የጠንካራ ትስስራችን መሠረት

ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከርና እጅና ጓንት በመሆን እውን እያደረጉት ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ባለፉት ዓመታት የነበረው አፈጻፀም በታቀደው መሠረት በመከናወን ላይ ይገኛል። እስካሁን በግንባታው ሂደት የተመዘገቡትን ለውጦች የበለጠ ለማጠናከር ኅብረተሰቡ በያለበትና በየተሰማራበት የሥራ መስክ አስተዋጽኦ ማድረጉን ቀጥሏል። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ዳር ለማድረስ ቆርጠው ተነስተዋል። በቅርቡ በካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ድጋፋቸውን ለማድረግ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስብሰባ ማድረጋቸው ተሰምቷል።

 

አገሪቱ ባለ ሁለት አኃዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት በማስመዝገብ በዓለም ፈጣን ዕድገት እያሳዩ ካሉ አገሮች መካከል ተጠቃሽ አገር ለመሆን በቅታለች ያሉት በካናዳ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሣደር፤ ዕድገቱ በአስተማማኝ መልኩ እንዲቀጥል የኃይል አቅርቦት ወሣኝ ሚና አለው ብለዋል። የኃይል አቅርቦቷን  አስተማማኝ ለማድረግ 6000 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም  ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታው በአሁኑ ወቅት ሰባ በመቶ ደርሷል። አገሪቱ በዘርፉ የያዘቻቸው ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ  ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር ወሣኝ ድርሻ አለው። 

 

የግድቡ መጠናቀቅ  አገሪቱ ከአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር ነው። በካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ አቅማቸው በሚፈቅደው ሁሉ ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። መንግሥትም ይህንን የሕዝብ ንቅናቄ በማስተባበር ግንባታውን ዳር ለማድረስ እየሰራ ይገኛል። ይህ በአገር ሃብት የሚገነባ ትልቅ ፕሮጀክት አገሪቱ ድህነትን ለመቅረፍ ለሚታደርገው ጥረት የተለየ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል።

 

የአባይ ተፋሰስ ሰፊ ሃብት ነው። ለቀጠናው ሕዝቦች ልማት መረጋገጥ ትልቅ አቅም ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል። ኢትዮጵያም የአባይ ውኃ ከፍተኛ አመንጭ  የመሆኗን ያህል ከሌሎች አገራት ጋር በመተባበር ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች በማከወን ላይ ትገኛለች።

 

የአባይ ጉዳይ ሲነሳ በማንኛውም ኢትዮጵያዊ አዕምሮ የሚመጣው ጉዳይ አገሪቱ የሃብቱ ባለቤት የመሆኗን ያህል ተጠቃሚ አልሆነችም የሚል ነው። አዎን! ላለፉት ዘመናት ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ ሳይሆኑ ዘልቀዋል። ይልቁንም አባይ የዘመናት የሕዝብ ቁጭትና እንጉርጉሮ ሆኖ ቀርቶ ነበር። በአባይ ውኃ ልማት የማይታሰብ ተደርጎ መደምደሙም የማይረሳ ጉዳይ ነው።  

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ አባይን ከሚያህል ትልቅ የተፈጥሮ ፀጋ ተጠቃሚ ባለመሆኑ የተነሳ ለዘመናት በእያንዳንዱ ዜጋ ሲብሰለሰል የኖረው ቁጭት ብቻ ነበር። አሁን ያ ቁጭት መቋጫውን አግኝቷል። አባይ ከዚህ በኋላ የቁጭትና የእንጉርጉሮ የሚሆንበት ዘመን ያበቃ ሆኗል።  አባይ ዳቦ ለመሆን በመንገድ ላይ ነውና።  

 

አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ በታላቅ ተስፋ ላይ ይገኛል። ለዘመናት ሲንጠው የኖረውን  ድህነት ለማራገፍ በአንድነት ደፋ ቀና እያለ ነው።  ከድሀነት የመውጣት ተስፋው ለምልሟል። ለዚህም እያንዳንዱ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። አባይ የሀገር ሲሳይ፤ የዘላቂ ልማት መሠረት መሆኑ የግድ ሆኗል።

 

ይህንን የተፈጥሮ ሃብት በተለይ በኤሌክትሪክ ማመንጫነት መጠቀም የጎላ ጠቀሜታ አለው። እንደሚታወቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ለአንድ አገር ዕድገት መሠረት ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት እያስመዘገበች የመጣችው ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከኃይል ማመንጫ ውጭ የሚታሰብ አልነበረም። መሠረታዊ የዕድገት ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በቂ የኃይል ምንጭ ካለ ብቻ ነው።

 

አገሪቱ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት መጠነ ሰፊ  የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ አካሂዳለች። የተከዜ፤ የፊንጫ የግልገል ጊቤ አንድ፤ ሁለትና ሦስት፤ የጣና በለስና ሌሎች ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ የተደረገባቸው የኃይል ማመንጫ ግድቦች ናቸው።  የነበራትን ዝቅተኛ የኃይል መጠን ማሳደግ በመቻሏ በአገሪቱ ኢንቨስትመንት እየተስፋፋ መጥቷል። የኢንዱስትሪ ልማቱም በዚያን ልክ እያደገ ነው።

 

ይህ አገሪቱ ለተለያዩ የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ከሌሎች የልማት ሥራዎች ጋር ጎን ለጎን አጣጥማ መሥራት በመቻሏ ምክንያት የመጣ ነገር ነው።  ከውኃ ከሚገነቡት የኤሌክትሪክ ግድቦች በተጨማሪ አገሪቱ የነፋስና የፀሀይ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ መሰረተ ልማቶችን በመስራት ላይ ትገኛለች።   

 

ይህንኑ የተገነዘበው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የኃይል ምንጭ ግድቦቹን የበለጠ በማጠናከር ላይ ይገኛል። አዳዲስ ግድቦችን የመገንባት ሥራው  ልዩ ትኩረት ካገኘው አንዱ ዐቢይ የልማት ዘርፍ  ነው። በዘርፉ በዕቅድ ተይዘው እየተሰሩ ካሉ ግድቦች መካከልም የአንበሣውን ድርሻ የያዘው  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው።

 

ታለቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሩህ ተስፋ ነው። አገሪቱ በአባይ ወንዝ ላይ መገንባት ከምትችላቸው ልማቶች ሁሉ በግዙፍነቱም ሆነ በጠቀሜታው የጎላ ድርሻ ያለው ግድብ ነው። የህዳሴው ግድብ  አገሪቱ ከድህነት ለመላቀቅ የምታደርገውን ጉዞ ለማሳካት የሚኖረው አስተዋጽኦ ተኪ አይኖረውም። ይህንን ለግብጽ ሕዝብ በግልጽ የማቅረብና እውነታውን የማሳመን ተግባር የኢትዮጵያ መንግሥት በሰፊው እየሠራ ይገኛል። ይህ ደግሞ በአገራቱ ቀደም ሲል የነበረውን ግንኙነት በመቀየር ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር የግድ ስለሚል ነው።

 

በአገራቱ በቀደሙት ሥርዓታት የነበረው ግንኙነት በጥርጣሬና በሥጋት የተሞላ ነበር። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ምንም ዓይነት የልማት ፕሮጀክት እንዳትገነባ ስትከላከል የኖረችው ግብጽ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ እያቀረበች ያለውን አማራጭ መቀበል የግድ ሆኖባታል።

 

በግብጽ የተመረጠው የአል ሲሲ መንግሥት ግብጽና ኢትዮጵያ የነበራቸው ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ አንዳንድ አዎንታዊ ተግባራትን እያከናወነ መምጣቱ የዚህ ጥረት ውጤት ነው። የአዲሱን መንግሥት መቋቋም ተከትሎ ታላቁን የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ አስመልክቶ ቀደም ሲል ተቋርጦ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይት ቀጥሏል።

 

ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤት አገራትም ሆነ ከሌሎች የዓለማችን አገራት ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ የድንበር ወሰን ካላቸው እንደ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያና ኤርትራ የመሳሰሉ አገራት በሠላም አብሮ የመኖርና የጋራ ተጠቃሚነት ስትራቴጂ እንደምትከተል ይታወቃል።   

 

ባለፉት ሥርዓታት ኢትዮጵያ ድንበር ከምትጋራቸው አገሮች ጋር የነበራት ግንኙነት  መልካም እንዳልነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ግንኙነቱ በጥላቻና በጦርነት ላይ የተመሠረተ ነበር። ግብጽን ጨምሮ በሌሎቹ አገራት የነበሩ መንግሥታትም ቢሆኑ ለሠላምና ለጋራ ጥቅም ቅድሚያ ባለመስጠታቸው የተነሳ በቀጠናው ሠላም አልነበረም። ይሁንና ባለፉት ሃያ አምስት  ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለውንና ተግባራዊ  ያደረገውን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መሠረት ያደረገው የውጭ ግንኙነት ኢትዮጵያ ከሁሉም አጎራባች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻሻልና እንዲጠናከር አስችሎታል። ይህን ለሕዝቦች የጋራ ጥቅም የቆመውን ፖሊሲዋን ተግባራዊ በማድረጓ የተነሳ ተጠቃሚ የሆነችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በአካባቢዋ ያሉት አገራት ጭምር በመሆናቸው በአገሪቱ ላይ አመኔታ ማሳደር ችለዋል። ለዚህ አንዱ ማሣያ ደግሞ ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራት ያላት ሠላምን የማረጋገጥ ተሳትፎ በዋናነት በተለይ ደግሞ በደቡብ ሱዳንና ሆነ በሱዳን መንግሥት አመኔታን አግኝታ በሁለቱ አገራት አጨቃጫቂ በሆነው የጋራ ድንበራቸው አብዬ ሠላም አስከባሪ እንድታሰማራ በሁለት ጎረቤት አገራት መመረጧ የአገሪቱ ፖሊሲና የህዝቦቿ ታማኝነት ምን ያህል የተጠናከረ መሆኑን ያመላክታል።

 

ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሠረት የሚያደርገው የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና አገራዊ ህልውናን በማረጋገጥ እንዲሁም በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባትና ለአካባቢው ሕዝቦች ጥቅም በጋራ በመሥራት ላይ ነው። ይህ የውጭ ፖሊሲ ለሁሉም አገራት የሚሰራ በመሆኑ በግብጽ ላይ የተለየ አቋም ሊኖራት አይችልም። እናም የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን ነው ከግብጽ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት የተጠቀመችበት ያለው፤

 

የሕዝቦች የጋራ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር እያጠናከረች የመጣችው ኢትዮጵያ  ይህንን  ትስስር የሚያጠናክሩ የተለያዩ ዘመናዊ የመሠረተ ልማት አውታሮች እንደ መንገድ፣ የባቡር ሐዲድ፤ የአውሮፕላን የበረራ መስመሮች፣ የኃይል አቅርቦት፣ የፀጥታ ትብብርና የመረጃ ልውውጥ ግንኙነቶችን በማጠናከር ሁሉንም ሕዝቦች ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ትገኛለች። ይህንን ሰፊ የምጣኔ ሀብት ትስስር ለመፍጠር ከምትጠቀምባቸው ዘርፎች አንዱ ለጎረቤት አገራት ኃይልን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ነው። አገራቱ በኢትዮጵያ እየተገነቡ ካሉ ትላልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች በሰፊው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ እያመቻቸች ትገኛለች።

 

ይህ የምጣኔ ሀብት ትስስር ግብጽንና ሕዝቦቿንም ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ነው። ግብጽ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ትችላለች። ይህንን ኃይል በመጠቀምም የኢንዱስትሪ ልማቷን ማስፋፋት የሚያስችላት ዕድል ይሰፋል።  

 

በሁለቱ አገራት ያለው ግንኙነት እንደ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ኤርትራና ጅቡቲ የጋራ ድንበር ወሰን ባይኖረውም የአባይ ውኃ ያስተሳስራቸዋል። የአባይ ውኃ ለግብጾች ህይወታቸው እንደሆነው ሁሉ ለኢትዮጵያዊያንም ሕይወታቸው እንደሆነ መረዳት የግድ ይላል። ግብጻዊያኑ የእርሻ ልማታቸውም ሆነ የሚጠጡት ውኃ አባይ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከድህነት ለመላቀቅ ያላቸውን ያላቸው ዋናው አማራጭ የአባይን ወንዝና ሌሎችንም የውሀ ሀብቶች መጠቀም ነው። ታላቁ መለስ ዜናዊ  በህይወት ዘመናቸው ለግብጽ ሚዲያ በሰጡት የሁለቱ ህዝቦችና አገራት ግንኙነት “ፍቺ ሊፈፀምበት የማይቻል ጠንካራ ጋብቻ” ነው በማለት ነበር የገለጹት።

ኢትዮጵያዊያን ጠላታችን ድህነት ብቻ ነው ብለው ያምናሉ። ድህነትን ድል ለማድረግ ደግሞ አባይን ጨምሮ ያላቸውን ሃብት መጠቀም የግድ ይላል።