ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የተፋሠሡ ሃገራትን ጥቅም በጠበቀና ማንንም በማይጎዳ የWin-Win (ማሸነፍ – ማሸነፍ) ግጭት አፈታት መርሆ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት መጀመሯን ተከትሎ (የግብጽ መዋዠቅ እንደተጠበቀ ሆኖ) የተፋሠሡ አባል ሃገራት እና በተለይም ሱዳን ዓባይን በትብብር ለማልማትና ለማበልጸግ ያላቸውን ፍላጎት በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል። የላይኞቹ ተፋሠሥ ሃገራት በአንቴቬው ስምምነት የተዘጋጀውን የትብብር ማዕቀፍ መቀበላቸውን በፊርማቸው አረጋግጠው ለተግባራዊነቱ በየሃገራቱ ፓርላማ በማጸደቅ ሂደት ላይ መሆናቸውና ኢትዮጵያና ኮንጎ ደግሞ የየሃገራቸው የስልጣን የበላይ በሆነው ምክር ቤት ማጽደቃቸው ይታወቃል። ከዚሁም ጋር ተያይዞ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሠስ ሃገራት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ካለ ኑ በጋራ እንመርምር በሚል ኢትዮጵያ በራሷ ተነሣሽነት ባቀረበችው ሃሳብ መሠረት የተቋቋመውና የግብጽ ልዑካንን ያካተተው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ግድቡ በታችኛው ተፋሠሥ ሃገራት ላይ የሚያስከትለው አንዳች ጉዳት እንደሌለ፤ ይልቁንም በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግብጽና ሱዳን የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በገለጹበት ማግስት በሙርሲ ጊዜ የነበሩት የግብጽ ባለሥልጣናትና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ቀረርቶና ክተት አዋጅ አሰምተው የነበረ መሆኑም ይታወሳል። ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እውን እንዳታደርግ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን መቀየሣቸውን አውቀው በስህተትም ይሁን ሳያውቁት በድፍረት መናገራቸውን በቀጥታ የሃገሪቱ ቴሌቪዥን ሲተላለፍ መመልከታችንም ይታወሳል፡፡
ዛሬ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተሳካ ሁኔታና የተፋሰስ ሃገራቱን የላቀ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ በሚያረጋግጥ የግንባታ ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም የሙርሲው ካቢኔ እና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ካስቀመጧቸው የማሠናከያ ስልቶች ውስጥ ኢትዮጵያን ማተራመስ ለዚህ ደግሞ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ የሚገኙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን መጠቀም የሚለው ግንባር ቀደም እና በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ተቀምጦ የነበረ መሆኑ አይዘነጋም።
ግብጽ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለማሰናከል ከዘረጋቻቸው ሥትራቴጂዎች መካከል ተቃዋሚውንና የጎረቤት ሃገራትን በተላላኪነት እና በአፍራሽ ተልዕኮ ማሣተፍ ነው የሚሉትን ሁለት አማራጮች በሙርሲ የተተካው የአልሲሲ መንግስት እንደማያደርገው ቃል ከመግባት አልፎ ለድርድር በሩን መክፈቱ ግብፅ ወደተሻለና ዘመናዊነት እየመጣች ስለመሆኗ ምስክርንት ይሰጣል። የአልሲሲ መንግስት አሁንም የቆመበት ትክክለኛውን ቦታ ደምድሞ ለመናገር አስቸጋሪ ቢሆንም ከቀደሙት የተሻለ እና የሰለጠነ መንገድ ላይ ለመቆም ፍላጎቱ እንዳለው አረጋጋጭ የሚሆኑ በርካታ አስረጂዎችን መጥቀስ ይቻላል።
በግድቡ ግንባታ ዋዜማና ሰሞን የነበሩትን እንኳ ትተን ስለግድቡ ግንባታ የምህንድስና ሳይንስ የአባይ ወንዝ ተፈጥሯዊ የጉዞ አቅጣጫውን እንዲይር በተደረገ ጊዜ የነበረውን የግብጽ አንዳንድ ልሂቃኖችና መገናኛ ብዙሃኖች ዋይታ ተከትሎ የነበሩትን የሶስትዮሽ ውይይቶች ብንመለከት ይህንኑ ወደመግባባት ያመራ ድርድር የሚያጠይቅ እና የአልሲሲ ካቢኔን ወደሚያዋጣው መንገድ የማጋደሉን እውነታ እናገኛለን ።
በዚያ ሰሞን የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በሚያግባባቸው ነጥብ ላይ ለመድረስ ለቀናት መደራደራቸው ይታወሳል። ወደተሻለው እና ወደሰለጠነው መንገድ ግብጽ ስለማጋደሏ ፍንጭ የሚሰጠው አስረጅ ይህ ብቻ አይደለም። ቀደም ሲል በተደረጉ ውይይቶች አገራቱ በፍጥነት ወደ ስምምነት መምጣት ስላልቻሉ፤ ጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል በሚል ግብፅ ውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችንም አካቶ እንዲካሄድ በጠየቀችው መሰረት ከአገራቱ የውሃ ሚኒስትሮች በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እነዚህን ውይይቶች መቀላቀላቸውም ሌላኛው አስረጅ ነው።
በተለይ በካርቱም ተካሂዶ በነበረውና በትንሹ ሶስት ቀናት በወሰደው የሚንስትሮቹ ድርድር ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ተግባብተው የተፈራረሙበት ሰነድ እና ባለፈው መጋቢት ወር የሶስቱ አገራት መሪዎች የፈረሙበትን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት ላይ ተወያይተው ተግባብተው መለያየታቸው የአልሲሲን መንግስት የአባይ ፖለቲካ አወንታዊ ዝንባሌ የሚያጠይቅ ነው።
በተለይ የካርቱሙ ስብሰባ ውሳኔዎች ዝርዝር በአራት ነጥቦች ላይ ብቻ ያተኮረ እና ሃገራቱ በአባይ ወንዝ በትብብር የሚለሙበትን እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለመቀበል ዝግጁ ስለመሆናቸው ፍንጭ የሰጠ መሆኑና በዚህም ጽንፈኞቹ የግብጽ ልሂቃንና ሚዲያዎች የበለጠ ያበጡበት አጋጣሚም የተፈጠረበት ክስተት የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ የማይዘነጋ እና የግብጽ ባለስልጣናትን በትብብር ስለመልማት ያላቸውን አቋም በመለወጥ ሂደት ላይ ስለመገኘታቸው ያመላከተ ነው።
ከነዚህ አስደማሚ እና የአቋም ለውጥ ከታየባቸው አጀንዳዎች የመጀመሪያው እና ስለጉዳያችን መጠቀስ የሚገባው ነጥብ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መሪዎች ደረጃ የተፈረመውን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት ለመተግበር ቁርጠኝነታቸውን ያረጋገጡበት መሆኑን የተመለከተው ነው።
በአገራቱ መካከል የበለጠ መተማመን ለመፍጠርም በዚህ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች ግድቡን እንዲጎበኙ ግብዣ አቅርባም ይህንን ግብዣ አገራቱ መቀበላቸውም ስለትብብር ስምምነቱ እና ማንም አሸናፊ እና ማንም ተሸናፊ ለማይሆንበት ልማት ግብጽ ቁርጠኛ እየሆነች የመምጣቷ ነገር ከመምሰል ወደመሆን እየተሸጋገረ መሆኑን ያመላከተ ነው።
ኢትዮጵያ አንዳንድ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ያልተነሱ ጉዳዮችን በማንሳት እና መግባባት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ባልተገባ መንገድ በመተርጎም ከእውነታ የራቀ ዘገባዎችን እያወጡ ስለመሆናቸው በየስብሰባው ላይ እያነሳች መሞገቷ ተገቢ ሲሆን፤ ግብጽም በበኩሏ እርሷን የማይወክል መሆኑን በመንግስት ደረጃ በተደጋጋሚ ማውሳቷ በትብብር ስለመልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑ አያከራክርም።
በውይይቱ ላይ ግብፅ የሚካሄዱት ጥናቶች እስከሚጠናቀቁ ድረስ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እንድታቆም ጠይቃለች ወይም በዚህ ስብሰባ ትጠይቃለች የሚሉ የተዛቡ ዘገባዎች ወጥተው የነበረ ቢሆንም ግንባታው እስካሁን ያለአንዳች ፋታ የቀጠለ መሆኑና በድርድሩ ከስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ነጥቦችም አንዳች ለውጥ ያልተደረገባቸው መሆኑ ይታወቃል። የአልሲሲ መንግስት የሚመራው የግብጽ ቴሌቪዥን ካላም ጁራይድ ወይም የጋዜጦች ወሬ በሚለው ፕሮግራሙ ያሰራጨው ዘገባ ግን ግብጽን አይወክልም ብሎ ለመቀበል የሚከብድና (ምንም እንኳ ዘገባው ሙልጭ ያለ ቅጥፈት መሆኑ የማያከራክር ቢሆንም) ምናልባትም ከላይ የተመለከተውን እና በግንባታው የልጅነት እድሜ የሙርሲ ካቢኔ ያቀረባቸውን አማራጮች ተግባር ላይ ከማዋል እንደማይመለሱ ጥቆማ የሚሰጥ ነውና ዘገባውን በጥቅሉ ተመልክተን እንደምታውን እንፈትሽ።
የዚህን ዘገባ ጭብጥ ስናጤን ከላይ በተመለከተው መልኩ ከቀደሙት የግብጽ መንግስታት የተሻለ ለውጥ አሳይቷል በተባለው እና በአልሲሲ በሚመራው የመንግስት ቴሌቪዥን የተላለፈ ዘገባ እንደሆነ ባለመዘንጋት መሆኑን በቅድሚያ ማስታወስ ያስፈልጋል።
በአልሲሲ በሚመራው መንግስት ባለቤትነት ስር የሚገኘው ይህ ቴሌቪዥን የካላም ጁራይድ ፕሮግራሙን ሲጀምር አስደሳችና የግብጻውያንን ጉሮሮ የሚያርስና ልባቸውን በሃሴት የሚሞላ ዜና የደረሰው መሆኑን በመግለጽ ነው። ይህም ዜና ወደታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሚያመሩ መንገዶች ሁሉ መዘጋታቸውን የተመለከተ ነበር። ለዚህም ዜናው ምንጭ ያደረጋቸውን የኮንጎ ወንዝ አስተባባሪ ዶክተር ናንሲ ኡመር በቀጥታ ስልክ ያስገባው የካላም ጁራይድ አዘጋጅ ዶክተሯ ከኦሮሞ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ መሪዎች ጋር ቁጭ ብለው የተደወለላቸው መሆኑን በመግለጽ እነዚህ ተቃዋሚዎች በሰሞኑ አመጽ የግብጽን ባንዲራ እንዳውለበለቡ እና መንገዶችን ሁሉ ስለመዝጋታቸው አውስተው፤ መላው የግብጽ ህዝብ እና መንግስት ይህን አመጽ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሞ ህዝብን የኩሽ ነገድ እንደሆነ እና የግብጽ አካል መሆኑን እስከመግለጽ የደረሱት ጋዜጠኛ እና ዶክተር ናንሲ ዶክተር ፋዮም የተባሉ የሃገራቸው ምሁር እና በአባይ ላይ በተለየ እና ጽንፍ በረገጠ አቋሙ የሚታወቀውን ናስር አባይን በተመለከተ ከተናገሯቸው እኛ እድሜ ልካችንን አናርፍም፤ በየመንገዳችን ከቆመው ጋር ሁሉ እንቀላቀላለን የሚለውን እና ለመሞቱማ እዚያው ሄደን እንሞታለን የሚለውን በመጥቀስ፤ ይልቁንም ፕሬዝዳንት አልሲሲ እነሱ የማደግ መብት እንዳላቸው ሁሉ እኛም የመኖር መብት አለን ማለታቸውን በማጉላትና ስንቅ በማድረግ የግብጽ ህዝብ እንዳይተኛ እና ተቃውሞውን በመደገፍ ግንባታውን ማሰናከል የሚገባው መሆኑን የሚያሳስብ ነበር አጠቃላይ የሆነው የፕሮግራሙ ጭብጥ።
የኦሮሞ ህዝብ ሺህ ጊዜ ቢከፋው የግብጽን ባንዲራ ያውለበልባል ማለት ሙልጭ ያለ ስህተት መሆኑ ቢታወቅም የመንግስት ሃላፊና የመንግስት የሆነው ሚዲያ በዚህ አግባብ ያላቸውን ጥላቻ ማንጸባረቃቸው በእርግጥም የሙርሲ ካቢኔ ካቀረባቸው አማራጮች የመጀመሪያውን እና ከላይ የተመለከተውን ከማድረግ የማይመለሱ መሆኑን ያሳያል።
የግብጽ የምን ጊዜም ዓላማ ኢትዮጵያ ለዘላለም ከርስ በርስ ጦርነት እንዳትላቀቅ መሆኑንም ያጠይቃል፡፡ በእርግጥ እንደ አብዛኛው የአላማችን ግዙፍ የውሃ ሃይል ማመንጫ ግድቦች እና የናይል ጉዳይ እንደመሆኑ ታለቁ የህዳሴ ግድብ አለማቀፋዊ መልክ የያዙ ፈተናዎችን መጋፈጡ አይቀሬ ነው፡፡ እየተጋፈጠም ነው፡፡ ታዲያ ፈተናዎቹ ከሃገር ሃገር ክብደታቸው ይለያይ ይሆናል እንጂ የመከሰታቸው ነገር የማይካድ ወይም ‹‹ለምን መጣ?›› የማይባል ነው፡፡ ብዙ ሃገራት እነዚህን ፈተናዎች ተጋፍጠው አላማቸውን ከግብ አድርሰዋልና፡፡ ዋናው ሃገራዊ መሰረታቸውን መጠበቃቸው፣ በቁርጠኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ መታገዛቸው፣ በህዝባዊ የእኔነት ሥሜት መደገፋቸው ወዘተ…ነው የፈተናዎቹን ክብደት የሚያቃልለው፡፡
የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመስርተን እንደምንሰራና ለዚሁም የሰጠናቸው በርካታ ማረጋገጫዎች በግብጽ ዘንድ መተማመን እየተፈጠረ መምጣቱን የአልሲሲ መንግስት ይፋዊ በሆኑ መድረኮች በሰጣቸው መግለጫዎች ብንገነዘብም፤ ከላይ በተመለከተው አግባብ በመንግስት ሚዲያና በመንግስት ሃላፊ እንዲህ ሲባል መስማትና ማየት በእርግጥም ለእነርሱ የመኖር መብት የኛን የማደግ መብት መንፈግ አስፈላጊ መሆኑ ላይ የቆረቡ ስለመሆናቸው የሚያጠይቅ ነው።
ያም ሆኖ ግን ስለታላቁ የኢትጵያ ህዳሴ ግደብ ታላቅነትና ጠቀሚነት ለመመስከር ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ አዎ! ሰው መሆን ብቻ!!! ዛሬ በኒኩለር ጣጣ፣ በነዳጅ ተኮር ኢኮኖሚ (Resource curse economy) መዋዥቅ፣ በኢ-ታዳሽ የኃይል ማመንጫዎች እንከን ወዘተ … ለምትታመሰው ዓለማችን፣ እንደታላቁ ህዳሴ ግድብ ዓይነት ፕሮጀክቶች እንደውድ ሽልማት ሊቆጠሩ እንጂ የውዝግብ መንስኤ ሊሆኑ እንደማይገባ በእርግጥም የግብጽን መንግስት የማይወክሉ ከሆነ አልሲሲ እነዚህን ነውጠኛ ሚዲያዎችና ልሂቃኗን አደብ በማስገዛት ስለጋራ ልማት ያላቸውን አቋም ሊያረጋግጡ ይገባል።
እንደ ታለቁ የህዳሴ ግደብ ዓይነት ፕሮጀክቶች በየትኛውም መስፈርት ልቆ የሚወጣ የሚተነተንና ሰርክ የሚዘከር ገድል ያላቸው መሆኑንም በአደባባይ ከመናገር አልፈው ከላይ የተመለከተው ዘገባን ሊያስተባብሉ ይገባል ።
በኛ በኩል የህዳሴው ግድብ ለተፋሰሱ ሃገራት ሁሉ የተሻለ ጠቀሜታ እንዳለው በተለይም ለግብጽና ሱዳን ደግሞ የላቀና ዘለቄታነት ያለው ፋይዳ እንዳለው በማስገንዘብ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲፈጠርና ግድቡም የሠላም ፕሮጀክት እንደሆን በተግባርም ሆነ በወረቀት ሃገራችን ለአለም እያረጋገጠች ነው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሃገራዊ መግባባት ፈጥኖ የሁሉንም ህዝብ አሻራ በማኖር ቀን ከሌት እየተገነባ የሚገኝ የባንዲራ ፕሮጀክታችን እንጂ በአመጻ የሚቆም እንዳልሆነም አልሲሲም ሆኑ ሹሞቻቸው ለህዝባቸው ሊገልጹና ሊያረጋግጡ ይገባል። የህዳሴው ግደብ በዚህ ዘመን የተገኘ የሃጋራችንና የህዝቦቿ ታላቅ ስጦታና ቀን ከሌት የምንተጋለት እንጂ በካላም ጁራይድ የጋዜጦች ወሬ የማይሰናከል፣ ድንቅና የሁሉም ኢትዮጵያውያን አይንና ጆሮ ቀን ከሌት የማይነጠለው መሆኑንም ግብጻውያን አውቀው በሰለጠነና አዋጭ በሆነው የትብብር መንፈስ ብቻ እንዲጓዙ እና ተንኳሾቻቸውን እንዲያስታግሱ እንሻለን።
የህዳሴው ግድብ በዚህ ዘመን የተገኘ የሃጋራችንና የህዝቦቿ ታላቅ ስጦታ እንጂ በጋዜጦች ወሬ የሚርድ አይደለም። ይህ ብቻ አይደለም የህዳሴው ግድብ እንደአድዋ ድል እስከወዲያኛው ለትውልድ የሚዘክር እና የኢትዮጵያውያን ቋሚ ሃውልት እንደሆነም እንዲታወቅልን እንፈልጋለን። በጥናትም በተግባርም ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጉዳት እንደሌለው የተረጋገጠ በመሆኑም ፕሮጀክቱ ሃይል የማመንጫ ብቻ ሳይሆን የሰላም ፕሮጀክት እንደሆንም ግብጻውያን እንዲያውቁትና መዋዠቃቸውን እኒዲያቆሙልን እናሳስባለን።
የሀገራችንን የልማት ጉዞ በጥበብና በእውቀት ለማሳለጥ እና በትብብር የመልማትን ሚስጥራት ለመግለጥ የታላቁን ግድብ ዱካ መከተል ለብቻው በቂ ነው፡፡ የሃገሪቱን የልማት ጉዞ ቁልጭ አድርገው ስለሚያሳዩ ግዙፍና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶቻችን ልምድ የምንቀስምበት፣ ተሞክሮ የምንቀምርበት፣ ይቻላልን የምንረዳበት ብቻ ሳይሆን ልናወራቸውም መነሻና መንደርደሪያ የሚሆነን ይልቁንም የማደግ መብታችን በደማቁ የተገለጠበት፤ የእነርሱም የመኖር መብት በላቀ ደረጃ አስተማማኝ የሚሆንበት ይኸው ታላቁና ዕንቁ ፕሮጀክታችን ነው፡፡
ይህ ፕሮጀክት የባለሙያዎቻችንን ላብ እየጨመቅን፣ የምሁራኖቻችንን እውቀት እየተነተንን፤ ሃገራዊ ደረጃችንን እየመዘንን ወዘተ … ብሄራዊ መነቃቃት እንድንፈጥርበት የተሰጠን የዘመኑ ስጦታችን መሆኑንም አለም በተገነዘበው አግባብ ከላይ የተመለከትናቸው ነውጠኞችም በመንግስታቸው ልክ እንዲገነዘቡን እንሻለን፡፡ ለሌሎች ፕሮጀክታችን እና ልማታዊ ጉዟችን ማጀቢያ የሚሆነን ሙዚቃ፣ ስኬቶቻችንን የምናደንቅበት ስጦታ፤ ልማታዊ ድርሳኖቻችንን የምንለብጥበት፣ ኢትዮጵያዊነታችንን የምናጀግንበት፤ የነገዋን ኢትዮጵያ እያየን ህዝባዊ ተሳትፎን የምናጠነክርበት፣ የእነርሱንም ተስፋ የምናለመልምበት ፕሮጀክታችን እንደሆነም እንዲገነዘቡን እንሻለን፤ አጥብቀን እንሻለን!!!!