የፖለቲካ ድርጅቶች በየትም ሀገር ላይ ቢሆን ከወቅቱ ብሄራዊና አለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታና አሰላለፍ ጋር እራሳቸውን እየፈተሹና እየገመገሙ መሄድ ካልቻሉ በሚመሩት ወይንም እንወክለዋለን በሚሉት ህዝብ ዘንድ ፈታኝ ትግሎች ያጋጥማቸዋል፡፡በታሪክ ውስጥም በተደጋጋሚ ታይቶአል፡፡ኢህአዴግ ስርነቀል ለውጥ በማድረግ የህዝቡን ጥያቄ የሚመልሱ የእርምት እርምጃዎችን በመውሰድ ሰላምን ማስፈን ይተበቅበታል፡፡
ትላንት በታማኝነታቸው የሚታወቁ የህዝብ አገልጋይ ነን የሚሉ ሰዎች የተደላደለ ፖለቲካዊ ስልጣን ሲጨብጡ የተነሱበትን በመርሳት ወደኪራይ ሰብሳቢነት ሙሰኛነት አልጠግብ ባይ አጋባሽነት ተለውጠው በመጨረሻውም ታሪካቸው በውርደት ምእራፍ የተዘጋበትን ሁኔታ በብዙ ሀገራት ታሪክ አይተናል፡፡
በከፍተኛው አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉም በነበረው ጽናትና ታማኝነት ንጽህና ሁሉም ቃሉን ጠብቆ ይገኛል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ድርጅቱ ወይም ፓርቲው ተከታታይ በሆነ ደረጃ እራሱን እየፈተሸ እያረመ እየገመገመ እያጣራ ካልሄደ በህዝብ ተቀባይነትና አመኔታን በማጣት የጨበጠውን የፖለቲካ ስልጣን እስከማጣት ይደርሳል፡፡
የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ረዥም ዘመን የዘለቀበት ምስጢር በተለያዩ የቀድሞ ዘመናትም ሆነ ዛሬ በውስጡ በሚያካሂደው የሬክትፊኬሽን ሙቭመንት (የማጣራት የማረም የማስወገድ) ዘመቻና ንቅናቄ ነው፡፡በእርግጥም የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ በጎሳና በጎጥ የተደራጀ ፓርቲ አይደለም፡፡
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጎሳና ብሄረሰብ ሳይለይ የሰው ልጅ በመሉ እኩል ነው በሚል መርህ የታችኛውን የህብረተሰብ ክፍል በዋነኛነት ከድህነትና ከኃላቀርነት ለማላቀቅ ታላቅ ትግል ያደረገና የተሳካለት ፓርቲ ነው፡፡
ቻይና እንደ ታላቅ ሀገር በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ብሄር ብሄረሰቦች ባህሎች ሀይማኖቶች ቓንቓዎች ያሉዋት በአለም በህዝብ ብዛት የመሪነቱን ብዛት የያዘች በአለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ስትሆን የእኛ አይነት ችግር የለባትም፡፡ከእዚህም ኢህአዴግ ታላቅ ትምህርት ሊወስድ ይገባዋል፡፡
ቻይና ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን በተመለከተ በረዥም የበርካታ አመታት ውስጥ ምህረት የለሽ የእርምት እርምጃና ንቅናቄና በማራመድ በህዝብ አገልጋይነት የተሰጣቸውን የፓርቲና መንግስታዊ ሀላፊነት በመጠቀም የህዝብና የመንግስትን ሀብትና ንብረት የዘረፉ የመዘበሩ የከበሩ ከፍተኛ የፓርቲና የመንግስት ሀላፊነት ላይ የነበሩትን ነባሮች ብዙ መስዋእትነት የከፈሉ አባላቱንም በፍርድ የቀጣችበት ተደጋጋሚ ታሪኮች አሉዋት፡፡ ከሀገርና ከህዝብ በላይ አይደሉምና፡፡
ዋናው የእርምቱና የንቅናቄው ዐቢይ ምክንያት የፓርቲው የህዝብ አገልጋይነት መርህ ተጥሶአል፡፡ የገባችሁትን የአደራ ቃል ክዳችኃል፤ሀገርን ህዝብን ዘርፋችኃል፤ገንዘቡን ከሀገር ውጭ አሻግራችኃል በሚል ከባድ ክስ ተጠያቂ አድርጎ ከባድ ቅጣት ይጥልባቸዋል፡፡ለሌላውም የፓርቲ አባል ትምህርት የሚሰጥ ተጠንቅቆ እንዲሰራ ስህተት ላይ እንዳይገኝ ማስጠንቀቂያ መሆኑ ነው፡፡
በቻይና ታግለን መጥተናል የደም መስዋእትነት ከፍለናል ከማኦሴቱንግ ጋር የነበርን ነን ቢሉም ህጉ አይሰማቸውም፡፡የታገላችሁት ህዝባችሁንና ሀገራችሁን ለተሻለ ህይወት ለማብቃት ለማልማትና ለማሳደግ የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ እንጂ ህዝብና ሀገርን ለመዝረፍ ለግላችሁ ለመክበር አይደለም ነው መልሱ፡፡ሆኖም ተደርጎም ታይቶአል፡፡
ነባር ታጋዮቹንም በተመለከተ መስዋእትነት ስለከፈላችሁ ካሳችሁ የህዝባችሁ ህይወት ተለውጦ አድጎ ማየት እንጂ ልትዘርፉት ልትሰርቁት ደም ከፍለናል በሚል ልትመዘብሩት በላዩ ላይም አምባገነን ሆናችሁ ልትጫወቱበት አይደለም፡፡ከህዝቡ የተለየ እንድትኖሩም ህጉ አይፈቅድላችሁም በሚል ብዙዎች እንደጥፋታቸው ደረጃ ከሃላፊነት ተነስተው ታስረዋል፡፡ተባረዋል፡፡በሞት ፍርድ የተቀጡም አሉ፡፡በዚህ መልኩ ነው ፓርቲው የእርምት እርምጃ እየወሰደ ነው ችግሩን መግታት የቻለው፡፡ዛሬም ድረስ የቀጠለው፡፡
በቻይና በሃላፊነት ተቀምጦ የህዝብና የመንግስትን ሀብት መዝረፍ በከባድ ድርብርብ ወንጀል ያስጠይቃል፡፡ይህን መሰሉን እርምጃ በየግዜው እየወሰዱ የአመራሩን ደረጃ እየገመገሙ የህዝብን የውስጥ ስሜት የልብ ትርታ እያዳመጡ ተቀባይነታቸውን እየገነቡ ነው ከድህነት ወለል ተነስተው ዛሬ የአለም መሪ ኢኮኖሚ እስከ መሆን የደረሱት፡፡
አንድ የፖለቲካ ድርጅት ወይንም ፓርቲ የግዜውን እድገት እያነበበ እራሱን እያበቃ መሄድ ካልቻለ ይገረጅፋል፡፡ያረጃል፡፡ይሞታል፡፡ትላንት በአለም ፖለቲካ ውስጥ ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸው ግለሰቦች ዛሬ ላይ ስልጣን ባመጣው ዘረፋና ገንዘብ ተለውጠው ማንነታቸው ሲቀየር ማየት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡
የፖለቲካ ድርጅቱ እራሱን ሁሌም የሚፈትሽ የሚመረምር አባላቱን በህጉ መሰረት መሄዳቸውን የሚመዝን ከሆነ ለወድቀት አይበቃም፡፡ከህዝብ ጋር እንዳያላትሙት እንዳያጋጩት ቁጣ እንዳይቀሰቀስበት ይጠነቀቃል፡፡
ትላንት መስዋእትነት ስለከፈሉ እንደፈለጉ የህዝብና የመንግስትን ሀብት ይዝረፉ ያግዙ ህዝብንም ያስለቅሱ ፍትህን ይርገጡ የሚል ህግና ስርአት በአለም የለም፡፡ካጠፉ በህግ ይጠየቃሉ፡፡ይቀጣሉ፡፡አጥርቶ መፈተሽ የፓርቲው መሰረታዊ ተግባር ነው፡፡
ይህን አለም አቀፋዊ ተሞክሮ በስሱ ካየን ወደእኛ እውነት ስንመለስ ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር የፍትህ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግርን ከስሩ ነቅሎ ለመጣል በየጉባኤው ውሳኔ ቢያሳልፍም ተግባራዊ ለማድረግ በውስጡ ታላቅ ፈተና ገጥሞት ቆይቶአል፡፡
አለኝ የሚለውን የዲሞክራሲና የመተራረም ባህልና ባህርይ ሙሉ በሙሉ እያጣ የሄደበት አይንያወጣ ሙስና እየነገሰ የመጣበት በቡድንና በኔትወርክ የተደራጁ ሹሞችና አገልጋዮች ተላላኪዎቻቸው ጭምር በዘረፋ በተገኘ ሀብት የከበሩበት ሁኔታ ገዝፎ መታየቱ ይህም በርካታ አመታትን አስቆጥሮ የህዝብ ቁጣን መቀስቀሱ እውነት ነው፡፡ፈተናውም አደጋውም ይሄ ነው፡፡
በድርጅቱ ውስጥ ገነው የታዩት እነዚሁ ክፍሎች ጭርሱንም በመልካም አስተዳደር በፍትህ እጦት በሙሰኞች በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ኢህአዴግ ለማድረግ የወሰነውን የሞት የሽረት ትግል አቅጣጫውን እንዲስት ያጨነገፉበት በእነሱም ምክንያትና መነሻነት በየቦታው ህዝባዊ አመጽ የተቀሰቀሰበት ሁኔታ በአደባባይ ጎልቶ መታየቱን ነው ህዝቡ የሚናገረው፡፡
እንደ ዜጋ ማንም ሰው ሀገሩ ሰላም እንዲያጣ እንዲበጠበጥ አይፈልግም፡፡አብዛኛው ህዝብ ሩጦ አዳሪ የእለት እንጀራውን አባራሪ ለፍቶ ደክሞ ኑሮውን ለማሸነፍ የሚተጋ ነጋዴውም ገበሬውም የፋብሪካም ሆነ የመንግስት ሰራተኛው በሰላም ሰርቶ በሰላም መግባትን የሚፈልግ ሁከት ትርምስና ብጥብጥን አይፈልግም፡፡
ብዙሀኑ ህዝብ በእለት ሰርቶ ከሚያገኘው ወይንም በወር ከሚጠብቀው ገቢ ውጭ ለነገ ብሎ ያስቀመጠው ወይንም የሚያስቀምጠው የሌለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ለዚህ ነው ሰላምና መረጋጋትን የሚደግፈው፡፡በሰላም ውሰጥ ነው የቤተሰብም የሀገር እድገትም የሚገኘው፡፡ በሰላም ውስጥ ነው ተምሮም ሆነ ሰርቶ ነግዶም መመለስ ማትረፍም ማፍራትም ማደግም የሚቻለው፡፡
የሀገር ሰላምና ደህንነት መረጋጋት በምንም ዋጋ የሚሰላ የሚተመንም አይደለም፡፡ ከቢሊዮኖችም ከትሪሊዮኖችም በአለም ከከበሩትና ውድ ከሆኑትም ሁሉ በላይ ውድ ነው፡፡ አንድ ሀገር ሰላምና መረጋጋት ከሌላት ልማትም እድገትም የላትም፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ኢኮኖሚውም ንግዱም የቱሪዝም ገበያውም ይሞታል፡፡ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ አፍስሰው ሰርተን እናገኛለን ተጠቅመን ሀገሪቱንም እንጠቅማለን እውቀትና ልምድ እናካፍላለን ለዜጎቻቸው የስራ እድል እንፈጥራለን ብለው የገቡት ሀብታቸውን ያፈሰሱትም የውጭ ዜጎች ሌላ ሰላምና መረጋጋት ያለበት ሀገር ፈልገው ለቀው ይወጣሉ፡፡ሀብታቸውንም ይዘው ይሄዳሉ፡፡ይህንን ተከትሎ ብዙ ስራ የነበራቸው ዜጎች ወደ ስራ ፈትነት ይለወጣሉ፡፡
ይሄ ደግሞ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ጉዳትና ውድቀት ነው፡፡ሀገራችን ወደዚህ የቀውስና ትርምስ ሁኔታ ውስጥ በፍጹም መግባት የለባትም፡፡መንግስት ህዝቡን በመስማትና በማዳመጥ ችግሩን በሰላም መፍታት ግድ ይለዋል፡፡
ሰላም ከሌለ የንግድ ልውውጥና ግብይት የለም፡፡ለእለት ፍጆታ የሚሆኑ ሸቀጦችን እንኩዋን ገዝቶ ለመጠቀም አይቻልም፡፡ሰላም ከሌለ ከክልሎች ወደ መሀል ሀገር የሚገቡ እህሎችን ሌሎችንም ለማምጣት አይቻልም፡፡ይህንን ችግር ለመቓቓም የሚያስችል አቅም ሀገሪትዋ የላትም፡፡በዋነኛነት ተጎጂው ህዝብ ነው፡፡
በቀውስና በትርምስ መህል የገበያውም ዋጋ እየናረ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን ያስከትላል፡፡ ሀብት ካላቸው በስተቀር ማንም ዜጋ ሊቓቓመው አይችልም፡፡ይህም የህዝብን መጎዳት በከፍተኛ መጠን ያጎነዋል፡፡ይህ እንዲሆን የሚፈልጉ ወገኖች ተጎጂው ማን እንደሆነ ሊያስቡበት ይገባል፡፡መፍትሄው በሰላምና በውይይት ችግሮችን መፍታትና ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ብቻ ነው፡፡የሀገርና የህዝብ መታመስ ለማንም አይጠቅምም፡፡
የሀገራቸውን ሰላም ውላ ሰላም ማደር ሁሌም ዜጎች አጥብቀው ይመኙታል፡፡ከሰላም በላይ ምንም ውድ ነገር በምድር ላይ ስለሌለ ነው፡፡ሰላም ከሌለ ህጻናትም አዛውንትም ቤተሰብም ገንዘብ ቢኖርም እንኳን የሚመገቡትን ገዝተው ሊያገኙ አይችሉም፡፡ወጥቶ በሰላም መመለስም ብርቅ ይሆናል፡፡ሰላም ከሌለና ከደፈረሰ መብራት ውሀም የሚጠፋበት ሁኔታ በበርካታ ሀገራት ታይቶአል፡፡ሰላማችንን ያብዛልን ይበጃል፡፡
ይህንን ክፉ መአት በመንግስትና በተቃዋሚ ፖለቲከኞቻቸው ግትርነትና መካረር ጽንፈኛ በሆነ እልህ መጋባት በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት ቤታቸውን ንብረታቸውን ሀብታቸውን ከሁሉም በላይ ሰላማቸውንና ሀገራቸውንም ያጡት የአረቡ አለም ሀገራት ህዝቦች ከወረደባቸው መከራ በተግባር አይተውታል፡፡ለዚህ ነው ከትርምስ ከሁከት ከስሜታዊነት ባለፈ በዘለለ ስለሀገር ሰላምና ደህንነት አርቆ ማሰብ የሚገባን፡፡
የሰላሙና የሀገሩ ባለቤት ህዝብና ህዝብ ብቻ ነው፡፡መንግስትም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት በአንድ የታሪክ ወቅት ይመጣል፡፡ጥሩም ሆነ መጥፎ ብርቱም ሆነ ደካማ ግዜውን ጠብቆ ያልፋል፡፡ቓሚ የሆነ መንግስት የለም፡፡ሀገርና ህዝብ ግን በትውልድ ፈረቃ ቓሚ ሁነው ይቀጥላሉ፡፡ፍሰታቸው አይቓረጥም፡፡ሰላሙን መረጋጋቱን ሀገሩን የሚጠብቀው ህዝብ ነው፡፡ህዝብ ከህዝብ አይጋጭም፡፡ይህ የእኩይ ፖለቲከኞች ሴራና ወጥመድ ነው፡፡ለሀገርና ለህዝብ ሰላም ሲባል መታገልም የግድ ነው፡፡
በታሪኩ ውስጥ ብዙ ፈተናና መከራን ጦርነትን ያሳለፈ የሰከነ ሕዝብ በአበዱ የጥላቻ ፖለቲካ አራማጆችም ሆነ በተሳሳቱ ሹሞች የጥፋት እሳቤ አይመራም፡፡እነሱ ካለፉም በኃላ የቆየውና የነበረው አብሮነት እንደሚቀጥል ያውቃል፡፡ጥንትም የሆነው ወደፊትም የሚሆነው ይሀው ነው፡፡
ሀገር በሁከት በትርምስ በግርግር ወደከፋ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ የሚሹ ወገኖች ተሳስተዋል፡፡ሁሉም ችግር በህዝቡ መመካከር መወያየት መፍትሄ በማበጀት ይፈታል፡፡ይቓጫል፡፡ትላንትም ዛሬም ነገም ወደፊትም ሀገራቸው ህዝቡም ህዝባቸው መሆኑን ከጥፋትና ከውድመት ስርአተአልበኛነት ከማስፈን የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ ይበልጥም ተጎጂው ሀገርና ህዝብ መሆኑን ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል፡፡
ከሀገርና ከሰላም መጥፋት ተጠቃሚ ለመሆን ያሰፈሰፉ ህግና ስርአት ሲጠፋ ለዘረፋ ለንጥቂያ እራሳቸውን አዘጋጅተው የሚጠብቁ የውስጥና የውጭ ሀይሎች ሁሌም እንዳሉ ይታወቃል፡፡በትርምስና ሁከት አጋጣሚዎች የከበሩ የሚከብሩ ሁኔታው ከመንገድና ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ የሚሰሩ በዚህ የተካኑ አለም አቀፍ የማፍያ ተቓማትም አሉ፡፡ለዚህ ሶርያ ሊቢያ የመንን ሌሎችንም መመልከቱ ይበቃል፡፡ይህ አይነቱ ሁኔታ በኢትዮጵያ እንዲከሰት የሚሻ የሚፈልግ አይኖርም፡፡እንደ ህዝብም እንደ ሀገርም ልንከላከለው የሚገባን ታላቅ አደጋ ነው፡፡
መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎች በአግባቡ የማዳመጥ የመፍታት ግዴታ አለበት፡፡ይህ ዘመኑ የሚፈቅደው ስልጡን አካሄድ ነው፡፡ድርጅትም ሆነ ፓርቲ የህዝብ ድምጽ ከተነፈገው መቀጠል አይችልም፡፡መንግስት ካለህዝብ መንግስት ሊሆን አይችልም፡፡በአለም ታሪክም አልታየም፡፡ኢህአዴግ ራሱን በስርነቀል ለውጥ አድሶ የህዝብ ይሁንታን ለማግኘት የሚያስችሉ መሰረታዊ የእርምት እርምጃዎችን በመውሰድ ሰላምን ማስፈን ይጠበቅበታል፡፡