የነቃን ህብረተሰብ የሚመጥነውን አመራር ይፈልጋል

የኢህአዴግ ምክር ቤት የአስራአምስት ዓመታት ሂደት ግምገማው ሃገሪቱ የምትገኝበትን ሁኔታ አስቀምጧል፤ እንደግምገማው ከሆነ፣ በአሁኑ ሰአት ሃገሪቱ በአንድ ወገን በሚያስጎመጅ በሌላ በኩል ደግሞ በሚያስፈራ ሁኔታ ውስጥ ነው የምትገኘው። እነዚህ ሁኔታዎች በተጨባጭ መኖራቸውንና የአሁን የሃገሪቱ  ነባራዊ ሁኔታ መገለጫ መሆናቸውም ታምኖበታል። የሚያስጎመጀው የሃገሪቱ ገጽታ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በገጠር በግብርና፤ በከተማ በአገልገሎት፣ በኢንደስትሪና በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት እንዲሁም በትራንስፖርት – በመንገድ፣ በባቡርና በአቪየሽን፤ በሃይል፤ በማህበራዊ ልማት – ትምህርትና ጤና፣ . . . የተመዘገበው እድገት ነው። ይህ ብቻ አይደለም የሰለጠነና በስራ ፈጠራ ስኬታማ መሆን የሚፈልግ ዜጋ ተፈጥሯል። ልብ በሉ በ70ዎቹ የነበሩ የተማሩ ወጣቶች ተስፋ የቆረጡ ስለነበሩ ወደማስቲክ ዓለም ነበር የሚያዘነብሉት፤ በወቅቱ የራምፓን መፅሃፍት ማንበብ የተለመደ የተማሩ ወጣቶች ተግባር ነበር። የአሁን ዘመን የተማሩ ወጣቶች ግን ነባራዊውን ዓለም ተገንዝበው ሰርተው ስኬታማ መሆን የሚያስችሏቸውን መጽሃፍት ሲያነቡ ነው የሚታዩት። ይህ የስራና የስኬት ተነሳሽነት ትልቅ የመወንጨፊያ አቅም ነው። አሁን በሃገር ውስጥ የካፒታል አቅም አለ። ይህም ቀደም ሲል ያልነበረ ትልቅ እምቅ አቅም ነው። በአጠቃላይ ይህ የባለፉት አስራአምስት ዓመታት ተከታታይ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት፣ የአመለካከት ለውጥና የካፒታል አቅም የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ አቅም ነው።

በእነዚህ ዘርፎች የተመዘገቡና ሃገሪቱን በማስወንጨፍ ህዳሴዋን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስኬቶች ዙሪያ ያሉ አሃዞችና የእድገቱ ምክንያት የሆኑ ፖሊሲዎች በተደጋጋሚ የተነገሩ፣ ውይይት የተደረገባቸውና ታትመው የተሰራጩ በመሆናቸው እዚህ መድገሙ አንባቢን ማሰልቸት እንዳይሆንብኝ ስለሰጋሁ አለማንሳቱን መርጫለሁ። ግን ባለፉት አስራ አምስት አመታት በግብርና፣ በኢንደስትሪ፣ በማህበራዊ ልማት፣ በመሰረተ ልማት፣ በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ፣ በዲፕሎማሲና ሰላም ወዘተ የተገኙ ስኬቶች ሃገሪቱን ወደህዳሴ የማሸጋገር አቅም ያስገኙ መሆናቸው የሚያጠያይቅ አለመሆኑን በድፍረት እናገራለሁ። እናም በዚሀ ፅሁፍ በስኬቶቹ በመወንጨፍ የሃገሪቱን ህዳሴ የሚያረጋግጥ ሂደት ላይ የተጋረጠ የሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ሌላኛው ገጽታ የሆነ አስፈሪ ስጋት ላይ አተኩራለሁ። ይህ ስጋት የሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንዱ መገለጫ ነው። የኢህአዴግ ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው ግምገማ ይህን ስጋት መርምሮ መፍትሄ ያላቸውን አማራጮች አስቀምጧል።

ለአንድ ተኩል አስርት ዓመታት ተከታታይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ማሰመዘገብ ቢቻልም የህዝቡ ተጠቃሚነት ግን የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱ አንዱ ስጋት ያስከተለ አስፈሪ ሁኔታ ነው። ይህ የህዝብ ፍላጎት አለመሟላት ቅሬታ ፈጥሯል። ቅሬታው እዚህም እዚያም በተቃውሞ መልክ ሲፈነዳ ይታያል። ቅሬታው የሀገሪቱ ጠላቶች ስርአቱን ለማፍረስና ሃገሪቱን በታትኖ ለማዳከም እንዲነሳሱ ያደረገ አመቺና ተቀጣጣይ ሁኔታንም ፈጥሯል።

ይህ ቅሬታን የፈጠረና ወደተቃውሞነት ያደገን የህዝብ ፍላጎት በሚያረካ አኳኋን  አለመሟላት የተለያዩ መነሻ ምክንያቶች አሉት። አንዱ ምክንያት ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት የሃገሪቱ የህዝብ ቁጥር በእጥፍ ያህል መጨመሩ ነው። ህዝብ አእምሮውንና ጉለበቱን ተጠቅሞ የማምረት ስራ ላይ መሰማራት የሚችለበት ሁኔታ ሲኖር የሃገር አቅም የሚሆነውን ያህል፣ ይህ አቅም ተሟጦ ስራ ላይ ካልዋለ ግን እዳ ነው የሚሆነው። በሃገሪቱ የተፈጠረውን ተጨማሪ የሰው ሃይል ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ማሰማራት ባለመቻሉ በቀላሉ የማይገመት ቁጥር ያለው ከስራ ውጭ የሆነ ለዛውም የተማረ የሰው ሃይል ተፈጠሯል። እነዚህ ከማምረት ስራ ውጭ ሆነው ለጥገኝነት የተዳረጉ ዜጎች ስርአቱ ላይ ቅሬታ ተፈጥሮባቸዋል።

ሌላው የቅሬታ ምንጭ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገቱ የፈጠራቸውን ተጨማሪ ፍላጎቶች ማሟላት ካለመቻል የመነጨ ነው። ከሃያአምስት ዓመታት በፊት ከአርሶ አደሩ ልጆች የመማር እድል የሚያገኙት እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። አሁን ግን በተለያየ ደረጃ ማለትም 8ኛ ክፍል ያጠናቀቁ፣ 10ኛ ክፍል ያጠናቀቁ፣ በተለያየ ደረጃ ከቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ ተቃማት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የወጡ በርካታ የአርሶ አደር ልጆች አሉ። እነዚህ እንደአባቶቻቻው በነባሩ የግብርና ሰራ ላይ ተሰማርተው በገጠር የመኖር ፍላጎት የላቸውም። በሌላ ስራ ላይ ተሰማርተው ካደጉበት በተሻለ የኑሮ ሁኔታ በከተሞች የመኖር ፍላጎት ነው ያላቸው። ይህን የተማሩ የአርሶ አደሩን ልጆች ፈላጎት ሙሉ በሙሉ ማሟላት የሚችል የስራ እድል እስካሁን አልተፈጠረም።

በአጠቃላይ የሃገሪቱ ህዝብ ፍላጎት ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃጸር በእጅጉ ጨምሯል። ይህ የፍላጎት መጨመር ከኢኮኖሚ እድገቱ የመነጨ ነው። ቀደም ሲል የአበዛኛው የከተማ ነዋሪዎች የንፁህ ወሃ ፍላጎት በጣም ውስን ነበር። የህዝቡ የውሃ ፍላጎት በመጠጥ ወሃ፣ በሳምንት አንድ ግዜ ገላ ለመታጠብና ልብስ ለማጠብ ከሚውል ፍላጎት የዘለለ አልነበረም። የከተሞች የዕለት የነብስ ወከፍ የውሃ ፈላጎት እጅግ ቢበዛ ከአምስት ሊትር አይበልጥም ነበር። አሁን ግን ይህ ተቀይሯል። በአዲስ አበባ ብቻ ችምችም ባሉ መንደሮችና ደሳሳ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በጋራ የጉደጓድ መጸዳጃ ቤት እየተጠቀሙ ይኖሩ የነበሩ ከ5 መቶ ሺህ የማያንሱ ነዋሪዎች (ከ100 ሺህ በላይ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች ተሰጥተዋል) አሁን ደረጃቸውን በጠበቁ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ውስጥ ነው የሚኖሩት። የኮነዶሚኒየም ቤቶች ዘመናዊ መጸዳጃና የመታጠቢያ ፋሲሊቲ ያላቸው በመሆኑ፣ የነፍስ ወከፍ የውሃ ፍላጎት ቀደም ሲል ከነበረው ቢያንሰ በአምስት እጥፍ ጨምሯል። በከተሞች አዲሰ አበባን ጨምሮ ለመኖሪያና ለተለያዩ አገልገሎቶች የተገነቡ ዘመናዊ ህንጻዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ይፈልጋሉ። ይህም የነፍስ ወከፍ የውሃ ፍላጎትን ጨምሮታል። በከተሞች የሚከናወኑት ከተሞቹን የኮንስትራክሽን  ዎርክ ሾፕ ያስመሰሉ የኮንስትራክሽን ስራዎች ከፈተኛ መጠን ያለው ወሃ ይፈልጋሉ።

ይህን ተጨማሪ የውሃ ፍላጎት ቀደም ሲል በነበረው የወሃ ምንጭና የስርጭት አውታር ማሟላት አልተቻለም። ይህ ሁኔታ ከከተሞች የቆዳ ስፋት መጨመር ጋር ተዳመሮ የውሃ ፈላጎትን ማርካት ያልተቻለበትን ሁኔታ አስከትሏል፤ ይህ በበኩሉ የህዝብ ቀሬታን ፈጥሯል። በተደጋጋሚ አዲስ አበባን ጨመሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች በመገናኛ ብዙሃን የምንሰማው የውሃ ተቋረጠብን፣ ውሃ አልደረሰንም የሚል የመረረ አቤቱታ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል።

በኤሌትሪክ ሃይል ፍላጎት ረገድም ያለው ሁኔታ ተመሳሰይ ነው። ባለፉት አስራአምስት አመታት የሃገሪቱ የሃይል አቅርቦት በአስር እጥፍ ገደማ ቢጨምርም ሃይል አልደረሰኝም፣ ይቆራረጥብኛል . . . የሚሉ አቤቱታዎች ግን ከመቀነስ ይልቅ ጨምረዋል። ባለፉት አስራ አምስተ ዓመታት ከዚያ ቀደም በአወራጃ ደረጃ ካሉ ከተሞች ያላለፈው የኤሌትሪክ ስርጭት አሁን በሁሉም ከተሞች ሊባል በሚችል ደረጃ ተዳርሷል። እንኳን ከተሞች አርሶ አደሩ የሃይል አቅርቦት ጥያቄ የሚያቀርበበት ደረጃ ላይ ተደረሷል። የሃይል ስርጭቱ ከመስፋቱ በተጨማሪ የሃይል አጠቃቀመ ሁኔታው ተቀየሯል። ቀደም ሲል የኤሌትሪክ ሃይልን ከመብራት ያለፈ የሚጠቀሙ ዜጎች ቁጥር እጅግ አነሰተኛ ነው። በተለይ በሃገሪቱ መካከለኛና አነስተኛ ከተሞቸ የነበረው የሃይል ፈላጎት በመብራት የተገደበ ነበር።

ዛሬ ይህ ሁኔታ በእጅጉ ተቀይሯል። የቤተሰበ የኤሌትሪክ ፈላጎት ከምሽት ብርሃን አልፎ ሪፈሪጀሬተር፣ ቴሌቪዥንና መሰል የኤሌክትሮኒክስ ፋሲሊቲዎች፣ ለማገዶ ወዘተ ወደመሆን ከፍ ብሏል። ይህ ሁኔታ የቤተሰብ የሃይል ፍላጎት ከአስር እጥፍ በላይ እንዲያድግ አድርጓል። የሃይል መቆራረጥ ኑራቸውን ያመሰቃቅለዋል። እናም ሊታገሱት የማይችሉት ሆኗል። ቀደም ሲል በአንድ የኤሌትሪከ ቆጣሪ አራት፣ አምስትና ከዚያ በላይ ቤተሰቦች የሚጠቀሙበት ሁኔታ ተቀይሮ የኤሌትሪክ ቆጣሪ ፍላጎት በቤተሰብ ደረጃ ሆኗል። ይህ በአጭር ግዜ የተፈጠረ ከፍተኛ የኤሌትሪክ ፍጆታ ማደግና የስርጭት አለመቆራረጥ ፍላጎት ለመንግስት ፈተና ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ባሉት ግዜያት ለነበረው ዝቅተኛ የኤሌትሪክ ፍላጎት  ይውል የነበረው የሃይል ማከፋፈያና መሰመር ከፍተኛውን የሃይል ፍላጎት መሸከም እያቃተው ለሃይል መቆራረጥ ምክንያት ሆኗል። ይህን ፈታኝ ሁኔታ በአጭር ግዜ ውስጥ ማሟላት አለመቻል የህዝብ ቅሬታ ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ ባሻገር በየደረጃው ያሉ የመንግስት አመራሮች የህዝብ አገልጋይነት መነፈስ አጦትና ኪራይ ሰብሳቢነት ደገሞ የህዝብን ፈላጎት የማሟላት ተግባር እንቅፋት መሆኑን የኢህአደግ ምክር ቤት በግምገማው ማረጋገጡን አስታውቋል። በሃገሪቱ ዋነኛው የካፒታል ኢንቨስተር መንግስት ነው። መንግስት በየዓመቱ በተለይ መሰረተ ልማትንና ሌሎቸ ወሳኝ የሆኑ የግል ባለሃበቱ ሊሰማራባቸው የማይችላቸውና ፍቃደኛ ያልሆነባቸው የስኳር፣ ማዳበሪያ . . . ፋበሪካዎች ላይ በብዙ ቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ  ይመድባል። በዚህ ዙሪያ ከፕሮጀክት አሰጣጥ፣ አፈፃፀምና የበጀት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር ይስተዋላል። ፕሮጀከቶች በጥቅም ግንኙነት አቅም ለሌላቸው ተቋራጮች የሚሰጡበት ሁኔታ የተለመደ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ አቅመ ቢስ ተቋራጮች ፕሮጀክቶቹን አጠናቀው ማስረከብ በሚኖረባቸው ግዜ ገና ጅምር ላይ ሲዳከሩ መመለከት የተለመደ ነው። ፕሮጀከቶች እጅግ በተራዘመ ግዜ ከተያዘላቸው በጀት ከእጥፍ በላይ በልተው የሚጠናቀቁበትም ሁኔታ እንዲሁ የተለመደ ነው። በዚህ አኳኋን መድረሻቸው መገንባት እስኪመስል ድረስ መጨረሻ የሌላቸው በርካታ ግዙፍ ፕሮጀከቶችን ታዝበናል። የዚህ ምክንያት በከፊል በመንግስት የስራ ሃላፊዎችና በግል ተቋራጮች መሃከል ያለ የጥቅም ግንኙነት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የብቃት እጥረትም በዚህ ውስጥ ድርሻ አለው። ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት በሚገባ ተፈትሾ የተረጋገጠ ዲዛይን እንዲኖራቸው አለማድረግ፣ በዚህ ምክንያት ተደጋጋሚ የዲዛይን ማሻሻያ ማከናወን፣ አንዳንዴም ጭራሽ የተሟላ ዲዛይን ሳይዘጋጅ በሂደት ይሰራል በሚል ወደግንባታ መሸጋገር ወዘተ ለፕሮጀከቶች የተንዛዛ መጓተትና ከተያዘላቸው ባጀት ከእጥፍ በላይ እነዲፈጁ ማደረግ ምክንያቶች መሆናቸው ተረጋግጧል።

ይህ ሁኔታ ግዙፍ ፕሮጀከቶች በግዜ ተጠናቀው የህዝቡን ፍላጎት እንዳያሟሉ ምክንያት ሆኗል። ሌሎች ፍላጎቶችን ለማሟላት ተግባር ይውል የነበረን ከፍተኛ የሃገር ሃብት በማባከን መንግስት እጅ እንዲያጠረው ያደረጉበት ሁኔታም አለ። ይህ ደግሞ የህዝብን እርካታ ማማሏት የሚያስችል አቅም በማሳጣት ለህዝብ ቅሬታ መፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪ ከመሬት አሰተዳደር፣ ከግብር አሰተዳደርና ከኮንትሮባንድ ንግድ . . .ወዘተ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት በመንግስት የስራ ሃላፊዎችና በግለሰቦች ሲመዘበር ቆይቷል። ይህ የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ዜጎች ፍትሃዊና ህጋዊ ጥያቄዎቻቸውን ማስፈጸም የሚያስችል መልካም አስተዳደር እንዲጓደል ምክንያት ሆኗል።

ከህዝብ የልማትና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ጋር በተገናኘም የተሰተዋሉ ችግሮች አሉ። በተለያየ የሃገሪቱ አካባቢዎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በሚያሳለፉት ወሳኔ ዙሪያ ህዝብን አስቀድመው አለማወያየታቸው፣ ወሳኔዎቹ የልማት ተጠቃሚ እንዳልሆን ያቅቡኛል፣ ህገመንግስታዊ መብቴን ሊጥሱ ይችላሉ . . . የሚል ስጋት የተፈጠረበትን ሁኔታ አስከትሏል። የኦሮሚያውን፣ የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ረቂቅ ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። ከዚሀ በተጨማሪ የማንነትና ሌሎች የመብት ጠያቄዎች ተነስተው በወቅቱ ፈጣን ምላሽ ሳያገኙ የሚቀሩባቸውም አጋጣሚዎች የተለመዱ ናቸው። እነዚህ ስጋቶችና ቅሬታዎች  ውስጥ ውስጡን ተብላልተው አመቺ አጋጣሚ ሲያገኙ ወይም አመቺ ሁኔታ ሲመቻችላቸው የፈነዱበት ሁኔታም ታይቷል። በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያጋጠሙ ሁከቶች ለዚህ በቂ አስረጂዎች ናቸው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላው መታየት ያለበት ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተማረ ሃይል ተፈጥሯል። በተለይ ሲቪክስ እየተማረ ህገመንግስቱን፣ የመንግስትን ምንነት፣ መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ ተገንዝቦ ያደገው አዲሱ ትውልድ ጠያቂ ትውልድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የፕሬሰ ነፃነት መረጋገጡና ዓለምን አንድ ትንሽ መንደር ያደረገው የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ወቅታዊ፣ ሃገራዊና ዓለም አቀፍ መረጃዎችን እስኪበቃው አስታጥቀውታል።

እንግዲህ ይህን የተማረ፣ መረጃ የታጠቀና ከላይ በተገለጹት ሁኔታዎቸ ቅሬታ ያደረበትን ጠያቂና ወጣት ትውልድ ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት በነበረው መንገድ ማስተዳደር የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አሁን በሃገሪቱ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ብቃት ያለውና የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ያለው አመራርን የግድ እያለ ነው።

ከላይ የተጠቀሱት የህዝብ ቅሬታዎች የፈጠሩት ሁኔታዎች፣ ወደተቃውሞ ማደጋቸው፣  ተቃውሞዎቹን ለራሳቸው ዓላማ መጠቀም የሚፈለጉ የሃገሪቱ ጠላቶች ከመኖራቸው ጋር ተዳመሮ የሃገሪቱን ቀጣይ እጣ ፈንታ አደጋ ላይ ሊጥል እየቃጣው ነው። የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው የአስራ አምስት ዓመታት አፈፃጸም ግምገማ ይህን አስፈሪ ሁኔታ ለይቷል። ችግሮቹን አቃሎ የህዝብ እርካታ መፍጠር አማራጭ የሌለው መሆኑን ተረድቷል፤ የመፍትሄ አማራጮችም አስቀምጧል። ተግባሩንና ውጤቱን ደግሞ ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል።

በአጠቃላይ፣ ሃገርን ብቃትና የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ባላቸው የስራ ሃላፊዎች በመምራት እድገትና ልማት ከህዝብ ቁጥር እድገት እንዲሁም  እድገትን ተከትሎ እየጨመረ ከሚሄድ ፍላጎት ጋር ተጣጥሞ የህዝብን ፍላጎት ማርካት ካልተቻለ፣ የመብት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ካልተሰጣቸው ህዝብ ቅሬታ መፈጠሩ አይቀሬ እውነት ነው። ቅሬታው ወደቁጣና የከረረ ተቃውሞ መሸጋጋሩም እንዲሁ አይቀሬ ነው። ህዝብ ይህን ቅሬታውንና ቁጣውን በውክልና የሰጠውን ስልጣን ድምጹን በመንፈግ ሽሮ የሚገልጽበት መብት ያለው መሆኑ ሳይዘነጋ፣ ይህን ሰላማዊ መንገድ ገፍቶ ገንፍሎ ተቃውሞውን በሁከት የሚገለፅባቸው አጋጣሚዎችም እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ ውጫዊና ውስጣዊ ሁኔታዎች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም። በተገባደደው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሱት ሁከቶች ለዚህ በአስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

በመሆኑም መንግስት የህዝብን እውቀትና ጠያቂነት በሚመጥን የአስተዳደር ስርአትና ብቃት ባላቸው፣ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ በነገሰባቸው የስራ ኃላፊዎች ህዝብን በማስተዳደር ፍላጎቶቹን ማርካት፣ ጥያቄዎቹን አያዳመጠ አሳታፊ በሆነ መንገድ ምላሸ መሰጠት ይኖረበታል።

የህዝብን ቀሬታ በአግባቡና በወቀቱ አለመመለስና የህዝብን ፍላጎት ማርካት አለመቻል የወለደው ተቃውሞና ቁጣ ስርአቱን ለአደጋ አጋለጦ ባለፉት አስራአምስት ዓመታት ስኬቶች የተፈጠሩትን ሃገሪቱን ወደህዳሴ ዘመን ሊያሻግሩ የሚችሉ አጓጊ መልካም ሁኔታዎችን አምክኖ እንዳያስቀር ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ቀዳሚው እርምጃ የህዝቡን እውቀትና ጠያቂነት የሚመጥን ስርአት መዘርጋትና በቃትና የአገልጋይነት መነፈስ ያላቸው የስራ ሃላፊዎችን መመደበ ነው። ይሄው ነው።