የቤት ሥራችንን በአግባቡ ሠርተን እናጠናቅቅ!

ብ. ነጋሽ

ብቅ ጥልቅ እያለ ምቾት በሚነሳ የሰላምና መረገጋት ሁኔታ ውስጥ መኖር ከጀመርን ከራረምን፤ በአገራችን የምንኖር የሰላምና የተሻለ ህይወት ተስፈኞች ኢትዮጵያውያን፤ ይህ ብቅ ጥልቅ የሚል ምቾት የሚነሳን ሁኔታ የጀመረን በ2004 ዓ.ም. አጋማሽ ነበር። አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ የእስልምና ተቋምና መስጊድ ውስጥ እስላማዊ መንግሥት የመመስረት የሩቅ ግብ ይዞ በጥቂት ግለሰቦች ተጀምሮ የነበረው የአክራሪነት እንቅስቃሴ ነው። ይህ የአክራሪነት እንቅስቀሴ ከቀፎው ወጥቶ በአዲስ አበባ አንድ ሁለት መስጊዶች ውስጥ የዐርብን ዕለት የፀሎት ሠርዓት አስታኮ በየሳምንቱ፤ እንዲሁም በትልቅ ጀማ የሚከበሩ የኢድ የጸሎት ሥርዓቶችን እየጠበቀ ከሁለት ዓመታት በላይ ምቾት ሲነሳን እንደነበር እናስታውሳለን።

ይህ የአክራሪነት እንቅሰቃሴ እዚሁ አገር ውስጥ የተፀነሰ ቢሆንም፤ መቀመጫቸውን ኤርትራ ባደረጉ የኤርትራ መንግሥት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች፤ እንዲሁም የሩቅ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሲራገብ እንደነበረም እናውቃለን። በኤርትራው Horn TV አማካኝነት የሚተላለፈው ኢሳት የተሰኘ የቴሌቪዥን ስርጭት፤ እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው በድረገፅና በፌስ ቡክ የአክራሪነት እንቅስቃሴውን ሲያበረታቱ እንደነበረ እናስታውሳለን። ሕዝበ ሙስሊሙ ከየት እንደመጡ የማያውቃቸውን የሁከት ጥሪዎች እያስተላለፉ ስሜታዊ ወጣቶችን በማነሳሳት ሰላማዊ የፀሎት ሥርዓቶችን እስላማዊ ባልሆነ አኳኋን ያውኩ እነደነበረም አናስታውሳለን። ይህን ዓለምን ያሸነፈ የአሸባሪነት ርዕዮተ ዓለም የአክራሪነት ዝንባሌ በዘገባ ሽፋን በአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ፕሮግራምም (ቪኦኤ) ይቆሰቁስ ነበር። በወቅቱ ቪኦኤ ያሰራጫቸውን ዘገባዎችና ፕሮግራሞች ለማስታወሻ ብላችሁ ዳውን ሎድ አድርጋችሁ የያዛቸሁ ካላችሁ መለሰ በሉና አዳመጡ። እንዴት አደገኛ እነደነበረ አሁን በደንብ ይታያችኋል።

ያም ሆነ ይህ፤ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ያህል በኤርትራ ተላላኪዎችና እዚህ አገር ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ካባ ደርበው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ሲራገብ የቆየው የአክራሪነት እንቅሰቃሴ የሕዝቡን ድጋፍ ስላላገኘ፤ በተለይ አብላጫ ቁጥር ባለው ሙስሊሙ ሕዝብ ባለመታቀፉ፤ እንዲሁም መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ተግባር በያዘው ፅኑ አካሄድ ይፋ ወጥቶ ማወክ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ። ጠፍቷል ማለት ግን እንዳልሆነ ልብ በሉ። እስላማዊ አክራሪነት ዓለም አቀፍ መረብ ያለው በመሆኑ እንዲህ በቀላሉ የሚጠፋ አይደለም። ተዳፍኖ ይቆያል፤ ይገኛል።

ይህ የአክራሪነት እንቅስቃሴ ተዳፍኖ ዓመት እንኳን ሳይቆይ በኦሮሚያ ክልል ሕዝቡ ያነሳውን “ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ይከበርልኝ” የሚል ጥያቄ እንዲሁም፤ የመልካም አስተዳደር መጓደልና የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት የፈጠረው ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መዛነፍ ያስከተለው ቅሬታ የቀሰቀሰውን ተቃውሞ በመጥለፍ ለህይወት መጥፋት፤ ለመንግሥትና ለግለሰቦች ንብረት መውደም ምክንያት የሆነ ሁከት ተቀስቀሷል። ይህ በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች በቅብበሎሽ እየተዛመተ ለወራት የዘለቀው ሁከት ይመራና ይራገብ የነበረው በእነዚያው የአክራሪነቱን እንቅስቃሴ ሲመሩ በነበሩ የኤርትራ መንግሥት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች ነበር። ቪኦኤም እንደተለመደው ይህን ሁከት በማጋነንና በማበረታታት የድርሻውን ተወጥቷል።

ይህ በዋናነት በማህበራዊ ሚዲያ፤ በተለይ በፌስ ቡክ እየተመራ እዲሁም በኢሳትና በቪኦኤ እየተበረታታ በኦሮሚያ ከተሞች ተቀስቅሶ የነበረውና በአብዛኛው እድሜያቸው እስከ 16 ዓመት በሚሆኑ ልጆችና እስከ 10ኛ ክፍል ባሉ ተማሪዎች የተካሄደው ሁከት የአብላጫውን ሕዝብ ድጋፍ ባለማገኘቱ፤ መንግሥትም ተገቢ በሆኑ ጥያቄዎች ዙሪያ ከሕዝቡ ጋር በየደረጃው ባደረገው ውይይት አንዳንዶቹ ምላሽ በማግኘታቸው፤ ሌሎቹ ላይ ደግሞ ምላሽ የማግኘት ተስፋ ስለተፈጠረ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ሊጣስ ነው የሚል ስጋት አሳድሮ የነበረው የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ረቂቅ ሕዝቡን ከስጋት ነጻ በሚያደርግ አኳኋን እንዲሰረዝ በመወሰኑ፤ ወዘተ. ሁከቱ እንዲበርድ ተደርጓል፤ ውጥረቱም ረግቧል።

ከዚሁ የኦሮሚያ ከተሞቸ ሁከት ጎን ለጎን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ጎንደር ዞን ለቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ከተሰጠው ምላሽ ጋር በተያያዘ ሁከት ተቀስቀሷል። በዚህ ችግር ዙሪያ በተወሰነ ደረጃ የክልሉ አመራር የፈጠረው ችግር እንዳለ የሚያመለክቱ ሁኔታዎች ቢኖሩም፤ ሁከቱ ይመራ የነበረው ግን ያው በኤርትራ መንግሥት ስር በተጠጉ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች ነበር።

ይህ የኦሮሚያውና የአማራው የሰሜን ጎንደር ዞን ሁከት ከሞላ ጎደል ተቀልበሶ መንፈቅ እንኳን ሳንቆይ እነዚያው የኤርትራ መንግሥት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ የአሃዳዊ ሥረዓት ተስፈኛ ትምክህተኞችና የመገንጠል አባዜ የሚነዳቸው ጠባብ ብሄረተኞች በማህበራዊ ሚዲያ የሁከት ክተት አወጁ። በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች፤ ከአስራ አምስት ቀናት በፊት በጎንደር ከተማ የተካሄደው መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች የተሳተፉበት ሕገ ወጥ ሰልፍ፤ በባህርዳር ከተማ የተካሄደውና በተለይ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተሞክሮ የከሸፈው ተመሳሳይ ሕገ ወጥ ሰልፍ ኤርትራ ውስጥ የተጠጉ ትምክህተኞች በማህበራዊ ሚዲያ የመሩት ነው። በሌሎች የክልሉ ከተሞች ሁከት ቀመስ ሕገ ወጥ ሰልፎች እንዲካሄዱ ተመሳሳይ የማህበራዊ ሚዲያ ጥሪ ቢተላለፍም፤ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ በፈስቡክ ወሬነት ቀርቷል።

በኦሮሚያም በምስራቅ ወለጋ በነቀምት፤ በምእራብ አርሲ በሻሸመኔ እና በምስራቅ ሐረርጌ በአወዳይና በሐረር ከተማ አቅራቢያም ተመሳሳይ ቅስቀሳ ተደርጎ ኃይል አዘል ሕገ ወጥ ሰልፎች ተካሂደዋል። በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ተመሳሳይ ኃይል አዘል ሰልፎች እንዲካሄዱ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢተላለፍም ግን ሳይሳካ ቀርቷል። በሕዝቡ ጥሪውን አልቀበልም ባይነት፤

በአዲስ አበባም ተመሳሰይ ሁከት አዘል ሕገ ወጥ ሰለፍ እንዲካሄድ በፌስቡከ መጠራቱን እናስታውሳለን። በመጀመሪያው ጥሪ ላይ እንዲሳተፉ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ጭምር የኦነግን አርማ የያዙ ጥቂት ሰዎችን ጨምሮ እስከ 300 የሚደርሱ ሰዎች ያሉበት ቡድን  ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም በሕዝቡ ጥቆማና መንግሥት በወሰደው የሕግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ ሳይሳካ ቀርቷል። ይህ በሆነ በሁለተኛው ሳምንት የተጠራውና ከፍተኛ ሁከት ይቀሰቀስበታል ተብሎ በድብቅ የተደገኑ ካሜራዎች ሲጠብቁት የነበረው ሰልፍ ግን በሕዝቡ እምቢ ባይነት ከጥሪነት ሳያልፍ ቀርቷል።

እንግዲህ፤ አራት ዓመት ያህል ወደኋላ ተጉዤ ምቾት የነሱንን የሰላምና መረጋጋት ሁኔታዎችን ማስታወስ የፈለኩት ሁከቶቹ መነሻ ምክንያታቸውና ግባቸው ፍፁም የተለያየ ቢሆንም፤ ሁሉም በተመሳሳይ አካላት የታቀዱና የተጠለፉ፤ ተጠያቂነት በማያስከትሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተመሩ መሆናቸው እንዲስተዋል በማሰብ ነው። ሁከቶቹንና ብጥብጦችን፤ የዘር ጥላቻ ቅስቀሳ ጭምር አቅደው በማህበራዊ ሚዲያ በርቀት ሲመሩ የነበሩት የኤርትራን መንግሥትና ሌሎችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶቻች ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ የማስፈፀም ተልዕኮ የተቀበሉ ቡድኖች ናቸው። የአዋኪዎቹ ዓላማና የሁከቶቹ መፈክር ፍፁም የተለያየ ሆኖ ሳ፤ለ በአንድ አካል መመራታቸው አንድ በግልፅ የሚያመለክተው ነገር አለ። ይህም መድረሻቸው ኢትዮጵያውያንን በብሔርም ይሁን በሃይማኖት እርስ በርስ በማጋጨት ከተሳካ አገሪቱን ማፍረስ፤ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎችን ማደናቀፍ፤ የአገሪቱን ገፅታ ማበላሸትና በዓለም ፊት ኮሳሳ አገር ሆና እንድትታይ ማድረግ ነው።

እነዚህ ምቾት የነሱን ሁከቶችና ብጥብጦች የተመሩት በኤርትራ መንግሥት ተላላኪዎችና በሌሎች ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ቢሆንም፤ በእነርሱ ላይ ብቻ አላክኮ መተዉ ግን ስህተት ነው። እነዚህ ኢትዮጵያን አተራምሶ የማዳከምና የመበተን ዓላማ ያላቸው የውጭ ኃይሎችና ጉዳይ አስፈፃሚዎቻቸው በቀላሉ በማህበራዊ ሚዲያ በሚነዙት ውዥንብርና በሚሰጡት ትእዛዝ ሁከት መቀስቀስ እንዲችሉ ያደረጋቸው አመቺ ሁኔታ አለ። ይህ አመቺ ሁኔታ ደግሞ በውጭ ኃይሎች የተፈጠረ ሳይሆን፤ በቀዳሚነት ሕዝብን እንዲያገለገሉ በተሾሙ የሥራ ኃላፊዎችና ሕዝብን እንዲያገለገሉ በተቀጠሩ ባለሞያዎች የተፈጠረ ነው።

በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ያሉ ባለስልጣኖች ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ፤ ስልጣንን ለግል ጥቅማቸው ማዋል በአዋጅ የተፈቀደላቸው እስኪመስል የተስፋፋበት ሁኔታ ይታያል። ይህ የሥራ ኃላፊዎች ከባለሞያዎች ጋር በመመሳጠር የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት የገቡበት የኪራይ ሰብሳቢነት አረንቋ፤ በተመሳሳይ የማይገባቸውን ጥቅም ማግኘት ከሚፈልጉ ተለጣፊ ባለሃብቶች ጋር የሚከናወን ነው። በዚህ ዙሪያ የገዢው ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ አስፍሮታል። ውሳኔው፤

ስራ አስፈፃሚው ይህን መነሻ በማድረግ ባካሄደው ግምገማ፤-

በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ፤ የመንግሥት ስልጣን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ፤ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋግጧል። ይላል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ተከታታይና ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረገ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገት ማስመዝገቧ ሊሸሸግ የማይችል ገሃድ እውነት ነው። ይሁን እንጂ እውነታው፤ ከላይ ባነሳናቸው የሕዝብ አገልጋይነታቸውን በዘነጉ ኪራይ ሰብሳቢ የሥራ ኃላፊዎች ፈተና ገጥሞታል። ይህ ሁኔታም ፍትሃዊውን የሃብት ክፍፍል በማዛባትና ብልሹ አሰራርን በማስፈን ሕዝቡን አማርሮታል።

አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ፤ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ መንግሥት በተለይ፤ መሰረተ ልማትንና ማህበራዊ ልማትን በማስፋፈት ረገድ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር የካፒታል በጀት ይመድባል። እዚህ ላይ በየዓመቱ ለካፒታል በጀት የሚያዘውን ገንዘብ ልብ ይሏል። ይህን ግዙፍ የካፒታል በጀት የሚያስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ከፕሮጀክት አሰጣጥና ከአፈፃፃም ክትትል ጋር በተያያዘ ከተለጣፊ ባለሃብቶች ጋር በመመሳጠር የማይገባቸውን ኃብት የሚያካብቱበት ሁኔታ አለ። ይህንን ሕዝቡ ያውቃል። ያለወጉ የሚጋነንበትና የተሳሳተ ትርጉም የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩ ሳይዘነጋ፤ ሕዝቡ ስለሚፈጸሙት ዘረፋዎች፤ በማንና እንዴት እንደሚፈፀሙ… ሁሉ መረጃ አለው።

ይህ ገሃድ ዘረፋ ሥራ አጥ ዜጎችን በሥራ ፈጠራ ፕሮግራም ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ ለማድረግ በተዘጋጁ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ደረጃም አለ። መሬት እንደ ጣቃ እየተለካ ሲቸበቸብ፤ የመንግሥት ተሿሚዎችና ደላሎች በዚህ የመሬት ችርቻሮ ሲከብሩም ሕዝቡ ያውቃል። በአዲስ አበባ ዙሪያ ወዳሉ ከተሞች ሄዳችሁ ማንኛውንም የከተማ ኗሪ ብትጠይቁ ዝርዝር መረጃዎች ታገኛላችሁ።

እነዚህ ሁኔታዎች በአንድ በኩል ጥቂት ግለሰቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከብሩበትን፤ ሌሎች ደግሞ ባሉበት ድህነት ውስጥ ሲዳክሩ የሚታይበትን ሁኔታ ፈጥሯል። የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቅ የሚፈለገውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት፤ የሥራ እድልን ጨምሮ መፍጠር እንዳይችሉ አድርጓል። ኪራይ ሰብሳቢነት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ከማዛባቱ በተጨማሪ፤ ሕዝብን በብልሹ አሰራር ያስከፋል። ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማጥፋት መልካም አስተዳደርን ያበላሻል።

እነዚህ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ውስጥ ያሉ ችግሮች የፈጠሩት ከቅሬታ አልፎ እስከተቃውሞ ማሰማት የደረሰ መከፋት ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ ላላቸው የቅርብና የሩቅ ጠላቶችና ለተላላኪዎቻቸው አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ሆድ ለባሰው . . . እንዲሉ በኤርትራ መንግሥት ሚዲያዎችና በማህበራዊ ሚዲያዎች ተስፋ አስቆራጭና የፈጠራ ወሬ የሚደርሰው ሕዝብ በግብታዊነት በመንግሥት ላይ ወደመቆጣትና ወደመቃወም፤ ለማንኛውም ተቃውሞ የተሰለፈን ወገን ወደመደገፍ የሄደበት ሁኔታ ተስተውሏል።

እናም፤ ከምቾት ነሺ የሰላምና መረጋገት ሁኔታ ለመገላገልና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመታደግ በሕዝብ ላይ መከፋት የፈጠሩ፤ በተለይ ከመንግሥት አሰራር የመነጩ ችግሮችን መፍታት ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት። ከውጭ የሚወረወረውን እሳት ለመቀበል አመቺ የሆነው ተቀጣጣይ ሁኔታ የተፈጠረው መንግሥትና ምናልባትም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ተወጥተው የሕዝብ እርካታ መፍጠር ባለመቻላቸው፤ ከአቅም በላይ የሆኑና በጊዜ የሚፈቱ ችግሮችንም በተመለከተ፤ ሕዝብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ባለመደረጉ መሆኑን ማወቅ ወደመፍትሄ የሚወስደን የመጀመሪያ እርምጃ ነው። የሰላማችን ዋስትና እና የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችን ፀነቶ የመኖር ሁነኛ ማረጋገጫው መንገድ ይህ ብቻ ነው። እርግጥ ሲካሄዱ የቆዩት ሁከቶች ሌላም የሚጠቁሙን ክፍተት አለ። ይህም፤ አሁንም በፌደራላዊ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ሕዝቡ የተሟላ ግንዛቤ የሌለው መሆኑን ነው። ይህን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት መስራትም ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ሆኖ ይሰማኛል። እነዚህ ተግባራት በአግባቡ ከተከናወኑ የውጭው የሁከት ፈጠራና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የመናድ ሙከራ እዳው ገብስ ነው።