ፌዴራላዊ ሥርዓት፤ ብቸኛው አማራጭ!

 

ኢትዮጵያ በፌደራላዊ  ሥርዓተ መንግሥት የምትተዳደር አገር ነች። ፌደራላዊ ሥርዓቱ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተመሰረተ ነው። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 1 የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ በሚል ርዕስ ስር ይህ ህገ መንግስት ፌዴራላዊ የመንግስት  አወቃቀር ይደነግጋል። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል ይላል። የፌደራል ሥርዓት ወይም ፌዴራሊዝም በተለያየ የሥልጣን ወሰን የታጠሩ ሁለት መንግሥታትን  አጣምሮ የያዘ ሥርዓት ነው። በፌዴራላዊ ሥርዓት ስር ያሉ አገራት ማዕከላዊውን ወይም የፌዴራል መንግሥቱንና እንደየአገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ የተመሰረቱ የግዛት ወይም የክልል መንግሥታት ይኖሯቸዋል።

በፌዴራል መንግሥት ስር ያሉ የክልል ወይም የግዛት መንግስታት ቀደም ሲል በአሃዳዊ ሥርዓት ስር የነበሩና በኋላ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ አብረው በመኖር ለመቀጠል የተስማሙ ወይም፤ ራሳቸውን ችለው የነበሩና በአንድ ታሪካዊ አጋጣሚ ለመሰባሰብ የወሰኑ ሊሆኑ ይችላሉ። የኢትዮጵያን የፌዴራል መንግሥት አወቃቀር አስመልክቶ ምሁራን ሁለት የተለያየ አቋም ያንጸባርቃሉ። በአንደኛው ወገን ያሉ ምሁራን ቀደም ሲል በአሃዳዊ ሥርዓት ስር የነበሩ ብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ሕዝቦችን ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ አድርጎ የቀጠለ ነው ይላሉ። በሌላኛው ወገን ያሉት ደግሞ፤ የመጨረሻው አሃዳዊ ሥርዓት የነበረው የወታደራዊው ደርግ መንግሥት ሲፈርስ በአሃዳዊ ሥርዓት ስር የነበሩት ብሄሮችና ብሄረሰቦች በየራሳቸው ወደሚተዳደሩበት ሥርዓት ለመሄድ መንገድ ይዘው፤ በኋላ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ለመኖር ተስማምተው የተሰባሰቡበት ነው ይላሉ። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት የነበሩትን አቅፎ የዘለቀም ይሁን ተበታትነው የነበሩትን ያሰባሰበ፤ በዋናነት በብሄራዊ ማንነትና በቋንቋ ላይ ተመስርተው በተዋቀሩ ክልላዊ መንግሥታት የተገነባ ነው። 

እንግዲህ ከላይ እንደቀረበው፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ የታቀፉት  ክልላዊ መንግሥታት በንጉሣዊና በወታደራዊ ቡድን አሃዳዊ የመንግሥት ሥርዓት ስር ከላይ ወደታች በሚወርድ የተማከለ መዋቅር ሲተዳደሩ የነበሩ ናቸው። የፌዴራሉ መንግሥት አካል የሆኑት ክልላዊ መንግሥታት የተዋቀሩት በአመዛኙ በብሄር አሰፋፈር ላይ በመመስረት ነው። የክልልን አወቃቀር በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፋር፤ ቋንቋ፤ ማንነትና ፈቃድ ላይ ነው” ሲል ይደነግጋል። በዚህ መሰረት የፌዴራል መንግሥቱ አካላት የሆኑ ዘጠኝ ክልሎች ተዋቅረዋል። የፌዴራል መንግሥቱ ማለትም፤ የኢፌዴሪ መንግሥት በእነዚህ ክልሎች የተዋቀረ ብቻ ሳይሆን ስልጣኑም የመነጨው ከእነዚህ ክልሎች ነው። የፌዴራል መንግሥቱ ከክልሎቹ ውጭ የራሱ ህልውና የለውም። የፌዴራል መንግሥቱ የሚኖረው የክልሎቹ መንግስታት እስካሉ ድረስ ብቻ ነው።

በክልሎች የተዋቀረው ፌዴራላዊ መንግሥት ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት አስገኝቶላቸዋል። በሚኖሩበት ክልል፤ ዞን ወይም ወረዳ በመረጧቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ይተዳደራሉ። በቋንቋቸው የመንግሥት አገልገሎት ያገኛሉ። ልጆቻቻውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያስተምራሉ። ታሪካቸውን፤ ባህላቸውንና ትውፊታቸውን ያጠናሉ፤ ይንከባከባሉ፤ ያስተዋውቃሉ፤ ያጎለብታሉ። በወሰናቸው ውስጥ ያለውን እምቅ የኢኮኖሚ  አቅም ለሕዝባቸው የተሻለ ህይወት ጥቅም ላይ ያውላሉ። ሁሉም ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳደሩና ፌዴራል መንግሥቱን የመሰረቱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል በሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በሕዝባቸው ቁጥር ልክ ወንበር/መቀመጫ ይጋራሉ።

በመከባበርና በእኩልነት አብረው የመኖር የቃል ኪዳን ሰነዳቸው የሆነውን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ሰጥቷል። እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረሰብና ሕዝብ በዚህ ምክር ቤት ውስጥ ውክልና አለው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን በተመለከተ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 61፤

  • ዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራሉ መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች፣ ህዝቦች የሚልኳቸው አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነው።
  • እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ሕዝብ ቢያንስ አንድ ተወካይ ይኖረዋል፤ በተጨማሪም የብሄሩ ወይም የብሄረሰቡ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ተጨማሪ ወኪል ይኖረዋል። ይላል።

በአስፈጻሚው አካል ውስጥም በተመሳሳይ ብቃት ዋጋ የሚሰጠው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የተመጣጠነ የብሄር ተዋጽኦ እንዲኖር ማድረግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት አለ።

በኢፌዴሪ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ አንድ ብሄር የበላይ ሆኖ ሌሎችን ከፈቃዳቸው ውጭ መግዛት፤ ወይም በክልላዊ ጉዳያቸው ውስጥ ጣልቃ መግባት የሚያስችል ሥልጣን የለውም። ኦሮሚያን የሚያስተዳድሩት ኦሮሞዎች የወከሏቸው ልጆቻቸው ናቸው። ከፌዴራል መንግሥት ወይም ከሌላ ክልል አስተዳዳሪ አይላክባቸውም። የማያውቁትና ያልወከሉት አስተዳዳሪ አይሰየምባቸውም። ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ሕግ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ማለትም፤ በክልላዊ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው የሚጸድቀው፤

በአጠቃላይ፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፤ የአማራን ክልላዊ መንግሥት፤ የትግራይን ክልላዊ መንግሥት፤ የኢትዮጵያ ሶማሌን ክልላዊ መንግሥት፤ የአፋርን ክልላዊ መንግሥት፤. . . የሚያስተዳድሩት ክልሎቹን የመሰረቱት ብሄሮችና ብሄረሰቦች ናቸው። አማራ ወይም ትግራይ፤ የኢትዮጵያ ሶማሌን ወይም ኦሮሚያን ወይም አፋርን በበላይነት ማስተዳደር የሚያስችላቸው አንድም መንገድ የለም። ይህ አሁን በአገሪቱ በተጨባጭ እየታየ ያለ ዕውነታ ነው። እናም በአገሪቱ የአንድ ብሄር ወይም አንድን ብሄር የሚወክል ፓርቲ የበላይነት አለ በሚል የሚቀርበው ውትወታ ፍጹም መሰረተ ቢስ ነው። በብሄራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተው ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ይህን ማድረግ የሚያስችል ክፍተት የለውም።

የመጨረሻው አሃዳዊ መንግሥት የነበረው የወታደራዊ ደርግ መንግሥት የተወገደው የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ለብሄራዊ መብታቸውና ነፃነታቸው መረጋገጥ በየአቅጣጫው ባካሄዱት የትጥቅ ትግል ነው። ወታደራዊውን መንግሥት በማስወገዱ ትግል ውስጥ በተለያዩ ታሪካዊ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች የአንዳቸው ድርሻ ከሌላኛው ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም፤ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ በብሄራዊ ማንነት የተደራጁ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ከሃያ በላይ ነበሩ። ይህን የወታደራዊው መንግሥት ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ባደረጉት የመጨረሻ ንግግራቸው ተናግረውት እንደነበር ይታወሳል።   

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ወታደራዊው ሥርዓት ሲወገድ በየአቅጣጫው ለብሄራዊ ነፃነት የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ የነጻነት ድርጅቶች የሚወክሉት ብሄር ወይም ብሄረሰብ የሚኖርበትን አካባቢ ነፃ አውጥተው የማስተዳደር አቅጣጫ ወደመከተል ነበር ያዘነበሉት፤ ይሁን እንጂ፤ አንድ ብሄር ወይም ብሄረሰብ ተገንጥሎ ነፃ አገር መመሰረቱ በራሱ መብቱና ነፃነቱ የተረጋገጠበትን ሁኔታ የሚፈጥር በቸኛ አማራጭ አልነበረም። መድረሻቸው የሆነው ብሄራዊ መብትና ነፃነታቸው ተከብሮ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነትና በመከባበር ከሌሎች ጋር አብረው የሚኖሩበትን ሥርዓት ለመመስረት ተስማሙ። ይህን ሥርዓት ለመመስረት ባቋቋሙት የሽግግር መንግሥት  የኢፌዴሪን ሕገ መንግሥት አጸደቁ።

ይህ ሕገ መንግሥት በፌዴራላዊ ሥርዓት ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ  በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ያላት አገር መስርተው ለመኖር የተማማሉበት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። የዚህ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መፍረስ ውጤት የአገሪቱ መፍረስ ነው።

እናም፤ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የአገሪቱ ህልውና የመቀጠል ወይም ያለመቀጠል ጉዳይ ነው። አገሪቱ በወሰን ሳይሆን በሕዝቦች ጥምረት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት እንዲኖራት ከተፈለገ ፌዴራላዊውን ሥርዓት መጠበቅና ማጽናት ያስፈልጋል።