መሬት በህገ መንግስቱ ምላሽ ያገኘ እንጂ፣ የሁከት ምክንያት ሊሆን አይችልም!

አንዳንድ ወገኖችና ተቃዋሚዎች በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ቀውስ ከመሬት ስሪቱ ጋር ሊያያይዙት ሲሞክሩ ይስተዋላል። ምናልባትም ከማስተር ፕላኑ ጋር ተያይዞ የመሬት ጉዳይ የችግሩ መነሻ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ይሁንና በእኔ እምነት መንግስት የሚከተለው የመሬት ስሪት ፖሊሲ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ለተከሰተው ሁከት ዋነኛ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም በሀገራችን ውስጥ ያለው የመሬት ፖሊሲ በህገ መንገስቱ መሰረት ምላሽ ያገኘ በመሆኑ ነው። እናም በዚህ ፅሑፍ ላይ ከተቃዋሚዎች በኩል ጉዳዩን አስ መልክቶ የሚነሱ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ለማረቅ እሞክራለሁ።

እንደሚታወቀው በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ መሬት የህዝብና የመንግስት መሆኑ በሚገባ ተደንግጓል። ላለፉት 21 ዓመታትም ይህ ድንጋጌ ገቢራዊ ሆኖ ሀገራችን ባላት የመሬት ሀብት ተጠቅማ ልማቷን ማፈጠን ችላለች። ተቃዋሚዎች ግን ይህ አይዋጥላቸውም። በኦሮሚያ የተከሰተው ችግር ከመሬት ጋር የተያያዘ ስለሆነ መሬት መሸጥና መለወጥ አለበት ይላሉ። ይህ ፍፁም የተሳሳተ እሳቤ ነው።

እርግጥ መሬት እንዲሸጥ እና እንዲለወጥ ቢደረግ እንኳን በኪራይ ሰብሳቢዎች ከሚደርሰው ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ዝቅጠት ባሻገር፤ ሀገራችን እያስመዘገበችው ባለው ዕድገት ላይ ምን ያክል ተጽዕኖ እንደሚያመጣ ነገሩን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መሬት ቢሸጥና ቢለወጥ ጉልበትን በሰፊውና በብቃት የመጠቀምና ካፒታል የመቆጠብ ዕድልን አጥብቦ፣ ልማቱ ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው እንዳይሆን ስለሚያደርግ ነው፡፡ ሆኖም ጥቅም ላይ ብቻ ያሰፈሰፉት ተቃዋሚዎች ሁኔታው እንዳላስጨነቃቸው ከድርጊታቸው ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡

እርግጥም እነርሱ እንዳሉት ቢደረግ፤ በሀገር ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በተለይም በመሬቱ ላይ ኑሮውን ላደረገው አርሶ አደሩ ምን ያክል ከባድ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ መሬት እንዲሸጥ እና እንዲለወጥ ቢደረግ አርሶ አደሩ በጊዜያዊነት በሚገጥመው ችግር መሬቱን ሽጦ በቀጣይነት ሊደርሱበት የሚችሉ ችግሮች ከባድ ናቸው፡፡

ይኸውም አርሶ አደሩ ባለው መሬት ላይ  አርሶ ከሚያገኘው ምርት ሽጦ ጊዜያዊ ችግሩን መፍታት እየቻለ አሊያም አርሶ አደሩ በየአካባቢው በተቋቋመለት የብድር ተቋማት አማካኝነት በጊዜያዊነት መቅረፍ እየቻለ ማለቴ ነው፡፡ መሬቱን ሸጠ ማለት ግን ችግሩን በዘላቂነት ማባባስ ቻለ ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መሬት ቢሸጥና ቢለወጥ ጥገኛው ባለሀብት ምናልባትም ደግሞ ይህን ሃሳብ  እራሳቸው ያፈለቁት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሬት ገዝተው እያከራዩ በኪራይ ሰብሳቢነትና በጥገኝነት ሰፊ ዕድል ያገኛሉ፡፡ ከዚህ ዕውነታም መሬትን መሸጥ እና መለወጥ አርሶ አደሩን ገዳይ፣ ጥገኛውን ግን የሚጠቅም እንዲሁም ልማቱን የሚያደናቅፍ ብሎም ለሀገራችን የማይጠቅም አጉል አስተሳሰብ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው— ምርጫ በደረሰ ቁጥር የሚያመጡት አማራጭ ሀሳብ ውሃ የማይቋጥረው፡፡ የራሳቸውን አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ ተስኗቸው ጥገኛውን ባለሀብት በሚጠቅም የቀነጣጠበ የሊብራሊዝም አቋም ሲያራምዱ የሚታዩትም ምክንያቱ ይኸው ነው፡፡

ለነገሩ የእኛ ሀገር ተቃዋሚ ፖለቲከኞች “የፋርስ ድርሰት” ከጊዜ ወደ ጊዜ አስገራሚና ትወናውም የሚገርም እየሆነ ነው። “መሬት እንዴት ይሸጥ ይለወጥ ትላላችሁ፤ አርሶ አደሩን ባዶ እጁን ልታስቀሩት ነው ወይ?” ተብለው ሲጠየቁ፤ በተጠናወታቸው “የዓይኔን ግባር ያድርገው” አባዜ “ያልነው የአርሶ አደሩ መሬት መሸጥ የመለወጥ መብት ይከበር ነው” የሚል አልሸሹም ዞር አሉ አይነት ያፈጠጠ ያገጠጠ ክርክር ሲያስደምጠን መመልከት የተለመደ ነው፡፡

ዳሩ ግን እነዚህ ወገኖች ያልተረዱት እውነታ አለ፡፡ ይኸውም አንድ መብት እንዲከበር ከተፈለገ፤ መብቱን በወረቀት ብቻ አስፍፎ እንዲቀር በማድረግ አለመሆኑን ነው፡፡ መሬትን የመሸጥ መብት እንዲከበር ከተፈለገ፣ አርሶ አደሩ መብቱን በወረቀት ላይ አስፍሮ እንዲያኖረው ሳይሆን በመብቱ እንዲጠቀም ብሎም እንዲሸጥ እና እንዲለውጥ ለማድረግ ብቻ ነው ሊሆን የሚገባው፡፡ ስለሆነም “መብቱ ይከበር አልን እንጂ፤ መሬት ይሸጥ አላልንም” የሚለው አባባል፤ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ፀረ- አርሶ አደር እና ፀረ – ልማት የሆነው አቋማቸው እንዳይጋለጥ የተከተሉት የማጭበርበር ስልት መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡

ተቃዋሚዎች በአንድ መልኩ “ለምን ኢንቨስተሮች ከውጭ መጥተው ሀገር ያለማሉ?” የሚል ጥያቄ ያነሱና ትንሽ ቆይተው ደግሞ፣  መንግስት የሚከተለው የሶሻሊዝም ስርዓት ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እነዚህን ሁለት የተለያዩ ጉዳዮችን አጣምረው ለማቅረብም ይሞክራሉ፡፡ የሊበራሊዝምን አስተሳሰብ እናራምዳለን የሚሉት ተቃዋሚዎች፣ የሊበራሊዝም ዋነኛ መገለጫ የሆነውን ኢንቨስትመንትን የመሳብ ጉዳይ ያብጠለጥላሉ። በሌላው ጎኑ ደግሞ በፍፁም የዕዝ ኢኮኖሚ ስር የሚተዳደረውን የሶሻሊዝም ሥርዓትን መንግስት ይከተላል የሚል ሃሳብ ያነሳሉ።

ሆኖም ሁላችንም እንደምናውቀው ሶሻሊዝም ከውጭ የሚመጣን ማንኛውንም ዓይነት ኢንቨስትመንት የማይቀበል ስርዓት ነው፡፡ እንዲያውም ሀብት የሚያፈራ የሀገር ውስጥ ባለሀብት ከተወሰነ የገንዘብ ጣራ በላይ ካለው የሚወረስበት አሰራርን የሚከተል መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡

በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው ስርዓት የሚመራው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን በርካታ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማፍራት የቻለ ነው፡፡ እናም በገሃድ የሚታየው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ፤ ልማታዊ መንግስትን ከሶሻሊዝም ጋር ማያያዝ ምንም ስሜት ሊሰጥ የማይችል ክርክር ይመስለኛል፡፡

ለነገሩ አንድ ሀገር በብዛት ያላትን የልማት አቅም በስፋት ተጠቅማ፣ እጥረት ያለባትን አቅም በመቆጠብ ዕድገት ማምጣት እንደምትችል ይገልጻል፡፡ እርግጥ በሀገራችን በርካታ የሰው ሃይል ጉልበት ሲኖር ከፍተኛ የካፒታል እጥረት እንዳለ አያጠያይቅም፡፡ ይሁን እንጂ የካፒታል ችግሩን በመቅረፍ ያለውን ከፍተኛ ጉልበት ስራ ላይ ማዋል የሚቻለው መንግስት በቀየሰው የግብርና መር የልማት ፖሊሲ መሆኑ እየታወቀ፤ ተቃዋሚዎች ግን የተፈጥሮ ሀብት ባላቸው ሀገራት ውጭ የምስራቁ ይሁን የምዕራቡ ሀገራት ይህን የልማት አካሄድ እንደሚከተሉት በዚህም ያደጉ ሀገሮች እንዳሉ እንኳን ለመመስከር ፍቃደኛ አይደሉም፡፡ ሃቁ ግን እንዲያ ነው፡፡

አዎ! መንግስት የተከተለው “መሬት የመንግስትና የህዝብ ነው” ፖሊሲ የሀገሪቱን ምጣኔ-ሃብታዊ ዕድገት ያሳደገ ብሎም ህዝቦቿን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን እነዚህ ወገኖች ሊያውቁት የሚገባ ይመስለኛል። እንደ ተቃዋሚዎቹ ፍላጎት መሬት ቢሸጥና ቢለወጥ ኖሮ፤ ሰፊ ጉልበት መጠቀም ሲገባን አርሶ አደሩን ከማሳው አፈናቅሎ በከተማ ወይም በገጠር ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ከፍ ባደረግን ነበር፡፡

ይህም የልማት አቅማችንን የሆነውን ጉልበትን አምክኖ ልማትን ማዳከሙ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም ዛሬ ላይ ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ከመጣው የሀገራችን ህዝብ አኳያ የስራ አጡ ቁጥር አሁን ካለው በብዙ እጥፍ በጨመረ ነበር። ይህ ያልሆነበት ምክንያት መንግስት የመሬት ተጠቃሚነትን ጉዳይ በህገ መንገስቱ መሰረት ገቢራዊ ስላደረገ ነው። እርግጥ ተቃዋሚዎቹ ከሚሸጠው መሬት ተጠቃሚ እስከሆኑ ድረስ አርሶ አደሩ ቢፈናቀል፣ ባይፈናቀል ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ ገዥውን ፓርቲ ለመቃወም እስካስቻላቸው ድረስ የሌላው ጉዳይ ደንታቸው የሆነ አይመስልም፡፡

ሆኖም ማንም ሰው በግልፅ እንደሚገነዘበው ዛሬ አርሶ አደሩ የመሬት ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ መሬቱን ከፈለገ ያወርሳል፣ ቢያሻውም ያከራያል፡፡ መሬት በመንግስትና በህዝብ እጅ ሆኖ ፈጣን ዕድገት እየተረጋገጠ ነው፡፡ ለዚህም ነው— ለከታታይ 13 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ የተቻለው፡፡ ነገሩ ተቃዋሚዎች እንደሚያቀርቡት ሃሳብ ሳይሆን፣ መንግስት ቀደም ባሉት ስርዓቶች ያላደረጉትን አርሶ አደሩን በመሬቱ የመጠቀም መብት የማረጋገጥ እንዲሁም በምርቱ በነፃ የመጠቀም መብትን የማጎናጸፍ ተግባራትን ለመተግበር በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል፡፡ የሚቀሩ ተግባራት ቢኖሩም ከተገኘው የህዝብ ጠቀሜታ አኳያ ይህን ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለመገንዘብ የሚከብድ አይመስለኝም።

አዎ! የመሬት ተጠቃሚነት ጉዳይ በህገ መንግስቱ ምላሽ ያገኘ እንዲሁም በህገ መንግስቱ መሰረት ተግባራዊ ሆኖ ሀገራችንን በልማት ጎዳና እንድትራመድ ያደረጋት ነው። በተቃዋሚዎች በኩል በተለይም ከኦሮሚያ ክልል ጋር ተያይዞ የሚነሳው የመሬት ስሪት ጉዳይ የሁከትና የብጥብጥ መንስኤ አለመሆኑ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል። ምናልባትም ከመሬት አኳያ ሊነሱ የሚችሉ ጉዳዩች ካሉ ምላሽ የሚያገኙት በህገ መንግስቱ ማዕቀፍ ውጪ እንጂ ህገ መንግስቱን በመናድ አለመሆኑን እነዚህ ወገኖች ይገነዘቡታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።