ወጣቱና የዚያ ማዶ ሰዎች 

ወጣቱ የህብረተሰቡ ወሳኝ ሀይል ነው፡፡ የነገው ትውልድ ተረካቢ፤ የሀገር መሪና አስተዳዳሪ ነው፡፡ ወጣቱ ትኩስ ጉልበትና አዳዲስ የፈጠራ ችሎታን እምቅና ያልተነካ ጉልበትን የያዘ በመሆኑ ለሀገር ግንባታና ሰላም ያደረገው አስተዋጽ ተኪ የለውም፡፡ በትምህርትና በእውቀት የታነጸ ወጣት ሀገሩን ወደ ተሻለ ደረጃ የማሸጋገር፣ የማሳደግ አቅሙና ጉልበቱም ከፍተኛ ነው፡፡ ወጣቱ የሀገሩም ትልቅ ሰብአዊ ሀብት ነው፡፡
ሀገሬና ወገኔ ብሎ የሚሰራ ለዚህም ታላቅ መስዋእትነትን የሚከፍልና የከፈለ ወጣት ትውልድ በየዘመኑ ታይቶአል፡፡ ወጣትነት ትኩስ እምሮና ጉልበት ባለቤት ሲሆን በለጋ እድሜው ለሀገር ታላላቅ ፋይዳ ያላቸውን ለለምነቷና ለእድገትዋ የሚያግዙ ተግባራትን ይከውናል፡፡
የተፈጥሮ ህግና የእድሜ ሂደት ስለሆነም ሁሌም ወጣት ተሁኖ አይኖርምና ለሀገር የሚበጀውን ሁሉ መስሪያው፣ መከወኛው በተግባርም መዋያው የወጣትነት እድሜ ነው፡፡ በቀድሞው መንግስታት ዘመን በሀገሪቱ የስርአት ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ተጋድሎና መስዋእትነት የከፈለው የያኔው ወጣት ትውልድ ነው፡፡ በዘመኑ የህብረተሰቡን ዋነኛ ጥያቄዎች በማንሳት በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርስቲዎች የመሬት ላራሹን ጥያቄዎች፣ የዲሞክራሲን ያለገደብ ጥያቄን የመሰብሰብ የመደራጀት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ጥያቄን በማንሳት ይህ ቀረው የማይባል ትግል አድርጎአል፡፡ ለለውጡ ግንባሩን ሰጥቶ የተዋደቀው የሰፊው ህዝብ የድሀው ልጅ ነው፤ ታላቅ መስዋእትነትም ከፍሎ አልፎአል፡፡
ይህን ሁሉ ሲያደርግ ከድህነት የወጣች፣ ከኃላቀርነት የተላቀቀችና በኢኮኖሚም ያደገች ሀገር የመፍጠር ራእይና አላማ ይዞ ነበር፡፡ የያኔው ዘመን ለህዝቦች ነጻነትና እኩልነት በባርነት፣ በብሄራዊ ጭቆናና በቅኝ ግዛት  ቀምበር ስር ለነበሩት ህዝቦች ዋነኛ መታገያና የርእዮተ አለም መመሪያ ሁኖ ያገለግል የነበረው የማርክሳዊ ርእዮት ስለነበር የኢትዮጵያ ወጣቶችም ይሄንኑ ተቀብለው የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግር እንዴት መፍታትና አዲስ ሶሻሊስታዊ ህብረተሰብ መፍጠር ይቻላል? በሚለው ላይ ሰፊ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ውይይቶችን ሲያደርጉ፣ ሲከራከሩ፣ አይሆንም ይሆናል፣ የለም ሌላ አማራጭ ነው መከተል ያለብን ሲሉ ኖረዋል፡፡
የተለያዩ ድርጅቶችን፣ ህብረቶችን፣ መድረኮችን፣ ፓርቲዎችን ሲፈጥሩ፣ በሀሳብ ሲለያዩ ሲፋለሙ፣ ከዛም አልፎ ጎራ ለይተው ሲጠፋፉ፣ ሲወነጃጀሉ፣ አንዱ በሌላው ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲያደርግ፣ መገለል እንዲፈጠር ሲሰሩ፣ እጅግ በጣም ብዙ የሚባሉ፣ ለሀገር ያልበጁ ጥፋትና ውድመት ያስከተሉ ታሪኮች አልፈዋል፡፡
አስገራሚው ነገር በሁለት የአመለካከትና የአስተሳሰብ ጎራ ተለያይተው፣ በጠላትነት ተፈራርጀው፣ እስከመጠፋፋት ይደርሱ የነበሩት የሀሳብ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው፣ ለሀገርና ለህዝብ ሲባል አብረው ቆመው፣ ሀገራቸውን ወደተሻለ ምእራፍ ማድረስ ያልቻሉት፣ ለዚህም ያልበቁት መሰረታዊ የሚባል ልዩነት እንኩዋን የሌላቸው የህዝቡ ልጆች ነበሩ፡፡
በዚህ መልኩ ስንትና ስንት ለሀገርና ለህዝብ የሚበጁ፣ ብዙ ሊሰሩ የሚችሉ፣ ከፍተኛ እሳቤና እውቀት የነበራቸው ሀገሪቱ ለፍታና ደክማ ያፈራቻቸው ምሁራን በእርስ በእርስ መናቋቆርና መባላት በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክር ጠፍተዋል፡፡ ይሄ ሁሉ ለአንድ ደሀና ታዳጊ ሀገር ወጣቶች በሰላምና በመግባባት ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ማገልገልና መጥቀም፣ ማሳደግም ሲችሉ ታሪካቸው በመጠፋፋትና በሰዶ ማሳደድ መደምደም አልነበረበትም፡፡
አብዛኛው በስደት ሀገሩን ለቆ ቢወጣም ይሀው የቆየ ሀገርና ትውልድን ከፉኛ የጎዳ የመጠፋፋትና የመበላላት፣ የስም ማጥፋትና መገለል እንዲፈጠር አንዱ በሌላው ላይ የሚያደርገው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻና ቅስቀሳ ስራቸው ባህር ማዶም አብሮ ተሰዶ ዛሬም ከ40 እና 50 አመታት በኋላ እዛው ላይ ሁነው ጭቃ እያቦኩ ይገኛሉ፡፡ እንደ ሀገር፣ እንደ ህዝብ አለመታደልም ነው፤ ከወጣትነት እስከ ሽምግልና የዘለቀ ክፉ በሽታ ፡፡
ዛሬ ላይ፣ እነሱ ከሀገር ከወጡ በኋላ የተፈጠረውን አዲስ ትውልድ በተለይም ወጣቱን ኢላማ አድርገው እነሱ በሄዱበት የውድመት፣ የጥላቻ፣ የመናቋቆርና የመባላት መንገድ እንዲነጉድ ከባህር ማዶ ሁነው በማህበራዊ ሚዲያና በመሳሰለው የጥላቻና ሁከት ዘመቻ እያወጁ ይገኛሉ፡፡
እነሱ ልጆቻቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን የተወለዳቸውንና የተዛመዳቸውን ሁሉ ከሀገር  አውጥተው በአሜሪካና በአውሮፓ ዜግነት ተገማሽረው በድሎትና በምቾት እየኖሩ በሀገር ቤት ያለው ወጣት የደም መስዋእትነት እንዲከፍል ይቀሰቅሱታል፡፡ ዛሬም ከትላንትናው ውድቀታቸው አልተማሩም፤ መሰረታዊ ስህተታቸውን አልፈተሹም፡፡ ለምን በተደጋጋሚ ወደቅን? ለምንስ ለውጤት አልበቃንም? ችግራችን ምን ነበር? ብለው ለማየት አልበቁም፡፡ 
ከኢትዮጵያ 12 ሺህ ማይልስ እርቀው በሰላም ሀገር እየኖሩ ሀገር እንዲታወክ፣ የሰው ህይወት በተለይም ወጣቱ እሳት ውስጥ እንዲማገድ እየቀሰቀሱ ወጣቱ ረግፎና ሞቶ እነሱ ደግሞ በህዝብ ልጅ ደምና መስዋእትት የፖለቲካ ስልጣን መጥተን እንይዛለን ብለው የደንቆሮ እሳቤ ያስባሉ፡፡ በሀገር ቤት በሚፈጠሩ ግጭቶች የዜጎችን ፎቶዎች በማንሳት በሚያሰቅቅ ሁኔታ መነገጃ ገንዘብ ማግኛና እርዳታ መሰብሰቢያ አድርገውታል፡፡
በሀገር ቤት የተፈጠረውና የሆነውን ሁኔታ ለማረም ለማስተካከል ተገቢ ያልሆኑትንም እርምጃዎች ህዝቡ ራሱ እየተቃወመ፣ መብቱ እንዲከበር እየታገለ ባለበት ሁኔታ የአክራሪው ጽንፈኛ ተቃዋሚ ሀይል ሁሉም ባይሆኑም ለግብጽና ለሻእቢያ አሽከርነትና ተላላኪነት አድረው ድርጎም እየተሰፈረላቸው በመክለፍልፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በእርግጥ የሀገሬና የወገኔ ጉዳይ ያሳስበኛል በሚል ተቃውሞውን በውጭ ሀገራት የሚያሰማው ዲያስፖራ ችግሮቹ ሰላማዊ መፍትሄና እልባት እንዲያገኙ፣ ሀገሪቱ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ እንዳትገባ፣ የመከፋፈልም ሆነ የመፍረስ አደጋ እንዳያጋጥማት መንግስት ማረምና ማስተካከል ያለበትን እንዲያርምና እንዲያስተካክል ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ዜጎች ልክ በሀገር ቤት ያለው ህዝብ እንደሚለው ህጋዊ የሆነው የመብት ጥያቄአችን በህጉና በአግባቡ ይመለስልን፤ መብታችን ተረግጦአል፤ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የፍትህ እጦት ነግሶአል፤ መልካም አስተደደር የለም፤ ባለስልጣናት የመንግስትና የህዝብን ሀብት መሬት  ዘርፈዋል፤ ይህንን ማረምና ማስተካከል ከቻላችሁ አርሙ፤ ካልቻላችሁ ህዝቡ ከዚህ በላይ መታገስ አይችልም፡፡ ሀገር የህዝብ እንጂ የመንግስት የግል ንብረት አይደለችም፤ በሚል የሚሰማውን የህዝብ እሮሮ የሚጋሩና ለሰላማዊ መፍትሄም ድምጻቸውን የሚሰሙ ናቸው፡፡ ሀገራቸው እንድትበጠበጥ፣ ህዝባቸው ፍጅት ውስጥ እንዲገባ በግርግሩም ሻእቢያና ግብጽ ኢትዮጵያን የመበታተንና የማጥፋት እድሉን እንዲያገኙ የሚፈቅዱ አይደሉም፤ ይሄ ተገቢ ነው፡፡
በሌላኛው ጫፍ ያለው ጽንፈኛና አክራሪ በጥላቻ ዳፍንት ተውጦ የሚዋኘው ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ በህዝቡ ውሰጥ የታየውን ተቃውሞ የመራሁት እንዲነሳም ያደረግሁት እኔ ነኝ  በህዝቡ ውስጥም ገብቼ እየሰራሁ ነው በሚል ህዝቡን ለማስመታትና ተመርሮ እንዲነሳ፣ የከፋ እልቂትም እንደፈጠር በማቀድ የፖለቲካ ቁማርና ንግድ በመጫወት ያለው የኤርትራና የግብጽ ቅጥረኛ ሀይል በህዝብ ስም መነገዱን ማቆም አለበት፡፡ በሌለበትና ባልዋለበት ጎራም ማቅራራቱንም እንደዛው፡፡
የሀሰት ቅስቀሳና የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ በመርጨትና ወጣቱን በማነሳሳት ለተፈጠረው የህይወት መጥፋትና የንብረት መውደም በታሪክም በህዝብም ፊት ተጠያቂ ናቸው፡፡ በአማራውም ሆነ በኦሮሚያ የተነሳው ጥያቄ  የመብታችን ይከበር ጥያቄ በራሱ በህዝቡና በህዝቡ ብቻ የተመራ ነው፡፡
ይሄንን አጋጣሚ በመጠቀም እኛ ነን የመራነው በሚል የፖለቲካ ትርፍና አለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት ያስችለናል፤ የገንዘብና ሌሎችም እርዳታ እናግበሰብስበታለን ብለው በልዋሉበት የሚያናፉት ጽንፈኞች በህዝብ ስምና ደም እየነገዱ ገንዘብ እየሰበሰቡ በድሀው ልጅ መውደቅ የንግድ ስራ እየሰሩበት መሆኑን ህዝቡ ካወቀው እጅግ ሰንብቷል፡፡ ዛሬም በህዝብ ቁስል ላይ እንደገና ቤንዚን እያርከፈከፉ ሀገርን ለማጥፋት፣ ህዝብንም የመረረ ዋጋ ለማስከፈል ዘረኛ ግጭት ቆስቋሽ መርዛቸውን እየረጩ ይገኛሉ፡፡ የበላይ አለቆቻቸው ግብጽና ሻእቢያ መሆናቸውን ህዝቡ ጠንቅቆ አውቆታል፡፡ ስለዚህም ከእነሱ የሚጠበቅ አንድም ነገር የለም፡፡
በሀገር ውስጥ የተፈጠረው ችግር መነሻ ምክንያቱ በውል የሚታወቅ በመሆኑ የህዝብ “መብቴ ይከበርልኝ፤ ህገመንግስታዊ ጥያቄዬ ይመለስል” ሲል ያነሳው ጥያቄ ስለሆነ ህግና ስርአት ባለው መልኩ፣ በሰላማዊ ሁኔታ የሚፈታ እንጂ ለሻእቢያና ለግብጽ ፍላጎትና አላማ መሳካት አንዲትም ቀዳዳና በር የሚከፍት አይደለም፡፡ ወጣቱንም የእዚህ እርኩስ አላማቸው መጠቀሚያ ሊያደርጉት አይችሉም፡፡ አውቆአቸዋል፡፡ ህዝቡም ልጆቹን አሳልፎ ለጥፋት ሀይሎች አይሰጥም፡፡ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መሳሪያም አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ለዘልአለም ትኑር!!!!