አካሄዳችንን ልንፈትሸው ይገባል!

 

በአገራችን  ተቃውሞ  ማካሄድ አዲስ ነገር አይደለም። በሰላማዊ መንገድ የሚካሄዱ ተቋውሞዎችም መጥፎ  አይደሉም። ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ በማራመድ የሃሳብ ብዘሃነት መኖር የዴሞክራሲ መገለጫ ነው። ይሁንና እስካሁን በአገራችን የተካሄዱ ተቃውሞዎች ሁሉ በጥፋትና በውድመት የታጀቡ ነበሩ። ለምሳሌ፤- በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ሶስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ  በተከሰተው ተቋውሞ የበርካቶች ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል። በቅርቡም በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የተካሄዱ ተቃውሞዎች ፈር የለቀቁ እንደነበሩ ተመልክተናል።

በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ አካባቢዎች  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የነውጥ ኃይሎች የህብረተሰብን ጥያቄ ከለላ በማድረግ ለነውጥ ያነሳሳል ያሉትን ስሜት ኮርኳሪ ነገሮችን በመጨማመር ወጣቱን ወዳልተፈለገ መንገድ እንዲያመራ አድርገውታል። በዚህም ንጹሃንን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ህይወት ጠፍቷል፤ አካል ጎድሏል፤ ንብረት ወድሟል፤ ስነልቦናዊ ውድቀት ደርሷል። የአገራችንን መልካም ስም አጉድፏል። በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ ትልቅ አሉታዊ ጫና ይፈጥራል። በአገር ወስጥ ምርትና የወጪ ምርቶቻችን ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል።

ይህን እንደዝና የሚያወሩ አንዳንድ የዳያስፖራ ፖለቲከኞችን ስሰማ እጅግ ያሳዝነኛል። መንግሥት ይመጣል መንግሥት ይሄዳል። አገርና ሕዝብ ግን ቀጠይ ናቸው። ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ይህን ጉዳይ ያሰቡበት አይመስለኝም። ኢህአዴግ ፓርቲ ነው። በቀጣይ ምርጫ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል። አገራችን ግን ሁሌም ትኖራለች። እንግዲህ ይህችን የሁላችንንም ቤት ለማፍረስ መሯሯጥ የጤንነት አይመስለኝም።

በአገራችን ልዩነትን ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት እውን ሆኗል። ይህ አሠራር በአገራችን ብዙም ጠንካራ ባህል አይሁን እንጂ ሃሳብን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማራመድ የሚቻልበት ሥርዓት ተዘርግቷል። ልዩነትን በኃይል ለማራመድ መሞከር ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው። በተቃውሞ ስም የሻዕቢያን ተልዕኮ የምንፈጽም ከሆነ፤ የግብጽ መንግሥት ተላላኪ ከሆንን፤ አልሻባብ የሚመኘውን ካደረግንለት እኛው ከጠላቶቻችን ብሰን ተገኘን ማለት አይደለምን?

የአገራችን ሕገ መንግሥት የዜጎችን ሰብዐዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ማረጋገጥ የቻለ የብሄሮች፣ የብሄረሰቦችና ሕዝቦች የቃልኪዳን ሰነድ ነው። አገራችን ሕግ መንግሥታዊ መብቶች የተረጋገጡባት፤ ማንም የፈለገውን ሃሳብ  በሰላማዊ መንገድ  ማራመድ የሚችልባት አገር በመሆን ላይ ትገኛለች። የፌዴራል ሥርዓቱ የሕገ መንግሥቱ አንዱ ትሩፋት ነው። በፌዴራል ሥርዓቱ ምክንያት ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በማንነታቸው እንዲኮሩ፤ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ እድል አግኝተዋል። ይህን ሥርዓት በኃይል ለማፍረስ  ከሚንቀሳቀስ ወገን ጋር ማበር የሕግ ተጠያቂነት ያስከትላል።

መንግሕት በአሸባሪነት የፈረጃቸው የኦነግና የግንቦት ሰባት ልሳን የሆኑት ኢሳት፤ ኦ ኤም ኤንና አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች በበሬ ወለደ አሉባልታ ወጣቶችን ለአመጽና ለሁከት እየቀሰቀሱ ለጥፋት ድርጊታቸው ተጠቅመውባቸዋል። አሁንም ለመጠቀም በመሯሯጥ ላይ ይገኛሉ። ኦነግና ግንቦት ሰባት የተባሉት በአሸባሪነት የተፈረጁት ድርጅቶች በየጊዜው አጀንዳ እየፈጠሩ ሕዝብን ከሕዝብና ሕዝብን ከመንግሥት ጋር ለማጋጨት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

የሰላምን ዋጋ የሚያውቀው ሰላም ያጣ ብቻ ነው። የሰላምን ዋጋ አብዛኛው እድሜው ከ30ዎቹ አጋማሽ የዘለለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በደርግ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ያየው ጉዳይ በመሆኑ በደንብ  የሚያስታውሰው ነገር ነው። ብልህ ከጎረቤቱ አሊያም ከሌላ ስህተት ይማራል ይባላል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን በራሳችን ላይ በደረሰው እጅግ ዘግናኝ ጦርነት በአግባቡ የተማርን አይመስለኝም። ዛሬም የሁከትና የብጥብጥ ገፈት ቀማሾች እየሆንን ነው። ዛሬም ተመልሰን የዓለም መዘባበቻ እንድንሆን አንዳንድ ጽንፈኛ ኃይሎች መርዛቸውን እየረጩብን ነው። ሕዝብ የሚያነሳቸውን ተገቢ ጥያቄዎች ከለላ በማድረግ አገርን የሚያውኩ ዘረኛ ድርጊት የሚፈጽሙ ኃይሎችን ልንቃወማቸው ይገባል። 

የአገራችን ወጣቶች አንዳንድ የውጭ የኤሌክትሮኒክስ፤ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም የዳያስፖራ ፖለቲከኞች የሚያስተላልፏቸውን የተሳሰቱ መረጃዎች በማመን ለጥፋት ቡድኖች መሳሪያ ከመሆን መቆጠብ ይኖርባቸዋል። በእርግጥ የአገራችን የዴሞክራሲ ባህል ገና ለጋ ነው። በወረቀት ላይ የሰፈሩት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሁሉ ተግባራዊ አልተደረጉም። ይህ ተግባራዊ የሚሆነው ኅብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ በመታገል እንጂ ያለችንን ንብረት በማውደምና ህይወት በመቅጠፍ ሊሆን አይገባም። 

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከዜሮ በታች ከሆነ የኤኮኖሚ ደረጃ የተነሳች አገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩና የሚዳሰሱ ተጨባጭ ለውጦች ማስመዝገብ ችላለች። በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ባለሁለት አኃዝ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነቱን ካረጋገጥን  በመጪዎቹ አስርና አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ አገሪቱ ወደ ላቀ የእድገት ደረጃ መሸጋገሯ አይቀሬ ይሆናል። ይህ እውን የሚሆነው ግን ያለንን አስጠብቀን ተጨማሪ ልማት ማስመዝገብ ስንችል ብቻ ነው።

 

ሌላው አገራችን በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተቀባይነት እጅጉን አድጓል። ይህ የኢትዮጵያ ዕድገት ምቾት የማይሰጣቸው በርካታ መንግሥታት አሉ። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በቀንዱ አካባቢ፤ እንዲሁም በአፍሪካና በዓላም አቀፍ መድረኮች ዕያደገ የመጣው ተሰሚነቷ በአንዳንድ አካሎች ላይ ስጋት ፈጥሯል። በመሆኑም እነዚህ የኢትዮጵያ ዕድገት ምቾት የማይሰጣቸው አካላት በአገራችን የተጀመረውን ልማት ለማደናቀፍና ሰላሟን ለማደፍረስ በየጊዜው የተለያዩ ስትራቴጂዎችን እየነደፉ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።

 

ከስትራቴጂዎቹ መካከል በሃይማኖት፤ በብሄር፤ በነጻ ጋዜጠኝነት ስም፤  በመሬት ቅርምት  ወዘተ. የሚሉ አጀንዳዎች ጥቂቶቹ ናቸው። እነዚህ የፈጠራ አጀንዳዎች አገሪቱን ወደ ብጥብጥና ሁከት በማስገባት የልማት እንቅስቃሴዋን ለማስተጓጎል ያለሙ ናቸው። 

ጠንካራዋ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ስጋት የምትሆንባቸው አገራት እንዳሉ እናውቃለን። ለእነሱ አቅመ ቢስ ኢትዮጵያን መፍጠር ትልቁ ህልማቸው ነው። ለእነዚህ እኩይ ኃይሎች መጠቀሚያ መሆን ደግሞ የታሪክ ተወቃሽነትን ያስከትላል።  

 

እነዚህ ኃይሎች የአገሪቱን ልማት ለማደናቀፍ አማራጭ የሚሏቸውን የጥፋት አካሄዶች ሁሉ ሞክረዋል። አንዱ ስልት ሲከሽፍ ሌላ ስልት በመቀየር በእንቅስቃሴያቸው ገፍተውበታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱትን ችግሮች በአንክሮ ለተመለከተ እጅግ አሳፋሪ ድርጊቶች ናቸው። ጽንፈኛ የዲያስፖራ ፖለቲከኞች አገርን የሚያፈርስ አካሄድ በመከተል ታሪካዊ ስህተት ፈጽመዋል። የገነገነ የዘረኝነት ስሜት በማራመድ ንጹሃንን ተጠቂ የማድረግ እጅግ የወረደ ተግባር ላይ ተዘፍቀው ነበር። ጽንፈኛ የዲያስፖራ ፖለቲከኞች ትንሿን እንከን የማጉላትን አካሄድ ተክነውበታል። ሁሉን ነገር በማጥላላት አባዜ ተጠምደዋል።

 

ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ከአገራችን ቀንደኛ ጠላቶች ከኤርትራና ከአንዳንደ የአረብ መንግሥታት ጋር በመወገን፤ ተላላኪ ከሆኑት ከኦነግና ከግንቦት ሰባት ጋር በማበር አገራችንን ለማወክ በመሯርጥ ላይ ናቸው። የዳያስፖራ ፖለቲከኞች የንጹሃን ህይወት መጥፋትና አካል መጉደል፤ ስቃይና ስደት፤ የሕዝብና የአገር ንብረት መውደም አይገዳቸውም። ለዳያስፖራ ፖለቲከኞች የአገር ብሔራዊ ጥቅምም ሆነ ሉዓላዊነት ቦታ የለውም። ለእነሱ ትልቁ ነገር የናፈቋትን የሥልጣን ማማ መቆናጠጥ እንጂ የሕዝብ ጥቅም፤ የአገር ደህንነት አያሳስባቸውም።

 

ጽንፈኛ የዲያስፖራ ፖለቲከኞች ዲስኩር የሚያዝ የሚጨበጥ ነገር የለውም። ኢህአዴግ/ ህወሃትን ዘረኛ ሲሉ ቆይተው ነበር። ነገር ግን በተግባር የተያው በተገላቢጦሽ ነው። ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ዘረኝነት፤ አመጻና፤ ጦረኝነት የባህርያቸው ዋንኛ መገለጫ ሆኗል። በእርግጥ አብዛኛው ጽንፈኛ ዳያስፖራ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የተዘፈቀው በኑሮው ጫና ሳቢያ በደረሰበት የሥነ-ልቦና ውድቀት ነው። ጽንፈኛ የዲያስፖራ ፖለቲከኞች ለአገርና ለሕዝብ ሰላምና እድገት የሚያስቡበትም ሆነ የሚጨነቁበት ጭንቅላት የላቸውም። እነሱን የሚገዳቸው ሥልጣንና ጥቅም ብቻ ነው። እንዲህ ያለውን ቅጥ ያጣ አካሄድ ሁላችንም ሃይ ልንለው ይገባል። 

የሕግ የበላይነት የሚከበረው በመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሰላም ወዳድ ኅብረተሰብ እገዛ ጭምር በመሆኑ አጥፊዎችን ወደ ህግ ማቅረብ ተገቢ ነው። በስሜታዊነት  የሚቀሰቀስ አመጻና ነውጥ መነሻውም መድረሻውም አይታወቅም። በአጭር ጊዜ በአገራችን በተከሰተው ሁከት የበርካታ ዜጎቻችን ህይወት ጠፍቷል፤ በቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል። ባለፉት 25 ዓመታት በከፍተኛ በጥረት የተገነቡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋልል። ማህበራዊ መገልገያዎች ወድመዋል።እንዲህ ዓይነት ቅጥ ያጣ የተቃውሞ መገለጫ አንገት የሚያስደፋ ነው። ያለንን እያጠፋን ለውጥ መጠበቅ የሚታሰብ ነገር አይደለም። በመሆኑም አካሄዳችንን ልንፈትሸው ይገባል።