ማንነትን የሌብነት ምሽግ ማድረግ አይቻልም!!

 

 

ከዚህ በቀደመ አንድ ተረኬ በሃገራችን ስለተስተዋለውና ከሰሞኑ ተነስተው የነበሩ ሁከቶችን መነሻ ያደረገ፤ የትኩረት አቅጣጫውን ደግሞ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና ልማት ላይ ያደረገ የፌደራላዊ ስርአትን የአዋጭነት ሂሳብ አስልተን የነበረ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህ ተረክ ያቆየነውን እና ስሌቱን ሰሞንኛ ለነበሩት ሁከቶች  ባንዲራ ሆኖ ከፊት ሲውለበለብ የነበረውን ከማንነት ጋር የተያያዘውን ደግሞ ይህ ጽሁፍ ለሙግትም ሆነ ሃገራዊ ግዴታን ከመወጣት አንጻር የሚዛናችንን መነሻ ለማጠየቅ በሚያግዝ መልኩ ይተርካል፤ ያሄሳልም።

በአገራችን እየተገነባ ያለው የፌዴራል ስርአት በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ስርአት ነው ስንል በርካታ ማሳያዎችና ተጨባጭ እውነታዎች ስላሉን ነው። አዳሜ እየተነሳ የሚያብጠለጥለውም ሆነ “የፖለቲካዊ ስራው” ቁልፍ ተግባር ነቀፌታ ያደረገው ኢህአዴግ፤ የዘመናት የብሄራዊና የመደብ ድርብ ጭቆናዎችን የተመለከቱ የህዝብ ጥያቄዎችን ከመሰረቱ ለመለወጥ ከተከተላቸው ቁልፍ የፖለቲካ አቋሞችና ከወሰዳቸው ወሳኝ ፖለቲካዊ እርምጃዎች መካከል የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ የመገንጠል መብቶችን ማረጋገጥ ቢሆንም ከዚሁ ባልተናነሰ አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር የመጨረሻው ግብ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ሃገራችን በህዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተች፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ዴሞከራሲያዊ አንድነት የሚንፀባረቅባት ሃገር እንድትሆን የመንግስትም ሆነ የመሪ ድርጅቱ መዘናጋትና መተኛት እንደተጠበቀ ሆኖ እየተተጋ ይገኛል።  

ይህች እየተተጋላት የምትገኝ ሃገር ሰብእዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ የሚከበሩባት፣ የዴሞከራሲ ባህልና ተቋሞች የሚያብቡባት፣ ህዝቡ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ህይወት የነቃ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን የሚያረጋግጥበት፣ በህዝቦች መብት መከበር፣ በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠንካራ አንድነት የሚጎለብትበት፣ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ የመድበለ ፓርቲ ስርአት መፍጠር ነው በማለት በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ስርአት መገንባትን በመንግስትም ሆነ በመሪ ድርጅቷ ደረጃ ቁልፍ ተግባሯ መሆኑ የህልውናዋ እንጂ ለይስሙላ ያስቀመጠች ሃገር አለመሆኗም የሚታወቅ፤ ለይስሙላ ብትሻውም ነባራዊ ሁኔታው የማይፈቅድላት ሃገር ነች። ይሁን እንጂ ሰሞንኛ የነበረው የሁከት ኃይል ይህን የህዝብና የመንግስት ጥረት በአሉባልታና በጥርጣሬ በማደናቀፍ የከሸፈበትን ሁከት ለማስቀጠል በመጣር ላይ ነው፡፡ በውይይቶቹ ላይ እንደታየውም የመንግስትን የለውጥ ዝግጅት የመጠራጠር ዝንባሌ በህዝብ ውስጥ ታይቷል፡፡

እነዚህ ጸረ ሰላም የጥፋት ኃይሎች ያነገቡት ድብቅ አጀንዳና ተልዕኮ የሕዝብ አጀንዳ አለመሆኑን በውል እየተረዳ የመጣው ህብረተሰብ ከራሱ እየነጠላቸውና እኩይ ተግባራቸውን እያጋለጠ በመምጣቱ በአሁኑ ጊዜ በብዙ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች መረጋጋት እየተፈጠረ ቢመጣም የማንነት ጥያቄን በጸረ ዴሞክራሲያዊ መንገድ በመተርጎም ለድብቅ አጀንዳው ማስፈጸሚያ ሊያውል የሚችለው ሃይል መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን መጠርጠር ሃገር ወዳድ ከሆነው ዜጋ ሁሉ ይጠበቃል።  

መንግሥት ሥልጣን ለሕዝብ ሰፊ ተጠቃሚነት እየዋለ መሆኑንና ያም ሆኖ ግን እስካሁን በነበረ አፈጻጸም በየደረጃው የታዩ ክፍተቶችን በማረምና በማስተካከል መርሁን በተሟላ አፈጻጸም ለማከናወን መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት እያሳየ ቢሆንም፣ ይህንንም ላለመጠራጠር መንግሥት እያከናወነ ያለው ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ይህንን በሚያግዝ መጠንም ከውጭ እየተገኘ ያለውን ሰፊ ዓለም አቀፍ ድጋፍ፣ ብድርና ዕርዳታ በቀጥታ የሕዝብን ዘለቄታዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ዘርፎች ላይ የመዋሉ ውጤት መሆኑን ተጨባጭ ማሳያዎች ቢኖሩም ጸረ ሰላም ሃይሉ ማልያውን እየለዋወጠ ፌደራላዊ ስርአቱን የሚፈታተኑ ሃይሎችን ከማሰማራት አልቦዘነምና ከማንነት ጋር የተያያዙትን (ምንም እንኳን ሽፋን ቢሆኑም) ጥያቄዎች  ማጥራት ተገቢ ይሆናል። 

ይህ ማለት ግን የችግሩ ዋነኛ መንስኤና ሽፋን  የነበረውን፤ ህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም ቀደም ሲል አንስቷቸው የነበሩ ተቀባይነት ያላቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመመለስ በኩል የነበረበትን እጥረት መደበቅ ወይም ማድበስበስ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ የህዝብ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃልና።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገርን ወደፊት የማራመድ ስራ የሚሳካው ግን ህገ – መንግስታዊ ስርአቱ ተጠብቆ ሰላምና መረጋጋት ሲሰፍን ብቻ መሆኑን ማመንና አምኖ ተቀብሎም ስለዚሁ ስርአት ቀጣይነት በመታገል መሆኑ ላይ ባለው አለመናበብ ላይ ግን ልዩነቱን ማጥበብ ተገቢ ነው ።ለምን ቢሉ? አሁን ባለው ሁኔታ ጸረ ሰላም ኃይሎች በተለይም የትምክህትና የጠባብነት አመለካከት አራማጆች አጀንዳቸውን በህዝብ ላይ በመጫን ሃገሪቱንና ህዝቡን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ለመምራት እየሰሩ ስለመሆኑ ከሰሞንኛ ሁከቶቹ እና ከሁከቶቹ ውጤት መገንዘብ ተችሏልና ነው፡፡ ከነዚህ ማገናዘቢያዎች መካከልም የሕዝብ መጠቀሚያ የሆኑ ግንባታዎችን፣ ቁሶችንና የግል ኢንቨስትመንት ተቋማትን የማውደም ዘመቻቸው የሕዝብ ተጠቃሚነትን በግልጽ ስለመጻረራቸው አንዱና ዓይነተኛ መገለጫ  መሆኑን በግልጽ ያመላከተ ነው። እነዚህ የውድመት ሴራዎች የተቀነበቡት ደግሞ ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዙ ህገ መንግስታዊ በሚመስሉ አጀንዳዎች መሆኑ በተግባር ተስተውሏልና ጉዳዩን በጥልቀት መመልከት ተገቢ ነው።

ይህን በተመለከተ ህገመንግስታዊ ስልጣን የተሰጠውና ህጋዊ ሃላፊነት ያለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፉት አመታት ካስመዘገባቸው ድሎች መካከል በአገራችን ሰላማዊ ሽግግርና በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት እንዲገነባ ማስቻሉ መሆኑ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ህገመንግስታዊ መሰረት ያላቸው ሆነው የተገኙ እና በተለያዩ ጊዜያት የቀረቡ የማንነት ጥያቄዎች ለምሳሌ የስልጤ፣ የአርጎባ፣ የቅማንት ጥያቄዎችን የፌዴሬሽን ምክርቤት በተናጠልና ከክልሎች ጋር በመነጋገር ምላሽ እንዲያገኙ ያደረገ መሆኑም ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ አካላት የሚነሱ ጥያቄዎች ሕገመንግሥታዊ መሠረት የሌላቸው ከሆኑ ሕገመንግሥታዊ ያለመሆናቸውን ከህገመንግሰቱ መርሆዎች በመነሳት ምላሽ ሲሰጥ የቆየ መሆኑም ይታወቃል።    

ያልተማከለው የፌዴራል ስርአቱ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ስርነቀል ለውጦችን ስለማስከተሉም ያጣጣመው ሁሉ የሚገነዘበው ነው። ከሁሉ በፊት የዘመናት የአገራችን ጭቁን ህዝብች ጥያቄዎች የነበሩት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት፣ የመናገር፣ የመፃፍ፣ ሃሳብን በተለያዩ መንገዶች የመግለፅ እንዲሁም የመደራጀትና የመዘዋወር ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ተግባራዊ ማድረግ የተቻለውም  በዚሁና በማንነት ጥያቄ ስም በሚዘመትበት ስርአት መሆኑም ይታወቃል። 

ሁከቱ መሰረታዊ መርሆዎችን እና የህግ የበላይነትን የተጻረረ ቢሆንም  የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል ድረስ ያላቸው መብት እንዳይሸራርፍ በፅናት የታገለው ኢህአዴግ  ህገመንግስታዊ መብታቸው በተከበረበት ሁኔታ በነፃ ፍላጎታቸውና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት እንዲኖራቸው ያደረገው ጥረት ፍሬ መሆኑንም ማስተባበል አይቻልም፡፡ ህዝቦች በየአካባቢያቸው ራሳቸውን የማስተዳደር፣ በቋንቋቸው የመጠቀም መብታቸው በጥብቅ እንዲከበር ከማድረጉም በላይ ህዝቦች በአካባቢዊና በጋራ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሙሉ ስልጣን እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡

ህዝቦች አካባቢያቸውን የማልማት እኩል መብት እንዲኖራቸው በመደረጉም በልማት ተሳታፊና በተሳተፉት ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለው ይኸው የፌደራላዊ ስርአት ነው፡፡ በልማት ወደኋላ የቀሩ አካባቢዎች እንኳን የማስፈፀም አቅማቸውን ለማጎልበትና የመሰረተ-ልማት አውታሮችን ለመዘርጋት የሚያስችል ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያገኙና በዚህም የተመጣጠነ የክልላዊ ልማት እንዲሰፍን ያስቻለው ይኸው ስርአት ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በአግባቡ መመለስ ስላስቻለ ነው፡፡  

የአገራችን ህዝቦች የራስን እድል በራስ ማስተዳደር እስከመገንጠል መብት  ህገመንግስታዊ ዋስትና ያገኘውም በዚሁ እና ብዝሃነት በብዙ መልኮች በሚንጸባረቅባት ሃገራችን አማራጭ የሌለው መሆኑ በተመሰከረለት ፌደራላዊ ስርአት ነው፡፡ የኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀፅ 52 ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን ድንጋጌ አስቀምጧል። በዚህም መሰረት ክልሎች ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር የማዋቀር፣ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባት፣ የፌደራሉን ህገመንግስት የመጠበቅ፣ የመከላከልና፣ ህገመንግስትና ሌሎች ህጎችን የማውጣት ስልጣን ተጎናፅፈዋል። በተጨማሪም  የፌዴራሉ መንግስት በሚያወጣው ህግ መሰረት መሬትና የተፈጥሮ ሃብት የማስተዳደር፣ ለክልሉ በተወሰነው የገቢ ምንጭ ክልል ግብርና ታክስ የመጣልና የመሰብሰብ፣ የክልሉን በጀት የማውጣትና የማስፈፀም መብቶችን ተጎናፅፈዋል።  ክልሎች በክልል ውስጥ የመሰረቱትን የመስተዳድር ሰራተኞች አስተዳደር የስራ ሁኔታዎች በተመለከተ ህግ የማውጣት፣ የማስፈፀም፣ የክልል የፖሊስ ሃይል የማደራጀትና የመምራት እንዲሁም የክልልን ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ስልጣኖች በህገመንግስቱ ዋስትና እንዲያገኝ ያስቻለውም ይኸው ስርአት ነው ።

በዚህ መሰረት ከላይ የተመለከቱት ቀርነቶች እንደተጠበቁ ሆነው በአገራችን የሚገኙ ዘጠኙም ክልሎች በህገመንግስቱ የተሰጣቸውን ስልጣን በመተግበር በማህበራዊና ኢኮኖሚ ልማት ዘርፎች፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ፈጣን ልማትና ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ ፍትሃዊ እድገት በማስመዝገብ ላይ መሆናቸው የማያስተባብሉት እውነታ ነው ።

ሁሉም ክልሎች የየራሳቸው ህግ አውጭ ምክር ቤቶች በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ የህዝብ ምክር ቤቶች ያሏቸው ሲሆን የክልሉቹ ነባራዊ ሁኔታ በፈቀደ መጠን ደግሞ የተለየ ማንነት ያላቸው ብሄረሰቦች ባሉባቸው አካባቢዎች በልዩ ዞንና በልዩ ወረዳ ደረጃ እንዲደራጁና የየራሳቸው አስተዳደር ማቋቋም የሚችሉበት ፍትሃዊና ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታ ተፈጥሯል። በአገራችን ከ1983 ወዲህ የተዘረጋው ያልተማከለው ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ክልሎች በየደረጃው የህዝቡን የነቃ ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያማከለ ፍትሃዊ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ እንዲሁም ፍትሃዊ የማህበረ-ኢኮኖሚ ስርጭትና ክፍፍል  ለማረጋገጥ አስችሎአቸዋል።

የዳር አገርነትና የገጠሬነት ስያሜ ተሰጥቶአቸው የኋላቀርነትና የድህነት ምሽግ ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩ ክልሎቻችን ያልተማከለው ፌዴራላዊ ስርአት በአገራችን እውን መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አንፃራዊ ልዩነት ቢኖርም በሁሉም አካባቢዎች ፈጣን ልማት በማረጋገጥ ላይ የሚገኙ፣ የፖለቲካና የአስተዳደር ማእከላት መሆናቸውም አያከራክርም።  

ክልሎች ያልተማከለው የፌዴራል ስርአት በፈጠረላቸው እድል ኢኮኖሚያቸው ሊያመነጭ የሚችለውን ግብርና ታክስ በመጣል ለወጪ ፍላጎታቸው ማሟሟያ የሚሆን የሃብት ግኝት በማሰባሰብ ረገድ በየአመቱ እያደገ የሚገኝ አፈፃፀም በማስመዝገብ ላይ የሚገኙ መሆኑም ይታወቃል።  

ስለሆነም አስቀድመው እና ከላይ በተመለከቱ አግባቦች ፌደራላዊ ስርአቱ የመለሳቸውን እና መመለስ የሚችላቸውን የማንነት ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ አሉባልታ በሚነዙ ሃይሎች ህብረተሰቡ ሊደናገር የማይገባው መሆኑን በሚገባ ሊያጤን ይገባል፡፡