የተሀድሶው ጥልቀት እስከየት??

የኢህአዴግ ነባር አመራሮች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተከታታይ ያደረጉትን ውይይት ህዝቡ በአንክሮ ተከታትሎታል፡፡ የመጀመሪያው በህዝቡ ውስጥ ያደገና ስር የሰደደ ብሶት፣ ምሬት መከፋት እያደገ መምጣቱን ከሰላማዊ ተቃውሞም አልፎ ለግጭት መንስኤ መሆኑን ችግሩን በተለያየ ደረጃ ሊፈታና ሊቀርፍ ይገባው የነበረው አመራር ብቁ የሃላፊነት ድርሻውን ባለመወጣቱ ሁኔታው ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ ሊደርስ መቻሉን በሰፊው አብራርተዋል፡፡ ጥልቀት ያለው ተሀድሶ እንደሚደረግም ተገልፇል፡፡ የተሀድሶው ጥልቀት እስከየት ድረስ ይራመዳል? የሚለውን ለማየት እጅጉን ጓጉቷል፡፡

ኢህአዴግ ሊያደርገው የወሰነው ተሀድሶ ስፋትና ጥልቀት እንዳለው አመራሮቹ የገለጹ ሲሆን እስከምን ድረስ ይዘልቃል? በምን መልኩስ ይካሄደል? ከቀድሞዎቹ ግዜያት የሚለይበት ባህርይውስ ምንድነው? በውስጥ ያለው የኪራይ ሰብሳቢ ሀይል ሂደቱን ለማደናቀፍ ቀድሞ ያለውን አቅም በመጠቀም እንቅፋትና መሰናክሎች ቢፈጥር መስተጓጎል አይፈጥርም ወይ?? የሚሉትን ጥያቄዎች በመደጋገም እያነሳ ይገኛሉ፡፡

አመራሮቹ ግዜ ቢወስድባቸውም የተፈጠሩትን ችግሮች በተግባር ማየታቸውን ማመናቸው ለዚህም ኢህአዴግ በከፍተኛው አመራርና በምክር ቤት ደረጃ ጉዳዩን በሰፊው መርምሮ ቁርጠኛ አቋም በመያዝ ጥልቀት ላለው ተሀድሶ በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ መጀመሩን በውይይታቸው ወቅት አስረድተዋል፡፡

ኢህአዴግ ስለሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ ችግር በተለያዩ አመታት ጉዳዩን በማንሳት ሰፊ ውይይትና ክርክር አድርጎ ችግሩን ከስሩ ነቅሎ ለመጣል ለህብረተሰቡም ጥያቄ መልስ ለመስጠት ውሳኔዎችን ቢያሳልፍም ተግባራዊ አድርጎት ወደ ስራ ሳይገባ ቆይቷል፡፡ ለምን ለሚለው ጥያቄ ውስጣዊው ችግር የጎላና የገዘፈ ሁኖ መቆየቱን ይጠቁማል፡፡

ለምን እስከዛሬ ድርጅቱ ችግሩን በጥልቀት እያወቀ እርምጃ ለመውሰድ ተሳነው? የሚለውን ጥያቄ አሁንም ድርጅቱ ሊፈትሸው፣ ሊመረምረውና ደግሞ ደጋግሞ ሊያየው ይገባዋል፡፡ ጥልቀት ያለው ተሀድሶ ሲባል ምን ማለት እንደሆነም ህዝቡ በሚገባው መልኩ ደግሞና ደጋግሞ ማብራራት፣  መንተነተን አስፈላጊ ነው፡፡

ድርጅታዊ ተሀድሶውና ጥልቀቱ እስከምን ድረስ ይሄዳል? ከኢህአዴግ መሰረታዊ መርሆዎች ከፖለቲካዊ መስመሩ ቅኝት ከትላንት ፈታኝ ሁኔታዎችና አደጋዎች ተምሮ ወደፊት ሊያስፈነጥረው የሚያስችለው መሰረታዊ የተባሉት ችግሮች የሚፈቱበት ወይንም ሊፈቱ የታቀዱበት መንገድ ምን መልክ አለው? የሚሉትን ጭብጦች ህዝቡ አበጥሮ ሊያውቃቸው ይገባል፡፡

እንደቀድሞው እዛው ሞላ እዛው ፈላ ከሆነ፣ አዲስ አቅጣጫና መንገድ የሚያስጨብጥ ካልሆነ የህዝቡን ቅሬታና ችግር መሰረታዊ መፍትሄ አያስገኝለትም የሚሉ ጥርጣሬዎች ከየአቅጣጫው ጎልተው ይሰማሉ፡፡ ከአለም የፖለቲካ  ድርጅቶች ታሪክ መማር የሚቻለው ሁሉም ነገር በነባራዊ የለውጥ ህግ ውስጥ የሚሄድና የሚመራ መሆኑን ነው፡፡ የዘመኑን ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ለውጦችና እድገቶች ተከትሎ የነበረበትን አጣጥሞ ከህዝቡም አዳጊና ተለዋጭ ፍላጎት ጋር በማጤን መራመድ ግድ ይላል፡፡ ትላንትን ብቻ እያወደሰ በአስተሳሰብ እልፍ ሳይል የተቸከለ ከሆነ ለውጥ የማምጣት አቅም አይኖረውም፡፡

በእስተሳሰብም ሆነ በእምነት ቀድሞ በነበረበት ደረጃ ሁኖ ለውጥና መሻሻልን ካልተቀበለ፣ በግትርነት ሙጥኝ ብሎ አልንቀሳቀስ ካለ፣ አዲስና የህዝቡን መሰረታዊ አዳጊ ፍላጎቶች መሰረት ያደረገ ለውጥ ለማስመዝገብ ካልበቃ ህዝቡ በአመለካከትም በአስተሳሰብም ቀድሞ ሲስፈነጠር የአደገና የዘመነ መስመርን ሲመርጥ ድርጅቱ ኋላ ይቀርና አለመጣጣም፣ አለመግባባት፣ አለመደማመጥም በሰፊው ይነግሳል፡፡ ህዝቡ የሚፈልገውንና ያለውን ሳይሆን ከህዝቡ ፍላጎትና ምርጫ ውጪ ድርጅቱ የራሱን ፍላጎትና ስሜት እያዳመጠ በራሱም መንገድ መሄድን ከመረጠ በመጨረሻው መለያየትን መፋታትን ያስከትላል፡፡ ይሄ ትልቅ እውነት ነው፡፡ በበርካታ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ ውስጥም ታይቶአል፡፡

በጥልቀታዊው ተሀድሶ ውስጥ መፈተሸና በአግባቡ መታየት ያለበት አቢይ ጉዳይ አንድም ድርጅቱ በግምገማው እንዳስቀመጠው ከህብረተሰቡ እድገት ጋር አብረው የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎችን ፈጥኖ ለመመለስ አቅሙን አስተማማኝ ማድረግ ነው፡፡

የህዝቡ ጥያቄ ኢህአዴግ ለሀገር አልሰራም፤ አልደከመም ለውጥ አላዝመዘገበም አይደለም፤ በዚህ ደጋፊውም ተቃዋሚውም አይከራከርም፡፡ ሀገራዊ ለውጦቹ እንዳሉ ሆነው በመንግስታዊ ሀላፊነት የተቀመጡ እንዲሰሩ የተመደቡ ሰዎች የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራና ሀላፊነት በመተላለፍ በስልጣን ያለአግባብ ተጠቅመዋል፤ ከብረዋል፤ መልካም አስተዳደርና ፍትህን ረግጠዋል፤ አድልዎና መድልዎ ፈጽመዋል፤ ህዝብ እንደ መረጣቸው ዘንግተው በህዝብ ላይ ምሬትን ያስከተለ በደል ፈጽመዋል የሚል ነው፡፡

በተለያየ የኢህአዴግ አመራርና ሀላፊነት ከላይ እስከታች ድረስ ያሉት የህዝብና የመንግስትን ሀብት እንደግል ንብረታቸው በመቁጠር ያሻንን ብናደርግ ጠያቂ የለንም ወደሚል ትምክህት ደረጃ ለአመታት ተረማምደዋል፤ አይነኬዎች ነን የሚል መታበይን ለአመታት ገንብተዋል፡፡

በውስጥ ያለው ኪራይ ሰብሳቢ፣ ሙሰኛ፣ ጥገኛ ሀይልና ስብስብ በውጭ ካለው ደላላ ጋር በመቀናጀት በመንግስትና በህዝብ ሀብት ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል ዘረፋ መካሄዱ በመሬት ዘረፋና ቅርምት፣ በግንባታ፣ በኮንስትራክሽን፣ በቤት ልማት ዘርፍ ወዘተ የህዝብን ተቃውሞና ቁጣ ቀስቅሶአል፡፡ ለህዝብ ይሰራሉ ተብለው በሀላፊነት የተቀመጡት ሰዎች አደራቸውን ረግጠው በህዝቡ ላይ ሰርተውበታል የሚሉ ምሬቶች ሁሉ ይደመጣሉ፡፡

የእኛው ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር የቀድሞዋን ሶቪየት ህብረት ለውድቀት አሳልፎ የሰጣት፡፡ ኮምኒስቶቹ መሪዎች በረዥም ግዜ ሂደት ወደሀገር ሀብት ዘረፋና ምዝበራ ሆ ብለው ገቡበት፡፡ ቤተሰባቸውን፣ ጎሳቸውን፣ ወዳጆቻቸውንና ልጆቻቸውን ሳይቀር በሀብትና በክብረት ማማ ላይ አነገሱዋቸው፤ መሰረታዊውን የፓርቲውን መርህ ደረመሱት፤ በልተን፣ ዘርፈን እንኑር ባይ ሆኑ፤ ከእኛ በላይ ሰው የለም በሚል ድውይ አስተሳሰብ ተመጻደቁ፤ ግዙፉ ፓርቲ እንደግለሰቦቹ ሁሉ አርጅቶ አፍጅቶም ነበር፡፡ እርምት ለውጥ ተሀድሶ አላደረገም፡፡ በግዜ ሂደት እየተሸረሸረ ሄደ፡፡ ከብሬዥኔቭ ሞት በኋላ ተተኪ የሆኑት አራት አዛውንቶች ፕሬዚደንት ለመሆን ቢበቁም ተራ በተራ በጥቂት አመታት ውስጥ በሞት አሸለቡ፡፡ በመጨረሻ የተተኩት ሚካኤል ጎርቫቾብ ግላስኖስትና ፕሬስቶሪካ የሚባል ኮምኒስት ፓርቲውንም አጠቃላይ መዋቅሩንና መንግስታዊ አሰራሩን የሚለውጥ ተሀድሶ ተግባራዊ አደረጉ፡፡ ይህም የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ አልቻለም፡፡ ታላቅዋ ሶቪየት ህብረት ፈራረሰች።

የሶቪየት ህብረትን መውደቅ ለረዥም ግዜ ሲጠብቁት የነበሩት የውጭ ሀይሎች አጋጣሚውን ተጠቅመው የቤት ስራቸውን ሰሩ፡፡ በግዛትዋ የነበሩ ሀገራት ተገንጥለው ወጡ፡፡ ቦሪስ የልሲንም በቅጡ ሊመሩት አልቻሉም፡፡ የሩሲያ ህዝብ ሀገሩን ለመታደግ ታላቅ ዋጋ ከፈለ፡፡ በመጨረሻ አንድ ጥሩ ተግባር ፈጸሙ፡፡

ቦሪስ የልሲን የአሁኑን መሪ ብላድሚር ፑቲንን ለስልጣን አበቁ፡፡ ሩሲያ በፑቲን መሪነት ከወደቀችብት ተነሳች፡፡ በአለም የነበራትን የተሰሚነት ክብር ዳግም ተጎናጸፈች፡፡ የቀድሞው ውድቀትዋ ዋናው መንስኤ የፓርቲው መሪዎች በከፍተኛ ደረጃ በሙስና፣ በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በመልካም አስተዳደርና በፍትህ እጦት ችግር ህዝቡን ይህ ነው በማይባል ሁኔታ አስመርረውት ስለነበር ነው፡፡

የህዝቡ መብት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የተረገጠበት፣ ባለስልጣናት የፓርቲው መሪዎች የመንግስት ሹሞች ዲሞክራሲን አፍነው ረግጠው በአምባገነንነት መግዛት መጀመራቸው ሁሉ የውድቀታቸው የመጀመሪያ መንደርደሪያ ነበር፡፡ በኋላም የሚሆነው ሁሉ ሆነ፡፡

አንድ ፓርቲ ዛላቂና ቋሚ በሆነ የእርምትና የተሀድሶ ሂደት ውስጥ ሀገራዊ ሁኔታዎችን ከባቢያዊና አለምአቀፍ ሁኔታዎችን እለት በእለት እየገመገመና እየተነተነ፣ የህዝቡን ትክክለኛ ስሜት እየፈተሸ፣ ወቅቱን የሚመጥን አመራር እየሰጠ መራመድ ካልቻለ ያለጥርጥር ይወድቃል፤ ፓርቲም እንደ ሰው ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ይጎለምሳል፤ ያረጃል፤ ይሞታልም፡፡

የትላንት ተጋድሎን፣ የትላንት መስዋእትነትን፣ ድል አድራጊነትን በማግነን፣ የቀደሙትን ብቻ በመኮነን ከእኛ የተሻለ ከእኛ የበለጠ ለዚህች ሀገር የሰራ የለም የሚለውን  ሁሌም አታካች ውዳሴ ማሰማት የአላዋቂዎች ድርጊት ነው፡፡ የእድገት ህግንም ታሪክንም ይጻረራል፡፡ ሀገርና ትውልድ በቅብብሎሽ ውስጥ የሚያልፉ ናቸው፡፡ ያረጀው በአዲሱ በወጣቱ እየተተካ ይሄዳል፡፡

ያለው መስራት ካቃተው የተሻለ ሊሰራ፣ ሊያደርግ የሚችል ደግሞ ሀገር ትፈጥራለች፡፡ ተወደደም ተጠላ እውነቱ ይሄ ነው፡፡ አመራሩ ብቻ አይደለም አባላቱም በህዝብ አገልጋይነት እምነት በሚገባ ተሞርደው የተቀረጹ አለመሆናቸውም በአደባባይ እየታየ ነው፡፡ ለዚህ ነው የተሀድሶው ጥልቀት በነበሩት ብቻ ቢካሄድ አዲስ አስተሳሰብና አዲስ የመስራት ጉልበትን እስካልጨመረ ድረስ ብዙም ርቀት ሊራመድ አይችልም የሚል አስተያየት የሚደመጠው፡፡

በውዳሴ ከንቱ የሚባክን ግዜ በተለይም ከእኛ በላይ የሚለው ኋላቀር እሳቤ ያላቸው ወገኖች የሽረት ሽረት ህግ እንዳለ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ ያረጀው አስተሳሰብ ሲሞት ከውስጡ አዲስና የተሻለ እምነትና አስተሳሰብ እንደሚወለድ ወይም በሌላ አዲስ ሊተካ እንደሚችል መረዳትና ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ እንዲያውም የዲያሌክቲክስን ህግ ዛሬ ምን ያህሉ ሰው እንደሚያውቀው ባይታወቅም  የውስጥ ፍጭትና ትግል ሲፋፋም በመሀል አዲስ ለውጥ፣ አዲስ እድገት ይመጣል፤ ይወለዳል ነው የሚለው፡፡ ዛሬ ከጥቂቶች በስተቀር ምን ያህሉ በስልጣን ወንበር የተቀመጠው ተተኪ ይህንን ማህበራዊ ሳይንስ የቀደሙ ሀገራትን የህዝብ ትግልና ተሞክሮ የሚከሰቱ ቅራኔዎችን ደረጃቸውን አያያዝና አፈታቱን ወዘተ አንጥሮና አበጥሮ እንደሚያውቅ ለመናገር ያስቸግራል፡፡

አንድ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ፓርቲ የሚሞተው መንገዱን ስቶ ሲሄድ፣ መለወጥና መታደስ ሲያቅተው፣ አመራሩ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት፣ በጥቅም አጋባሽነት ውስጥ ገብቶ ሲርመጠመጥና የህዝብን አደራ የሚበላ ሲሆን ነው፡፡ በዚህ ግዜ ከህዝብ ጋር መላተምና መጋጨት ውስጥ ይገባል፡፡ ቀዳዳውን ክፍተቱን ለመጠቀም አጋጣሚ ሲጠብቁ የነበሩ ክፍሎች መነሻቸው ትክክል ይሁንም አይሁን ይሄንን አይነቱን ወርቃማ ብለው የሚጠሩትን ሁኔታ ለመጠቀም የሀይል ሚዛኑን ወደራሳቸው ለማዞር ይሰራሉ ማለት ነው፤ ይህ በብዙ ሀገራትም ታያቶአል፡፡ ለዚህ ነው ስርነቀል የሆነ ጥልቀት ያለው ተሀድሶና ለውጥ ለኢህአዴግም መሰረታዊና አስፈላጊ ሁኖ የተገኘው፡፡

ታግለን ከባድ የትውልድ መስዋእትነት ከፍለናል በደማችን ነጸነት አምጥተናል ለሚሉትም ማስተዛዘኛ አይሆንም፡፡ የታገሉት፣ የትውልድ መስዋእትነት የከፈሉት፣ የደሙትና የቆሰሉት ለሀገርና ለህዝብ ነጻነት ከሆነ በግላቸውና በቡድን እየተደራጁ የተሰጣቸውን የህዝብና የመንግስት ሀላፊነትና አደራን በመተላለፍ መዝረፍ፣ መመዝበር፣ ህዝብን ማስመረር ውስጥ ሊገቡአይገባቸውም ነበር፤ ስልጣንም ሆነ ሀብት ዘላለማዊ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡

እንደዚህ የሚያስቡ ካሉ የኢትዮጵያን ህዝብም ሆነ ውስብስብ የሆነውን የመንግስትነት ታሪክ የማያውቁ፣ ከእውቀት ላይታረቁ የተፋቱ ናቸው ማለት ነው፡፡ እንደነዚህ አይነት ግለሰቦች በኢህአዴግ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ አሉ፤ ይኖራሉም፡፡ የህዝብና የሀገር ጥቅም እስከተነካ ድረስ የድርጅት አባል መሆን ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ መሸሸጊያ ሊሆናቸውም አይችልም፡፡ ነገ መጠየቅም ሕዝብ ፊት መቆምም ይመጣል፡፡ ዘመንም ግዜም እንደዚህ ነው፡፡ ከህግ ተጠያቂነትም ማምለጥ አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ተሀድሶው በእርግጥ ተሀድሶ ከሆነ ጥልቀት ያለው ፍተሻ ማድረግ አለበት የሚባለው፡፡ ተሸካክመን እንወጣለን ተሸፋፍነንም እናመልጣለን ማን ማንን ይነካል የሚለው አስተሳሰብ ሲተሻሽ ሲብላላ ቆይቶ ደፍሮ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ነው የህዝቡ ተቃውሞና ቁጣ ገንፍሎ በየአካባቢው የወጣው፡፡ አሁንም ተሀድሶው ጥልቅና ስርነቀል ካልሆነ የህዝቡን አመኔታ ለማግኘት ይከብዳል፡፡

ስህተታችንን ገምግመናል፤ እናርማለን፤ እንለውጣለን ሲባል እነዚህ ሰዎች ለሀገር ሰርተዋል፤ ተጨባጭ ለውጥ አሳይተዋል፤ በተደጋጋሚ አመታትም ግዜ ሰጥተን እንመልከታቸው በሚል ሲታገስ የኖረው ህዝብ በደሉን በደሉ አድርጎ ይዞ የቆየ ቢሆንም መሰረታዊ ለውጥ ልናመጣ ካልቻልን ከዚህ በላይ ሊታገሰን አይችልም ሲል ራሱ የኢህአዴግ ግምገማ በተጨባጭ አሳይቷል፡፡ በሰፊውና በዝርዝር በጥልቀትም በመረጃም አስደግፎ አቅርቦታል፡፡ ጠልቆ ያውቀዋል፡፡ የሚነገረው አዲስ ነገር እንደሌለ ይረዳል፡፡ አሁን ህዝቡ የሚጠብቀው በፍጥነት የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ ወደ ማሳየቱ ተግባር እንዲገባ ብቻ ነው፡፡

ድርጅቱ ራሱን ከጎጥና ከጎሳ አመለካከት፣ ከከፋ ጠባብነትና መንደርተኛ አስተሳሰብ ሁሉንም እኛ ብቻ እንያዘው ከሚል ስግብግብነት ህዝብን ሀገሬ አይደለም ወይ? እስኪል ድረስ ካንገፈገፈው በሽታ ከትምክህትና አውዳሚ አስተሳሰብ አላቆ ስልጣን በጎጥና በጎሳ የኮታ ምደባ ሳይሆን በብቃት፣ በችሎታ፣ ልምድ ባካበቱና ብዙ ሊሰሩ የሚችሉ ዜጎችን በማቀፍና በማካተት፣ በማሳተፍ ቢሰራበት የተሻለ ለውጥ ማስመዝገብ ይቻላል፡፡ የተሀድሶው ጥልቀት እስከየት ድረስ ይዘልቃል? የሚለው የህዝብ ጥያቄ ተጨባጭ ተግባራዊ ምላሽን ይጠብቃል፡፡