ስህተትን አምኖ በመቀበልና በመታረም ቁርጠኝነት ኢህአዴግን የሚተካከለው ማነው?!!

በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በተለይ ደግሞ በኦሮሚያና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች የተፈጠሩት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችና የተቃውሞ ሠልፎች፣ የብዙ ዜጐችን ሕይወት ከመቅጠፍ ባለፈ ለበርካታ ንብረቶችም ውድመት ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ዕቅድን መነሻ ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰው የተቃውሞ እንቅስቃሴ መፍትሔ የተሰጠው መሆኑ ቢታወቅም፣ በአማራ ክልል ደግሞ በቅማንትና በወልቃይት የማንነት ጉዳይ የተነሱ ጥያቄዎች የሚፈቱባቸው ህገመንግስታዊ አካሄዶች ሊኖሩ ሲገባና ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል አሰራርና ስርአት በተዘረጋበት ሃገር ላይ እንዲህ አይነት ጥፋቶች መከሰታቸው በእርግጥም ያሳስባል፤ ያሳዝናልም።

ይህን ተከትሎም መንግስት የተለያዩ የውሳኔ ሃሳቦችን እና የችግሮቹን መንስኤ የተመለከቱ መረጃዎች እየሰጠ ባለበት ጎን ለጎን ከተለያዩ አካላቶች የተለያዩና ይልቁንም አባባሽ የሚሆኑ ትችቶችን በገዢው ፓርቲ ላይ ሲሰነዝሩ ሉይታያ። ይህ ተረክም እንደሃገር የሚጠቅመው የትኛው መሆኑን ለማጠየቅ እየተሰነዘሩ ከሚገኙት አባባሽ ትችቶች ሁነኛ ማሳያ ሊሆኑ ከሚችሉት ጥቂቶቹን ጠቅሶ ገዢ የሆነውን ፓርቲ ይመዝናል።

እንዲህ ያለ አስቸጋሪ ነገር ሊከሰት እንደሚችል በተደጋጋሚ ለመንግሥት አሳውቀን የነበረ ቢሆንም መንግሥት ሊሰማን ባለመቻሉ ሕዝቡ ችግሩን ራሱ ወደ አደባባይ ይዞት መጥቷል በማለት፣ አሁን የተከሰተው ችግር ሥር የሰደደና ሲንከባለል የመጣ ነው በማለት  መንግሥትን ክፉኛ ከሚተቹት ፓርቲዎች እንደማሳያነት ለዚህ ጽሁፍ ከተመረጡት አንደኛው መኢአድ ነው ፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት ዋናው ቁም ነገር መንግሥት ችግሩ ምንድነው? የችግሩ መፍትሔስ ምንድነው? እነዚህ ችግሮች በየቦታው የሚፈጠሩት ለምንድን ነው? ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል ሲሉ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ ለሪፖርተር ጋዜጣ መናገራቸውን አንብበናል፡፡

ይህን ሲያደርግም ተጠያቂውን ሌላ አካል ማድረግ ሳይሆን በእኔስ በኩል መሟላት ያለበት ምንድነው? የሚለውን አትኩሮ መመልከት አለበት። ‹‹ኢሕአዴግ ሁልጊዜ ሌላውን ስህተተኛ ራሱን ደግሞ ምንም ስህተት የማይሠራ እያስመሰለ ነው ችግሮችን ለመፍታት የሚሞክረው፡፡ ይህ ደግሞ እንደማይሠራ የሰሞኑ የአገሪቱ ሁኔታ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው፤›› የሚለውን ትችትና ኢሕአዴግ የሌሎችንም ሐሳብ እንዲያዳምጥና የመፍትሔው አካል ማድረግ እንዳለበት ማሳሰቢያም ጭምር ስለመስጠታቸው ከዚሁ ጋዜጣ አይተናል።

በተመሳሳይ የሕዝቡ ጥያቄ በተለያየ መልኩ ሲንከባለል የመጣ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ቃላቸውን የሰጡት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ፣ ችግሮቹን ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ ቆም ብሎ ጉዳዩን ማጤንና መመርመር ያሻል ማለታቸውም በጋዜጣው ተመልክቷል፡፡

ሌሎቹም በአብዛኛው ከላይ የተመለከቱ አይነቶችን አስተያየት የሰጡ በመሆኑ ስለአጀንዳችን እንደማሳያነት እነዚህ በቂ ይሆናሉ። በእነዚህ ማሳያዎች አግባብ በዋናነት ገዢው ፓርቲን የምንመዝነው “ችግሮችን ውጫዊ ያደርጋል፤ እራሱን ከመፈተሽና ከማረም ባሻገር ችግሮችን ውጫዊ የማድረግና ህዝብን የማይሰማ ድርጅት በመሆኑ የመጣ ጣጣ ነው” የሚሉ ጭብጦችን የተመለከተውን ነው። ስለሆነም ኢሃዴግ ህዝብን ባለመስማትና እራሱን ባለማረም የሚገለጽ ድርጅት ነው ወይስ ሌላ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መሻት ትክክለኛው መረጃ እና እውነታ ላይ ያደርሰናል።

የቀድሞው የኢህአዴግ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ በአንድ ወቅት የተናገሩትን እዚህ ጋር ማስታወስ ስለአጀንዳችን ተገቢ ይሆናል። ከግንባሩ ስህተትን የተመለከቱ ጉዳዮች  ጋር ተያይዞ እንዲህ ነበር ያሉት “የመላዕክት ስብስብ” ሳይሆን፣ የሰዎች ስብስብ በመሆኑ ስህተት ከመስራት ውጭ አልነበረም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ይልቁንም እንደ ማንኛውም የሰዎች ስብስብ ስህተት የሰራና ሊሰራም የሚችል ነው፡፡” የሚል አስተያየትን ነበር የሰጡት።

አገራችን  ለዘመናት ከምትወቀስበትና መለያዋ ተደርጎ ከምትታወቅበት ወጥታ ወደ ፈጣን እድገት የተራመደችውና ይህም ለሩብ ምዕተ ዓመት የቀጠለው መንግስትን የሚመራው ፓርቲ በጉዞው ምንም አይነት ፈተና ሳያጋጥመው መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ ስለነበረ እንዳልሆነ ከላይ የተመለከተው የቀድሞው ሊቀመንበር ንግግርም ሆነ ተፈጥሯዊ የሆነ አመክንዮ መሆኑ የመጀመሪያው እና ወደፍተሻችን ከመዝለቃችን አስቀድሞ ሊሰመርበት የሚገባው ነው፡፡

ስለሆነም ይህንን የመሰለ እድገት ያመጣው ድርጅት ተወደደም ተጠላ ከአንድ ምዕራፍ ወደሌላ ምዕራፍ በተሸጋገረ ቁጥር ከባድ ፈተናዎች ገጥመውት የነበረ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በእርግጥ ከላይ የተመለከቱት እና እንደማጠየቂያ የተወሰዱት ትችቶችም ስህተትን የተመለከተ ሳይሆን ልዩነታቸው ከስህተት መማርን የተመለከተ ቢሆንም ስለሚዛናችን ከስህተቱ መነሳት ተገቢ ነው። ይህም ሆኖ ደግሞ ሁሉም እንኳ ባይሆን የአንዳንዶቹ ፈተናዎች ምንጭ ከውጭ መሆኑንም መካድ ተገቢ ስለማይሆን አስረጅ በመጥቀስ እውነታውን ማረጋገጥ ካለንበት ውዥንብር ለመውጣት ጠቃሚ ነው፡፡

ስለሆነም ድርጅቱ እነዚህን ከመሳሰሉ ፈተናዎች ውጭ ኖሮ የማያውቅ ድርጅት ስለመሆኑና ህልውናው  ባለመፈተን ሳይሆን በመፈተንና ፈተናዎችን በፅናትና በብስለት በመፍታትና በማለፍ ላይ የተመሰረተ ድርጅት የነበረ መሆኑን ዛሬም ከዚህ የተለየ ህልውና የሌለውና ሊኖረው የማይችል ድርጅት  መሆኑን ይዘን ከላይ የተመለከቱ ትችቶችን እንመዝን፡፡

ከመጣው የኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ እና በዚህም ሃገሪቱ  በተማረ የሰው ሃይልና ጠያቂ ትውልድ መጥለቅለቋ ከውስጥ ፈተናውን ያጠናከረበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤  ከዚሁ እድገት ላይ መቀራመት የሚሻው የኒዮ ሊበራሊዝም ጥቃት ሳያሰልስ እየተካሄደበት ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ከውስጥና ከውጭ ቅጥረኛ ሃይሎች ኪሳቸውን ያሳበጡ ፅንፈኛ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክራሪዎች ሁሉ በጉዞው ላይ መሰናክል መሆናቸውንም የኒዮ ሊበራሉን ሚዲያና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡  ከሁሉ በላይ ደግሞ ጥገኛ ዝቅጠት በድርጅቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ ፈተናውን ያበዛበት መሆኑንም ማንም ሳይገርፈው እራሱ እየተናገረ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የገጠመው ፈተና በአንድ ወቅት የድርጅቱን መሰነጣጠቅና መፈረካከስ የቅርብ አደጋ እስከማድረስ ደርሶ በነበረው ደረጃ መሆኑንም ጭምር በመግለጽ ነው፡፡

ታዲያ በዚህ ደረጃ ችግሮቹን የሚገልጽ ድርጅት በምን አግባብ ችግሮቹን ሁሉ ወደውጭ ይገፋል ተብሎ ይተቻል?። 

ይህም ሆኖ የፈተናዎቹ ብዛትና መልክ የተለያየ ቢሆንም የድርጅቱን ህልውና ለማጥፋት የተቻላቸው አልነበሩም፡፡ አሁንም እየሆነ ያለው ይህ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ በአጋጣሚ ሳይሆን ችግሬ ነው ብሎ የተቀበለውን ስህተት ከመላው ልማትና ሰላም ወዳድ ህብረተሰብ ጋራ ሆኖ በማረም፤ ይልቁንም እያንዳንዱን ፈተና ከተቻለ አስቀድሞ በመዘጋጀት፣ ካልሆነ ደግሞ ከመጣ በኋላ በብቃት ተዘጋጅቶ በመግጠም ለመቋቋም የሚችል ብቃት በመገንባቱ ነውና ሰሞንኛዎቹን ግርግሮች ለማባባስ የሚሰጡት ከላይ የተመለከቱ እና መሰል አስተያየቶችን ማስላት የሚገባው ከዚሁ ብስለትና ብቃት አኳያ ነው፡፡

 

ድርጅቱ ለረጅም ጊዜ ካካሄደው ትግልና ካካበተው ልምድ በመነሳት ብዙዎቹን ችግሮች አስቀድሞ እየገመተ በመዘጋጀት የሚያመክንበት ወቅት ትንሽ ያልነበረ መሆኑንም “ከስህተቱ የማይማር” ሲሉ የሚያብጠለጥሉቱ ሁሉ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ምን ይህ ብቻ ድርጅቱ ይህ ችሎታ በአንድ በኩል የፖለቲካ ብስለትን፣ በሌላ በኩል የነገሮችን አዝማሚያ ከማንኛውም ዓይነት ስሜታዊነት በፀዳ አኳኋንና ከህዝብ መብትና ጥቅም በመነሳት ብቻ በመገምገም፣ የተገነባ ብቃት መሆኑንም ጭምር ፖለቲከኛ ነን የሚሉቱ ቀርቶ የትኛውም ተርታ ህብረተሰብ ያውቀዋል፡፡

 

በ97 የተደረገውን አራተኛው ዙር ሃገራዊ ምርጫ ተከትሎ ሃገሪቷ ገጥሟት ከነበረው የቀለም አብዮት አደጋ መትረፍ የቻለችው ድርጅቱ ጉዳዩን በጥልቀት በመገምገምና ብቁ ስትራቴጂና ታክቲኮች ነድፎ በፅናት ተግባራዊ በማድረግ  ትግሉን በሚያጎለብት ደረጃ በመፍታቱ መሆኑንም ሰሞንኛዎቹን ግርግሮች ለማባባስ የሚሹ ሃይሎች በሙሉ ይቅርና መላው ህብረተሰብ ያውቀዋልና ትችቶቹን መመዘንና ስለሃገራችን ሰላም ማጠየቅ የሚገባን ከነዚሁ ጥሬ ሃቆች በመነሳት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ብዙዎች እጃቸውን በሰጡበት ዓለም ባለመንበርከክና በፅናት ተፋልሞ ግቡን የማሳካት ባህልና ልምድ ያለው ድርጅት ከላይ በተመለከቱት አራጋቢ እይታዎች ያበቃለታል ብሎ ማሰብ ተራ ክጀላ ነው፡፡

በአገራችን  የአፈና እና የግጭት ምዕራፍ ተዘግቶ ቀጣይ እድገት የተረጋገጠበት ሂደት ለሩብ ምዕተ ዓመት ያህል የዘለቀው በእርግጥም መንግስትና መሪ ድርጅቱ በብስለት፣ በፅናትና በፍፀም ህዝባዊ ወገንተኝነት አቋም ችግሮችን የመፍታት ብቃት ስለነበራቸው እና ስላላቸው እንጂ ህዝብን ስለማያደምጡ መቼም ሊሆን አይቻልም፡፡ ይህን ብቃት በማንኛውም ምክንያት አሳንሶ መመልከት እብደት ወይም ቅናት የሚበዛውና ከተላላኪነት ጉርሻ የሚመነጭ ነው፡፡ በወቅታዊነት የተጋረጡ ችግሮች በበዙበትም ሁኔታ ቢሆን ድርጅቱ ለድርድር የማያቀርባቸው ህዝባዊና አገራዊ ጥቅሞችን በሚገባ አስረግጧልና  ሰላም ወዳዱ ህዝብ ትችቶችን እና ማናቸውም ሰበካዎችን መመዘን ያለበት ከነዚሁ አቅጣጫዎች አኳያ ብቻ ነው፡፡

 

ስለሃገራችን ሰላምና እድገት ቀጣዩ ትግልም በእነዚህ ላይ ተመስርቶ የሚዳብር መሆኑ ፈፅሞ ሳይዘነጋ እነዚህን ድሎችና የድል መንስኤዎች በመጠበቅና በማስቀጠል ራዕያችንን ለማሳካት ሚዛናችን ከላይ በተመለከተው አግባብ ሊቃኝ ከተገባው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ይህም ሲሆን ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ድርጅቱ በቅጡ ባልፈፀማቸው ተግባራት፣ ወይም ደግሞ በፈፀማቸው ስህተቶች ምክንያት የተፈጠሩትን ጎጅ አዝማሚያዎች በመገንዘብና በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሶ ለማስወገድ መዘጋጀቱ ይፋ ሆኗልና ስለሚዛናችን ይህንንም ማስታወስ ይገባል፡፡