በጥላቻ ያደገም ሆነበጩኸት የፈረሰ አገር የለም !!

በአማራና ኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ዕውቅና የሌላቸው ሠልፎች ሲካሄዱ የቆዩና እነኚህም ሠልፎች ባለቤት ያልነበራቸው፣ በዋናነት በማህበራዊ ሚዲያዎች አስተባባሪነት ከሀገር ውጪ በሚገኙ አካላት ይመሩ የነበሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሠልፎቹ ጥቂት የማይባል የማህበረሰብ ክፍል የተሳተፈባቸው፣ በዘረኝነት ቅስቀሳ የታጀቡ፣ በረብሻና በሁከት የተሞሉ የመሆናቸው ሚስጥር በአንድ በኩል፤ በሰልፎቹ ላይ የተላለፉ መልዕክቶች ህገመንግስታዊ ስርዓቱን የሚኮንኑ፣ የፌዴራል ስርዓቱን የሚያወግዙ መሆናቸው ደግሞ በሌላ በኩል ስለሃገሪቱ የህዳሴ ጉዞ ስለሚያስፈልገን ሰላም ሲባል የዚህ ጽሁፍ አጀንዳ ነው፡፡

ይህንን አጀንዳ ወሳኝ ስለሆነው ሰላማችን ስናነሳ መካድ የሌለባቸውና ወደፊትም ትኩረት ተሰጥቷቸው ካልተፈቱ የብጥብጥ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮች መኖራቸውን በመካድ ሳይሆን ይልቁንም አስምረንበት በማለፍ ነው። የመጀመሪያውና የቅሬታ መነሻ በመሆን በቶሎ ካልተፈታ አደጋ ሊፈጥር የሚችል መሆኑ ይልቁንም ከላይ በተመለከቱት ቦታዎች ላይ የሁከት አጀንዳዎች ሽፋን በመሆን ማገልገሉ በማይተባበል መልኩ የተስተዋለውና ሊሰመርበት የሚገባው  ነጥብ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው። ይህን ችግር ለመፍታትና ቅሬታን ለማቅረብ የሚያስችል ሁኔታ ያለ ቢሆንም፣ በሰልፎቹ የተስተናገዱት ሃሳቦችና መፈክሮች ናቸው አጀንዳውን አንስተን በጥልቀት እንሟገትበት ዘንዳ ምክንያት የሆነን ፡፡

ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዙትን በሌላና የዚህ ተከታይ በሆነ አጀንዳ የምንመለከተው ሆኖ ስለዚህ አጀንዳችን ግን በእነዚህና በዋናነት የመልካም  አስተዳደር ችግሮችን ሽፋን ባደረጉት ሰልፎች የተንጸባረቁ መፈክሮች በይፋ እንደተስተዋሉት ህገ መንግስታዊ ስርዓትን በኃይል የማፍረስ ተልዕኮ ያነገቡ መሆናቸው የሙግታችን የመጀመሪያና ቁልፍ መነሻ ነው፡፡ ተልእኮውን ለማሳካት ሲደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎችም የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት የሚጎዱ መሆናቸው በተጨባጭ ማሳያዎች የተረጋገጠ መሆኑም ተከታዩ እና ግን ደግሞ ተያያዥ የሆነው ቁልፍ መነሻ ነው፡፡

አንዱን ህዝብ በሌላው ላይ የማነሳሳት ስራ የተካሄደባቸው የመሆኑ ነገር ደግሞ ስለቀጣይቱ ሃገርና ህዝብ ጉዳዩን ከፌደራላዊ ስርአቱ የአዋጭነት መለኪያዎች አንጻር እንድንፈትሸው ግድ የሚለን መነሻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሀገራቸው ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውና እኩልነታቸው መረጋገጡ በመላ ሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር ሰላምን ከማስፈኑም ባሻገር ለአዲስ ኢትዮጵያዊነት ግንባታ መሰረት የመጣሉን እውነታ የሚቀበል ህብረተሰብ ቀድሞ ነገር የሚኖረውን አጀንዳና ቅሬታዎች ሁሉ በዚሁ ማእቀፍ ስር ሊያጤነው ግድ ይለዋል፡፡

ስለምን? ቢሉ ደግሞ  በፌደራላዊ ስርአቱ መልስ ያገኘውን የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርን እና የማስከበሪያ ስርአቶች መዘርጋታቸውን (የመናገርና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የመሳሰሉቱ) የዘነጉትና ይልቁንም የኢትዮጵያ ህዝብን ግንዛቤ የሌለው አድርገው በወሰዱት ንቀት የተሞሉት የቀደመው ስርአት አቀንቃኞች (ሊያውም ውጭ ሆነው ሳይሆን እዚሁ በህዝብ ጉያ ውስጥ ሆነው) ኢ-ዴሞክራሲያዊ ቅስቀሳቸውን ለዴሞክራሲያዊ ፕሬስ ቦታ እስኪጠብ ድረስ ያጧጧፉትና መድረኩን በጩኸት የሞሉት የነበረ ቢሆንም  የሚፈልጉትን ሰሚ ጆሮ ያላገኙ መሆናቸው በሚታወቅበት አግባብ ከውጭ ሆነው በፌስ ቡክ ትእዛዝ የሚሰጡ ሃይሎችን ስብከት ጥቂቶች ቢሰሙትም የትም መድረስ የማይቻላቸው መሆኑ ይታወቃልና ፡፡

ከሰሞኑ ሁከቶች በስተጀርባ ማጤን የሚቻለው አንድ ነገር የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 የተደነገገውን እና የፌደራላዊ ስርአቱ አማራጭ የለሽነት ሁነኛ ማሳያ የሆነውን  የፕሬስ ነፃነት የአፈና ስርዓታቸውን ለመመለስ የተጠቀሙበት መሆኑና፤ ግን ደግሞ ለሁከቱም መነሻችን ነው የሚሉትን ዴሞክራሲያዊ ስርአት ማን እያፈነና ማን እያስከበረ የመሆኑን እውነታ ነው፡፡ ፌደራላዊ ስርአቱ ተግባር ላይ በዋለ እና ቅሬታዎች መስተናገድ የሚችሉባቸው ዴሞክራሲያዊ ስርአቶች በተበጁ  ማግስት የተደረጉ ጥናቶች እንዳረጋገጡት  በሀገሪቱ እንደ አሸን ከፈሉት የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች አብዛኛዎቹ የደርግ የፕሮፖጋንዳ ሰራተኞች በነበሩ የኢሰፓ አባላትና ወታደራዊ መኮንኖች ባለቤትነት ያለበለዚያም በትምክህት ኃይሎች ቀጥታ ፋይናንስ የሚደረጉ ናቸው።

ይሁንና መሰረታዊ መብቶቹ የተረጋገጡለት ሕዝብ መሃል ሆነው ምንም መፍጠር ያልቻሉ መሆናቸውንም የፌስ ቡክ አዝማቾቹም ሆኑ ይልቁንም ዘማቾቹ ሊገነዘቡና ከላይ ለተመለከቱት አይነት ችግሮችም በዚሁ ማእቀፍ ውስጥ ሆነው ቅሬታ ሊያሰሙ በተገባ ነበር፡፡ ያለፈው ቢያልፍም ከሁከቱ በስተጀርባ የነበረውን ትርፍና ኪሳራ በማስላት ወደፊትን በዚህ አግባብ መቃኘት ለራስም ሆነ ለሃገር ጠቃሚነቱ አያከራክርም።

ውጤቱ ጥፋት ቢሆንም የሰሞኑ ሁከት ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግስት የት እንደነበሩ አሳይቷል፤ ይልቁንም ከዚህ መማርና ሁሌም ሊዘነጉት እንደማይገባ አመላካች መሆኑም ታይቷል። ይኸውም በፌደራላዊ ስርአቱ የተገኘው ሰላምና መረጋጋት በተለይም የመሪ ድርጅቱ ህዝባዊ መሰረት የሆነው አርሶ አደሩ ዕርካታ የመንግስትን ስልጣን የተቆጣጠረው መሪ ድርጅት ባለበት እንዲያንጎላጅ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑ ነው፡፡ ይህም የመሬት ጥያቄው በብቃት የተመለሱለት አርሶ አደርን ጨምሮ ዴሞክራሲያዊ መብቱ በህግ የተጠበቁለት ሕዝብ ለአመታት ጎትጓችና ቀስቃሽ ሆኖ አለመገኘቱ እና ሲብስበት ከጥፋት  ሃይሎቹ አጀንዳ ጋር ተቀላቅሎ መገንፈሉ መሪው ድርጅት ወደፊት ያለመንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን ባለበት ተኝቶ  የነበረ መሆኑ የተረጋገጠ ሃቅ ነው፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖና ገዢው ፓርቲ በሚገባ ሊያጤነው እንደሚችል ገምተን፤ በሕገ-መንግስቱ መግቢያ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በሀገራቸው ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ማህበራዊ ዕድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነፃ ፍላጎታቸው በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውንና መተማመናቸውን የገለፁበት የቃል ኪዳናቸው ሰነድ ከመሆኑ በተቃርኖ ተሰልፎ ወደኋላ የሚመልሱን መሆናቸው በማያጠያይቁ አጀንዳዎች መጠለፍ ብሄራዊ ስብእናን ማራከስ መሆኑ ላይ በተለይ ዘማች የነበረው ክፍል ሊያንሰላስለው እና በውጤቱም እራሱን ሊገስጽ መገባቱ ሃገር ወዳድ ነኝ እስካለ ድረስ አያከራክርም፡፡

ምክንያቱም የፌደራላዊ ስርአቱን መነሻና መድረሻ አድርገው የተቀረጹት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የከተማና ገጠር ትስስርን ለማቀላጠፍ ያስቻሉ መሆናቸው መታወቁ የመጀመሪያው እና ዘማቾቹ ሂሳብ ሊያወራርዱ የሚያስችላቸው ግብአት ነው።

በየክልሎቹ የሚከናወነው የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ፈጣንና በየደረጃው ህዝብ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሆነ ልማት በማረጋገጥ ደረጃ የራሱን በጎ አስተዋፅኦ ማድረጉም ከፌደራላዊ ስርአቱ ተቃርኖ ተሰልፈው የተሰሙትን መፈክሮችና ያሰሙ ሃይሎችን ሂሳብ ለማስላት ያስችላል። መጠንና ጥልቀቱ መሪ ድርጅቱም ሆነ መንግስት ከላይ በተመለከተው አግባብ ከመተኛታቸው ጋር ተያይዞ በህዝቡ ፍላጎት ልክ ባይሆንም በገጠር ሁሉን አቀፍ የመንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም /URRAP/ መሰረት ወረዳን ከወረዳ፣ ቀበሌን ከወረዳና፣ ወረዳን ከዞን ማእከላት የሚያስተሳስሩ የገጠር መንገዶች ግንባታ ተከናውነው ከዚህ በፊት ከልማት ተገልለው የቆዩና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ተዳርገው የቆዩ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና የታዳጊ ክልሎች ተወላጅ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከልማቱ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባስቻለው ፌደራላዊ ስርአት ላይ ከላይ በተመለከተው አግባብ መደራደር እንደገና ዳገት ለመግፋት እንደመዘጋጀት ካልሆነ ሌላ ትርፍ የሌለው መሆኑም በምንምና በማናቸውም መመዘኛ ሊረጋገጥ የሚችል ሃቅ ነው።

አሁንም ከላይ በተመለከተው እና የገዢው ፓርቲ ምክር ቤት ባደረገው ግምገማ እንዳረጋገጠው መተኛቱም ሆነ ማንጎላጀቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ይብዛም ይነስ ግን መንግስት ለመሰረተ ልማት ግንባታና መስፋፋት በሰጠው ልዩ ትኩረት በየክልሎች በሚገኙ  የከተማና የገጠር አካባቢዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የኤለክተሪክ፣ የቴሌኮም፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በስፋት በመዘርጋት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ተመጣጣኝና ተቀራራቢ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ያስቻለው ፌደራላዊ ስርአት ላይ ከላይ በተመለከተው አግባብ መዘባበት ሃገሬን እወዳለሁ የሚለውን ሁሉ ቢያስቆጨው እና ቢጸጽተው እንጂ ከዚያ ውጭ የሆኑ እይታዎችና ምልከታዎች ሁሉ ጤናማ ሊሆኑ አይችሉም። ይህ የመጣው ደግሞ ያለፉ ኢፍትሃዊ መንግስታት  በገጠርና በከተማ፣ በሴቶችና በወንዶች፣ በአርብቶ አድር እና በአራሹ መካከል የፈጠሯቸውን ኢፍትሃዊና የተዛባ የልማት ስርጭት ችግሮችን ለማመጣጠንና ለማቀራረብ እንዲያስችል ሆኖ ተግባር ላይ በዋለው ፌደራላዊ ስርአትና በፌደራላዊ ስርአቱ ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ መንግስት በወሰዳቸው ሁሉን አቀፍ እርምጃዎች እንጂ በሌላ አለመሆኑንም ማጤን ሃገሬ ከሚለው ሁሉ የሚጠበቅ ነው።

ለዘመናት አገዛዞቹ ሲከተሉት በቆየው ኢፍትሃዊ የሃብት ድልድልና ፀረ ልማት አቅጣጫ የተነሳ ለተደራራቢና ውስብስብ ችግር የተጋለጡት የአገራችን ከተሞች ከጉስቁልናና እርጅና ወጥተው መታደስ የጀመሩት፣ ይልቁንም ሁሉም የከተማ ነዋሪዎች በገቢውና በአቅሙ ልክ እንደዜጋ በእኩልነትና በፍትሃዊነት ተጠቃሚ መሆን የጀመሩት አሁን ባለው ፌደራላዊ ስርአት ነው።

መንግስት እጅግ የተጋነነ ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረውን የከተማውን ህዝብ የአኗኗርና የመጠለያ ችግርች ስርነቀል በሆነ ልማታዊ አቅጣጫ በመንደፍ ነዋሪው በአደጉ አገሮች ደረጃ እውን ሊሆኑ የሚችሉ ብቻ አድርጎ ሲማልልባቸውና ሲመኛቸው የነበሩትን ደረጃቸውን የጠበቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶችንና አውራ መንገዶችን በመገንባት ህዝቡን የቤት ባለቤት፣ የዘመናዊ መሰረተ ልማት ተጠቃሚና ተቋዳሽ ለማድረግ የቻለው የፌደራላዊ ስርአቱ ምንጭ በሆናቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተመርቶ እንጂ በውጭ ሃይሎች ትእዛዝና እጅ ጥምዘዛ ተንበርክኮ አይደለም።

መንግስት በከተማ በሚኖረው ህዝብ የነቃ ተሳትፎና የባለቤትነት ስሜት እየታገዘ   በከተሞች ለስራ አጥነት ተጋልጦ የኖረውን ሰፊውን የወጣት ሃይል በየአካባቢው በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪ ልማት ተደራጅቶ በእንጨትና ብረታብረት ስራ፣ በምግብና ሸቀጣሸቀጥ በእደ ጥበብና ሽመና ወዘተ ተሰማርቶ ራሱንና ቤተሰቦቹን ኑሮ እንዲለውጥና እንዲያሻሽል በማድረግ ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻለው በእርሱ ብቃት ብቻ ሳይሆን ፌደራላዊ ስርአቱ ይህንን ለማድረግ ሁነኛ መደላድል ስለሆነለት ነው። 

ስለሆነም ከሰሞንኞቹ ሁከቶች በስተጀርባ የሚገኙትና ስልጣንን ከሃገርና ህዝብ የሚያስበልጡ ሃይሎች በውስጥና በውጭ ሆነው ኢህአዴግና እሱ የሚመራው መንግስት በከተሞች ለአመታት ሳይሰራና መፍትሄ ሳያገኙ ተከማምረው የሰነበቱትንና ካለፉት ጨቋኝ ስርአቶች የወረሷቸውን የመጠለያ ቤት እጦትና የስራ አጥነት ችግሮችን ለመቅረፍ፣ በከተሞች መሰረተ ልማት ለማስፋፋት የሚያደርጋቸውን ጥረቶች እየተከታተሉ መንቀፍና ማውገዝ የለት ተለት ስራቸው መሆኑን አውቆ እነርሱም እንኳ ወደስልጣን ቢመጡ የማይደራደሩበትን እና አማራጭ የሌለውን ፌደራላዊ ስርአት መጠበቅና ግን ደግሞ በስርአቱ ውስጥ ተሸፍነው ህዝብ የሚያስለቅሱ ሃይሎችን ስርአቱ በፈጠረው አግባብ መታገል ተገቢ ይሆናል።

የአገራችን ወጣት ልማታዊ መንግስቱ ያመቻቸለትን እድል ተጠቅሞ ራሱንና ቤተሰቦቹን ለመለወጥ፣ እሴት ለመፍጠርና በቀጣይ የራሱን የስራ መስክ ከፍቶ ለማደግ ያለውን ጉጉትና የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ከማበረታታና ከመደገፍ ይልቅ ወጣቱን ድጋይ ፈላጭና ቀለም ቀቢ አደረጉት በማለት የወጣቱን የስራ ተነሳሽነት ለማዳከምና ለመድፈቅ የሚተጉ ሃይሎችም ጀርባቸው የስልጣን ጥም መሆኑን አውቆ ለፌደራላዊ ስርአቱ ዘብ መቆምና በዝባዦችን ደግሞ ስርአቱ በዘረጋው ህጋዊና ሰላማዊ አግባቦች ሊታገል ይገባል።