ህገ- መንግሥቱ የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ነው!

ዛሬ ሀገራችን ውስጥ ለተከሰተው ወቅታዊ ችግር መፍትሔው ህገ- መንግስቱ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ማናቸውንም ችግሮች የመፍታት ብቃት አለው። ይህ ብቃቱ ከምንም የመነጨ አይደለም—በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሙሉ ፍላጎትና ፈቃደኝነት የፀደቀ ስለሆነ ነው።

እንደሚታወቀው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ዛሬ ለተጎናጸፈችው የሠላም፣ የፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ድሎች መሰረት ለሆነው የኢፌዴሪ ህገ -መንግስት ነው። ህገ- መንግስቱ የህዝቦችን የዘመናት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ምላሽ የሰጠ ነው። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መኖሪያ ብትሆንም፤ እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ለዘመናት በአፈናና በጭቆና ሥርዓት ቀንበር ስር ወድቀው ከመማቀቅ ያዳናቸው ይኸው ህገ መንግስት ነው። ለዚህም በምሳሌነት በአምባገነኑ የደርግ ዘመነ መንግስት ወቅት የተካሄደው ግፍና ሰቆቃ ዋነኛ ተጠቃሽ ነው።

አምባገነኑ የደርግ ሥርዓት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የእኩልነትና የነጻነት ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጥ ባልቻለው የፊውዳላዊ ሥርዓት ላይ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞና አመፅ በፈጠረለት አጋጣሚ ያቆጠቆጠና የህዝቦችን የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት በኃይል ነጥቆ በመዳፉ ማስገባት እንደቻለ ይታወቃል። የደርግ ሥርዓት ከመነሻው የህዝቦችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ፍላጎት ያለው ኃይል መስሎ ብቅ ቢልም አጀንዳው ግን በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ መሆኑ በገሃድ ተስተውሏል፡፡

በመሆኑም ሥርዓቱ የህዝቦችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ አልቻለም፡፡ ይልቁንም በአፄው ሥርዓት ላይ በርትቶ የነበረውንና ደርግም ወደ ሥልጣን  ከመጣ በኋላ የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማዳፈን የኃይል ርምጃን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ንጹሐን ዜጎች ያለፍርድ በመጨፍጨፍ ታሪክ ምንጊዜም የማይረሳው ወንጀል ፈጽሟል፡፡ በወቅቱ የደርግ መንግስት በዜጎች ላይ የሚወስደው ጭካኔ የተሞላበት ርምጃ ቢያይልም፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ተቃውሞአቸውን ከማሰማት ብሎም ትግል ከማካሄድ የገታቸው አልነበረም፡፡ ለ17 ዓመታት የተካሄደው መራርና እልህ አስጨራሹ የፀረ ደርግ ትግል የሚያሳየን እውነታም ይህንኑ ነው፡፡

ህዝባዊ ድሉ በአንድ በኩል አምባገነናዊው የደርግ ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ እንዲወገድ ያስገደደ ሲሆን፤ በሌላም በኩል ደግሞ በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትመራ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት መሰረት የተጣለበት ነው፡፡ ይህም የሀገራችን ህዝቦች ለዘመናት ሲመኙት የነበረውንና በጥያቄነት አንግበው የተነሱትን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ መፍታት ችሏል።

በህዝቦች ሙሉ ፍላጎት የፀደቀው ህገ -መንግስት በስራ ላይ ከዋለ ወዲህ ሀገራችን ትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ ይዛ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ በድል ለመረማመድ በቅታለች፡፡ የብሔሮችና ብሔረሰቦች እስር ቤት እስከመባል ደርሳ የነበረችው ሀገራችን፤ የህዝቦቿ መብት የተረጋገጠባት፣ የዕድገትና ልማት ብሩህ ተስፋን የሰነቀች፣ የእኩልነትና የፍትህ አምባ ለመሆን ችላለች። ይህ የህገ መንግስቱ ችግር ፈቺነት አንዱ ማሳያ ይመስለኛል።

በመሆኑም የአፈና አገዛዝ፣ የግፍ ቀንበር ተጭኖት የኋላቀርነትና የበታችነት ተምሳሌት ተደርጎ ይታይ የነበረው የብሔር ብሔረሰቦቿ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ የህዝቦቿ መኩሪያና መከበሪያ፣ የሀገራችን መድመቂያ ጌጥና የመልካም ገጽታዋ መገለጫ ወደ መሆን ተሸጋግሯል—ባለፉት 21 ህገ መንግስታዊ ዓመታት። የተለያየ እምነትና የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመግባባትና በመረዳዳት መንፈስ አብሮ በመኖር በዓለም የሚታወቁበት የመቻቻል ባህልም ከመቼውም በላቀ ሁኔታ ዳብሯል። እነዚህ ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራችን ተጨማሪ ክብርና ሞገስ ከማላበስ አልፎ ለፈጣን ዕድገት ስራዎች የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት ወደ ሚችሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ ይመስለኛል።

ከምንም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሊቀየር ችሏል። በዚህም ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል። ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ያስቻለ ሁኔታ ነው። መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የዚሁ ህገ መንግስት ሌላኛው ችግር ፈቺነት ማሳያ ይመስለኛል።

በሀገራችን እውን በመሆን ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ የመንግስት ሥርዓት ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ በመገንባት ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ  ላይ ለተመሰረተ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ማስገኘት ችሏል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ረጅሙንና አስቸጋሪውን የፀረ-ደርግ የትግል ምዕራፍን በድል አድራጊነት በቋጩ ማግስት በጋራ ተወያይተውና አምነው ዕውን እንዲሆን ያደረጉት ህገ- መንግስት የዘመናት ጥያቄዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ የመለሰ ከመሆኑም ባሻገር፤ በቀጣይ ለሚያካሄዷቸው የጋራ አጀንዳዎች ዘላቂነትና ውጤታማነት ዋስትና የሰጠ ነው።

የሀገራችን ህዝብና ህገ መንግስቱ በብዙ መልኮች እጅግ የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው በመሆናቸው፤ የሚያጋጥማቸውን ጊዜያዊ ችግሮች የሚፈቱትም በእርሱው አግባብ ነው። ለዚህ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ጉዳይ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህገ- መንግስቱ ባለቤቶች መሆናቸው ነው፡፡ ህዝቡ ህገ- መንግስቱን ያቋቋመ፣ የመንግስትን አወቃቀር የነደፈ ነው። ይህም በህገ- መንግስቱ ላይ በግልፅ ተመልክቷል።

ሌላኛው የሚነሳው ጉዳይ ህገ- መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ስለሆነ፤ ሰነዱን ከማንኛውም አደጋ የመጠበቁ ኃላፊነትም የሁሉም ህዝቦች መሆኑ ነው።  ይህ እውነታም የህገ- መንግስቱ ባለቤት የሆኑት ዜጎች በተደራጀ መልኩ ህገ -መንግስቱንና የሥርዓቱን ደህንነት መጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል። እንዲያውም ህገ-መንግስቱን ከመጠበቅ ባሻገር ተጠቃሚም በመሆኑ የሰነዱ ዋስትና በእያንዳንዱ ዜጋ እጅ ያለ ይመስለኛል። እናም ህገ መንግስቱንም ይሁን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን መጠበቅ ማለት ዛሬም እንደ ትናንቱ የሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝ የሚገባ ይመስለኛል።

እርግጥ በህገ – መንግስቱ አፈፃፀሞች ላይ ምንም ዓይነት እንከን የለም ማለት አይቻልም። ሀገራችን ጀማሪ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አራማጅ መሆኗ፣ ዜጎችም ለእንዲህ ዓይነቱ ስርዓት አዲስ መሆናቸውና ያለው ግንዛቤም ያልዳበረ መሆኑ፣ በአፈፃፀም ረገድም ከአመለካከትና ከአቅም ማነስ ጋር ተያይዞ በህገ መንግስቱ አግባብ ችግሮች በወቅቱ አለመፈታታቸው እንዲሁም በአስፈፃሚዎች ዘንድ ስልጣንን ለህዝቡ ጠቀሜታ ሳይሆን የግል መጠቀሚያ የማድረግ ዝንባሌና ተግባር መኖሩ ለችግሮቹ መንስኤዎች ይመስሉኛል።

ይህ ማለት ግን ህገ-መንግስቱ በራሱ የችግሮች መንስኤ ነው ማለት አይደለም። ምክንያቱም ህገ መንግስቱ ምርጥ የሚባሉ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የያዘና ማናቸውንም ችግር ስልጡን በሆነ መንገድ መፍታት የሚችል ተራማጅ ሰነድ ስለሆነ ነው። ላለፉት 21 ህገ መንግስታዊ ዓመታት ሀገራችን ውስጥ የታዩት እመርታዎችም የህገ መንግስቱን ችግር ፈቺነት እንጂ የችግር መንስኤነትን የሚያሳዩ አይደሉም።

ለነገሩ ህገ-መንግስቱ ፀድቆ በስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ነው— ሀገራችንና ህዝቦቿ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች እጅግ ውጤታማ ተግባር ማከናወን የቻሉት። በህገ መንግስቱ መርሆዎች ሀገራችንና ህዝቦቿ ከራሳቸው አልፈው የአፍሪካ ፖለቲካዊ ድምፅ እስከ መሆን ድረስ ደርሰዋል። በመርሆዎቹ የሀገራችን የድህነትና ኋላቀርነት ገፅታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊለወጥ ችሏል። የህዝብን ተጠቃሚነት በየደረጃው ማረጋገጥ የቻለ የልማት ተምሳሌት ሆነንም ለአፍሪካውያን ልምዳችንን እስከማካፈል ድረስ ደርሰናል። በመርሆዎቹ የህዝቡ ተቻችሎና ተከባብሮ በጋራ የመኖር እሴቶች እየተገነቡ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

እነዚህ ሁሉ ተግባራት የተከናወኑት በህገ-መንግስቱ ቁልፍ መፍትሔ ሰጪነት ነው። አዎ! ባለፉት 21 ዓመታት ህገ-መንግሰቱ የችግር መፍቻ ቁልፍ ሆኖ ዛሬ ላይ አድርሶናል፤ ነገም ችግሮችን በህገ-መንግስቱ ማዕቀፍ ውስጥ መፍታት ይቻላል። በዚህ ላይ መወላወል ሊኖር አይገባም—የህገ-መንግሰቱ የትናንት የችግር አፈታት መንገዶች ነገንም የሚያሳዩ ናቸውና። እናም ማንኛውም ሀገርና ህዝብ ሊያጋጥመው እንደሚችለው ጊዜያዊ ችግር ሁሉ፤ ዛሬ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ዕድገታችንንና ሰላማችንን በማይሹ አንዳንድ የውጭና የውስጥ ሃይሎች ሳቢያ የተከናወኑ ተግባሮችም በህገ-መንግስቱ አግባብ በፅናት የሚፈቱ መሆናቸውን ማንኛውም ዜጋ ግንዛቤ መያዝ ያለበት ይመስለኛል።