…ቅዝምዝም ወዲያ !!

በህዝቡ ውስጥ የተነሱትን የመብትና የፍትህ ይከበር፣ ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች አስመርረውናል፣ መሬታችንን ተቀራምተዋል ወዘተ…ህዝብ በራሱ ጊዜ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመጥለፍና የራሳቸው ለማድረግ የሚቅለበለቡ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ነን የሚሉ ግለሰቦች በእኔ ነኝ እኔ ነኝ የመራሁት ያስነሳሁት የሚል ተልካሻና አይረቤ ቅርምት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ እነሱ አልመሩትም፡፡ የሉበትም፡፡ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ይሏል ይኼ ነው፡፡

በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በአብዛኛው የራሳቸው ውስጥ ችግር መሠረቱ ያልፀና ድርጅት፣ ፓርቲ፣ ፎረም፣ የጋራ መድረክ፣ ህብረት እያሉ ሲሰባሰቡ ትንሽ ቆይተው ሲጣሉ ሲዘናጠሉ እንደገናም አሥርና ሀያ ቦታ ተበጣጥሰው የድሮው ይቅርና ዛሬም ከ50 ዓመታት በኋላ በዚያው መንገድ እየነጎዱ ያሉ ናቸው፡፡ ተቻችሎ ተደማምጦ ለሀገር መሥራት ለህዝብ መቆም ስለሚመጣውና ስለሚሄደው መንግሥት ሳይሆን ቋሚና ዘላለማዊ ስለሆነችው ሀገር ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ማሰብ ብሎ ነገር የለም፡፡ ይኼ ትልቁና መሠረታዊው ችግራቸው ነው፡፡

አድሮ ቃሪያ አድሮ ጥጃ ማለት ናቸው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ የታፈረች የተከበረች ሀገር መኖር መቀጠል አለባት፡፡ ሀገርን ለማፍረስ ዝንተ ዓለም ጉድጓድ ከሚቆፍሩ ጠላቶቿ ጋር ተሰልፎ በገንዘብና በመሣሪያ እየተረዳ ያለ ተቃዋሚ ሀገሬ ወገኔ ቢል ሰሚም አድማጭም የለውም፡፡ ለኢትዮጵያ ሻዕቢያ ግብጽ መቼም ሆነ መቼም አሳቢም ተቆርቋሪም ሆነው አያውቁም፡፡ ሊሆኑም አይችሉም፡፡

አብዛኛው ተቃዋሚ እርስ በእርሱ ከመወነጃጀል፣ ስም ከመጠፋፋት፣ ከመሰዳደብ፣ ከዘለፋ፣ ከመናቆር እኔ ብቻ ነኝ ትክክል እኔን የነቀፈ የተቃወመ የተለየ ሃሳብ ያቀረበ የህዝብ ጠላት የሀገር ጠላት ነው ብሎ የሚያሳብ ከዚህ የዘለለ ታሪክ የሌለው በከፋ የአስተሳሰብ ድህነት ውስጥ ተዘፍቆ የሚንከላወስ መሆኑን ህዝብ አይቶ አይቶ ታዝቦ ታዝቦ ልጆቹን በመማገድ ያስከፈሉትንም ዋጋ በመራርነት እያስታወሰ በቃችሁን ማለቱ እውነት ነው፡፡ ዛሬም የረባ ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ራዕይ ያለው እከሌ የሚባል ተቃዋሚ ድርጅት አለ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ላይ አይደለም ያለነው፡፡ ለዚህ ነው ኢህአዴግ መንግሥታዊ አደረጃጀትና ቅርጹን ሙሉ በሙሉ ለውጦ በውስጡ ያለውን ሥር የሰደደና የከፋ ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎችን የመልካም አስተዳደር ጠንቅ የሆኑትን እንዲያም ሲል ጎጠኛና ጠባቦችን የትምክህት ኃይሎችንም አራግፎ የህዝብን ጥያቄ በመመለስ ሀገሪቷንም ላሰፈሰፈው የውጭ ኃይል አሳልፎ ላለመስጠት መቀጠል ያለበት፡፡

አሜሪካ ሆኖ በፌስ ቡክ በሚታወጅ ጦርነት ህዝብን ከህዝብ ወገንን ከወገን ለማናከስ ለማፋጀት ሀገሪቷ የጦርነት ማሣ እንድትሆን የተገነባውም እንዲፈርስ የተጀመረውም የሀገር ልማትና ግንባታ የተሰራውም ወድሞ ሁሉም ነገር ጠፍቶ ባዶ መሬት እንዲሆን የሚሰብኩ የሚቀሰቅሱ ሁሉ በሥራቸው ሊያፍሩ ይገባቸዋል፡፡ ለሀገራቸው መውደምና መጥፋት በግብጽና በኤርትራ ተላላኪነት የተሰለፉ እኩይ አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው፡፡

በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የተነሳው የህዝብ አመጽና ቁጣ የተከተለው አላስፈላጊ ግጭት በሰው ህይወትም ሆነ በንብረት የደረሰው ጥፋት እንደ ሀገር እንደ ዜጋ በእጅጉ የሚያሳዝን እንጂ እንደ ሀገሪቷ ጠላቶች ጮቤ የሚያስረግጥ አይደለም፡፡ ቢገባቸው እውነተኛ ሀገርና ወገን አፍቃሪዎች ቢሆኑ ኖሮ ሁሉም ነገር በሠላምና በውይይት በድርድር በንግግር እንዲፈታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ቢያደርጉ ኖሮ ጥፋት አይከሰትም ነበር፡፡

ዛሬ ሻዕቢያና ግብጽ ሌሎችም የተፈጠረው ቀውስ ቀጣይነት ኖሮት ኢትዮጵያ ትርምስምሷ ይወጣል ትበታተናለች ህዝቡም እርስ በእርሱ ይጋጫል በዚህም መሠረት የተገነቡት ታላላቅ ሀገራዊ የልማት ሥራዎች በነውጠኞች እንዲፈርሱ ይደረጋል፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይም ያበቃለታል ብለው አምነዋል። አለማወቃቸው ነው፡፡

ሰሞኑን በተነሳው ሁከትና ትርምስ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚያስፈልጉ የግንባታ ግብዓቶች ከአዲስ አበባ  ወደ ሥፍራው የሚሄዱበት መንገድ ተዘግቷል አበቃለት እያሉ የግብጽና የኤርትራ መሪዎችና የደህንነት ሹሞች ሥራችንን ሰርተናል ተሳክቶልናል እያሉ በደስታ ተውጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወስጥ ሁከትና ብጥብጥ ትርምስ አለመረጋጋት እንዲሰፍን ቀደም ካሉ ዓመታቶች ጀምሮ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አፍሰዋል፡፡ ዛሬም በተጠናከረ ሁኔታ ከገንዘቡ ሌላም የጉዳዩ ባለቤት ሆነው የሚሰሩ ሀገሪቱን ለማተራመስ አመራር የሚሰጡ የደህንነትና ወታደራዊ ባለሙያዎች መድበው ጊዜው አሁን ነው በሚል ያለ የሌለ አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀም ለሊት ከቀን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በቅርብ ለመከታታል እንዲረዳቸውም የተሰባሰቡት ኤርትር ውስጥ መሆኑም ይታወቃል፡፡

በፍጹም ጥላቻ የታወረው ጽንፈኛው ተቃዋሚ ኃይልም ኢህአዴግን ከፖለቲካ ሥልጣን ለማውረድ ከሰይጣንም ሆነ ከአልሸባብ ጋር ያው አይሲስም ማለት ነው ተባብሬ እሰራለሁ ብሎ በአደባባይ የተናገረውም ተጠቃሽ ነው፡፡ ይሁን ኢህአዴግ ዘላለማዊ አይደለም ሥልጣን ይልቀቅ እንበል በፊትም ሆነ በኋላ ኢትዮጵያ ሀገራቸው ህዝቧም ህዝባቸው መሆኑን እንዴት ይዘነጉታል? ውድመቷንና ጥፋቷን ለምን ፈለጉት? ይኼስ የቅን ዜጋ መገለጫ ነው? ወይንስ ቻይኖቹ በቀለበት መንገድ ላይ የተሰራውን ብረት ሰዎች እየቆረጡ ሲወስዱ ተመልክተው በመገረም እንዴ  እነዚህ ሰዎች ሌላ ሀገር አላቸው እንዴ ብለው አሉ እንደተባለው ጽንፈኛውና አክራሪው ፖለቲከኛ አሜሪካ ኤርትራ ግብጽ እየተመላለሰ ሀገሪቷን ለማውደም የህዝቡን መተላለቅ በማወጅ የሚሰራው ሌላ ኢትዮጵያ ሌላ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚባል አላቸው ማለት ነው? ብሎ ለማለትም ያስደፍራል፡፡

የዘር ጥላቻን በሚዲያ መስበክስ ከጥንት ጀምሮ ከስንት ሺህ ዘመናት በፊት በአብሮነት ተጋብቶ ተዋልዶ ክፉና ደጉን አብሮ አሳልፎ በጋራ የመጣበትን ጠላት እንደ አንድ ሰው ሆኖ መክቶ ድልም አድርጎ በፍቅር በህብረት በመቻቻል በመደማመጥ ተከባብሮ የኖረን ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲፋጅ እንዲተላለቅ ይፋ መልዕክት ማስተላለፍስ አሁን ይኼ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ይበጃል? ይጠቅማል? ጭርሱንም አይጠቅምም፡፡ ለሀገሪቷም ለህዝቧም መቼም ሆነ መቼም መልካም ነገር አያመጣም፡፡

ከየትኛውም ብሄር ብሄረሰብ ውስጥ ግለሰቦች ቡድኖች ሊሳሰቱ ይችላሉ፡፡ ህዝብ ግን አይሳሳትም፡፡ ከየትኛውም ብሄር ብሄረሰብ ውስጥ በሥልጣን የባለጉ የዘረፉ የከበሩ የተሰጣቸውን የህዝብና የመንግሥት ኃላፊነት ተጠቅመው የህዝብንና የመንግሥትን ሀብት ንብረት እንደ ግል ይዞታቸው ቆጥረው ጠያቂ የለብንም ሥልጣኑም ወንበሩም በእጃችን ነው ብለው ዘረፋን እንደ ልዩ መብት ቆጥረው የኖሩ ሆኖም ግን ከህግ ተጠያቂነት መቼም ሆነ መቼ ሊደበቁ ሊሸሸጉ የማይችሉ ይኖራሉ፡፡

ህዝብን ግን በጅምላ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም፡፡ በዓለም ላይም ታይቶ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ሰይጣናዊ አስተሳሰብና አመለካከት መውጣት ስለሀገርም ስለህዝብም አብሮነትና ቀጣይነት ሰክኖ ማሰብ የዜጎች ሁሉ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

በሀገራችን የተፈጠረውን በህዝቡ በኩል የታየውን የተቃውሞና የአመጽ እንቅስቃሴ በተለይም ከመልካም አስተዳደርና ከፍትህ እጦት ከኪራይ ሰብሳቢው ከጥገኛውና ከደላላው ጋር በተቀነባበረ መልኩ በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ያሉት ሌቦች በውጭ ካሉት ሌቦች እጅና ጓንት ሆነው በመመሳጠርና በመተባበር በህዝብ ላይ የፈጠሩት በደል ግፍና መመረር ያመጣው ችግር ነው፡፡

ኢህአዴግ በድርጅታዊ ጉባዔው መርምሮ ከፍተኛ የሞት ሽረት ትግል ለማድረግ የወሰነበት ቢሆንም ታላቁ መሪ መለስ አንድ እጃችንን ተይዘን በአንድ እጃችን ነው የምንሰራው እንዳሉት ድርጅቱ ምን ያህል በኪራይ ሰብሳቢዎችና በጥገኛ ኃይሎች ተተብትቦ በውስጡ ያለው የለውጥ ኃይል ታፍኖ እንዳይንቀሳቀስ ተደርጎ ተይዞ በመቆየቱ የተከሰተ ችግር ነው፡፡

ህዝብ ላቀረበው የመልካም አስተዳደር የፍትህ እጦት ወዘተ…ጥያቄዎች ፈጥኖ ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት ባለመቻሉ ነው በተለያዩ ክልሎች የህዝብ ተቃውሞና አመጽ የተነሳው፡፡ ዛሬ ተቃዋሚው እኔ ነኝ የለም እኔ ነኝ የመራሁት እያለ መባላት እንደጀመረው አሳፋሪ ሥራ ሳይሆን ህዝቡ ራሱ ያለመሪ ተቃዋሚ ድርጅት የመራው እንቅስቃሴ ነው፡፡

በኦሮሚያውና በአማራ ክልሎች የተነሳው ጥያቄ በወቅቱ ለህዝቡ ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ ባለመሰጠቱ የተቀሰቀሰ የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን ህዝቡ ራሱ ተናግሮታል፡፡ ህጉን ተመርኩዘን ላቀረብነው ጥያቄያችን በአግባቡ መልስ ይሰጠን ነው ያልነው ብሏል፡፡ ሁኔታው እያደር የህዝብን ቁጣና ተቃውሞ ወለደ፡፡ ይህን ተከትሎም የሰው ህይወት መጥፋት ከፍተኛ የንብረት ውድመት የእለት ተእለት ህይወትና ሥራ መስተጓጎል ተከሰተ፡፡ ጥያቄው የህዝብና የህዝብ ብቻ ነው፡፡

ለዚህ ነው በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አልተመራም፤ ባለቤትም አይደሉም፡፡ ይኼንን ያስነሳሁት እኔ ነኝ…እኔ ነኝ ለማለትም የሞራል ድፍረት የላቸውም፡፡ የስመ ብዙው ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መንጫጫትም ሆነ የእርስ በእርስ ሽኩቻ ጉንጭ አልፋና ቦታ የለውም የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ አንድም ምንም መሠረት የለውም፡፡

በሀገር ውስጥ ያሉትም ወንበር ከማሞቅ ዓመታት ጠብቀው በምርጫ ወቅት ከሚሰፈርላቸው ገንዘብ ባለፈ መንግሥት ስህተት ሲሰራ ለማረም ጉድፎችን ነቅሶ በማውጣት እንዲስተካከሉ የህዝቡን ጥያቄ ለማቅረብ ያልቻሉ ሠላማዊ አስተዋጽኦና መፍትሄ ለማምጣት ያልቻሉ ናቸው፡፡

የሚሰጣቸው ገንዘብ የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ መሆኑን በዕዳ የሚጠየቁበት ዛሬ ላይ ግን በህዝብ ስም ገንዘብ አራት መቶና አምስት መቶ ሺህ እየወሰዱ የሚነግዱበት የሚከፋፈሉበት እስከ መጪው ምርጫ ድረስ የዓመታት ቀለብ የሚገዙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ከዚህ የበለጠ አሳፋሪ ነገር የለም፡፡ ሀገር እንዲህ ሲናጥ ማረጋጋት ሠላማዊ መፍትሄ ማፍለቅ ካልቻሉ ሀሳብ የላቸውም ማለት ነው፡፡

ወንበር ከማድመቅ በተሰጣቸው ገንዘብ ከረባትና እንስት ከመለዋወጥ ውጭ ለሀገርም ለህዝብም ለመንግሥትም አንድም ምንም የማይፈይዱ የተሻለ ሀሳብም የሌላቸው የሀገር ሸክሞች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ ይኼንንም አንዱ ደካማ ጎኑ አድርጎ ሊያርመው ይገባል፡፡ አሁን አነጋግራለሁ የሚለው እነሱን ከሆነ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ሌሎቹን ቢያነጋግር ይቀለዋል፡፡

ይልቁንም ህዝቡ ራሱ ተቃዋሚ ነን ከሚሉት ፖለቲካ ድርጅቶች ብዙ እጥፍ ቀድሞ መራመዱን ያሳየበት ያስመሰከረበት ተጨባጭ ሁኔታ ነው የታየው፡፡ ኢህአዴግም እንዳለው ህዝቡ መብቱን ለማስከበር ያደረገውን ትግል በአክብሮት እናየዋለን እናደንቃለን ያለውም ለዚህ ነው፡፡

ህዝቡ ግንቦት ሰባትንም ሊሎቹንም በውጭ ያሉትን በጓዳችን አትግቡብን ይኼ የእኛ ጉዳይና በእኛ የሚመራ እንጂ ከእናንተ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም ብሎ እስከመናገር ደርሷል፡፡ በቅርቡ ነባር ታጋይ አቶ በረከት ስምኦን እንዳሉት ጥያቄውን ፈጥኖ ምላሽ መስጠት ማስተካከል ውስጡን ፈትሾ ማጥራት በውስጡ የተሰበሰበውንና በኢህአዴግና በድርጅቶች ስምና ካባ ተጠልሎ ተጠቅልሎ ሲዘርፍ ህዝብን ሲያስመርር የኖረውን ጥገኛና ፓራሳይት በሁሉም ድርጅቶች ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ያለልዩነት መረቡን በመበጣጠስ ትክክለኛ የህዝቡን ጥያቄ የሚመልሱ አሠራሮችን በመትከል የመንግሥትና የፓርቲ አሠራሮችን ለየብቻ በመነጠል ታላቅ ሀገራዊ እዳሴና የመስፈንጠር ጉዞ ከመስከረም ወር አንስቶ ይጀመራል። ይኼንን ሆኖ ለማየት ህዝቡ በታላቅ ጉጉት ይጠብቃል፡፡ ለዚህ ነው በውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ተቃዋሚ ኃይል በሌለበት ባልመራው እንቅስቃሴ እኔ ነኝ ማለቱ አሳፋሪ የሚሆነው፡፡ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ማለት ይኼ ነው፡፡