የወጣቶች ተሳትፎ … ከብልሽት የጸዳ አመራርን ለመገንባት

 

የኢትዮጵያ ወጣቶች በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳይ ውስጥ የነበራቸውን እና የሚኖራቸውን  ወሳኝ ሚና በአግባቡ እንዲወጡ አለመሰራቱ ወይም ቸል መባሉ ብዙ ዋጋ እንዳያስከፍለን አመላካች የሆኑ ክስተቶች ከሰሞኑ ታይተዋል። ስለሆነም መንግስት ራሱን በጥልቀት በመፈተሽ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እተጋለሁ ማለቱ በብዙ አግባቦች ተገቢነት ይኖረዋል። ለትጋቱ የግድነት ማጠየቂያው ደግሞ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በዋናነት የወጣቶች ሃገር መሆኗ ነው። የኢፌዴሪ መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አስቀድሞ ያዘጋጀው ስለዚሁ ተጨባጭ እውነታ ቢሆንም ፖሊሲና ስትራቴጂዎቹን የሚመጥን አመራር በየወቅቱ እያደሱ ባለማብቃቱ ግን የተፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም። አለመቻሉንም አምኖ መቀበል መቻል ደግሞ ተገቢና የወጣቶች ተስፋ አለመሟጠጡን አመላካች ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ዴሞክራሲዊ ስርአት ግንባታ ውስጥ የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛና የማይተካ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ አስፈጻሚ ያስፈልጋል የሚል አቋም ላይ የተደረሰውም ለዚህ ነው።

ባለፉት ዓመታት በትምህርት፣ በጤናና በመሠረተ ልማት ዘርፍ በተከናወነ ተግባር ጤናው የተጠበቀ፣ የተማረና መረጃ ያለው ወጣት ማህበረሰብ መፈጠሩ አይተባበልም። የኢህአዴግ ምክር ቤት በግምገማው እንዳረጋገጠውም፣ ይህ ወጣት በገጠርና በከተማ ለተነቃቃው ኢኮኖሚ ምክንያትም ቀጣይ አቅምም ነው። የግል ባለሀብቱና የህዝብ ፕሮጀክቶች ከሚፈጥሩት የስራ ዕድል በተጨማሪ ወጣቱ እየተደራጀ ራሱን የሚጠቅምባቸው የስራ መስኮች በስፋት ቢከፈቱም የአመራር ብልሽቶች እዚህም እዚያም በሃገሩ ጉዳይ ባይተዋር የሆነ ወጣት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል ።  

የኢፌዴሪ መንግስት ሀገራዊ ሁኔታውን በስፋት ገምግሞ ራሱን በጥልቀት ማደስ እንዳለበት ከወሰነባቸው ጉዳዮች አንዱ ይህ የወጣቶች የተጠቃሚነት ጉዳይ የሆነውም ለዚህ ነው። ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን አሟጦ ከመጠቀም አንፃር ለነበሩት ጉድለቶች በሙሉ ከፍተኛው ክፍተት በብልሽት የተተበተቡ አመራሮች ከለት እለት መበራከታቸው መሆኑም ላይ በኢህአዴግ ግምገማ የተረጋገጠ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የህዝቡም የለት ተለት ወሬ እና በተጨባጭም የሚታይ ሃቅ ነው ።

በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት እንዲሁም በከተማና ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂዎች የተቀመጡና በተሟላ ደረጃ ወደስራ ያልተቀየሩ ስልቶችን በማበልጸግ ይልቁንም ሊለሙ ሲገባቸው ጦማቸውን እያደሩ የሚገኙ በሚሊዮኖች ሄክታር የሚቆጠሩ መሬቶችን  ጭምር በስራ ላይ ማዋል ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው። በመሆኑም የወጣቱን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስፋት መታየት ያለባቸው አማራጮች ሁሉ ሊፈተሹ ይገባል ሲል ምክር ቤቱ አቋም ላይ መድረሱ ተገቢና ወቅቱ የሚጠይቀው ከአቋምም አልፎ በተግባር መገለጥ የሚገባው ጉዳይ ነው ።

ሃገሪቱ በተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ የተገኙ ተከታታይ ዕድገቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የተደራጀ የወጣቶች ተሳትፎ የማስፈለጉ እውነታነት በተመዘገበው ውጤት የተረጋገጠ ቢሆንም ይህ አካሄድ የመቀልበስ አዝማሚያ ስለማሳየቱ እና ይህም የአመጽ ሰለባ በመሆን የመገለጡ ምክንያት የአመራር ብልሽት መሆኑ አያጠራጥርምና  መሪ ድርጅቱም በዚሁ መልክ አይቶ በአዲስ መልክ ሊተጋ ማሰቡ ተገቢና የሚጠበቅበት ጉዳይ ነው። ስለምን ከተባለ እና ሁሌም ሊዘነጋ የማይገባው ምክንያት  በጀመርነው ልክ ድህነትን ለማጥፋት፣ የሀገራችንን ብልጽግናና ዕድገት ለማስቀጠል የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ ስለሆነ የሚለው መልስ ነው።

በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግስት ለወጣቶች የተሻለ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዕንቅፋት የሆኑ አሠራሮችን የሚፈትሽና የሚያርም መሆኑን በሃገር አቀፉ የወጣቶች ኮንፈረንስ ላይ በጠቅላይ ሚንስትሩ በኩል መገለጡ ተገቢና ግን ደግሞ ለተግባራዊነቱም ያልተቋረጠ የወጣቶች ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

የኢፌዴሪ መንግስት በዚህ መልኩ ክፍተቱን ገምግሞ መፍትሄውን መለየቱን እና ዝግጅት መጀመሩን ነግሮናል። ከመላው ሀገሪቷ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ቀድሞም ቢሆን የሚወያይ መሆኑ ቢታወቅም ከሰሞኑ ያደረገው ውይይት ግን ከቀደመው በተለየ የብልሽት ቦታዎችን ለመጠቆምና ለመተጋገል የሚያስችለውን መስመር ለመዘርጋት ነው። ይህን የመሰለው ውይይትም በሁሉም ደረጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል የተባለው ያለወጣቶች ተሳትፎ አንዳች ለውጥ ማምጣት ስለማይቻል ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት ወቅት ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኛ ወጣቶች፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ወጣቶች እንዲሁም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲን የወከሉ ወጣቶች በመድረኩ ተገኝተው ጥያቄዎቻቸውን በይፋና በቀጥታ የሚዲያ ሽፋን በተሰጠው አግባብ ማስተላለፋቸው የመንግስትን ዝግጁነት እና የማያወላዳ አቋም የሚያመላክት መሆኑን ወጣቱ ሊዘነጋ አይገባም ፡፡

ከየክልሎቹ ተወክለው የመጡት ወጣቶች ከየክልሎቻቸው አንፃር ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ የአብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ማጠንጠኛም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ እንዲሁም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የነበረ መሆኑ በእርግጥም ከፖሊሲውና ስትራቴጂው ተቃራኒ አፈጻጸም የነበረ ስለመሆኑና ሊሆን የሚችለው ምክንያትም በማያጠራጥር መልኩ የአመራር ብልሽት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

70 በመቶ የሚሆነው የአገራችን ሕዝብ ከ30 ዓመት በታች ነው፤ ይህም ማለት ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ናት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ከሆነች በሕዝቦች ፈቃድ ወደ ሥልጣን የሚመጣ መንግሥት የወጣቶች መንግሥት መሆን ግድ የሚለው መሆኑን የተገነዘበ እና ለዚህ የሚመጥን አመራር በየደረጃው ያስፈልጋል ማለት ነው።  

ሥራ አጥነትን ለመዋጋት ወጣቶች ራሳቸው ሥራ ፈጣሪ መሆን የሚችሉበትን እድል መፍጠርና ማስፋት የሚችል አመራርን እንጂ በብልሽት የጎበጠ አመራርን የሃገራችን ወጣቶች ያሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ማስተናገድ አይችልም።  

የመልካም አስተዳደር ጥያቄን በተመለከተ ወጣቶች በቻሉት መጠን ሁሉ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸውን አመራሮች በማጋለጥ ሚናቸውን መጫወት ይኖርባቸዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ማሳሰባቸውም ስለዚህ ነው፡፡ ወጣቶች ተስፋ ሳይቆርጡ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ጥያቄዎቻቸውን በማቅረብ፣ በአገሪቱ አሉ የተባሉ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ጥያቄዎችን ለማስመለስ መንቀሳቀስ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ከመሆኑም በላይ ወቅቱ የሚጠይቃቸው ብሄራዊ ግዴታቸው መሆኑን አጽንኦት ሊሰጡት እና ተከታታይነት ባለው መልኩ ሊመክሩበት ይገባል፡፡

በቅርቡ በተለያዩ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች የተከሰቱትን አለመረጋጋቶች አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ጥያቄ ያላቸው ወጣቶች ጥያቄያቸውን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ማቅረብ ሲችሉ ድንጋይ በመወርወርና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ መሆናቸው ማንንም እንደማይጠቅም አብራርተዋል፡፡

በዚህ ክረምት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በደም ልገሳ፣ በክረምት የማጠናከሪያ  ትምህርት፣ በአካባቢ ፅዳት አጠባበቅ፣ በችግኝ ተከላ፣ በትራፊክ አገልግሎትና በመሳሰሉት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ ተሳታፊ  የመሆናቸውን ያህል ገሚሶቹ ደግሞ የአመጽ ሰለባ በመሆን በሃገራቸው ልማት ላይ በተቃርኖ ተሰልፈው የጥፋት ሃይሎችን ደባ ሲያስፈጽሙ የነበረው እንደው ዝም ብለው ሳይሆን የከፋቸው ነገር ስላለ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም መንግስት ይህን ተገንዝቦ የማስተካከያ እርምጃዎች ለመውሰድ በተዘጋጀበት ሰአት የእነርሱም ተሳትፎ ያስፈልጋልና ሊነቁና ሊተጉ ይገባል። ተሳትፏቸውም የከፋቸውን ጉዳይ በሰላማዊና ህጋዊ በሆኑ አግባቦች በመጠየቅ ሊጀምርና ሊገለጽ ይገባል ።  

ከዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ጎን ለጎን ዞሮ ዞሮ  የተጀመረውን ህዳሴ ጉዞ ትሩፋቱ ሲበዛ የእነርሱው ነውና ጉዞውን  ከዳር ለማድረስ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ከመቸውም ጊዜ በላቀና በበለጠ ሊተጉ ይገባል፡፡