ዳግም ተሃድሶው ስር ነቀል እንዲሆን…

                                           
ኢህአዴግ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች የ‘እንኳን አደረሳችሁ’ መልዕክት አስተላልፏል። መልዕክቱ ድርጅቱ በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ህዳሴ እውን ለማድረግ ፓርቲው ራሱን ዳግም በማደስ የሀገሪቱን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማስቀጠልና ለማስፋት የገባውን ቃል ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ ህዝቡን እያማረሩ ያሉ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ትርጉም ባለው ደረጃ ለውጥ ማምጣት በሚያስችል መልኩ በማረም የህዝብን እርካታ ለማረጋገጥ በኃላፊነት መንፈስና ስነ ምግባር በመፈፀም ለተጀመረው የህዳሴው ጉዞ ዕቅድ ስኬት እንደሚረባረብ አስታውቋል። ለዚህም ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ድርጅቱ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚያደርገው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።
እርግጥ ማንኛውም ተግባር የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ካልታከለበት “በአንድ እጅ የማጨብጨብ” ያህል ይቆጠራል፤ የተወጠነው ሃሳብም እውን ሊሆን አይችልም። እናም ገዥው ፓርቲ ያቀረበው የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ጥሪ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑ አያጠያይቅም። በተለይም ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ህዝቡን የሚያማርሩ ተግባራት በቀጥታ የህዝቡን ህይወት የሚነኩ በመሆናቸው ተሳትፎው የግድ ይሆናል። 
እንደሚታወቀው መልካም አስተዳደር የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት በመንግስት ጥረት ብቻ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል መሆኑ ነው። በገዥው ፓርቲና በመንግስት በኩል መልካም አስተዳደርን ዕውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉና በአዲሱ ዓመትም የሚከናወኑት ቁርጠኛ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው፤ መላው ህዝብም ዛሬም እንደ ትላንቱ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይኖርበታል። በተለይም ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት በሚባሉት እንደ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዓይነቶችን በአግባቡ በመጠቀምና የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከታትሎ በማሳወቅ ለመልካም አስተዳደር እመርታ መትጋት ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው።
ገዥው ፓርቲና መንግስት መልካም አስተዳደርን አስመልክቶ የሚፈቱበት የራሳቸው የአፈፃፃም መንገድ ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ። የህዝቡ ተሳትፎም ከዚህ አኳያ መሳ ለመሳ መጓዝ ያለበት ይመስለኛል። በእያንዳንዱ የመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ከአቅም ማነስም ይሁን ሆን ብለው ህዝብን ለማማረር የተሰለፉ አስፈፃሚዎችን መታገልና ተገቢውን መንግስታዊ ግልጋሎት ማግኘት ይቻላል። ከህዝብ ዓይን ሊሰወር የሚችል ነገር ባለመኖሩ ህዝቡ እነዚህን አስፈፃሚዎች ልቅም አድርጎ ያውቃቸዋል። የትኛው የአቅም ማነስ ችግር እንዳለበት፣ የትኛው ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢና በመንግስት ስልጣን ራሱን ሊጠቅም የተሰለፈ መሆኑ ከህዝቡ የሚሰወር አይደለም። እናም ህዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ወሳኙ ኃይል መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።
እርግጥ በየትኛው ሀገር ውስጥ የመልካም አስተዳደር እመርታ የሚታሰበው ስርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ ነው። ታዲያ የሀገራችን ፖለቲካዊ ስርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ያለው ብቻ አይመስለኝም። ከዚህ ባሻገርም መልካምና የተመቻቸ ምህዳር ጭምርም የነገሰበት ነው። ምክንያቱም ግልፅ ይመስለኛል። ይኸውም ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ስልጣን የህዝብና የህዝብ ብቻ መሆኑን በግልፅ ስላስቀመጠ ነው። በህገ-መንግስቱ መሰረት ስልጣን የተገልጋዩ ህዝብ መሆኑ ደግሞ፤ ለመልካም አስተዳደር እመርታ የራሱ ጠቀሜታዎች አሉት። ምክንያቱም በጥቅልም ይሁን በጥልቀት የመልካም አስተዳደር ትግበራ ፍተሻ ውስጥ የህዝቡ ይሁንታ የአንበሳውን ድርሻ ስለሚወስድ ነው።
እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ሌላው ጉዳይ መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የንድፈ-ሐሳብ ጉዳይ አለመሆኑ ነው። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ተግባሩ ከዜጎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ስለሆነ በአተገባበሩ ላይ የስልጣኑ ባለቤት የሆነው ህዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለበት። ይህም ህዝቡ በህገ-መንግሰቱ የተጎናፀፈውን ስልጣን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ዕድል ይፈጥርለታል። አንድ ስርዓት በየዕለቱ ስለ መልካም አስተዳደር ስለተናገረ ብቻ ውጤት ሊያመጣ አይችልም። 
ጉዳዩ የንድፈ ሃሳብ ታሪክ ከመሆን ሊዘል አይችልም። እናም ንድፈ ሃሳቡ በተግባር ተገልፆ ህዝቡ የስልጣኑ ባለቤት መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል። አንድ የመንግስት ባለስልጣን አገልጋይነቱ ለህዝብ እንጂ፤ እርሱ ህዝቡን እያማረረ በህዝቡ ሊገለገልበት እንደማይችል ሊያውቅ ይገባል። በእኛ ሀገር ዕውን በሆነው ባልተማከለው ፌዴራላዊ ስርዓት መሰረት፤ ህዝቡ የፖለቲካ መሪዎቹንና ተወካዩቹን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ ድረስ ይሾማል፤ይሽራል። ህዝቡ በምርጫ ካርዱ አማካኝነት በቀጥታ የስልጣን ባለቤት በሆነበት በዚህ የአሰራር ስርዓት ወሳኝ ሚና እንዳለው አይካድም። ሆኖም በህዝቡ በቀጥታ የማይመረጡና ሊመረጡ የማይችሉ አካላት መኖራቸው የሚቀር አይመስለኝም። በዚህ የአሰራር ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቀሱት ስራ አስፈፃሚው፣ ሲቪል ሰርቪሱና የዳኝነት አካላት ናቸው። 
ዳሩ ግን እነዚህ አካላት ለመልካም አስተዳደር አተገባበር ያላቸው የማይተካ ሚና ስለሚታወቅ እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር በምክር ቤቶች የሚሾሙ ወይም ለምክር ቤቶቹ ተጠሪ ይሆናሉ። ይሁንና የየራሳቸው ነፃነት ያላቸው አካላት መሆናቸውን መዘንጋት ያለባቸው አይመስለኝም። በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ ስራ አስፈፃሚውና ሲቪል ሰርቪሱ ማንም እንዳሻው የሚፈነጭባቸው አካላት አለመሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል። ከዚህ ይልቅ ህዝቡና የህዝቡ ተወካዩች በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መክረው ያፀደቋቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ህጎች በተሟላ ሁኔታ የሚያስፈፅሙ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ያለ አድልኦ ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚጠበቅባቸው ናቸው። 
ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ህዝቡ መብቱን ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ መጠየቅ ይችላል። አስፈፃሚው የእርሱ አገልጋይ እንጂ በእርሱ ተገልጋይ አይደለምና። እናም ኢህአዴግ በአዲሱ ዓመት በሚያደርገው ዳግም ተሃድሶ ወቅት ህዝቡ የሚያደርገው የነቃ ተሳትፎ ከእነዚህ ዕውነታዎች አኳያ ሊመዘን የሚገባ ይመስለኛል። አዎ! ህዝቡ ለእነዚህ ነባራዊ ሃቆች ባዕድ መሆን የለበትም። እነዚህን ዕውነታዎች በመገንዘብም ከመንግስት ጋር በቅርበት መስራት ይጠበቅበታል። ይህ ሲሆንም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የህዝቡን እርካታ በሚያረጋግጥ ሁኔታ  ተግባሩን ስር ነቀል ማድረግ ይቻላል። 
እርግጥም ከልምድ እንደሚታወቀው ኢህአዴግ ዳግም በመታደስ ሂደት ውስጥ ራሱንና የመንግስት አሰራሮችን ሲፈትሽ መነሻውም ሆነ መድረሻው ስር ነቀል ለውጥን ማዕከል ያደረገ መሆኑ አይቀርም። አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት “አለባብሰው ቢያርሱ፤ በአረም ይመለሱ” ዓይነት ሊሆን አይገባውም። በእኔ እምነት መንግስት ከህዝቡ ጋር የተጀመራቸው የውይይት መድረኮች ለዚህ ትግበራ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ መድረኮች መንግስትንና ህዝቡን በቀጥታ ፊት ለፊት የሚያገናኙ እንዲሁም ያሉትን ችግሮች ከዋነኛ ተዋናዩ ማግኘት የሚያስችሉ በመሆናቸው ለስር ነቀል አፈታቱ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ። የችግሮቹን ትክክለኛ መንስኤዎች በተገቢው መንገድ ለማወቅ፣ አውቆም ለመረዳትና የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት መድረኮቹ ሊበራከቱ ይገባል።  
እርግጥ እነዚህ የውይይት መድረኮች ሁከትንና ብጥብጥን ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ ለሚሹ ኃይሎች የራስ ምታት መሆናቸው አይቀርም። እናም የሁከት ኃይሎቹ በህዝቡ ውስጥ ውዥንብርና አሉባልታ በመንዛት ውይይቶቹን ለማደናቀፍ መጣራቸው አይቀርም። ምናልባትም ባለማወቅ የጥርጣሬ ዝንባሌ ህዝቡ ውስጥ ሊፈጠር ይችላል። 
ይህን ጥርጣሬ ለማስወገድና መንግስትና ገዥው ፓርቲ ዛሬም እንደ ትናንቱ ቃላቸውን የማያጥፉና የህዝቡን ችግሮች በዳግም ተሃድሷቸው ሊፈቱ እንደሚችሉ ማስተማር ይገባል። ይህ ዕውነታም ለህዝቡ በየመድረኮቹ ላይ በግልፅ መብራራት ያለበት ይመስለኛል። የሁከትና የትርምስ ኃይሎች የሀገራችንን ዕድገትና ብልፅግና የማይሹ አንዳንድ የውጭና የውስጥ ሃይሎች እንጂ ከየትኛውም ብሔርና ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው መሆኑን ማስገንዘብ ይገባል።
እርግጥም በሁከት ኃይሎቹ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ የሚለቀቁ አሉባልታዎች እዚህ ሀገር ውስጥ የተጀመረውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዕድገቶችን የሚያቀጭጩ እንዲሁም አዲሲቷ ኢትዮጵያ የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ባካሄደችው ተሃድሶ ምክንያት እያስመዘገበች ያለችውን ዕድገት የሚገቱ የጥፋት መልዕክቶች ናቸው። መልዕክቶቹ የህዝቦችን ብሶቶች ከማራገብ ጀምሮ እስከ የፈጠራ ትረካዎችን የያዙ ጭምር ናቸው። ይህ የአሉባልታ መድረክ ደግሞ በቀጥታ ተፅዕኖውን የሚያሳርፈው በህዝቡ ተጠቃሚነት ላይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። 
ህዝቡ በሁከት ኃይሎቹ የአሉባልታ ዘመቻ ተታልሎ ባለማወቅ ሊያደርገው በሚችለው  ያልተገባ ተግባር ተጎጂው ራሱ መሆኑ አያጠያይቅም።ይህም በሁከት ኃይሎቹ ገፋፊነት በተለይም በአማራና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በተከናወኑ አጥፊ ተግባራት ህዝቡን መልሰው የሚጎዱ ተግባራት መፈጠራቸው ታይቷል። የየአካባቢው የሁከት ኃይል ተቀጥሮ የሚሰራበትን የባለሃብቶችን ንብረት የማቃጠልና የማፈራረስ እንዲሁም የራሱን የህዝቡን አንጡራ ሃብት የማውደም ብሎም አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር የማጋጨት ተግባራት ተከናውነዋል። 
ይሁን እንጂ አሁን እየተካሄዱ ባሉት ህዝባዊ የውይይት መድረኮች እነዚህ የጥፋት ተግባራት መልሶ ህዝቡን የጎዱት መሆናቸው ህዝቡ በራሱ አንደበት ሲናገር እያደመጥን ነው። ይህ ዕውነታም የሁከት ኃይሎቹ ተግባራት ምን ያህል ፀረ-ህዝብና ፀረ-ልማት መሆኑን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፤ ህዝቡ ሃቁን እየተገነዘበ መምጣቱን ያሳያል። እንዲሁም ችግሮች ከመድረሳቸው በፊት ህዝቡን ማወያየትና ማስተማር ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ረገቢ ትምህርት የተገኘበት ሁኔታ ይመስለኛል። በመሆኑም ገዥው ፓርቲና እርሱ የሚመራው መንግስት የሚያካሂዱት ዳግም ተሃድሶ ስር ነቀል በሆነ መንገድ ገቢራዊ ይሆን ዘንድ በህዝቡ ውስጥ ያሉትን የተሳሰቱ አስተሳሰቦችን በማረም በቂ ግንዛቤ ማስያዝ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል እላለሁ።