ዝምታው ይሰበር !!

ባለቤት ያልነበራቸው፣ በዋናነት ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች አስተባባሪነት እና ከሀገር ውጪ በሚገኙ ጽንፈኛ አካላት ድብቅ ሚና የተመሩ፤ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ያልተፈቀዱ ሠልፎች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡ ሠልፎቹ ጥቂት የማይባል የማህበረሰብ ክፍል የተሳተፈባቸው፣ በረብሻና በሁከት የተሞሉ መሆናቸውም በተመሳሳይ ይታወቃል፡፡ የመልካም አስተዳደር ቅሬታን በምክንያትነት ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታ ያለ ቢሆንም፣ በሰልፎቹ የተስተናገዱት ሃሳቦችና መፈክሮች በሙሉ የጽንፈኛ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ሴራ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
ባጠቃላይ በሰልፎቹ ላይ የተላለፉት መልዕክቶች በሙሉ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚኮንኑ፣ የፌዴራል ስርዓቱን ለመቀልበስ የሚያነጣጥሩ የነበሩ ስለመሆናቸው በብዙ አስረጂዎች ተደግፈው በአደባባይ ታይተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለሃገር ጠንቅና አደጋ ነው። አደጋ መሆኑም በሚገባ በሚያጠይቁ ጥፋቶች ተገልጧል። ይህ ትርክትም እነዚህን አስረጂዎች እያነሳ ስለሃገር ሰላም በሚጠበቅብን ጉዳዮች ላይ በየአካባቢው ልንወያይበት የሚያስችል መነሻ ሃሳብ የሚሰጥ ነው።
ማህበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ በውጭ የሚገኙ ጽንፈኛ ሚዲያዎች በሙሉ ለሃገር የተቆረቆሩ በሚመስሉ አጀንዳዎች ቢሸፈኑም ባህሪያቸው በተግባር ሲፈተሽ ግን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል የማፍረስ ተልዕኮ እንደነበራቸው መታየቱ የመጀመሪያውና በሃገር ጥፋት ላይ ያነጣጠረ የመሆኑ አስረጅ ነው፡፡ የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት የሚጎዱት ተግባራቶች ደግሞ የበዙና የሚሰቀጥጡ መሆናቸው በተግባር  ታይተዋል፡፡ ይህም ሰቅጣጭ የነበረ ሰበካ በዜጎች ንብረትና ህይወት ላይ ግልጽ ጥቃት  በማድረስ ተገልጧል፡፡ አንዱን ህዝብ በሌላው ላይ በማነሳሳት ስራ የተካሄደባቸውም ናቸው፡፡ ስለሆነም ነው ይህን አጀንዳ በማንሳት መንግስት የህዝቡንና የሀገሩን የሠላምና የደኅንነት ዋስትና ለማረጋገጥ አስፈላጊ እና የዜግነት የሆኑ ግዴታዎቻቸውን ሊወጡ ይገባል የምንለው ፡፡ 
ምንም እንኳን አሁን በመንግስትና በህዝብ ሰላማዊ እና ህጋዊ የትግል እንቅስቃሴዎች የሁከት አዝማሚያዎች በሁሉም አካባቢዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም፤ ዜጎች በየቤታቸው እስረኛ ሆነው አዲሱን አመት በጨለማ እንዲባርኩ የሚያደርግ መልእክቶች እየተላለፉ  የመሆናቸውን ጀርባ ማጤንም ተገቢ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ በአስተማማኝ መልኩ መቀየርና እንዳይሰፋ በማድረግ ሃገርን ከጥፋት መጠበቅ ይገባል፡፡ 
በእርግጥ ለዓመታት ምላሽ ያላገኙ የሕዝብ ጥያቄዎች በሚፈለገው መንገድ ባለመስተናገዳቸውና ለመፍትሔ የሚረዱ ውሳኔዎች መዘግየታቸውን ተከትሎ አደባባይ ሊያወጣ በሚችል ደረጃ ህዝቡ መማረሩ የማይተባበልና መንግስትም ያመነው ሃቅ ነው። ስለሆነም ነው ህዝቡ ምሬቱን የሚገልጽባቸው አሰራሮችና ህጋዊ አግባቦች እያሉ አገሪቱን አደጋ ውስጥ በሚከት መንገድ መንቀሳቀሳቸውን ማውገዝና መታገል ይገባል የምንለው።     ዜጎችን ለሞት፣ አገሪቱንም ለውድመት የሚዳርጉ ችግሮች ሲፈጠሩ ዝም ማለትም ሆነ በአያገባኝም ስሜት ችላ ማለት የበለጠ ጉዳት የሚያመጣና የሃገር ውለታን እንክት አድርጎ መብላት ነው፡፡  
አገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግሥት ለመታደስ ዝግጁ በሆነበትና ዝግጁነቱንም የሚያረጋግጡ ጅምር እርምጃዎች እየወሰደ በሚገኝበት ሰአት ላይ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩል ተጠቃሚነትና ለአገር ህልውና የማይጠቅሙ ነገሮችን እንዳላዩ ማለፍ ሊመደብ የሚችለው ከብሄራዊ ወንጀል ብቻ ነው።   
መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በምንም መልክ ለድርድር ማቅረብ አይገባም፡፡ የዜጎችንም ደኅንነት መጠበቅ ግዴታው መሆኑን በጽንፈኞች ሰበካ መርሳትና መዘንጋት ሃገርን ወደጥፋት ከሚመሩ ሃይሎች የማይለይ ወንጀል ነው፡፡ ይህ ማለት ግን መንግስት የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ አስተናግዶ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነቱንም ሲዘነጋ ዝም ማለት ይገባል ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ሕግ የማስከበር ተግባሩን ተቃውሞን በማዳፈን በዜጎች ሕይወትና አካል ላይ አደጋ በመፍጠር እንዳይገለጽ በአግባቡ እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱ በሚፈቅደው አግባብ አለመሞገትም በተመሳሳይ ብሄራዊ ወንጀልና ደባ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ 
በመንግስትም ሆነ በኛ የሚጠበቁትን ከላይ የተመለከቱ ሃላፊነቶችን እና ግዴታዎችን ባለመወጣታችን ያተረፍነው ነገር ቢኖር የውጭ ኃይሎችም ሆኑ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጥያቄዎቻችንን ነጥቀው እጃቸውን ከመንግሥት በላይ እንዲረዝም ማድረጋችን  እና ከገዛ ጥቅሞቻችን ጋር ተጻራሪ እንድንሆን መፍቀዳችን ብቻ ነው።
ከእንዲህ አይነቶቹ ህገ ወጥ አካሄዶች መራቅና ሰለባ ያለመሆን ሃገርን ከጥፋት የመታደግ የመጀመሪያው እርምጃ ከመሆኑም በላይ መንግሥት ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ዕርምጃዎች ራሱን እንዲሰጥ ያስችላል፡፡
ሕዝብና መንግሥት ለመነጋገርና ለመደማመጥ የሚረዱዋቸው በነፃነት የሚደረጉ ውይይቶች ብቻ ስለመሆናቸው መንግስት አምኖ መቀበሉም ከተጠቀምንበት ሃገርን ከጥፋት እኛንም ከምሬት የሚገላግለን ነው፡፡ መንግስት ሕዝብ በትክክል ምን እንደሚፈልግ  ማወቅ   የምችለው በነፃነት በሚደረጉ ውይይቶች ብቻ ነው ሲል ለመፍትሔ የሚረዱ ግብዓቶችም በስፋት የሚገኙት ከህዝብ ነው ማለት መሆኑንም ማጤን እና አለመዘንጋት ተገቢና ሃገርን ከጥፋት የመታደጊያው አንዱና ሁነኛው መንገድ ነው፡፡  
ሃገሪቱ በፅኑ መሠረት ላይ በመገንባቷ የመፈራረስና የመበታተን ሥጋት እንኳ ባይኖር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ብሔርንና ማንነትን የተንተራሱ ቅስቀሳዎችና የመሠረተ ልማት ውድመቶች መጪውን ጊዜ የሚያጨልሙ እና ወደኋላ የሚመልሱ መሆናቸውን ግን መንግስትም ሆነ ህዝብ መጠራጠር አይገባቸውም፡፡ የተነሱት የሕዝብ ጥያቄዎች በውጭ የሚገኙ ጽንፈኞች ተጠልፈው አቅጣጫቸውን እየሳቱ ለዜጎች ሕልፈተ ሕይወት፣ አካል ጉዳትና ንብረት ውድመት መባባስ ምክንያት ስለመሆናቸው በሚገባ አይተናልና በዝምታ ካለፍናቸው ውጤታቸው ሃገር ማፍረስ እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡  
በውጭ የሚገኙ ሃይሎችን ጨምሮ በሃገር ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከመንግሥት ጋር ጉዳይ አለን የሚሉ ማናቸውም ግለሰቦችና ተቋማት በእርግጥም እንደሚያወሩት ጉዳያቸው ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና ስለሃገር ልማት ከሆነ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ለማኅበራዊ ፍትሕ ትግል የሚደረገው አገር በማውደም እንዳይደለ ተገንዝበው ጫወታውን ማከናወን እንጂ የሚሉትን ሽፋን አድርገው ሊያፈርሱን እስከተንቀሳቀሱ ድረስ ዝም ልንላቸው የማይገባ መሆኑን ሰሞንኛ ከነበሩት ሁከቶች በላይ አስረጅ አይገኝም፡፡ ሕዝብን የሚያሸብሩ ሥጋቶች በመፍጠር ስልጣን ላይ የሚመጣ አካል መልሶ በማሸበር ሊገዛ የቋመጠ መሆኑንም መዘንጋት ተገቢ  አይደለም፡፡ 
በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ዴሞክራሲንና ሰብዓዊነትን የሚንዱ ቅስቀሳዎችን የማካሄድ ውጤቱን አይተናልና ዝምታው መሰበር ካለበት ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው፡፡ የግለሰቦችንና የቡድኖችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመዳፈር የሚካሄዱ ቅስቀሳዎች ፈራቸውን የለቀቁ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ሆነ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ኅብረተሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ትጋት የሚያደናቅፍ ነው፡፡ 
በተለያዩ ሥፍራዎች ከሰው ሕይወት በተጨማሪ፣ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰው ያ በመሰረቱ የቅስቀሳው ጡዘት እየፈጠረው ባለው ግለት መሆኑን መመስከር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ አገሪቱን ወደ ባሰ ድህነት አዘቅት የሚከቱና የሕዝቡን ተስፋ የሚቀለብሱ ውድመቶችን መስበክ እንኳንስ በተቃውሞ ጽንሰ ሃሳብ ሊሰላ  ጤነኛና የጤነኞች አስተሳሰብ  መሆኑንም ለመቀበል ይከብዳል፡፡
ሕዝብ ለሚያነሳቸው ማናቸውም ጥያቄዎች የመደመጥ መብት እንዳለው፤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንደሚያስፈልገው፤ በዚህም ሰብዓዊ መብቱ ሊከበር የሚገባው መሆኑ፤ በፍትሕ መዳኘት እንደሚገባውና የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሊኖረው የሚገባ መሆኑ ለድርድር መቅረብ በሌለበት አግባብ ህገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቷል፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታና መንግስትም እንዳመነው ጸረ ዴሞክራሲያዊና ስልጣንን ለሃብት ማካማቻ የሚሹ ሃይሎች በስርአቱ ውስጥ መበራከታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሃገሪቱን ለመገንባት የሚያስፈልገው በጥላቻና በክፉ መንፈስ በታጠረ የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ሳይሆን፣ ለዴሞክራሲና ለነፃነት በሚታገል ብሩህ እና ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ብቻ መሆኑንም ማስመር የሚገባን ከሆነ ትክክለኛው ወቅት አሁን ነው፡፡ የሕዝብን መሠረታዊ የመብት ጥያቄዎችን ማፈንም ሆነ፣ በጥያቄዎቹ ተከልሎ አገርን ማተራመስ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም የሚለውን እና ቁርጠኝነት የተያዘበትን የመንግስት ጥሪ ተቀብለን ዝምታውን የመስበር ብሄራዊ ሃላፊነታችንን እና ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡