ቃል ከተግባር ይገናኝ!!

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን የ15 ዓመታቱን የትግል ጉዞውን ስኬትና ተግዳሮቶች ለሥርዓቱ አደጋ ሆነው የተጋረጡ ፈታኝ መሰናክሎችን በመገምገም ችግሩን ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመፍታት ሥር ነቀል እርምጃዎችን እንደሚወስድ የአዲሱ ዓመት ቀዳሚ ሥራም ይህንኑ የተሀድሶ መፍትሄ መስጠት እንደሆነ ገልጾ ህዝቡም ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ አድርጓል፡፡ ቃል ከተግባር ይገናኝ ዘንድ የግድ ነው፡፡

የሥራ አስፈጻሚው ስብሰባና ግምገማ በትክክል እንዳሳየው ህዝቡ በመልካም አስተዳደር እጦት በፍትህ መዛባት በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ምን ያህል እንደተማረረ እንደተከፋ መገንዘቡን ገልጾ ህዝቡ መብቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ሠላማዊ ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪም አቅርቧል፡፡ መፈራትም መከበርም ያለበት ወሣኙ ህዝብ ነው፡፡

ለህዝብ ይሰራሉ ያገለግላሉ የተባሉ ከከፍተኛ እስከታችኛው እርከን ድረስ ያሉ ሹሞች በዘረጉት የጥቅም ትስስር መረብ የህዝቡን የአገሪቱን የመንግሥትን ሀብት ያለአንዳች ይሉኝታና ርህራሄ ያውም ህዝብ እያወቀ ግጠው ልጠው በልተውታል፡፡ ጊዜና አጋጣሚ የሰጣቸውን መንግሥታዊ ወንበር ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ለዘረፋና ቀማኛነት አውለውታል፡፡ መብታችን ተረግጧል በሚል ህዝብ ተስፋ በመቁረጡ ነው አምርሮ የተነሳው፡፡ ህዝቡ መንግሥት ችግሩን አድምጦ ፈጣን መፍትሄ ምላሽ እንዲሰጠውም ይጠብቃል፡፡

በየማዕዘናቱ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የተመራ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ እንዳለው የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ በየትኛውም ወገን ማሳበብ አይቻልም፡፡ እውነትም ነው፡፡ ይህ መነሻ ሆኖ እውነቱንም መቀበሉን በማድነቅ ራሱም ኢህአዴግ አምና መቀሌ ላይ ባካሄደው 10ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔው ሁሉም ድርጅቶች ሥራ አስፈጻሚዎችና ለጉባዔው የተወከሉ አባላት በተገኙበት ታዛቢዎችም ባሉበት ለቀናት ባካሄደው የቡድንና የጋራ ግልጽ ውይይት ችግሮቹን ሁሉ ከመሠረቱ ፈትሾ በማጠቃለያው ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ቁርጠኛ ውሣኔ በማሳለፍ ትግሉ የሞት ሽረት ወሣኝ ትግል እንደሆነ አውጆ ነበር፡፡

ይኸው ዘንድሮ ነሐሴ አንድ ዓመት ሞላው፡፡ ኢህአዴግን እንደ ድርጅት በእርሱ የሚመራውንም መንግሥት እንደመንግሥት በውስጡ ተንሰራፍቶ አቅምና ጉልበት ይዞ ዙሪያ ገባውን ተብትቦ አላላውስ ያለውን የሙሰኛና የኪራይ ሰብሳቢው ኃይል ያሻውን እየዘወረ የድርጅታዊ ጉባዔው ውሣኔ ተግባራዊ እንዳይሆን በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙሰኞች ላይ ትግል እንዳይደረግ የውስጥና የውጭ መሰናክሎችን በመፍጠር ሥርዓቱን ክፉኛ ታግሎታል፡፡ ይህንን ህዝቡ አውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሩት ከፍተኛ የኢህአዴግና የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት የሲቪል ሰርቪስ ሙያተኞች በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በናሙናነት በተመረጡ መሥሪያ ቤቶችና ከተሞች ላይ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ዙሪያ ያደረጉትን ሰፊ ጥናት በማስረጃ አቅርበዋል፡፡ ዝርዝሩ(800) ገጽ የያዘ ነው መባሉም ተደምጧል፡፡

ይህንን የቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት የተከታተለው በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖረው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠረው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የውይይቱ አመራርና ከሰጡትም አስተያየት በመነሳት ወሣኝ አገራዊ ርምጃዎች ይወስዳሉ የሚል ተስፋን ሰንቆ ቆይቶ ነበር፡፡

በእርግጥ ህዝባዊ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ህዝቡም ያለማመንታት የተፈፀመበትን ግፍና በደል ተናግሯል፡፡ በተወሰኑ ደረጃዎች በጣም ታች በነበረው አመራር ላይ የተወሰዱ ርምጃዎች ነበሩ፡፡ ከሥራ ማገድ ከደረጃ ማንሳት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዲታይ ማድረግ እነዚህ በሁሉም ክልሎች ተደርገዋል፡፡ በህዝቡ ዘንድ መጠነኛ ተስፋ ፈንጥቆም  ነበር፡፡

ኢህአዴግ የችግሩን ግዝፈትና አሳሳቢነት እያወቀ መረጃዎቹም ሆኑ ማስረጃዎቹ ከእሱ ሊሰወሩ እንደማይችሉም እየታወቀ ፈጥኖ ርምጃ ያልወሰደው ከፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ማጣት ነው የሚለው የህዝብ አስተያየት በሰፊው ይደመጣል፡፡ መዘግየቱ የአሁኑን የህዝብ ተቃውሞና ቁጣ ቀስቅሷል የሚሉም ብዙዎች ናቸው፡፡

ህዝባዊ ተቃውሞው ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ በመጀመሪያ በኦሮሚያ ሲነሳ የጉዳዩ አሳሳቢነት ደረጃ ወቅቱን ጠብቆ ሊፈጥር የሚችለው ችግር በሚገባ አልታየም ነበር፡፡ የውስጡም ሆነ የውጪው ኃይል ማንኛውንም በህዝቡ ውስጥ ሊነሳ የሚችልን አመጽም ሆነ ተቃውሞ ባገኘው ቀዳዳ ገብቶ ለመጠቀም መሞከሩ ምንም አያከራክርም፡፡

ዋናው የህዝብ መከፋትና አመጽ መነሻ አሁን ኢህአዴግ በውሣኔው እንደገለፀው ህዝቡ በሙሰኞች፣ በኪራይ ሰብሳቢዎች፣ በፍትህና በመልካም አስተዳደር ችግር መማረሩ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢውና ሙሰኛው መንግሥታዊ ወንበር የያዙ ሹሞችን በመጠቀም ህጋዊ የመንግሥት ማህተም ይዘው በህዝቡ ላይ አስከፊ ወንጀልና ግፍ ፈጽመውበታል፡፡

ሲያሻቸው እያስፈራሩ ለምን ብሎ የሚከራከር ከሆነ ደግሞ ምክንያት ፈጥረው እያሰሩ የግለሰቦችን ይዞታ ጭምር ለንግድ አመቺ ቦታ ላይ ካለ ለልማት ይፈለጋል በሚል እያፈናቀሉ መብቴን አላስነካም እምቢ ካለም በፖሊስ ተገዶ እንዲነሳ እያደረጉ እነሱ ከጀርባ ከባለሀብት ጋር ተደራድረው እየሸጡ የመንግሥትን መሬት ጭምር ምክንያት እየፈጠሩ በልማት ስም እየቸበቸቡ በዘረፋ መክበራቸው እውነት ነው፡፡

ኅብረተሰቡ በውል ለይቶ የሚያውቃቸው ምንም ያልነበራቸው ግለሰቦች በአንድ ጊዜ ወደ ሰማይ ተመንጥቀው ሚሊዬነሮች ሆነዋል፡፡ በአዲስ አበባም በክልሎችም የፎቅ ቤቶች፣ ባለእርሻ፣ ባለትላልቅ ሆቴል፣ አስመጪና ላኪ፣ ህንጻ ሰርተው አከራዮች፣ ባለምርጥ ዘመናዊ ሞዴል መኪናዎች ባለቤት፣ ባለኮሌጆች ወዘተ…ሲሆኑ ህዝብ በዓይኑ በብረቱ አይቷል፡፡

ኪራይ ሰብሳቢውና ሙሰኛው ሌላው ዜጋ ሊያገኝ የማይችለውን ከባለሥልጣናት ጋር ባላቸው የጀርባ ቁርኝትና ትስስር ቁልፍ መሬት የፕሮጀክት ቅድሚያ እድል በኔትወርካቸው በማግኘት ህንጻ ሰርተው አከራዮች እንዲያውም በሚያሳፍር መልኩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጭምር ከግለሰቦች በየወሩ በሚሊዮኖች እየከፈሉ የተከራዩበት ድራማ ሞልቶ ተርፏል፡፡ ጉዱ እጅግ ብዙና ተዘርዝሮ፣ ተነግሮና ተጽፎ የማያልቅ ነው፡፡

ከባለሥልጣናት ጋር በጥቅም ተጋሪነት የሚሰራው ኪራይ ሰብሳቢውና ዋነኛው ሙሰኛ ቀርቶ እነሱን የተጠጋው ደላላም በአቅሙ ሳይሰራ በዘረፋና በቀማኛነት የተገኘ ሀብት ባለቤት ለመሆን የበቃበትን ሁኔታ ህዝቡ ጠንቅቆ የሚያውቀው እውነት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ክልሎች በስም መጥራት እከሌና እነእከሌ ማለትም ይችላል፡፡

ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው በህገ ወጥ መንገድ ባካበተው መጠነ ሰፊ ሀብት የተነሳ በሌሎች አገሮች እንደታየውም መንግሥትን እሰከ መገዳደር ከፈለገም እስከመጣል ድረስ ይራመዳል፡፡ ለአንድ አገር ለመንግሥትም ህልውና ለህዝብም ሠላምና ደህንነት እጅግ አደገኛ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

ትላልቅ ወደ አገር ውስጥ ለመሥራት በገቡ የኢንቨስትመንት የፕሮጀክት ጨረታዎች ብቁና ለአገር ልማትና ዕድገት የሚጠቅሙ ፕሮፌሽናል ሙያተኞችን ከመምረጥ ይልቅ ለባለሥልጣኖቹ በኪራይ ሰብሳቢውና በሙሰኛው በደላላው አማካይነት ከጀርባ ዶላር ለሚሰጠው በሙያቸው ብቁ ላልሆኑ የተጭበረበረ የውጭ አገር የሥራ ልምድ በገንዘብ እያጻፉ ለሚመጡ እየተሰጠ ጥራት ያለው ሥራ ሳይሰራ የመንግሥትና የህዝብ ሀብት  እንደሚባክንና እንደሚዘረፍ  ሠራተኛውም ህዝብም ያውቃል፡፡

ኢህአዴግ ልማትና ዕድገት አሳክቷል፡፡ አገሪቷን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለማውጣት ዘመናዊና ያደገች አገር ለመመሥረት ተዘርዝረው የማያልቁ ፈርጀ ብዙ በሆኑ መስኮች ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡ ሰርቶም አሳይቷል፡፡ ሰፊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን አካሂዷል፡፡ መንገድ፣ ድልድይ፣ ግድቦች፣ ባቡር፣ የዘመናዊ  ከተማ ግንባታ ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡

በእነዚህና በሌሎችም ሥራዎቹ ውስጥ ደግሞ በኢህአዴግአዊነት ስም በውስጥ ያደባው ሙሰኛና ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል በራሱ በሥርዓቱ ውስጥ ሆኖ ተሸጉጦ ከውጭ ደላላውንና ተላላኪ ግብረ አበሮቹን በየማዕዘናቱ በማሰለፍ በከተማም በገጠርም ይህ ቀረው የማይባል በመንግሥትና በህዝብ ሀብት ላይ ዘረፋና ምዝበራ አካሂዷል፡፡

ኪራይ ሰብሳቢውና ሙሰኛው በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ በተለይም ቁልፍ አገራዊ ገቢ በሚያስገቡትና በሚያስገኙት ቦታዎች ላይ ካሉ መንግሥታዊ ሹሞች ጋር በመመሳጠር ይሰራሉ ተብሎ የተሰጣቸውን የኃላፊነት ቦታ በመጠቀም ዘመድ አዝማዶቻቸውን በመሰግሰግ ጭምር ዘርፈዋል፡፡ ከብረውበታል፡፡

የፌዴራሉ ጠቅላይ ኦዲተር ለፓርላማው በየዓመቱ በሚያቀርበው ሪፖርት ችግሩ ምን ያህል በአገር ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የወጨያቸው ምክንያት ያልታወቀ ማስረጃ የሌላቸው ያለህጉና ደንቡ እንዲወጡ የተደረጉ በሁሉም መሥሪያ ቤቶች ሲታይ ወደ ሁለት ቢሊዮን መባከኑን በዚሁ ዓመት ሪፖርት ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ እንዲያውም ጉዳዩ ክትትል ተደርጎበት ገንዘቡ ወደመንግሥት ካዝና እንዲመለስ ካልተደረገ የግለሰቦች ሀብት ሆኖ ይቀራል እስከማለት ደርሶ ነበር፡፡

በፋብሪካዎች፣ በመንገድና ቤት ግንባታ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመሬት አስተዳደር፣ በከተማ ልማትና መስፋፋት ስም መንግሥትና ህግ የለም ወይ እስኪባል ድረስ የመንግሥትን ወንበር በመጠቀም ህዝብም አምርሮ እስኪያነባ ዜግነቱንም እስኪጠላ ድረስ በሙሰኞች በኪራይ ሰብሳቢዎች ያልተደረገ ያልተፈፀመ ወንጀል፣ ምዝበራና ዘረፋ የለም፡፡

ኢህአዴግ እንደገለፀው በግምገማውም እንዳረጋገጠው ህዝብ አምርሮ ለመብቱ መከበር መታገሉ ተገቢም ትክክልም ነው፡፡ ታላቁ መሪ መለስ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት የራሳችንን ሌቦች እጃቸውን እንቆርጣለን ብለው የነበረ ቢሆንም በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩትና ያሉት ሌቦች ወንበራቸው ሳይነካ እጃቸውም ሳይቆረጥ ጭርሱንም ክንድና ጉልበታቸው ፈርጥሞና ደንድኖ በንቀትና በእብሪትም ተሞልተው ህዝብንም ክፉኛ አስመርረውና አንገሽግሸው አሁን ላለው አገራዊ ቀውስና ትርምስ ዋነኛ ምክንያት ለመሆን በቁ፡፡

ምናልባትም በየትኛውም መልኩ ለተነሱት የህዝብ ጥያቄዎች ወቅታዊና ህዝብን የሚያረኩ ምላሾች ተሰጥተው ቢሆን ኖሮ የህዝቡ ተቃውሞ እንዲህ የከረረ ደረጃ ላይ ባልደረሰ ነበር የሚሉ አስተያየቶችም ከህዝቡ ይደመጣሉ፤ ትክክልም ነው፡፡

አሁን አነጋጋሪ ሆኖ እየተነሳ ያለው ነጥብ ኢህአዴግ አምና ነሐሴ ወር በመልካም አስተዳደር፣  በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በፍትህ እጦት፣ በሙሰኞች በአጠቃላይ ባለው የሥርዓቱ ችግርና አደጋ ላይ ተወያይቶ ያሳለፈውን ውሣኔ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ አለመቻሉ በውስጡ ያለውን ሥር የሰደደ ችግር ያመላክታል፤ ይኼንን እንዴት ይወጣዋል የሚል ነው፡፡

ኢህአዴግ ውስጡ ባለመጥራቱ ጥገኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል አይሎ በመገኘቱ ከመጋለጤና ከመጠየቄ በፊት ትርምስ መፍጠሩ ያዋጣኛል በሚል ለተፈጠሩት ቀውሶች ሁሉ ምክንያት በመሆኑ ትናንትም ዛሬም ያለው አመራር ሳይተካካ  ለውጥም ሳያመጣ እንዴት ይህን ፈተና ሊወጣው ይችላል? ምንስ የተለየ ነገር ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል? የሚሉት የህዝቡ ጥያቄዎች በሰፊው ይነሳሉ፡፡ ተግባራዊ መልስም ይሻሉ፡፡

ኢህአዴግ ሥር ነቀል ለውጥ አድርጎ በውስጡ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢና ሙሰኛ ኃይል ማራገፍ ካልቻለ ጥገናዊ ለውጥ ካደረገ የባሰ ቀውሱን ከማባባስ ውጪ የተረጋጋ መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ያለው አማራጭ ወሣኝ በሆነ መልኩ ውስጡን መፈተሽና ከህዝቡ ጋር ሆድና ጀርባ ያደረገውን መሠረታዊ ችግር ለይቶ በማውጣት መፍትሄ መስጠት ብቻ ነው፡፡ ይጠበቅበታልም፡፡ ቃል ከተግባር ይገናኝ ዘንድ!!