የተረጋጋ ሰላም ለማምጣት !!

 

አሁን በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ሀገሪትዋን ወደ ተረጋጋ ሰላም የሚመልሳት በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ የተንሰራፋው ችግር እልባት ሲያገኝ ብቻ መሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡ ችግሩን ፈጥኖ መቅረፍና ቁርጠኛ ውሳኔ ማሳለፍ ሀገርንም ህዝብንም ከጥፋት ይታደጋል፤ የተረጋጋ ሰላም ለማምጣትም ይበጃል፡፡ ለዚህም ጥልቀታዊው ተሀድሶ ፍጥነቱን ጨምሮ ወደ ስራ ይገባ ዘንድ ግድ ነው፡፡

በኢህአዴግ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ አመራሮችም ሆኑ አባላት በእስከ አሁኑ የ25 አመታት ጉዞ ስኬት ድል ፈተናና ወሳኝ ታሪካዊ ሁነቶችን አይተዋል፡፡ ለሀገሪቱ ትልቅ ለውጥና እድገት የመስራታቸውንም ያህል አቻ በአቻ በራሳቸው ውስጥ ለህዝብ ምሬትና መከፋት መሰረታዊ የሆኑትን ስህተቶች ፈጽመዋል፡፡ ለሰላም መደፍረስ ምክንያቶቹም በአብዛኛው ራሳቸው ናቸው፡፡

መነሻቸውን የረሱ፣ በህዝብ ንቀትና ድፍረት የተሞላ አቋም ሲያራምዱ የነበሩ በመንግስት ሀብትና ንብረት በመሬት ዘረፋ የከበሩም ታይተዋል፡፡ በዘረፋ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ህዝብ አያውቅም፣ ቢያውቅስ ምን ያመጣል ማለት ግመል ሰርቆ አጎንብሶ የመሄድ  ያህል ብቻ ሳይሆን ህዝብን መናቅ ጭምር ነው፡፡ ህዝብ ምንም የማያውቀው ነገር እንደሌለ ይታወቃል፤ ትልቁ ፈታኝ ችግር ኢህአዴግ ይህ በውስጡ እያደገ የመጣውንና ከህዝቡ በተቃራኒ የቆመ የኪራይ ሰብሳቢዎችና የሙሰኞች ጥርቅም ከድርጅቱ ውስጥ ማጥራት ሳይችል መቆየቱና መዘግየቱ ነው፡፡

የመልካም አስተዳደር መዛባት፣ የፍትህ መጣስና የመብት መረገጥ፣ የህዝብን አደራ የበሉ አሳፋሪ ተግባርና ድርጊት ውስጥ ተዘፍቀው ሲዋኙ በነበሩትና ባሉት አባላቱ ላይ በወቅቱ መፍትሄ ቢያበጅለት ኖሮ ችግሩ ወደዚህ ጫፍ ሊራመድ፣ ሊያንሰራራ፣ ሊያድግ፣ ከፍተኛ የህዝብን ቁጣና ተቃውሞ ሊቀሰቅስ አይችልም ነበር፡፡ ይህ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረው ስርነቀል የለውጥ ሀይል በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መዳከሙን በገሀድ ያሳያል፡፡ ነባር አባላት እንደሚገልጹት ከስድስተኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ጀምሮ እስከ አስረኛው ጉባኤ ድረስ በውስጥ በተንሰራፉት የሙስና፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ችግሮችን እየመረመረ ታግሎ ለማስወገድ ውሳኔ ሲያሳልፍ ኖሮአል፤ ብዙ ርቀት ግን መራመድ አልቻለም፡፡

ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ በቆመውና ከማገልገል ይልቅ ወደዘረፋ በተሰማራው ሀይል ላይ እርምትና እርምጃ እንደሚወሰድና ተሀድሶ እንደሚደረግ ሲወሰን ይህ ቃል ወደተግባር ተለውጦ እናያለን የሚል ሰፊ የህዝብ እምነት ነበር፡፡ ቄሱም ዝም፤ መጽሀፉም ዝም አይነት ሆነና የውስጡ ችግር ብርቱ ስለሆነ ኢህአዴግ ህዝቡ የሚፈልገውን ለውጥ ማሳየት አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ፣ አሁን የደረሰበት ስር ነቀልና ጥልቀታዊ ተሀድሶ ለማካሄድ መወሰኑ የሚበረታታና የሚደገፍ ነው፡፡

ደጋግመን እንዳልነው ሀገር የህዝብ ነች፤ ባለቤቷም ህዝብ ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ፖለቲካዊ ስልጣን መንግስታዊ ሀላፊነት ዝንተ አለማዊ አይደለም፤ ይለወጣል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ራሳቸውን ከወቅቱ የህዝብ እድገትና ጥያቄ ጋር ማሳደግ፣ መራመድና መምራት ከተሳናቸው ቦታውን በዘላቂነት ወይም በውርስ ይዘውት ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ ህዝቡ በቃ ሲል ያበቃል፡፡

በሰለጠነው አለም አቀፋዊ ልምድና ተሞክሮ በምርጫ ወቅት ህዝቡ ድምጹን ሊነፍግ ይችላል፡፡ አልመርጥም ማለትም መብቱ ነው፡፡ ይሄ ሁከትና ረብሻ አመጽ ሳይታከልበት የሀገር፣ የመንግስትና የህዝብ ሀብትና ንብረት ሳይወድም በሰላማዊ መንገድ የሚገለጸው የተቃውሞ አይነት ነው፡፡ ስልጡን እሳቤና ተገቢም ነው፡፡ ምክንያቱም ሀገርም ህዝብም ቀጣይ ናቸው፡፡ የኮንትራት ውሉ የሚቋረጠው ከገዥዎቹ ጋር ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

ተቃውሞን በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ማሰማት መሰረታዊ ህገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡ ምንም አይነት ግጭት፣ የንብረትና የሀብት መውደም፣ የሰው ህይወት መጥፋት አያስፈልገውም፡፡ የግዴታ እኔ ካልመራሁ ወይም በግድና በሀይል ህዝብን አስተዳድራለሁ የሚል የትኛውም ወገን የመጨረሻው ምን እንደሆነ ገዢው ፓርቲ አይቶት፣ አልፎበት የመጣው መንገድ ስለሆነ ለዚህች ሀገር እንደማያስፈልጋት በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ለዚህም ነው የህዝብን ትክክለኛ ጥያቄ መረዳት፣ ስሜቱን ማወቅ፣ ለጥያቄዎቹም ትኩረት ሰጥቶ ከፍረጃ የወጣ መልስ ማስገኘት አጣዳፊና ወሳኝ የሚሆነው፡፡ የተሀድሶው ጥልቀትም አንዱ የሚለካው በዚህ ርቀት መሄዱ ነው፡፡

የህዝቡን መመረር፣ መከፋት፣ መንገፍገፍ ያስከተሉትን አቢይ ችግሮች የተሀድሶው ጥልቀት በውል መረዳትና መተንተን ይገባዋል፡፡ ምዝበራው፣ ዘረፋው ዜጎችን ለጥቂት ከበርቴዎች የማይጠግብ የአጋባሽነት ፍላጎት ሲባል አሳልፎ የሰጠ፣ ዜጎችን በልማትና እድገት አመካኝቶ በመንግስት ስም ማፈናቀል፣ በውድቅት ክረምት ሜዳ ላይ አውጥቶ መጣል በተኙበት በግሬደር ማፍረስ፣ ማረስ ያውም ህጻናት ባሉበት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፤ ለዛውም ዜጎችን ሊጠብቅ፣ መብታቸውንም ሊያስከብር ከሚገባው መንግስት፡፡

በምርጫ ካርዱ ይሁንታ ሰጥቶ ለመንግስትነት ያበቃ ህዝብ በመረጠው መንግስትና በተሰየሙ ሹማምንት እኛ እናውቅልሀለን ፈሊጥ መብቱና ዜግነቱ ሊደፈር፣ ሊደበደብ፣ የትም ሂድ ተብሎ ሊገፈተር አይገባውም ነበር፡፡ ይህም በህዝብ ዘንድ ቂም ያስቋጠረ፣ ትልቅና ያልተፈታ ችግር ነው፡፡ ባለስልጣናት ይህንን መስማት አይፈልጉም፡፡ እውነቱ ግን ይሀው ነው፡፡ በሽታውን ካላወቁ መድሀኒቱ አይገኝምና ቢመራቸውም ሊቀበሉት ግድ ነው፡፡ ህዝብ እንጂ የመረጣቸው በህዝብ ላይ ራሳቸውን ሊሾሙ፣ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ሊሆኑ በህዝቡም መብት ሊያዙ አይችሉምና፡፡

ኢህአዴግ እንደ መንግስትም እንደ ፓርቲም ከህዝባዊነት እየራቀ መምጣቱን የድሀውን የሰፊውን ህዝብ ሳይሆን የከበርቴዎችንና የሀብታሞችን ፍላጎት ለማስፈጸም መሰማራቱ ፖለቲካ ኪሳራ ውስጥ ከቶታል፡፡ የህዝብ አመኔታን አሳጥቶታል የሚለው የህዝብ አስተያየት ሰፊ ነው፡፡ ህዝብ ለሀገሩ እንደማያስብ፣ እንደማይቆረቆር፣ እነሱ ደግሞ ብቸኛዎቹ የሀገር አሳቢና ተጨናቂ ሁነው ህዝብን ፈተና፣ መከራና እንግልት ውስጥ የከተቱበት ሁኔታ ምሬቱን አጉኖታል፡፡ ኢህአዴግ በንጽጽር ሲታይ ቀድሞ ከነበረው የተሻሉ ህዝባዊ ባህሪዎቹ (ሙሉ ለሙሉ እንኳን ባይባል) አፈንግጦ ወጥቶአል፡፡ ዛሬ ላይ የትላንቱ ይሻላል የሚባልበት ወቅት መደረሱን የህዝብ ሀሳብ ይገልጻል፡፡

ቤቶቹ ፈርሰው፣ መሬቱ ታርሶ ለማን ነው የሚሰጠው ሲባል በአሳፋሪ ሁኔታ ለልማታዊ ባለሀብቶች፣ ለከበርቴዎች ነው የሚሆነው፡፡ ህዝብን ተጠቃሚ ያላደረገ ልማትም ሆነ እድገት መቼም ተቀባይነት አይኖረውም፤ ልማቱ ማተኮር ያለበት በህዝብ ተጠቃሚነት ላይ ነውና፡፡

በዚህ መልኩ ኑሮው የፈረሰ፣ ህይወቴን እለውጣለሁ ብሎ ጎጆ የቀለሰ በርካታ አመታት የኖረበት፣ ያገባና የወለደበት ልጆቹን ያሳደገበት መንደር አልጠግብ ባይ ሀብታሞችን የበለጠ ለማክበር ሲባል ልማትን ሽፋን አድርጎ በሚሰራ የተቀነባበረ ድርጊት እጅግ በጣም ብዙ ህዝብ መከፋቱን፣ መማረሩን ኢህአዴግ ቢያውቅም እስካሁን መፍትሄ ለመስጠት ሳይችል ቀርቶአል፤ በመሆኑም አሁን በተሀድሶው ይመለከተው ዘንድ ግድ ነው፡፡

በኢህአዴግ ስም የሚጫወቱት ተዋናዮች በሚሊዮንና በቢሊዮን ብሮች ከብረውበታል፡፡ ምናልባት ኢህአዴግ ሊለን የሚችለው ነገር ቢኖር ከተሞች ፈርሰው እየተሰሩ፣ እያደጉ፣ እየተለወጡ መሆናቸውን ነው፡፡ ከጀርባ የሚሰራውን ህዝብ ያስመረረ የሙሰኛውንና የኪራይ ሰብሳቢውን የምዝበራ፣ የዘረፋ ወደር የለሽ ግፍ እንደመንግስት ማወቅና መፍትሄ መስጠት የነበረበት ራሱ ነበር፡፡ ህዝቡ ይሄ ሁሉ ሲሰራ ኢህአዴግ የት ነበር ሲልም ይጠይቃል፡፡

የተሀድሶው ጥልቀት እስከምን ድረስ ይራመዳል? የሚለው ጥያቄ በተግባር የሚታይ ብቻ ይሆናል፡፡ የተረጋጋ ሰላም ለማምጣት የሚቻለው  የህዝቡ ቅሬታ እንዲፈታ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ ልማት ለህዝብና ለሀገር መሆኑ እየታወቀ ልማቱ ህዝብን ማእከል ማድረጉ ቀርቶ ህዝቡን ባለበት ማልማት ቤት መስራትም ሲቻል ቦታውን ከጀርባ በሚደረግ ምስጢራዊ ድርድር ለከበርቴዎችና ለጥገኛ ሀይሎች በኢንቨስትመንት ስም መሸጥ የከፋ የህዝብ ምሬትንና ቁጭትን ከቀሰቀሰው ውስጥ አንዱ ነው፡፡

ይህን ቁማር ሲጫወቱ የኖሩት በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ በአባልነት ስም ተሰግስገው የነበሩና ያሉ ስልጣናቸውን የግል መክበሪያና መጠቀሚያ ያደረጉ አደራ በላዎች ናቸው፡፡ መንደሮችን ባሉበት አፍርሶ ተሰርተው እስኪያልቁ ድረስ ለህዝቡ ግዜያዊ መጠለያ አዘጋጅቶ በነበሩበት መልሶ የተሻለ ቤት አግኝተው እንዲኖሩ ቢደረግ ነበር መንግስት በእርግጥም ለህዝቡ፣ በተለይም ለደሀው ያስባል፤ ልማታዊ ነው ልንል የምንችለው ይላል ህዝቡ፡፡

የተደረገው ፍጹም ከዚህ ውጭ ነው፡፡ ይሄም ሀገሪቱ ለሀብታሞች ብቻ መፈንጪያ እንድትሆን መንግስት ለድሀው ሳይሆን ለሀብታሞች ብቻ የቆመ፣ ጥቅማቸውንም ለማስከበር የሚንቀሳቀስ ነው የሚል መደምደሚያ አሰጥቶታል፡፡ የተሀድሶው ጥልቀቱ የሚወሰደው እርምጃ ከዚህ አንጻርም በህዝቡ ይመዘናል፡፡

በአዲስ መልክ መገንባትና ማልማት ሲቻል ብዙሀኑ ህዝብ በመንግስትና በልማት  ስም እየተፈናቀለ፣ እየተሰደደ፣ ቦታው ለጥቂት ሀብታሞች እየተሸጠ ከህዝብ በተጻራሪ የተፈጸመ ድርጊት መሆኑን ህዝቡ በምሬት ይገልጻል፡፡ አንዱም የከፋው ጥላቻና ተቃውሞ መነሻው ይሄ ነው፡፡

የግል ባለቤቶችና ባለይዞታዎች ያለተገቢ ካሳ ለዛውም የዘረፋ ያህል በሚቆጠር መልኩ ትንሽ ሳንቲም እየተወረወረላቸው በተቃራኒው ደግሞ ቦታው፣ ሰፈሩ፣ መንደሩ በብዙ ሚሊዮኖች እየተሸጠ ጥቂቶች በሀብት ክብረት ወደ ሰማየ ሰማያት የተወነጨፉበት፣ አብዛኛው ህዝብ ወደከፋ ድህነት ውስጥ እንዲገባ የተደረገበት ድራማ ሲሰራ መኖሩን ህዝብ ሳያቋርጥ ይናገራል፡፡ ይህን ላለመድገም የተሀድሶው ጥልቀት እስከ ምን ድረስ ይሄዳል? የሚለውም መልስ ይፈልጋል፡፡

ዜጎች በሀገራቸው ማንኛውም ጉዳይ ያገባቸዋል፤ ይመለከታቸዋልም፡፡ ለምን ይሄ ሆነ? ተደረገ? ብለው ሲጠይቁ በሀላፊነት ላይ ባሉት ሰዎች ጸረልማት፣ ጸረእድገት ተብለው ይፈረጃሉ፡፡ ማነው የሀገሩን ሰላምና እድገት የሚጠላው? እነሱስ እነማናቸው? ይሄን ለማለት በዘረፋ በሀገር ሀብት ሌብነት የተሰማሩ ሰዎች ይህን ለማለት የሞራል ብቃት የላቸውም ባይ ነው ህዝቡ፡፡

ማን የሀገሩን ልማትና እድገት ይጠላል? ድርጊቱ የሚኮንነው የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብት ያላከበረ፣ የናደ፣ በሀይል ጭምር የታጀበ በመንግስት ስም ባለስልጣናት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ጣልቃ እየገቡ በሚፈጥሩት ሁኔታ መሆኑን ህዝቡ ይናገራል፡፡

ማነው ሳይለፋ፣ ሳይደክም ሚሊዮነርና ቢሊዮነር ለመሆን የበቃው? ቢባል የሚታይ በመሆኑ ህዝቡ ያውቀዋል፡፡ በምሬትና በቁጭት ተሞልቶ ለእኔስ እውን ሀገሬ ናት? ዜጋ ነኝን? ብሎም ራሱን ይጠይቃል፡፡ አንዱም የህዝቡ ምሬትና መከፋት መነሻ ይሄ ነው፡፡ የተረጋጋ ሀገራዊ ሰላምን ለማስፈን ትልቁ ቁልፍ መፍትሄ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎችና ችግሮች በዘላቂነት መፍታት ብቻ ነው፡፡ የተረጋጋ ሰላም ይኑረን፤ ይብዛልንም፡፡