስቃሴ ግቡና መድረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ በመገንዘብ ኅብረተሰቡ ሊመክተው ይገባል፡፡  

ውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መስማማት፣ መፈራረምና አብረው መሥራትን የተመለከቱ ዜናዎች በመፈብረክ ህዝቡን ማወናበዳቸው የተለመደ ነው፡፡ ቢሆንም ግን፣ አብረው መስራታቸው መብት እና ለሃገራችንም ጠቃሚ መሆኑ አያጠያይቅም። ነገር ግን በኢትዮጵያ እየተገነባ ባለው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚጎለብተው እና የሚጠናከረው  ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ፓርቲዎች ብቻ መሆኑንም ህዝቡ፣ በተለይም ወጣቱ ካሳለፈው ታሪክ አስታውሶ ቆም ብሎ እራሱን ሊፈትሽ ይገባዋል፡፡ በየትኛውም ሃገር እንደሆነውና እየሆነ እንደሚገኘውም በሃገራችንም ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እየተደረገ ያለው ትጋት ለውጤት  የሚበቃው  ትግሉን የሚመሩት ፓርቲዎች እዚሁ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሲሆኑ ብቻ መሆኑንም በፌስ ቡክ ዘመቻዎች ልቡ የሚናጠው እና የአመጽ ሰለባ የሚሆነው ወጣት ሁሉ በውል ሊገነዘብ ይገባል፡፡

በተለይ በትጥቅ ትግል የሚያምኑና ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተባብረው ለኢትዮጵያ መፍትሔ እናመጣለን የሚሉ ኃይሎች አዳዲስ ችግር ይወልዱ እንደሆነ እንጂ፣ ምንም ዓይነት የተሻለ ለውጥ ሊያመጡ የማይችሉ መሆኑንም ሌላና ፖለቲካዊ አመክንዮ ሳንሻ ለራሱ መሆን ካቃተው እና ስለኛ ከሚዘላብደው የኤርትራ መንግስት መሰረታዊ ባህሪ በመነሳት አጢኖ መንቀሳቀስ  ስለሃገራችን ሰላም ይጠበቃል፡፡   

በሃገር ውስጥ የሚኖሩትንም  ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተመለከተ አንድ ፓርቲ ጠንካራ ነው የሚባለው ገዥው ፓርቲ የሚያሳድርበትን ተፅዕኖ በብቃት መቋቋም ሲችል መሆኑን በመገንዘብ መመዘን እንጂ ድክመቱን በገዢው ፓርቲ ላይ ነጋ ጠባ ሲደፈድፍ ልንሰማው አይገባም፡፡ ያም ሆኖ ግን ስለሃገራችን ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወሳኝ ናቸውና ሕዝቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መከተል ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተቃዋሚ እንዲፈጠር የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ያለበት መሆኑንም ለአፍታ መዘንጋት አይገባም፡፡ ራሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ውስጣዊ ዴሞክራሲ ኖሯቸው፣ ጠንካራ የሆነ የፖለቲካ ሥራ ሠርተው ማደራጀትና ሕዝቡን በዙሪያቸው ማሰባሰብ እንጂ በውሃ ቀጠነ አመጻን የትግል ስልት ማድረግ ዋጋው የበዛና ሳያውቀው የገባ ህዝብ እንደተለመደው ሰላምን ሲያጣት ለመናፈቅ ያበቃዋል ፡፡  

ሰላማችን ከደፈረሰና በኋላ ላይ ገብቶን በናፍቆት ከቆዘምን ድህነት ኢትዮጵያ ውስጥ ይንሰራፋል። በዚህም በደህና ሁኔታ ላይ የሚገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት ይገታል። ይህ ከሆነ ደግሞ የፖለቲካ ችግራችንም በዚያው መጠን እየተባባሰ መሄዱ የማያከራክር ይሆናል፡፡ በተቃራኒው ግን ሰላማችን አስተማማኝ ሲሆን ኢኮኖሚው ከዚህ በበለጠ ይፋጠናል። የኅብረተሰቡ ኑሮም እየተሻሻለ ወደ ጤናማና የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ የመግባት ዕድሉ እየሰፋ ይሄድና ሰላምን ከመናፈቅ ባሻገርም ማጣጣም ይቻለናል፡፡

በተስፋፋው መሠረተ ልማት ልክ የአገሪቱ አንድነት እየተጠናከረ መምጣቱንም መዘንጋት አይገባም፡፡ እየተሠራ ያለው መሠረተ ልማት ዳር አካባቢዎችን ሁሉ መሀል እያደረጋቸው መሆኑንም በተመሳሳይ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ ከምንም በላይ በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ነው። ከውጭ ሆኖ በፌስ ቡክ አብዮት የሚፈጠር ነገር ቢኖር ያጣነውን ሰላም መናፈቅ ብቻ ነው። ስለሆነም የበሰለ የፖለቲካ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖር የሚችለው መካከለኛ ገቢ ያለውና የተማረ ማኅበረሰብ ሲፈጠር መሆኑን አጢኖ እራስን ቆም ብሎ ማየትና ከላይ ከተመለከቱት እና መልስ ካገኙ የሰነበቱ መሆናቸው ከሚታወቁቱ መፈክሮች ባሻገር ለሚገኘው ሃይል ተገቢውን ምላሽ መስጠት ከተለመደው ሰላምን ስናጣት የመናፈቅ ልማድ ልንላቀቅ ይገባል፡፡