በልማት ስም …!!

ህዝብ ሀገሩ እንዲለማ፤ እንዲያድግ ይፈልጋል፡፡ መንግስትም ሀገሪትዋን ለማልማትና ለማሳደግ ሰፊ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በበርካታ መስኮች በተለይም በመሰረት ልማት፣ በመንገድ፣ በባቡር፣ በመኖሪያ ቤት፣ በትላልቅ ግድቦች ግንባታ፣ በትምህርት፣ በጤናና በመሳሰሉት ይህ ቀረው የማይባል ስራ ተሰርቶአል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በልማት ስምና ሽፋን ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ሀይል ርህራሄ የለሽ ዘረፋን አካሂዶበታል፤ በልማት ስም መነገድ፣ መዝረፍ የዘመኑ ፋሽን እስኪመስል ድረስ፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠር የሀገር ሀብት በግለሰቦች ትብብር የሚዘረፍበት፣ ፕሮጀክቶች ያለህጋዊ ጨረታ የሚሰጡበት፣  በታቀደው ግዜ የማያልቁበትና ሌላ ሚሊዮን ብሮች የሚጠየቅበት፤ በጥቅሉ በአሁኑ ዘመን፣ በሀገርና በህዝብ የሚቀለድበት፣ አይን ያወጣ ዘረፋ የሚካሄድበት ሁኔታ በግልፅ እየታየ ነው፡፡

በቅርቡ አቶ በረከት ስምኦን ባደረጉት ንግግር የእኛ ሌቦች ውጭ ካሉት ሌቦች ጋር በመተባበር የፈፀሙት ድርጊት ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ አያስችላቸውም ነበር ያሉት፡፡ መንግስት ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የሚሰራውን ያህል ልማቱን ሽፋን በማድረግ ኪራይ ሰብሳቢው፣ ሙሰኛውና ጥገኛው ሀይል ስልጣን ላይ ያሉ ሹማምንትን በመጠቀም የሚካሄደው አይን ያወጣ ዘረፋና ቅርምት ነው አንዱም የህዝብን ተቃውሞና ቁጣ የቀሰቀሰው፡፡

መሬት ቅርምቱ  ከባለስልጣናት  ጋር በጎሳ ወይም በጥቅም ቁርኝት በተሞዳሞዱ ሀብታሞችና  ስልጣን ላይ በተቀመጡ ማዘዝ በሚችሉ ፈጻሚና አስፈጻሚዎች አማካኝነት ሲፈጸም የኖረው ህገወጥ ድርጊት እንደ ህጋዊና ተገቢ ስራ ተቆጥሮ ሲሰራበት ህዝብን ያደማ፣ ያስነባ ተግባር ሆኖ ቆይቶአል፡፡

በልማት ስም ደሀውን ማፈናቀል፣ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ስም የሚካሄደው አይን ያወጣ ዘረፋና ውንብድና፣ ለግንባታው ጭራሽ ያልተጫረቱ ሰዎች ያለጥራትና ብቃት በኔትወርክ የጥቅም ትስስር ግንባታ ውስጥ በስፋት ተሰማርተው መገኘታቸው በየፕሮጀክቶቹ በዘመድ አዝማድና በወንዝ ልጅነት በመሰባሰብ ሲካሄድ የነበረውን ዘረፋ የተመለከተው ህዝብ የከፋ ቁስል ሁኖበት ከፍተኛ ምሬት ካስከተሉት መንግስታዊ አመራርና የአስተዳደር ችግር ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡

ስግብግብና በቃኝ የማይለው ኪራይ ሰብሳቢውና ዘራፊው ሀይል ይህን ሁሉ በደል በህዝብና በሀገር ላይ ሲፈጽም የሚጠቀመው መጫወቻ ካርዱ በመንግስትና በኢህአዴግ ስም ነው፡፡

የግለሰቦች ቤትና ነባር ይዞታ ቁልፍ ለንግድ የሚያመች ቦታ ላይ ካለ ኪራይ ሰብሳቢው የጥቅም ተጋሪ በሆኑት መሀንዲሶች አማካኝነት በመንግስት ማህተም ወደ ካሳና ምትክ መርተነዋል የሚል ደብዳቤ ሰጥተው የተመኙትን ይፈጽማሉ፤ ለግለሰቦቹ ትንሽ ካሳ ይሰጣል፡፡ እነሱ ከጀርባ ለባለሀብቱ በኢንቨስተርና በኢንቨስትመንት ስም ትንሽ የይስሙላ ጨረታ ያወጡና ቀድሞ ላዘጋጁት ሰው ህጋዊ ካርታና የይዞታ ማረጋገጫ ሰጥተው ይሸጡለታል፡፡ አካባቢው እንዲፈርስም ይደረጋል፡፡ እንዲህ በአደባባይ በህግና በመንግስት ስም የለየለት ወንጀል እየተሰራ ሀገርና ህዝብ መቀለጃና መጫወቻ ሲሆን ኢህአዴግ የት ነበርክ? ቢባል መልስ የለውም፡፡ ለምን? ቢሉ ስራውን የሚሰሩት በውስጡ ያሉና በስሙ የሚነግዱ ጉዶች ናቸውና፡፡

ህዝብ ምን አደረገ ምንስ በደለ ምንስ አድርጉልኝ አለ? ቢበዛበት ነው ተቃውሞውን ይዞ አደባባይ የወጣው፡፡ ፍትህ ስጡኝ ወይ ግደሉኝ ቢል ምን ይፈረድበታል፡፡ ዘራፊዎች ሀሳባቸውን ለመተግበር እንቅፋት የሆናቸውን ሰው በመንግስት መስሪያ ቤት ይሁን በግል ወይም የትም ይሁን የት መረባቸውን በመጠቀም የበቀል እርምጃቸውን ይወስዳሉ፡፡ ከስራ ያፈናቅላሉ፤ ያስራሉ ወዘተ.፡፡

በዘረፋና በሙስና መረብ የተቆላለፈው የታችኛውና የላይኛው ,አካል በክፍለ ከተማ ያሉ መሀንዲሶች ጭምር አዲስ ካርታ እየነደፉ እያወጡ አካባቢው ፈራሽ ነው ወደካሳና ምትክ ተመርቶአል በሚል ከማስተር ፕላኑም ውጪ በሆነ ሁኔታ በዜጎች ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል በደል በመንግስት ስም ሲፈፀም ቆይቷል፡፡ በከተሞች ማደግና መስፋፋት ስም አስከፊ ወንጀሎችና ታላላቅ ሀገራዊ ምዝበራዎች መፈጸማቸውን ህዝብ ሳያቋርጥ ይናገራል፡፡ ኢህአዴግ በጥልቅ ተሀድሶው ይሄንንም  በሚገባ ሊመረምረው ይገባል፡፡

በዚህ መልኩ በማስተር ፕላኖቹ ላይ ህዝቡ የከረረ ተቃውሞውን ቢያሰማ አመራሮቹ በፈጠሩት አስከፊ ተግባር ምክንያት እንጂ የህዝብ ችግር አይደለም፡፡ ጥቂት ግለሰቦችን የሀብታም ሀብታም ያደረገ እንደገናም በአዲስ እቅድ በማስተር ፕላኑ መሰረት ቀድመው ለሚታወቁ ጥቂት ሰዎች ቦታው የኢንዱስትሪ ዞን ነው በሚል እየተሸነሸነ መሸጡ በስፋት ይወራል፤ ይህ እውነት ወይም ሀሰት ስለሞሆኑ መንግስት ሊያጣራ ይገባዋል፡፡

ህዝብን ተጠቃሚ ያደረገ ስላልሆነ አንቀበለውም ቢል ማስረጃው በተግባር ተፈጽሞ የታየው በመሆኑ ህዝብን ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም፡፡ ለምን መብትህን ለማስከበር ተቃወምክ ማለትም ኢፍትህዊና ኢዲሞክራሲያዊ ነው የሚሆነው፡፡ በህዝብ ተመርጫለሁ የሚል መንግስት ህዝብን ሳያማክርና ይሁንታውን ሳያገኝ ምንም ነገር ሊያደርግ አይገባውም ነበር፡፡

ህዝቡ መሮት ድምጽ በማሰማት አቤት ቢልም ዳኝነትና ፍትህ በወንበሩ ላይ ሳይኖር  ቆይቷል፤ ተንገላቷል፡፡ ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ዘራፊ ሀይል ቦታውን ወስዶ የሚሰጠው ወይንም በሊዝ ስም የሚሸጠው ቀድመው ከተደራደሩት ባለሀብት ጋር ነው፡፡ ባለሀብት ወይም ልማታዊ ሲባሉ የነበሩትም ወገኖች በዚህ በህዝብ ላይ በተሰራ ግፍና በደል ከመጋረጃ ጀርባ ባለ ሰፊ ወንጀል ውስጥ እጃቸው በሰፊው እንዳለም ያደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

በየተቋሙ በየመንግስት መስሪያ ቤቱ በህዝብ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ጉቦ፣ አድልዎ፣ መድልዎ፣ የፍትህ መዛባት፣ ከእውነቱ ውጪ በፍርድ ቤቶች ጉዳይ ጣልቃ በመግባት፣ በባለስልጣናት ትእዛዝ ፍርድ መስጠት፣ በሀሰት ምስክሮች መወሰን የዜጎችን ሀብትና ንብረት ከህግ አግባብ ውጪ መውረስ፣ መሸጥ፣ መለወጥ ተንሰራፍቶ የህዝብን ብሶትና ምሬት አሳድጎታልና ተሀድሶው ይሄንንም ጠልቆ ይፈትሸው ዘንድ ግድ ይለዋል፡፡

ኢህአዴግ በውስጡ በከፍተኛ ደረጃ የተንሰራፋውን ሙሰኛና ኪራይ ሰብሳቢ ሀይል አራግፎ ካልጣለ በስተቀር ለህዝቡ ጥያቄ መልስ ሊሰጥ አይችልም፡፡ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን በተመለከተ ለስሙ የአደባባይ መግለጫ ቢሰጥም አስቀድሞ በተዘጋጀ ሴራ የራስ ሰዎችን መርጦና አዘጋጅቶ ቤቱን እንዲረከቡ ማድረግ በስፋት የታየ፣ ህዝብንም ያሳዘነና ያስመረረ ድርጊት ነው፡፡

በዚህች ምድር ላይ በመንግስትና በኢህአዴግ ስም ምን ያልተሰራ በደል፣ ግፍና ወንጀል አለ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ነው ተሀድሶው ጥገናዊ የወንበር ልውውጥ ሳይሆን ስርነቀል ለውጥን ማምጣት የሚጠበቅበት፡፡ የተሀድሶ ጥልቀቱ የህዝቡን በደልና መከፋት ምሬት ለመቅረፍ እስከምን ድረስ ይራመዳል የሚለው ጥያቄም ከብዙ ወሳኝ ሁኔታዎች ጋር ይቆራኛል፡፡ ዜጎች ሀገራቸውን እስኪጠሉ፣ መፈጠራቸውን እስኪያማርሩ ድረስ ምን ታመጣለህ በሚል እብሪትና ድንፋታ መንግስትንም ኢህአዴግንም አምርረው እንዲጠሉ ያደረጓቸው በመንግስትና በኢህአዴግ ስም ወንበሩን ይዘው በህዝብ ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል ጥላቻና ምሬት እንዲያድር አድርገው ሲሰሩ የነበሩት የራሱ የኢህአዴግ ሰዎች እንጂ ከሌላ ከየትም የመጡ አይደሉም፤ የሚገርመውም ይሄ ነው፡፡

ኢህአዴግ ውስጥ ጠንካራ ሀገራዊና ህዝባዊ ፍቅር ያላቸው ለሀገሪትዋ እድገትና ልማት ተግተው የሚሰሩ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል እጅግ በጣም ጠባቦች፣ አስተሳሰበ ደካማዎች በዘረኝነትና በጎሳ ልክፍት ተውጠው የሚያጓሩ፣ ከእኛ በላይ ማንም የለም ብለው የሚንጠራሩ በትምክህትም ያበዱ ሀይሎች አሉበት፡፡

እነዚህ ለህዝብ አብሮነት የማይበጁ፣ መቃቃርን፣ በጥላቻ መተያየትን የሚዘሩ በመሆናቸው ጥልቀታዊው ተሀድሶው በጥልቀት ፈትሾ እልባት ካልሰጣቸው ዘረኛነትን እየሰበኩ የትም መድረስ አይቻልም፤ታላቋን ሀገር ኢትዮጵያንም አይመጥንም፡፡

ጵንፈኛው ተቃዋሚ ብቻ ሳይሆን በራሱ በኢህአዴግ ድርጅቶችም ውስጥ እጅግ አክራሪና ጵንፍ የወጡ ዘረኛ ሀይሎች እንዳሉ ህዝቡ ይናገራል፤ ለሀገርና ለህዝብ ሰላም አብሮነትም ጠንቅ መሆናቸውም እንደዛው፡፡ በሁለቱም ጎራ ያሉት ጽንፈኞች ጉልበትና ጠመንጃ አምላኪዎች ናቸው፡፡ ህዝብን በዚህ ነውጠኛ ስሜት መምራትና ማስተዳደር እንደማይቻል ገና አልተረዱም፡፡

ትንንሽ ጭንቅላቶችና መርዘኛ አስተሳሰቦች እያደጉ ሲሄዱ ታላቅ ሀገራዊ ጥፋትና ውድቀት ያስከትላሉ፡፡ የጀርመኑ ናዚ መሪ አዶልፍ ሂትለር ከጦር ሰራዊት አስር አለቃነት እስከ ጀርመን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ድረስ ለመድረስ የበቃው በጀርመን ናሽናል ፓርቲ አማካኝነት ሲሆን በወቅቱ የህዝቡን በተለይም የሰራተኛውን መሰረታዊ ጥያቄዎች በማስተጋባት በኩል አቻ አልነበረውም፤ ስልጣን ከያዘ በኋላ ግን የለየለት ዘረኛነት ውስጥ ገባ፡፡ የአርያን ዘር (ደም)፣ የአለም ምርጡና የሁሉም የበላይ የሆነው ደም ስለሆነ አለምን መግዛትና ማስተዳደር ያለበት እሱ ብቻ ነው በሚል እብደት በቅርብና በሩቅ ባሉት ጎረቤቶቹ ላይ ሁሉ ጦርነት ከፈተ፤ በመርዝ ጋዝ 6 ሚሊዮን አይሁዶችን ገደለ፤ በማከማቻ ካምፕ አጎረ፡፡ ፈረንሳይን፣ እንግሊዝን ሶቪየት ህብረትን ወረረ፡፡ ይሀው አረመኔያዊ የዘረኝነት ልክፍቱ በስተመጨረሻው በከፋ ሁኔታ መንግስቱ ተንኮታኩቶ እንዲወድቅ አደረገው፡፡ ሂትለርም እራሱን አጠፋ፡፡

ዛሬ ድረስ የናዚ የጦር ወንጀለኞች ቢያረጁም በህይወት ካሉ ተይዘው ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡ ሂትለር በዘረኝነት መንፈስ የገነባው ስነልቡናና መንፈስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ  ወጣቶችን እሳት ውስጥ እንዲማገዱ አድርጓቸዋል። በስተመጨረሻውም ጀርመን ተመልሳ አንድ እስከሆነችበት ግዜ ድረስ ሁለት ሀገር ሁና ተለያይታ ኖረች፡፡

ይህ ሁሉ ኢሰብአዊ ድርጊት አስከፊና አደገኛ የዘረኝነት ፖለቲካ የወለደው፣ በአለም ታሪክ የተመዘገበ እጅግ ዘግናኝ እልቂትና ዘር ማጥፋትን ያስከተለ ነው፡፡ ዘረኛነት እጅግ ሊወገዝና ሊጸየፉት የሚገባ አስተሳሰብ ነው፡፡ በተለይ፣ በህዝቦች ተከባብሮ መኖር ለምትታወቀዋ፣ በልማትና እድገት ላይ ለምትገኘዋ ሀገራችን ጥፋት ነው፡፡ በመሆኑም፣ ተሀድሶው ፈጥኖ ስርነቀል እርምጃን መውሰድና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ይጠበቅበታል፡፡