ከመሰንበቻው ራሱን “ኦነግ” እያለ ከሚጠራው የሽብር ቡድን የተገለጠለውና አዲስ መለያ ለብሶ “ኦዴግ” በሚል ስያሜ ብቅ ያለው “የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር” እና አሸባሪው “ግንቦት ሰባት” አብሮ የመስራት አስቂኝ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል። የጠባብና የትምክህት ቡድን የውህደት የመጀመሪያ ምዕራፍ መሆኑ ነው። የእሳትና ጭድ የጥምረት ስምምነት ቢባልም የሚያስኬድ ይመስለኛል። እርግጥ ለእኔ ይህ “አብሮ የመስራት የመግባቢያ ሰነድ” ውሃን በወንፊት ይዞ የመሄድ ያህል ነው። ምክንያቱም ሁለት “ሞትኩ ለስልጣን” ባዮች ቢጣመሩና ያሻቸውን ዓይነት ሰነድ ቢፈራረሙ መጨረሻው የሚያምር አለመሆኑ ነው።
ስምምነቱ የተፈረመው በአሸባሪው “ኦነግ” ውስጥ ከ40 ዓመት በላይ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ እና ቀደም ሲል የጎዳና ላይ ነውጥ አራማጅ የነበረው ቅንጅት፣ ኋላ ላይም በለየለት ሁኔታ የኤርትራ መንግስት ተላላኪ በመሆን ሀገራቸውን በመክዳት ለባዕዳን ያደሩት አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ አማካኝነት ነው። እንግዲህ ግንቦት ሰባት በሻዕቢያ ትዕዛዝ ሲጣመር ለሁለተኛ ጊዜው መሆኑ ነው። ቀደም ሲል ራሱን “አርበኞች ግንባር” እያለ ከሚጠራውና ሻዕቢያ ሲያስነጥሰው መሃረብ ከማቀበል ውጪ ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ ግብ ከሌለው ፀረ-ሰላም ኃይልና አሁን ደግሞ ከኦነጉ ግንጣይ “ኦዴግ” ጋር። ይህም ግንቦት ሰባት የኤርትራ መንግስት እንዳሻው የሚቀጣጥለውና የሚሰፋው ተላላኪ መሆኑን የሚያሳይ ነው። “ኦነግ”ም ሻዕቢያ ካሻው የሚሰፋው፣ በል ሲለው ደግሞ የሚሰነጥቀው የአስመራው አስተዳደር ጀሌ መሆኑም እንዲሁ።
እናም በዚህ ፅሑፌ ላይ የሀገራችን ተቃውሞ ጎራ የመጣበቅና የመሰንጠቅ ፖለቲካ ማሳያ ሆነው ያገኘኋቸው የእነዚህ ሁለት የጥፋት ኃይሎችን አሰላለፍና የተክለ-ተቃውሞ ፖለቲካ ቦታቸውን ለማሳየት እሞክራለሁ። በመጀመሪያ ግን ከኦነጉ ግንጣይ ልነሳና ለጥቄ ወደ አሸባሪው “ግንቦት ሰባት” ላቅና።…ራሱን “ኦዴግ” እያለ የሚጠራው ቡድን “ኦነግ” አምጦና ተሰንጥቆ የወለደው ነው። ቡድኑን የሚመሩት አቶ ሌንጮ ለታ ዛሬ “ኦዴግን” እስከመሰረቱበት ጊዜ ድረስ የ“ኦነግ” መስራችና ሁነኛ ባለሟል የነበሩ ናቸው። እናም በእኔ እምነት የእርሳቸው ፖለቲካዊ ተክለ-ቁመና ዛሬ በአመራሮቹ የስልጣን ሽኩቻ ሳቢያ ከተሰነጣጠቀው ኦነግ ጋር የተያያዘ ነው። እናም ውድ አንባቢያን ስለ “ኦነግ” ሳወራ ስለ እርሳቸው እያወጋሁ መሆኑን ያውቅልኝ ዘንድ በእክብሮት እጠይቃለሁ።
እንደሚታወቀው ግለሰቡ የመሰረቱት አሸባሪው “ኦነግ” የዛሬው ህገ-መንግስት መነሻ የነበረውን ቻርተር እንዲረቅ ኋላ ላይም ለስልጣን ካለው ጥማት የተነሳ ራሱን ያገለለ ቡድን ነው። በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላይ በፈፀመው የግብረ-ሽበራ ተግባር፤ የሀገራችን ህዝቦች በወንጀለኝነት፣ በአሸባሪነትና በህዝብ ጨራሽነት የሚፈልጉት እንዲሁም ተቀባይነት ያጣ “ድርጅት” ነው።
የሽብር ቡድኑ በጋምቤላ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በመካከለኛውና በምሥራቅ የሀገራችን አካባቢዎች ጀሌዎቹን በማሰማራት በተደጋጋሚ ሠላምን የማደፍረስ ጥረት ለማድረግ ቢሞክርም፤ ከሠላም ወዳዱ ህዝባችን ዓይንና ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከማንኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ አደጋ ለመከላከል ቃል ከገባው የመከላከያ ሠራዊታችን ፈርጣማ ክንዶች ሊያመልጥ የቻለበትን ግን አላስታውስም። ጥረቱ ሁሉ መና ሆኖ የቀረ ጠባብ ቡድን ነው።
አዎ! እነ አቶ ሌንጮ ይመሩት የነበረው ይህ የሻዕቢያ ጀሌ የሁከትና የብተና ተልዕኮዎችን እየተቀበለ ሀገራችንን ለማመስ ቢጥርም ምኞቱ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል። ለዚህም ኢትዮጵያ ላለፋት 13 ተከታታይ ዓመታት በአፍሪካ ተደናቂና በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ህዝቦቿን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ መቻሏ ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ማስመዝገብ አይቻልምና። ዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ ማድረግ እንደማይቻልም እንዲሁ።
ይህ የሽብር ቡድን ከጀሌዎቹ ጋር ያልም የነበረው የሽብር ሴራ በመንግሥታችን የሰከነ አመራር ሰጪነት፣ በህዝባችን ንቁ ክትትልና በፀጥታ ኃይሎች የማያዳግም ምት መረቡ ተበጣጥሶ ዕርቃኑን በመቅረቱ፤ አሸባሪው “ኦነግ” ዛሬ ላይ አውሮፖና አሥመራ በሚገኙት ቢሮዎቹ ውስጥ ሊወሰን ችሏል። ለዚያውም የቡድኑ አባላት በዞን፣ በወረዳ፣ በመንደር፣ በጎጥ…ወዘተ. ተከፋፍለው በስልጣን በመሻኮት እንዲሁም በሻዕቢያም የማጣበቅና የመሰንጠቅ ድራማ ሳቢያ ውሉ የጠፋበት የጥጥ ባዘቶ ሆኗል።…እንግዲህ ይህን መሰሉን ታሪክ ካለው አሸባሪ ኃይል ተሰንጥቀው ነው— አቶ ሌንጮ ለታ በድንገት “ኦዴግ”ን መስርቻለሁ በማለት በየሚዲያው ሲያስደምጡን የነበሩት።
አቶ ሌንጮ በተለያዩ ወቅቶች “ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍትሕ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና የዴሞክራሲ መከበርና መታገልን መሰረታዊ ዓላማው ያደረገ አዲስ የኦሮሞ የፖለቲካ ንቅናቄ መመስረቱን በይፋ ለመንገር እንወዳለን” የሚል መግለጫ ሲሰጡ አድምጠናቸዋል። ከ40 ዓመት በላይ ለጠባብነት ሲታገል የነበረ ቡድንን የመሰረቱ ግለሰብ እንደምን “ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እናስባለን” ወደሚል መፈከር ውስጥ እንደገቡ ለማንም ግልፅ ባይሆንም፤ እርሳቸው ዛሬ በአዲስ መልክ ያነሱት መፈክር ግን በቅድሚያ በሽግግር መንግስቱ ቻርተር ላይ፣ ኋላ ላይም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ዕውን ባደረጉት የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ላይ በማያሻማ ሁኔታ ምላሽ የተሰጠባቸውና ላለፉት 21 ዓመታትም ተግባራዊ የሆኑ ናቸው። እናም በእኔ እምነት የእነ አቶ ሌንጮ አዲሱ ቡድን የያዘው ነገር በአቋራጭ ስልጣንን ለማግኘት ከመሻት ፍላጎት ውጪ ሌላ ግብ ያለው ነው ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም።
አንዳንድ የዋህ ወገኖች በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው ቡድን ከነበረበት ጠባብ የኦነግ አስተሳሰብ ወጥቶ በአስገራሚ ሁኔታ አቋሙን በመቀየር ወደ ኢትዮጵያዊነት ፊቱን ያዞረ ሊመስላቸው ይችላል። እኔ ግን በፍፁም አይመስለኝም። ምክንያቱም አቶ ሌንጮ የዛሬ ዓመት ገደማ ‘ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁከት ሊነሳ ይችላል’ በሚል ስሌት እንዲህ ዓይነት ወሬዎችን በመቃረም ከሚታወቀው ከአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ ‘ዓላማችሁን በሀገር ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ታደርጋላችሁ?’ ተብለው ሲጠየቁ፤ “በሁሉም መንገድ እንታገላለን” የሚል ምላሽ በመስጠታቸው ነው።
እርግጥ ይህ አባባላቸው “በኢሳት ላይ ወሬም ቢሆን በማንኛውም መንገድ ህገ- መንግስታዊ ስርዓቱን እናፈርሳለን” ከሚለውና ራሱን “ግንቦት ሰባት” እያለ ከሚጠራው አሽባሪ ቡድን አቋም ጋር ተመሳስሎነት ያለው መሆኑን አንዳንድ ወገኖች ሲናገሩ አድምጨ ነበር። እናም የእነዚህ ወገኖች አባባል መሬት ጠብ ያለ አይመስልም—እነሆ የትናንቱ የጠባብነት አራማጁ አቶ ሌንጮ ዛሬ በአዲስ መልክ ያቋቋሙት “ኦዴግ”ን ከአሸባሪው “ግንቦት ሰባት” ጋር በማጣበቅ የሻዕቢያን ትዕዛዝ ዕውን አድርገውታልና። እናም “ትንቢት ይቀድም ለነገር” እንዲሉ አቶ ሌንጮ በአዲስ የተቃውሞ ስያሜ ወደ ፖለቲካው ዓለም ቢመጡም፤ ከአሸባሪው “ግንቦት ሰባት” ጋር የፈፀሙት “ጋብቻ” የሚታወቅ እንዲሁም ስልጣንን በአቋራጭ ለማግኘት ሲባል የተደረገ ነው ማለት ይቻላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አቶ ሌንጮ ህገ- መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ትናንት የነበሩበትን የሽብር ቦታ አለመተዋቸውን የሚያሳይ ነው። እናም ከ“ግንቦት ሰባት” ጋር ያደረጉት የጥፋት “ጋብቻ” በስም ብቻ የተውትን “ኦነግ”ን የሽብር ዓላማ ለማሳካት የተደረገ ጥምረት ይመስለኛል።
“ኦዴግ”ን እዚህ ላይ ትተነው፤ ወደ አሸባሪው “ግንቦት ሰባት” ስናመራ ይህ በኤርትራ መንግስት እስትንፋስ የሚመራው ቡድን፤ በኤርትራ መንግስት እስከታዘዘ ድረስ ከማይቧደነው አካል ጋር የለም። ሻዕቢያ “ተጣመር” ሲለው ዓይኑን ሳያሽ ከሌላ ፀረ-ሰላም ኃይል ጋር የሚቀናጅ፤ “ተነጠል” ካለው ደግሞ ከመቅፅበት የሚቆራኝና በአስመራው መንግስት “የሙቀት መጠን” የሚንቀሳቀስ ነው። በአጭሩ የኢትዮጵያንና የሌሎች ጎረቤት ሀገራትን አሸባሪዎችንና ፀረ-ሰላም ኃይሎችን አቅፎ የያዘው የኤርትራ መንግስት አጀንዳ ሲያጣ የሚያቆራኘው፤ ጥርጣሬ ሲያድርበት ደግሞ “ተነጠል!” የሚለው የሙቀት መለኪያው ቴርሞ ሜትሩ ነው ማለት ይቻላል። የሽብር ቡድኑ በሻዕቢያ ሲቀጠል የሚሰፋና ሲቀደድ ደግሞ የሚተረተር ነው። የራሱ የሆነ ልኬታ የለውም። የኤርትራ መንግስትን የብተና ፖሊሲ ተከትሎ በተወጠረለት ቀጭን መስመር ላይ የሚሄድ እንጂ፤ ከስም በስተቀር ከኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር የለውም።
ይህ በሻዕቢያ ሳንባ የሚተነፍሰው የትምክህት ኃይል አስመራ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሳይጠሩት “አቤት!”፣ ሳይልኩት “ወዴት?” ብሎ የሚጠይቅ ነው። መሬት ላይ በሌለ ተጨባጭ ማንነቱ ከተለያዩ አካላት (በተለይም ከዲያስፖራው) “ለትግል” እያለ የሚሰበስበው ገንዘብ በአሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የግል የባንክ ደብተር ውስጥ የሚገባ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህም በተለያዩ ወገኖች “የግንቦት ሰባት” መሪ መሪ በሆኑት አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ዲያስፖራው የሚሰጠውን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው በማዋል፣ ልክ እንደ ኤርትራ መንግስት ተቃዋሚነትንና ግጭትን እንደ ንግድ እየተጠቀሙበት ነው የሚል ስሞታ እየቀረበባቸው ነው። ከዚህም አልፎ የሚገኘው የዲያስፖራ ድጋፍ ለኤርትራ መንግስት የደቀቀ ኢኮኖሚ ማገገሚያ እየሆነም እንደሆነ ይነገራል። አንዳንዶችም ‘ግንቦት ሰባት ከዲያስፖራው የሚያገኘውን ድጋፍ የኤርትራ መንግስት ልክ ውጭ ካሉት ዜጎቹ እንደሚሰበስበው የሁለት በመቶ መዋጮ ይቆጥረዋል’ ሲሉ ይደመጣሉ። እንግዲህ በዚህ መልኩ የሀገሩን ዲያስፖራዎች ገንዘብ ለሻዕቢያ የሚያቀብለው “ግንቦት ሰባት” በትዕዛዝ ከ“ኦዴግ” ጋር መቀናጀቱ የሚገርም አይሆንም።
ለነገሩ ይህ የሽብር ቡድን የትናንት ማንነቱ ሲፈተሽ ከዚህም የዘለለ ተግባር በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን ላይ ፈፅሟል። እርግጥ የሽብር ቡድኑ የሀገራችን ወጣት እየተመዘገበ ካለው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ተጠቃሚ መሆኑን እንዲሁም ልማታዊ ዕድገቱ የተገኘው ከሀገሪቱ ፍፁም የፀና ሰላም እንደሆነ እንኳን በቅጡ ስለማይገነዘብ በሻዕቢያ እየተመራ ብዙ ተራውጧል። ‘ለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ድጋፍ አታድርጉ’ ከማለት ጀምሮ የህዳሴውን ግድብ እስከ መቃወም ድረስ የደረሱ የጥፋት መልዕክቶችን በማንገብ የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጥረቶች ለማኮላሸት ጥሯል፤ ደክሟል። ሆኖም እንደ ማንኛውም የሽብር ቡድን ተስፋው ጉም የመዝገን ያህል ብቻ ነው የሆነው—አልተሳካለትም።
በልሳኑ “ኢሳት” አማካኝነትም ህዝቦችን ከህዝቦች ሊያጋጩ የሚችሉ ዘረኛ ፕሮግራሞችን በማስተላለፍ ብዙ ጥሯል። ይህም አልተሳካለትም። ዛሬ በብዙ የሀገራችን ዜጎች ዘንድ “ኢሳት” የተሰኘው የአሸባሪዎች ጣቢያ የመጀመሪያና የመጨረሻ ግቡ የሻዕቢያን ተልዕኮ ማስፈፀም እንደሆነ ይታወቃል። በጀቱም ይሁን የጣቢያው አጀንዳ ከአስመራ የሚመጣ መሆኑም እንዲሁ። እናም በዚህ የሽብር ማካሄጃ ጣቢያ አማካኝነት የሚነገሩ ማናቸውም መረጃዎች ኢ-ተዓማኒ መሆናቸውን በርካታው የሀገራችን ህዝብ ይገነዘባል—ውጭ ሀገር ሆነው እዚህ ሀገር ውስጥ የሚከናወኑ ትክክለኛ ተግባራትን ከማያውቁ ጥቂት ዲያስፖራዎች በስተቀር። እናም በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው “ግንቦት ሰባት” አዳዲስ የማደናገሪያ መንገዶችን እየቀየሰ ጥምረትና ውህደት ቢፈፅም የሚገርም አይሆንም።
በአጠቃላይ በሻዕቢያ ትዕዛዝ የተፈረረመው “አብሮ የመስራት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ” ለግለሰቦች ጥቅም ካልሆነ በስተቀር እዚህ ሀገር ውስጥ ላለው ህዝብ የሚፈይደው ምንም ዓይነት ነገር የለም። እርግጥም እንዲህ ዓይነቱ ስምምነት ፋይዳ የሚኖረው መስፋትና መቅደድ ለተካነው እንዲሁም የኢትዮጵያ አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ቡድኖች ሲዋሃዱና ሲነጣጠሉ የሚያገኘውን ጥቅም ቁጭ ብሎ ለሚያሰላው ሻዕቢያ እንጂ ለሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚያመጣው ለውጥ የለም። የኤርትራ መንግስት እስካለ ድረስ ግን እርሱ የሚሰፋቸውና የሚቀዳቸው እነዚህ ቡድኖች ነገ በሌላ ቅርፅ ሊለወጡ አለመቻላቸውን ማንም እርግጠኛ ሊሆን አይችልም— “ኦዴግ”ም ይሁን “ግንቦት ሰባት” ነገ ከማን ጋር እንደሚጣመሩም ሆነ እንደሚነጣጠሉ የሚወስነው ሻዕቢያ ብቻ ነውና።