ነገረ—“ኢንፍሉዌንዛ”…(ክፍል ሁለት)

በክፍል አንድ ፅሑፌ ላይ በአሜሪካ ኮንግረስ የአፍሪካ ጉዳዩች ንዑስ ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት የቀረበውን ረቀቅ ውሳኔ ተመርኩዤ፤ የሀገራችን መንግስት ተጠሪነቱ ለሀገራችን ህዝቦች እንጂ ለየትኛውም የውጭ ኃይል አለመሆኑን ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በረቂቅ ውሳኔው ላይ የተነሱት ነጥቦችን አግባብነትንም አመላክቻለሁ። በዚህኛው ክፍል ፅሑፌ ደግሞ ሌሎች ነጥቦችን በማከል ነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ”ን እንዲህ ተመልክቼዋለሁ።  
በእነ ሚስተር ስሚዝ የቀረበው ረቂቅ ውሳኔ፤ ሰላማዊ ሠልፈኞችና ተቃዋሚዎች የመናገርና የመቃወም መብታቸው እንዲጠበቅም ጥያቄ ያነሳል። እርግጥ ጥያቄው ተገቢ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አሁንም በአፈፃፀም ደረጃ ‘ዕውን ሰላማዊ ሰልፈኞችና ተቃዋሚዎች የመናገርና የመቃወም መብት የላቸውምን?’ የሚል ጥያቄ ስናነሳ፤ ጥያቄው ለማለት ያህል የቀረበ ከመሆንና ነባራዊውን ሁኔታ ያላገናዘበ ሆኖ እናገኘዋለን። ትክክለኛነት የጎደለውም ጭምር።
እዚህ ሀገር ውስጥ ያለን ሰዎች እንደምናውቀው በሀገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። እዚህ ላይ ቁጥሮችን ማንሳት አልሻም—ዋናው ጉዳይ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ያለው ህገ መንግስታዊ ፍላጎት ነውና። ያም ሆኖ ግን በቅርቡ የሀገራችንን ዕድገት በማይፈልጉ የውጭና የውስጥ ሃይሎች አቀጣጣይነት በመሳሪያ የታጀቡና ወደ ፀጥታ ሃይሎች በመተኮስ ጭምር ግድያ የፈፀሙ “ሰላማዊ ሰልፎችን” ሳይጨምር እጅግ በርካታ ሰልፎች ተካሂደዋል—በህጋዊ መንገድ። ይህ ደግሞ ህገ መንግሰቱ ለዜጎች ያረጋገጠላቸው መብት በመሆኑ በየትኛውም አካል ሊታገድ አይችልም።
በህገ መንግስቱ አንቀፅ 30 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ እንደተደነገገው ሀገራችን ውስጥ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት ተረጋግጧል። ዜጎችም መሳሪያ ሳይዙ ከሌሎች ጋር በመሆን በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አላቸው። እናም ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች ይህን ህገ መንግስታዊ መብት በተግባር ለማረጋገጥ ታስኖ ነው። ሆኖም የረቂቁ ባለቤቶች ‘ሰልፎች መሳሪያም ተይዘው መካሄድ አለባቸው’ የሚሉ ከሆነ አሁንም የሀገራችንን የስልጣን ሉዓላዊነት እየተጋፉ መሆኑን መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል። አለያ ግን አሜሪካ ውስጥም በመሳሪያ የታጀበ እንዲሁም የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ የተሰማራ የፖሊስ ኃይል እየሞተ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን ህጉ እንደማይፈቅደው ሁሉ፤ በተገላቢጦሽ እዚህ ሀገር ውስጥ ከህግ ውጪ በኃይል የታገዘ “ሰላማዊ ሰልፍ” እንዲካሄድ መመኘት ይሆናል። ይህ ደግሞ ህግም እየተጣሰ ቢሆን “እኛን ስሙን” የሚል ግልፅ ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ ይመስለኛል።
የረቂቁ ባለቤቶች እንዳሉት እዚህ ሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎች የመናገርና የመቃወም መብት የሌላቸው አይደሉም። ላለፉት 21 ህገ መንግስታዊ ዓመታት የመናገርና የመደራጀት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዕውን ሆነዋል። ተቃዋሚዎችም በፈለጉት መንገድ እየተደራጁ ሃሳባቸውን በነፃነት ይገልፃሉ። እናም ሃሳቡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ-መንግስቱ ባጎናፀፋቸው የመደራጀት መብት መሰረት ከ50 በላይ የመንግስት ተቃዋሚዎችን የዘነጋ ነው ማለት እችላለሁ። እንዲሁም የእነ ሚስተር ስሚዝ ሃሳብ ሚዛናዊ አይመስለኝም። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ውስጥ ያለን ሰዎች እንደምናውቀው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የራሳቸው ውስጣዊ ሽኩቻ ጠልፎ የሚጥላቸው ከመሆኑ በስተቀር፣ ዓላማቸውን ለማሳካት በሚያካሄዱት ማናቸውም የመናገር እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ የሚገባ አንድም የመንግስት አካል አለ ብሎ ማሰብ ስለማይቻል ነው። 
ያም ሆኖ ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜያት በመገናኛ ብዙሃን በሀገራዊ ጉዳዩች ላይ መግለጫ ይሰጣሉ፤ አቋማቸውንም ያንፀባርቃሉ። ተደራሽነታቸውን ለማስፋትም መገናኛ ብዙሃንን ተጠቅመው ዓላማቸውን ለህዝቡ ሲያደርሱ ማየት እዚህ ሀገር ውስጥ የተለመደ ነው። ከዚህ ባሻገርም ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ድርጅቶችን የሚያቀራርብና በወቅታዊ ጉዳዮች ያላቸውን አቋም የሚያንጸባርቁበት የክርክር መድረኮች መኖራቸው ብሎም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተፈጥሮ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ገዥው ፓርቲ ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው ሀገራዊው የዴሞክራሲያዊ መብቶች እየዳበሩ መሄዳቸውን የሚያሳይ በመሆኑ፤ የነገረ-“ኢፍሉዌንዛ”ን ጥያቄ ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። 
እርግጥ የነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” ባለቤቶች ለምን ይህን አቋም አንፀባረቅክ ተብሎ የታገደ ፓርቲም ይሁን የታሰረ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራርን በአስረጅነት ማቅረብ ባይችሉም፤ ሀገራችን ከራሷ ተጨባጭ ሁኔታ እንጂ የአሜሪካን የዴሞክራሲ ሂደት በመገልበጥ የምትከተለው መስመር ሊኖር እንደማይችል መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ ግን የኮንግረሱ አባላት ፍላጎታቸው የ250 ዓመታት ያህል የዴሞክራሲ ተሞክሮ ያላትን አሜሪካን የግድ ምሰሉ የሚሉ ከሆነ፤ ከእነርሱ በ225 ዓመታት ያህል ወደ ኋላ የቀረን ጀማሪዎች በመሆናችንና በመገንባት ላይ የምንገኘው የዴሞክራሲ ባህል ሀገራችን ውስጥ ካለው ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ እንጂ የአሜሪካን እንዳለ በመገልበጥ አይደለም። እናም ይህ ሃቅ “ዕውን ዴሞክራሲ እንደ ቁሳቁስ ከውጭ የሚገባ ነውን?” የሚል ጥያቄ እንዳነሳ ያደርገኛል። 
ዕውን ዴሞክራሲ እንደ ቁሳቁስ ከውጭ የሚገባ ነውን?
በአንድ ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲ ዕውን መሆን ያለበት ሀገሪቱ ከምትከተለው የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ስርዓት አኳያ መቃኘት ይኖርበታል። የሀገሪቱ ህዝቦች ባህል፣ ወግና ትውፈታዊ ስርዓት እንዲሁም እነዚህ ህዝቦች የመጡበት የታሪክ ዳራ ለመገነባው የዴሞክራሲ ባህል ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ከዚህ አኳያ ሀገራችን ስለ ዴሞክራሲ መስማት ከጀመረች ገና 25 ዓመቷ ነው። ህዝቧም ትናንት በፊውዳላዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች ፍዳውን ሲያይ የነበረ ነው። በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የእነዚህ ስርዓቶች የተዛቡ አስተሳሰቦች ሰለባ ሆኖ የቀየ ህዝብ ነው። 
ያለፉት ስርዓቶች ጥለውብን የሄዱትን እነዚያን ትክክለኛ ያልሆኑ እሳቤዎች በዴሞክራሲ መስመር ውስጥ ለማስገባት ጊዜን ይጠይቃል። ያለፍንባቸው 25 ዓመታት በቂ ያልሆኑ ብቻ ሳይሆኑ፣ የዴሞክራሲን ባህል ለመገንባት እንኳን የሚበቁ አይመስለኝም። እናም እዚህ ሀገር ውስጥ የሚገነባው የዴሞክራሲ ባህል ከእነዚህ ዓይነት ተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር እየተመዘነ በጊዜ ሂደት ውስጥ የሚተገበር እንጂ፣ ከእነ አሜሪካ በቀጥታ እንደ ቁሳቁስ ወደ ሀገር ውስጥ የምናስገባው የቴክኖሎጂ ውጤት አይደለም። እናም ዴሞክራሲ መሆን ያለበት ሀገር በቀል ነው።
እርግጥ ዴሞክራሲን እጅግ ከዳበሩት ሀገራት ገልብጦ ማስገባት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያነዝናል። በአተገባበሩ 225 ዓመት ያህል ልቆን የሄደ የዳበረ ዴሞክራሲ እዚህ ሀገር ውስጥ ማምጣት ማለት አንድን ብሎን በማይገጥመው አቃፊ ውስጥ በኃይል ቀጥቅጦ የማስገባት ያህል ነው። ወይም አንድ 36 ቁጥርን ለሚጫማ ሰው 49 ቁጥር ጫማን ገዝቶ በግድ እንዲጫማው የማድረግ ያህል ይቆጠራል። ይህ ከሆነ ደግሞ ሁለት ጉዳዩች መከናወን አለባቸው። አንድም፣ የሰውዬው እግር ያለተፈጥሮው በወረንጦ በኃይል ተጎትቶ ጫማው ውስጥ ማስገባት፤ ሁለትም፣ ጫማውን ተቆርጦ 36 ቁጥር እንዲሆን ማድረግን ይጠይቃል። ሁለቱም ሙከራዎች ግን አጥፊዎች ናቸው—የሰውዬውን እግር ከጥቅም ውጭ በማድረግና በገንዘብ የተገዛውን ጫማ መቁረጥ ያስከትላሉና። እናም 36 ቁጥር ጫማ ለሚያደርገ ሰው በልኩ የሚጫማውን ቁጥርን መግዛት ተገቢ ነው።
ዴሞክራሲም እንደ ቁሳቁስ ከውጭ ተገዝቶ ቢገባ የሚያስከትለው ችግር እንዲህ ዓይነቱን ነው። እናም የነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” የዴሞክራሲ መብቶች አጠባበቅ ጥያቄ ከዚህ አኳያ መታየት ይኖርበታል። በአንድ ሀገር ውስጥ የዴሞክራሲ ችግር አለ ተብሎ ከታመነ መፍትሔ መሰጠት ያለበት ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እንጂ በእነ አሜሪካ መለኪያ ሊሆን አይችልም። እናም ምንም እንኳን አሜሪካ በዓለም ላይ ዴሞክራሲን ሰጪ ወይም ነሺ ባትሆንም ቅሉ፣ የኮንግረሱ አባላት ጥያቄ ዴሞክራሲ ከአሜሪካ መንጭቶ ሌላ ሀገር ውስጥ መተግበር እንዳለበት የሚያሳስብ በመሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ለዚህም ይመስለኛል—የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ኃላፊ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ከአሜሪካ ተነስቶ ሊበለፅግ እንደማይችልና በሀገራችን ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ መምጣት ያለበት ከኢትዮጵያ መሆኑን ለሪፖርተር ጋዜጣ የገለፁት። 
የነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” ረቂቅ ውሳኔ ከዚህ ቀደም እነ ሂዮማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉ ፅንፈኛ የኒዮ-ሊበራል ስርዓት ርዕዩተ-ዓለም አራማጆች ስዕለት ያለባቸው ይመስል እየተፈራረቁ በዘመቻ መልክ ሲሉት የነበረ ጉዳይ በመሆኑ አዲስ ነገር የለውም። ምናልባትም ልዩነቱ በአሜሪካ ኮንግረስ አባላት አማካኝነት በረቂቅ ውሳኔነት መቅረቡ ብቻ ይመስለኛል። እነ ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚያራምዱት የፅንፈኝነት ኒዮ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ ዋነኛ መሰረቱ ‘ሁሉም ነገር ለገበያና ለግሉ ባለሃብት መተው አለበት፤ መንግስት ህግና ሥርዓትን ከማስፈን ውጪ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም’ የሚል ነው። ኒዮ-ሊበራሊዝም በየትኛውም ሀገር ውስጥ እንዲኖር የሚፈልገው ሃይል የሌለው ቀጫጫ መንግስትን ነው። መንግስት ከልማታዊ ስራዎች ርቆ ጥቂት ባለሃብቶች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እንዳሻቸው እያዘዙ፤ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የበይ ተመልካች ሆኖ እንዲቀመጥ ይሻል። መንግስት በገዛ ሀገሩ ኢኮኖሚ ውስጥ የዘበኝነት ተግባር ብቻ መወጣት አለበት ብሎም በጥብቅ የሚያምን ከአንድ በመቶ ለማይበልጡ ግለሰቦች የቆመ ነው። ልክ በቅኝ ግዛት ዘመን ወቅት የአፍሪካ ሀገራትን አንጡራ ሃብት እንደመዘበሩት ሁሉ፤ ዛሬም የርዕዩቱን ቀኖና ለማስፋፋት እነ ሂዮማን ራይትስ ዎችንና አምንስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ ፅንፈኛ አራማጆችን በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ሽፋን የአምላክ መልዕክተኛ የሆኑ ያህል ስለ መብቶች ለይስሙላ እያላዘኑ ነው።    
እናም እነ ሂዮማን ራይትስ ዎች ለጥቁር ህዝቦች መብት ከሰማየ ሰማያት አምላክ የላካቸው የክርስቶስ ታናሽ ወንድም መሆናቸውን ጠዋትና ማታ በሚደሰኩሩት ትረካቸው የርዕዩተ-ዓለም ቀኖናቸውን በኃይል እውን ሊያደርጉ ይሞክራሉ። ለዚህም ነው—ዛሬ እነ ሚስተር ስሚዝ ያቀረቡትን ‘የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት ይጣራ’ ጥያቄን በቅድሚያ 15 የሚሆኑ አክራሪ ኒዮ-ሊበራሊስቶች ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት አቅርበው የነበሩት። ለዚህም ነው—ጉዳዩ እንደ ኢንፍሉዌንዛ የተጋባባቸው ይመስል የርዕዩተ-ዓለም ጣጣቸውን ገቢራዊ ለማድረግ በየተራ የሪፖርት ጋጋታን የሚያዥጎደጉዱት።
ያም ሆኖ ግን ይህ የእነ ሂዮማን ራይትስ ዎች የርዕዩተ-ዓለም ጣጣ የኬንያ መሪ የነበሩት ጆሞ ኬንያታ (እ.ኤ.አ 1891-1978) በአንድ ወቅት የተናገሩትን ዕውነታ እንዳስታውስ አድርጎኛል። አዎ! ጆሞ ኬንያታ “…ከዘመናት በፊት ነጮች ክርስትናን እየሰበኩና ስለ ሰማያዊው መንግስት እያወሱ፤ በአንድ እጃቸው መፅሐፍ ቅዱስ በሌላኛው ደግሞ ጠብ-መንጃ ጨብጠው ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፣ ጥርጊያውንም አቅኑ’ በማለት ወደ አፍሪካ ገቡ። ‘የምድሩንም ተውት፣ ዋናው የሰማዩ ነው’ አሉን። እኛም አመንናቸው። ተንበርክከንና ጭንቅላታችንን ደፍተን ፀለይን። ቀና ስንል ግን እነርሱ ምድራችንን ወርረዋል፤ አልፍተውና አላሽቀውም ጨርሰውናል። በተርታ አሰልፈውም ለባርነት ሸጠውናል፤ ለውጠውናል።…” ነበር ያሉት። 
በእኔ እምነት እነ ሂዮማን ራይትስ ዎችም መልካቸውን ቀይረው ብቅ ያሉ ልክ በእነ ጆሞ ኬንያታ ዘመን በሃይማኖት ስም የሚነግዱ “ሚሲዮኖች” ዓይነት በሽፋን የታጀሉ የኒዮ-ሊበራል ርዕዩተ-ዓለም ፅንፈኛ አቀንቃኞች ናቸው። ‘እንዴት?’ ቢሉ፤ ትናንት በአፍሪካውያን ላይ ያደረሱት ያ ሁሉ ስቃይና መከራ ተረስቶ፣ ዛሬ ስለ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊሰብኩን ተነስተዋል። ስለ ትክክለኛውና በጎው መንገድም ሰባኪዎች እነርሱ ሆነዋል። የትናንት ቃል ኪዳናቸውን ሽረው ወንጌልን በሰበኩበት አፋቸው ክቡሩን አፍሪካዊ የሰው ልጅ ገበያ አውጥተው እየሸጡና እየለወጡ በዋጋ እንዳልተከራከሩበት፤ እነርሱው በተገላቢጦሽ ‘ቅዱስ’ ሆነው አፍሪካውያንን “ረከሳችሁ” እያሉን ነው። “የሰው ልጅ መብት አፍሪካ ውስጥ ተረገጠ፣ ዴሞክራሲንም ድምጥማጡ ጠፋ” በማለት የአዲሱ ዘመን መፅሐፍ ገላጮች ሆነዋል። በቀኝ እጃቸው ዴሞክራሲን በግራቸው ደግሞ ብድርና እርዳታን ይዘው፤ “የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲን መንገዶች አዘጋጁ፣ የፖለቲካውን ጥርጊያም አቅኑ” ያሉን ነው። “ምጣኔ ሃብቱን ተውት፣ ስለማደጉና ስለመበልፀጉ እንዲሁም ተደጋግፎ ስለ መስራቱ አትጨነቁ፤ እርሱን እኛ እናዘጋጀዋለን” እያሉን ነው። “ስለ ድህነታችሁና ስለ ኋላ ቀርነታችሁም አትመራመሩ፤ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብትና ለዴሞክራሲ ብቻ ስጡ” በማለትም እየዘመሩብን ነው። አዎ! እነ ሂዩማን ራይትስ ዎች የዚህ ዘመን የአዲሱ ሊበራሊዝም ርዕዩተ-ዓለም “ሚሲዩኖች” ሆነው ከእነርሱ አስተሳሰብ ውጪ በዕድገት የሚወነጨፉ ታዳጊ ሀገራትን በሰብዓዊና ዴሞክራሲ ስም ፍላፃ እየወረወሩባቸው ነው። ይህ ደግሞ ዘውጉን የቀየረ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።
ያም ሆነ ይህ ግን የኮንግረሱ አባላት በዚህ መንገድ በሰብዓዊ መብቶችና በዴሞክራሲ ታዛ ስር ተጠልለው የነዮ-ሊበራሊዝምን ቀኖና ለማራመድ የሚሰሩን የእነ ሂዮማን ራይትስ ዎችን የሰርክ ሪፖርት እንዳለ ገልብጦ በውሰድ ወቅቱን ጠብቀው ዛሬ ላይ “ሃጢያታችንን” ለማግዘፍ ለምን እንደሚጥሩ ግልፅ ይመስለኛል። እርሱም የርዕዩተ-ዓለም አንድነት ነው። ምናልባትም የላኪና ተላላኪ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ግን ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው ምክንያቶች አሜሪካም ይሁን ሌላ ሀገር ውስጥ ያለውን የኒዩ-ሊበራል አስተሳሰብን እንዳለ ገልብጠን መውሰድ አንችልም። የሀገራችን ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ሁኔታ ይህን እንድናደርግ አይፈቅድልንም። ቀኖናውን እንዳለ እንውሰድ ብንል እንኳን፤ በአንድ መልኩ ሊሰፋን፣ በሌላኛ ገፅታው ደግሞ ሊጠበን ይችላል። ያለ ልካችን የተሰፋ በመሆኑ ሊንቦረቆቅ ወይም ‘ጥብቆ’ ሊሆንብን ይችላል። አይበቃንም። እናም መፍትሔው ከውጭ ከሚመጣ እሳቤ ይልቅ ሀገር በቀሉ ዴሞክራሲ መሆኑን የነገረ-“አንፍሉዌንዛ” አራማጆች ሊያውቁት የሚገባ ይመስለኛል። አዎ! ዴሞክራሲን እንደ ቅንጦት ዕቃ ከውጭ ልናስገባው የምንችለው ቁስ አይደለም።
ከነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” በስተጀርባ እነማን ይኖሩ ይሆን?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ብዙም ምርምር የሚያስፈልገው አይመስለኝም። በእኔ እምነት ከረቂቅ ውሳኔው በስተጀርባ ሶስት ኃይሎች ሊኖሩ ይችላሉ። አንደኛው ቀደም ሲል ዓላማቸውንና ፍላጎታቸውን ለማሳካት በታዳጊ ሀገራት ላይ ትርምስ የመፍጠር ፍላጎት ያላቸው አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ኃይሎች ሲሆኑ፣ ሁለተኛው እዚህ ሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን መያዝ እንደማይችሉ የሚያውቁና በሀገራችን ህዝቦች በአሸባሪነት የተፈረጁ እንደ ግንቦት ሰባት የመሳሰሉ ቡድኖች ሊሆኑ ይችላሉ። ሶስተኛው ደግሞ የገራችንን ልማትና ዕድገት የማይሹ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ናቸው። በቀዳሚነት የጠቀስኳቸውን አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ኃይሎችን ፍላጎትና ዓላማ ከላይ ስለገለፅኩት እዚህ ላይ አልመለስበትም። ሁለተኛና ሶስተኛ አድርጌ የጠቀስኳቸውን ግን ትንሽ ፈታ አድርጎ መመልከት የሚገባ ይመስለኛል።
ሀገራችን ውስጥ በአሸባሪነት የተፈረጁት ቡድኖች በቀጥታ እዚህ ሀገር ውስጥ ገብተው ዓላማቸውን ማሳካት አይችሉም። በአሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ይመራል የሚባለው ግንቦት ሰባትና በዳውድ ኢብሳ የሚመራው “ኦነግ” ራሳቸውን ችለው ለህዝብ የቆሙ ሳይሆኑ፣ በኤርትራ መንግስት አሰማሪነትና ፍላጎት “ተወርዋሪ ድንጋይ” ሆነው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እናም እነዚህ ቡድኖች በስመ-የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚነት ሻዕቢያ ከአንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የሚሰበስበውን ገንዘብ በመርጨት እንዲህ ዓይነቱን ረቂቅ እንዲወጣ ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ። የኮንግረሱ አባላት በእማኝነት ያቀረቡትና በቅርቡ በሪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት ሌሊሳ ፈይሳን ብራዚል ድረስ ተጉዘው የተቀበሉትና ኋላ ላይም ወደ አሜሪካ እንዲሄድ ያደረጉት እነ ዶክተር ሼክስፒር ፈይሳ የግንቦት ሰባት ባለሟሎች መሆናቸውን ስንመለከት የረቂቁን ድራማ ለመገንዘብ አይከብደንም።
በእኔ እምነት ምንም እንኳን የግብፅ መንግስት የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ አስመልክቶ በተለያዩ ወቅቶች “በመተባበርና በጋራ ተጠቃሚነት እየሰራን ነው” ቢልም፤ ከሰሞኑ “የበለፀገች ኢትዮጵያ” በተባለው ድረ ገፅ ላይ የተለቀቀው ቪዲዮ የካይሮን መንግስት በበኩሌ እንዳላምነው አድርጎኛል። በቪዲዮው ላይ አንድ የግብፅ መንግስት ቴሌቪዥን “የጋዜጦች ዘገባ” በማለት ባቀረበው ጥንቅር ላይ የህዳሴው ግድብ መንገዶች እንደተዘጋጉና መቀመጫውን አስመራ ካደረገው የእነ ዳውድ ኢብሳ “ኦነግ” ጋር መነጋገራቸውንና በዚህም እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ያትታል። ይህን ስራ የሰሩት ተወዳጁ መሪ አል-ሲሲ በመሆናቸውም ልናከብራቸው ይገባል ይላል። ይህ የቴሌቪኑ አባባል እውነት ከሆነ፤ በእኔ እምነት የግብፅ መንግስት የህዳሴውን ግድብ ለማደናቀፍ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚካሄደውን ሁከት ከመደገፍ ይመለሳል ብዬ አላስብም። ይህን የሚከውን መንግስት ደግሞ በእነ ዳውድ ኢብሳ አማካኝነት የአሜሪካ ኮንግረስን ከመወትወት ወደ ኋላ ይላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል። ሌሎች የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና የማይሹ ሀገራትም ይህን መሰሉን መንገድ እንደማይከተሉ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል መንግስት ጉዳዩን በጥንቃቄ ማየት ያለበት ይመስለኛል።
ነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” በምን ይታከም?
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ‘የኢትዮጵያ መንግስት ኮንግረሱ ውስጥ ብዙ ወዳጆች ስላሉት ረቂቁን ለማስቀልበስ ወትዋቾችን አይቀጥርም’ ብለዋል። እርግጥ አሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገፅታና ሀገራችን በአፍሪካ ቀንድና በአህጉሪቱ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደረገች ያለችውን የሰላም ማስጠበቅ ተግባር እንዲሁም አሸባሪነትንና ሌሎች ዓለም አቀፍ ስጋቶችን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነት የሚገነዘቡና ለዚህም ዕውቅና የሰጡ የዋሽንግተን አስተዳደር ባለስልጣናት በርካታ ናቸው። ሰሞኑን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት 71ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ወደ አሜሪካ ያቀኑት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ እግረ መንገዳቸውን ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ባለስልጣናቱ የኢትዮጵያ መንግስት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ መናገራቸው ይህን ዕውነታ የሚያሳይ ይመስለኛል። እናም ለእነዚህ ወገኖች ከረቂቁ ጀርባ ያለውን የኃይሎች አሰላለፍ በሚገባ ማሳወቅ አስፈላጊ ይመስለኛል። 
ይህ ሁሉ የሚደረገው ግን በሁለቱ ሀገራት መካከል ከ110 ዓመታት በላይ የዘለቀውን ጠንካራ ግንኙነት ለማስቀጠልና በአሁኑ ወቅት ከአሜሪካ ጋር ያለንን የላቀ ትብብር ይበልጥ በማጎልበት የጋራ ተጠቃሚነትን ዕውን ለማድረግ እንጂ፤ እዚህ ሀገር ውስጥ ከውጭ የሚገባ ዴሞክራሲ ስለሚያስፈልገን አለመሆኑ ሊታወቅ የሚገባ ይመስለኛል። 
እርግጥ የነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” በሽታ ይታወቃል። የበሽታው መንስኤዎችም ከረቂቁ በስተጀርባ ያሉት ኃይሎች መሆናቸው ግልፅ ነው። እናም በሽታውንና መንስኤውን ካወቅን ዘንዳ፤መድኃኒቱን መፈለግ የሚከብደን አይመስለኝም። አዎ! መድኃኒቱም መመንጨት ያለበት ከእኛው እንጂ ከሌላ የውጭ ኃይል መሆን የለበትም። እናም መንግስት ላለፉት 25 ዓመታት እንዳደረጋቸው የህዝብ ታዛዥነት ተግባራቱ ሁሉ፤ ነገም ሆነ ከነገ ወዲያ ሀገራችን ውስጥ ለሚፈጠሩ ማናቸውም ወቅታዊ ችግሮች ከህዝቡ ጋር በመሆን ፈጣን ምላሽ መስጠት ይኖርበታል። ዛሬም እንደ ትናንቱ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ለየትኛውም ሀገር አለመሆኑን በሚገባ ማሳየት አለበት። ይህን ሲያደርግም የነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” ወረርሽኝ ዳግም እንዳያገረሽ ማድረግ የሚችል ይመስለኛል።