የትኛውም ስለሃገር እቆረቆራለሁ የሚል ዜጋ ሲያሻው በግሉ ሲያሻውም በቡድን መቆርቆሩን እና ተቃውሞውን ሲያሰማ ከዛሬ 25 አመታት አስቀድሞ ከህግ በላይ የሆኑትን ኢዴሞክራሲያዊ መንግስታት በማስወገድ በምትኩ ለመረጠው ህዝብና ለህግ ተጠያቂነት ያለው የዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት መጣሉን አምኖና ተቀብሎ ሊሆን ይገባዋል። በዴሞክራሲያዊ መንግስት የተቀረጹት ህጎች ሕገመንግስትንና ሌሎች ከሱ የሚቀዱትን ጨምሮ በማንኛውም ባለስልጣን ወይም ህግ ወይም ልማዳዊ አሰራር እንዳይጣስ የሚከላከልና የሚጠብቅ የፍትህ ስርአት በአገራችን እንዲገነባ በማለም ነው።
የመጨረሻው የስልጣን ባለቤት ህዝቡ በመሆኑ በህዝቡ ይሁንታ የጸደቁትን ህጎች ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊ የማድረግ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር፣ በጥቅሉ የህግ የበላይነት የነገሰባት አዲስ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት የፍትህ አካላቱን ጨምሮ ህዝቡም ስለህግ የበላይነት ከፍተኛ ሚና መጫወት የሚጠበቅበት መሆኑ ለድርድር መቅረብ የለበትም። ፈጣን የኢኮኖሚ እድገቱን ተከትሎ ዜጎች በውል/ህግ አሰራር ላይ የተመሰረተ ግልፅ የቢዝነስ ግንኙነት እንዲፈጥሩና ኢንቨስትመንት እንዲቀላጠፍ በህግ የበላይነት ስር ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
ይሁን እንጂ ዘርፉ ለበርካታ ዘመናት በልምድና በኋላቀር አሰራር ሲመራ የቆየ በመሆኑ የተለያዩ ተከታታይ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውና ለውጥም መመዝገቡ ባይካድም አሁንም ድረስ ዘርፉ ለኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ድርጊት የተጋለጠ ሆኖ ስለመቆየቱ የህግ የበላይነት አደጋ ላይ መውደቁን የተመለከቱ ክስተቶች ከሌሎቹ ጊዜ በተለየ እየተስተዋለ ነው። በጥቅሉ ሲታይ ከጀማሪ ዴሞክራሲ ስርአቱ በህብረተሰብ ደረጃ የህግ የበላይነትን የሚሸረሽሩ ኋላቀር አመላካከቶችና ፍላጎትን በሃይል የማስፈጸም ዝንባሌ አሁንም አለመቀረፉ የህይወትና የንብረት ዋጋዎች እያስከፈለን ሲሆን ከድህነት ጋር ዘመቻ ውስጥ የሚገኘውም ህዝብ በስጋት ተቀፍድዶ ለቀናት እንዲቆይ ምክንያት ሆኗል። ይህ ተረክም የስጋቱን ደረጃ በመጠቆም ስለህግ የበላይነት መንግስትና ህዝቡ የሚጠበቅባቸውን ለመጠቆም የሚሞክር ነው።
ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሳቢያ በተፈጠሩ የህግ የበላይነትን የጣሱ ክስተቶች የዜጎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡
ተቃውሞዎቹን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ለሕገወጥነት ተግባራቸው መጠቀሚያ ያደረጉ ቡድኖች እና ግለሰቦች በስፋትና በብዛት ታይተዋል፡፡ ሕገወጥነት በመስፈኑ ምክንያትም ጥቅል የሆነው የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ በመውደቁ በርካታ ዜጎች ስጋት ላይ ወድቀዋል፡፡ በዚህም ከለት ተለት እንቅስቃሴያቸው ተስተጓጉለዋል።
እንዲህ አይነት እንቅስቃሴዎች በዚህ ከቀጠሉ እና ሃይ ባይ ካላገኙ ሕገወጥነት የበላይነቱን በአስተማማኝ ሁኔታ ስለሚይዝ ዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባትና የመኖር መብታቸው ለአደጋ ከመጋለጡም በላይ፣ ሥርዓት አልበኝነት ሰፍኖ አገር የማትወጣው አደጋ ውስጥ መዘፈቋ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ማንም ሰው በሰላም የመኖር፣ የመሥራት፣ የመማር፣ የመንቀሳቀስ፣ ሀብት የማፍራት፣ የመሰለውን አመለካከት የማራመድና የመሳሰሉት መብቶች የሚከበሩለት የሕግ የበላይነት ሲኖር ብቻ መሆኑን ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም፡፡
የኢህአዴግ ምክር ቤትን ግምገማ ተከትሎ የሃገሪቱ ርእሰ መስትዳድር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳረጋገጡትም ሆነ የዘርፉ ልሂቃን እንደሚሉት የህግ የበላይነት አደጋ ላይ እንዲወድቅና ሰሞኑን ላየናቸው አይነት ውድመቶች የመጀመሪያው ምክንያት የሚሆነው በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ብሎ ምላሽ ሲፈልግ፣ መንግሥት በአግባቡ ተገቢውን መልስ የመስጠት ግዴታ ያለበት መሆኑን ሲዘነጋ ነው፡፡ ለጥያቄዎቹ ተገቢው ምላሽ በአግባቡና በጊዜው መስጠት ካልተቻለ የሕዝብ ጥያቄዎችን በመንተራስ ለጥፋትና ለውድመት የሚነሱ ኃይሎች ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠርላቸዋል፤ ሰሞኑን በተግባር የታየውም ይኸው ነው፡፡
የህግ የበላይነት አደጋ ላይ በመውደቁም ግለሰቦች ጥረው ግረው ያፈሯቸውን መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ መደብሮች፣ ማምረቻዎች፣ እርሻዎችና የመሳሰሉት በስርአት አልበኞቹ በእሳት ሲጋዩና መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ውድመቶች ሲደርሱ ለማየት አብቅቶናልና ብንሰጋ ወደን አይደለም፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች በግለሰቦችና በመንግሥት ተቋማት ላይ የተፈጸሙት የማውደም ተግባራት በዝርፊያ የታጀቡ በመሆናቸው የሕዝብ ጥያቄ ላልተፈለገ ዓላማ ስለመዋሉና ለስጋት የሚዳርግ ስርአት አልበኝነት ስለመንሰራፋቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በመንግሥት በጀት የተገነቡ መሠረተ ልማቶች፣ የመስተዳድር ጽሕፈት ቤቶችና ትምህርት ቤቶች ሳይቀሩ ወድመዋል፡፡ በየአካባቢው የሚገኙ የመስተዳድር አካላትና የፀጥታ ኃይሎች ሳይቀሩ ዓይናቸው እያየ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት፣ በብዙዎች ላይ ፍራቻን ከመፍጠራቸውም በላይ ወደተስፋ መቁረጥ እየወሰዳቸው መሆኑን ተገንዝቦ ከላይ በተመለከተው አግባብ ስለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በተቀመጠው የህግ ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ አስፈላጊ የሆነውን እርምጃ መውሰድና ህዝቡም ድጋፉን ከመስጠት ጀምሮ ስርአት አልበኞችን በማጋለጥና ቤተሰቡን በመምከር የሚገለጽ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ መሰረት መንግስት ጥያቄ አለኝ ብሎ ለተነሳው ህጋዊና ሰላማዊ ሕዝብ በአግባቡ እና በፍጥነት ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ሰላማዊ እና ህጋዊ ለሆነው ህዝብ መብት ሲሆን ዴሞክራሲያዊና ህዝባዊ ለሆነ መንግስት ደግሞ ግዴታ ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄ እየተደራረበና የምላሽ አሰጣጥ ሥርዓቱ ዘገምተኛ ሲሆን ነውጥ የመፈጠሩን አይቀሬነት በማመን ብቻ ሳይወሰን ከነውጡ መማሩንም ምክር ቤቱ ማረጋገጡ ስለዚህ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ሕገወጥ ድርጊቶች ሃይ ባይ ሲያጡ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች መደናገጣቸው እና የልማታችን እንቅስቃሴዎች ተስፋ ቢስ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም ማንኛውም የሕዝብ ጥያቄ አንግቤያለሁ የሚል ወገን ሕገወጦች የሚፈጽሙትን ተግባር ማጋለጥ ብቻ ሳይሆን ማውገዝም ስለህግ የበላይነት ግድ ይለዋል፡፡ በሥርዓቱ ላይ ደስተኛ ያልሆኑ ዜጎች ሳይቀሩ አገርንና ሕዝብን የበለጠ ትርምስ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ አደገኛ ድርጊቶች እንዲወገዱ፣ የሕዝብ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች በሕገወጦች እንዳይጠለፉና የሕግ የበላይነት ልዕልና እንዲያገኝ መትጋት ያለባቸው ስለመሆኑ የሰሞኑ እንቅስቃሴዎች ሁነኛ የማንቂያ ደወሎች ይሆናሉ ፡፡
መንግሥት ሕግ የማስከበር ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከማንም በላይም ለሕግ የበላይነት መኖር መሥራት ግዴታው መሆኑን ተገንዝቦ ለሚወስደው እርምጃ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግና እውቅና መስጠት ከየትኛውም ህጋዊና ሰላማዊ ዜጋ ሁሉ የሚጠበቅ መሆኑንም ከሰሞንኞቹ ህገወጥ እንቅስቃሴዎች በላይ ማስተማሪያ ማምጣት አያስፈልግም፡፡ በዚህ ጊዜ ሕግን በማስከበር ስም ከሚደረግ ሕገወጥ ተግባራት መራቅ ካልተቻለ ጊዜ ይወስድ እንደሆነ እንጂ አደጋው ከነበረውም የሚከፋ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ የሕግ የበላይነት መኖር ዋናው ጠቀሜታ ሥርዓት አልበኝነት አደብ እንዲገዛና ዜጎች ነፃነታቸው እንዲጠበቅ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ የሚፈልግ ዜጋ ሕገወጥነት ከዴሞክራሲ ይልቅ ወደ አምባገነንነት እንደሚያመራ መገንዘብ ይኖርበታል፡፡
የሰሞንኞቹ አይነት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር እያራመዱና የሚያራምዱ ሃይሎችን ዝም እያሉ ስለዴሞክራሲም ሆነ ስለሰብዓዊ መብት መረጋገጥ ለመደስኮር እና ለማሄስ መሞከር ግና ሲጀምር የከሸፈና ኢምክንያታዊነት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር ማንም ከሕግ በላይ አይሆንም፡፡ ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ይሆናሉ፡፡ ብዙኃን የበላይነት ሲኖራቸው የአናሳዎችም መብት ይከበራል፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት ይሆናል፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋ መብትና ግዴታ በሚገባ ይታወቃልና፡፡
የሕግ የበላይነት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተግባር እንዲረጋገጡ፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲሰፍን፣ ዜጎች በመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ቀረፃ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ውክልና እንዲኖራቸው፣ በሥልጣን ያላግባብ መገልገል እንዳይኖር፣ በሙስና መበልፀግ ነውር እንዲሆን፣ በአገር ጉዳይ ዜጎች የባለቤትነት ስሜታቸው እንዲጎለብት፣ ወዘተ የሚረዳ ፍቱን መሣሪያ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን የሠለጠነና ዘመናዊ አካሄድ ሐዲዱን በማሳት ሕገወጥነት እንዲሰፍንና ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ ማድረግ ለአገር ታላቅ በደል ነው፡፡ የሕዝብን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ተገን በማድረግ አገርን የሚያወድም ተግባር ውስጥ መሳተፍም ሆነ አይቶ እንዳላየ ማለፍ ሕገወጥነት ነው፡፡
የሕግ የበላይነት ዜጎች በምንም ዓይነት ሁኔታ ለጥቃት እንዳይጋለጡ፣ የሚወጡ ሕጎች በሙሉ መብቶቻቸውን እንዲያስከብሩ፣ እነሱም በአግባቡ ግዴታቸውን እንዲወጡ፣ ፍትሕ እንዲሰፍንና የዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች እንዲከበሩ ይጠቅማል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባውም ሆነ አገር ሰላም የምትሆነው የሕግ የበላይነት ሲሰፍን ብቻ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይገባም፡፡የሕግ የበላይነት በሌለበት አምባገነንነትና ፀረ ዴሞክራቲክ ድርጊቶች የሚበዙ ስለመሆኑም ከሰሞኑ በተቃውሞ ሰልፎች ስም ከደረሱት አውዳሚ ድርጊቶች በላይ ሌላ ማሳያ መጠበቅም ጅልነት ነው፡፡ ከሕግ የበላይነት በተቃራኒ የሚፈጸሙ ድርጊቶች በሙሉ ለአገር አይበጁም፡፡ እንዲህ ዓይነት ለሕዝብ የማይጠቅሙ ድርጊቶችን በቸልተኝነት ማለፍም የሚሆነው የድርጊቶቹ ተባባሪ መሆን ብቻ ነው፡፡
ስለሆነም ምክር ቤቱ በግምገማው የደረሰባቸውን እና አርማቸዋለሁ ያላቸውን ችግሮች ከማረም ባሻገር በቀጣይም የኢትዮጵያን ህዳሴ በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለመገንባት በሚደረገው ሁለገብ ርብርብ ማናቸውም እንቅስቃሴ በህግ የበላይነት ማእቀፍ ስር ሆኖ እንዲከናወን ሃላፊነቱን ሊወጣና ህዝቡም ከላይ በተመለከቱት አገባቦች ግዴታውን እንዲወጣ እናሳስባለን፤ ይጠበቃልም።