ባለፈው አንድ ወር ያህል ጊዜ ውስጥ በተለይ በአማራ ክልል የጎንደርና የጎጃም ዞን ከተሞች ሁከት ሲያስተናግዱ ቆይተዋል። ሁከቶቹ አሁንም ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው እየተሸጋገሩ እነዚህኑ የክልሉ ዞኖች ሰላም እየነሱ ይገኛሉ። በአማራ ክልል ሁለቱ ዞኖች አንዳንድ ከተሞች የሚቀሰቀሰው ሁከትና ውጭ አትውጡ፣ ስራ አትስሩ፣ አትነግዱ፣ አትግዙ የሚሉ የአዋኪዎቹ ትዕዛዞች ህዝቡን አስጨንቀውታል። አብዛኛው ነዋሪዎቻቸው በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በሚያገኙት ገቢ የሚተዳደሩባቸው እነዚህ አድማ እንዲደረግ ትእዛዝ የሚተላለፍባቸው ከተሞች ነዋሪዎች አይተጎሳቆሉ ነው። ስራቸውን ለማስፋፋት የሳምንትና የእለት እቁብ የበሉ በርካታ አነስተኛ ነጋዴዎች እዳቸውን መክፈል ተስኗቸው ግራ የተጋቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል። መጪው ሁኔታ አሳስቧቸዋል።
የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን የማተራመስ ውክልና የሰጣቸው ተስፋዬ ገብረአብ፣ ኤልያስ ክፍሌና የመሳሰሉ ግለሰቦች የሚመሯቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይ በፌስቡክ ገፆቻቸው በሚያስተላልፉት የረብሻና የአድማ ትእዛዝ አርሶ አደሩን ምርቱን ገበያ ማውጣት፣ ገበያ ወጥቶ መግዛት እንዳይችል አድርገውታል። አርሶ አደሩ ሁከት ስለሚሸሽ አዋኪዎቹ ትእዛዝ የተቀበሉ እለት ጭራሽ ወደከተማም አይወጣም። ይህ ሁኔታ አርሶ አደሩን፣ ነጋዴውን፣ ሸማቹን አማሯል። ህዝቡ የአድማ ትእዛዛቸውን አንፈፅምም ማለት ይፈራል። ትእዛዛቸውን የተላለፈ በጎረምሶች ይደበደባል፤ ንብረቱ ይወድማል፤ ዛቻና ማሰፈራሪያ ይሰነዘርበታል። በዚህ ምክንያት ህግና ስርአት እንዲሰፍንለት ይፈልጋል።
በሌላ በኩል ሁከቱን ውጭ ሃገር ሆነው የሚመሩት የኤርትራ መንግስትና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች “ጀግናው የምንትስ ከተማ ህዝብ መንገድ ዘግቶ ዋለ፣ ድልድይ ዘግቶ ዋለ፣ የከተማው ህዝብ ከቤት እንዳይወጣ አድርጎ ዋለ፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን አቃጠለ . . .” እያሉ በምክንያት ሳይሆን በስሜት የሚንዱ ወጣቶችን እየገፋፉ በሚያሳፍር ሁኔታ በጀብደኝነት አደባባይ እየወጡ በሁከቱ እንዲገፉበት እያደረጉ ነው። ኢሳያስ አፈውርቂም ቤተ መንግስታቸው ቁጭ ብለው ይህን “ግፋ በለው” ሲሉት ተነስቶ የራሱን ቤት እያቃጠለ ኢትዮጵያን የማተራመስ ህልማቸውን የሚያስፈፅም ስሜታዊ ወጣት በአድናቆት ሳይሆን በጅልነቱ እየታዘቡት እንዳሻቸው እያስነዱት መሆኑ ይሰማኛል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በማፈራራትም ሆነ በዲፕሎማሲ ማመስቆም ያልቻሉ ባለጋራዎቻችንም ከአሁን አሁን በእርስ በርስ ግጭት የተተረማመሰች፣ እንኳን ታላቁን የህዳሴ ግድብ የሚያክል ግዙፍ ፕሮጀክት ማከናወን ህዝቧን መመገብ የማትችል ደካማ ኢትዮጵያን ለማየት ጎምዥተዋል።
ይህ አሁን በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ሁከት ሁኔታ የሚገልፅ እውነት ነው።
ከሰሜን ጎንደር ዞን የጀመረው ሁከት መነሻ የሆነው የወልቃይት የአማራ ብሄረተኝነት ጥያቄ እንደነበረ ይታወሳል። ይህ ጉዳይ የወልቃይት ወረዳ የሚገኝበት የትግራይ ክልል ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት እልባት እንዲሰጠው፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች መሃከል የወሰን ጥያቄም ካለ የሁለቱ ክልሎች መንግስታት በመነጋገር እንዲፈቱት፣ ይህ ካልሆነ ግን ጉዳዩን በህገመንግስቱ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት እልባት እንዲያበጅለት የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ምክር ቤት ወስኗል። ይህ ውሳኔ የዘገየ መሆኑ፣ እንዲሁም የወልቃይት ጉዳይ ያገባኛል ብሎ የተደራጀው ቡድን የማንነት ጥያቄውን ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት ለትግራይ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳያቀርብ መቆየቱ እንደችግር የሚነሳ ቢሆንም ጉዳዩ ግን በህዝብ ውሳኔ መፍትሄ የሚያገኝበት ሃዲድ ላይ ወጥቷል።
ወጣቱን ብስሜታዊነት እንዲገነፍል ያደረጉት የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ የስራ አጥነት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ተጠቃሚ መሆን አለመቻል፣ ወዘተ ችግሮችንም ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ ትኩረት ለመፍታት እንደሚሰራ በህዝብ ውክልና ስልጣን የተረከበው ኢህአዴግ አስታውቋል። በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ችግሮች እንዲባባሱ ያደረጉ ስልጣንን ለህዝብ መገልገያነት ሳይሆን ለራስ ጥቅም ያዋሉ የስራ ሃላፊዎች መኖራቸውንም ምክር ቤቱ አሳውቆ በዚህ ላይ ከህዝቡ ጋር በመተባበር አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቋል።
በመሆኑም ወጣቱን ሁከት ውስጥ እንዲገባ የሚያስገድደው ምንም ዘለቄታዊ ፋይዳ የሚያመጣ ነባራዊ ሁኔታ የለም። በሁከት ዙሪያ ወጣቱ ሊገነዘባቸው የሚገባቸው እውነቶች አሉ። እነዚህም በሃይል የመንግስት ለውጥ ለማምጣት መሞከር በራሱ ህገወጥ መሆኑ፣ ሁከት አብዛኛውን ህዝብ የማይወክል ግብታዊ እርምጃ በመሆኑ በአብላጫ ድምጽ የተወከለን መንግስት ጥቂቶች በሚመሩትና በሚሳተፉበት ሁከት ለማስወገድ መሞከር ከሞራል አኳያም ጸያፍ መሆኑ እንዲሁም አላስፈላጊ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑ ናቸው። ሌላው ወጣቱ ሊገነዘበው የሚገባው ይህ በኢትዮጵያ የመንግስት አወቃቀር የማይቻል መሆኑን ነው።
የኤርትራ መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎችና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ቅጥረኞች፣ ባለማወቅ በስሜት ተገፋፍተው በሁከት የስርአት ለውጥ እናመጣለን ብለው የተነሳሱ ወጣቶችን ለማበረታታት መንግስት ተዳክሟል፣ ሊወድቅ ተቃርቧል ሲሉ ይደመጣሉ። እዚህ ላይ ግልፅ ያልሆነልን አንድ ነገር ቢኖር ይህ በሁከት የመንግስት ስርአት ለውጥ የማምጣት መከራ ከንቱና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ነው።
ከንቱ የሚያደርገው የኢፌዴሪ መንግስት አወቃቀር ማለትም ፌደራላዊው ስርአት ያልተማከለ በመሆኑ በሃገሪቱ አንድ ጥግ ወይም በአዲስ አበባ በሚቀሰቀስ ሁከት ሊናድ ወይም ሊፈርስ የማይችል መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ በአመዛኙ በብሄር ላይ ተመስርተው የተዋቀሩ ዘጠኝ ክልላዊ መንግስት ያላት ፌደራላዊት ሃገር ነች። የፌደራል መንግስቱ በራሱ ምንም ስልጣን የለውም። የፌደራል መንግስቱ ስልጣን የመነጨው ከዘጠኙ ክልላዊ መንግስታት ነው። የፌደራሉ መንግስት የሃገሪቱ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች የሆኑ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩባቸው ክልላዊ መንግስታት በእኩልነትና በመከባበር የህዝቦች አንድነት ያላት ሃገር ውስጥ ለመኖር በፍቃዳቸው የመሰረቱት ነው።
በመሆኑም ዘጠኙም ክልሎች በአንድ ጊዜ ተስማምተው ስርአታቸውን ካልቀየሩ ወይም ዘጠኙም ክልሎች ውስጥ የስርአት ለውጥ ተካሂዶ እነዚህ አዳዲስ የክልል መንግስታት የፌደራል መንግስቱን እንለውጥ ብለው በአንድ አፍ ካልተስማሙ አዲስ አበባ ላይ ወይም ባህርዳር ላይ በሃይል ቤተመንግስት በመያዝ መንግስት መለወጥ አይቻልም። ይህ በከተማ ሁከት የመንግስት ለውጥ የማምጣት አካሄድ የሚሰራው የመንግስት ስልጣን ከላይ ወደታች ወደጠቅላይ ግዛት ወይም ክፍለ ሃገር በሚወርድበት አሃዳዊ የመንግስት ስርአት ነው። በአሃዳዊ ስርአት “ሆ” ብሎ ቤተመንግስት የገባ ማንኛውም አካል በየክፍለሃገሩ ስልጣንና ባለስልጣን በማውረድ በቀላሉ የስርአት ለውጥ ማምጣት ይችላል።
አማራ ክልል ላይ ወይም አዲስ አበባ የሚነሳ ሁከት የኢትዮ ሶማሌን፣ የአፋርን፣ የጋምቤላን የኦሮሚያን ክልላዊ መንግስት አይነካም። አዲስ አበባ ወይም አማራ ክልል ቤተ መንግስት የገባ አካል ክልላዊ መንግስታትን ማዘዝ አይችልም። ስለዚህ የኢፌዴሪን መንግስት በሃይል የመለወጥ ሙከራ ትርፉ ድካምና ኪሳራ ብቻ ነው። አንድ ክልል ራሱን ከፌደራል ስርአት የመገንጠል ዓላማ ካለውም ምንም ልፋት ሳያስፈልገው ይህ ጥያቄ የህዝቡ መሆኑን በሚያረጋገጥ ህገመንግስታዊ መንገድ ማከናወን የሚቻልበት ስርአት አለ። እንዳጋጣሚ ክልላዊ መንግስታት አንድ ሃገር እንዲመሰርቱ ያደረጋቸውን የፌደራል መንግስት ሙሉ በሙሉ እንዳይሰራ የሚያደርግ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳን፣ ሃገር እንድትበታትን ከማድረግ ያለፈ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም።
እርግጥ በዚሁ የኢፌዴሪ የመንግስት ስርአት ውስጥ ስልጣን በውክልና የሚረከቡ አካላትን መቀየር ይቻላል። ይህንንም ቢሆን ማድረግ የሚቻለው በሰላማዊ የምርጫ ሂደት ብቻ ነው። የፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የየክልሉን ተወካዮች የያዘ በመሆኑ ይህን ምክር ቤት ከምርጫ ውጭ መቀየር የሚያስችል እድል የለም።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ወጣቶች በሃይል የስርአት ለውጥ ይመጣል የሚል ህልማቸውን ለማሳካት በመሳሪያነት ሊጠቀሙባቸው ያሰቡትን በውጭ ያሉ አካላት ችላ ብለው በሰላማዊ መንገድ የሃገሪቱን ዴሞክራሲ ለማጎልበት፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት፣ ልማትን ለማምጣትና ተጠቃሚ ለመሆን ሳይሰለቹ ለመስራት ቢነሳሱ የበልጥ ወደፊት ያዘልቃቸዋል። ሁከት መድረሻው ያው ሁከትና አላስፈላጊ መስዋእትነት ነው። ፌደራላዊ ስረአቱን ለመቀየር አያበቃም፤ አያስችልምም።