ታከለ አለሙ
የቀለም አብዮቶች በአለማችን ውስጥ ብዙ ጥፋትና ውድመት አስከትለዋል፡፡ መሪው አደራጁና አቀናባሪው አለም አቀፉ የኒዮ ሊበራል ሀይል ነው፡፡ ብሄራዊ ድንበር ዘለል አህጉር ዘለል የሆነ በአለም ደረጃ በሚገኙ ሀገራትና መንግስታት ውስጥ የራሱን አላማና ግብ ለማሳካት ከየሀገራቱ እምቅ የተፈጥሮ ሀብታቸውንና ጥሬ ሀብታቸውን እንደልቡ ለማጋበስና ለማግበስበስ እንዲመቸው የቀለም አብዮት እንዲቀሰቀስ ያደርጋል፡፡
በትርምስና በሁከቱ መሀል ቀድሞ ያደራጃቸውን ያሰለጠነናቸውን በአመጹን በመምራት ረገድ ስልጡን መሀንዲስ አድርጎ የቀረጻቸውን ሰዎች በአንድ ሀገር በሚገኝ ህዝብ ውስጥ በማሰማራት የህዝቡን ብሶትና ጥያቄ ችግር በመጠቀም አመጽና ሁከት እንዲነሳ እንዲቀጣጠል ያደርጋሉ፡፡ በስልጣን ላይ ያለውን ለእነሱ ፖሊሲ መፈጸም አልመች ያለውን መንግስት በሀይል በአመጽ በብጥብጥና በሁከት እነሱው በሚመሩትና በሚቆጣጠሩት መንገድ ተገዶ ከስልጣን እንዲወርድ ያደርጋሉ፡፡ አስቀድመው ለዚሁ ተግባር ያሰለጠኑዋቸውንና ያስተማሩዋቸውን ሰዎች በሀገር መሪነት ስልጣን ላይ እንዲቀመጡ ያደርጋሉ፤ አድርገዋልም፡፡
እነዛ ሰዎች ወይም የፖለቲካ ድርጅታቸው ወደፖለቲካ ስልጣኑ ከወጡ በኃላ ለኒዮ ሊበራሉ ሀይል የማይንበረከኩ ከሆኑ ደግሞ መልሰው በወኪሎቻቸው አማካኝነት በህዝቡ ውስጥ የአመጽና የሁከት ቅስቀሳ በማድረግ ህዝቡ የከረረና የመረረ ተቃውሞ በማሰማት አደባባይ እንዲወጣ ያደርጉታል፡፡
ስራ እንዲያቆም ኢኮኖሚው እንዲሽመደመድ ከጸጥታ ሀይሎች ጋር ግጭት እንዲፈጠር ሰው እንዲሞት ንብረት እንዲወድምና ውጥረቱ አይሎ አለም አቀፍ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ያደርጋሉ፡፡ ጆርጂያን ኡክሬንን ሌሎችንም የኤሽያ ሀገራት እንዲሁም ከአፍሪካ ግብጽን ሊቢያን ሶርያን የመንን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በግብጽ የሙባረክን መንግስት ከስልጣን ለማውረድ ሲል ኒዮ ሊበራሉ ሀይል የሸረበው ሴራ በአቀደው መሰረት አልሄደለትም፡፡ እነሱ ሳይንቲስቱን አልባራዳይን ነበር ከስደት አምጥተው ስልጣን እንዲይዝ የፈለጉት፡፡ በግብጽ አክራሪውና ጽንፈኛው የሙስሊም ብራዘር ሁድ ድርጅታዊ ክንፍ ሰፊ መሰረት የያዘና ከ40 አመታት በላይ የዘለቀ ታሪክ ያለው በመሆኑ የቀለም አብዮቱ እቅድና ንድፍ ኒዮ ሊበራሉ ሀይል ባቀደው መሰረት ሳይካሄድ ቀርቶ ተጠለፈ፡፡መጨረሻውም የከፋ ሆነ፡፡
በሊቢያም ጋዳፊን ከስልጣን ማውረድ ቢሳካላቸውም ሀገሪቱ በአክራሪ እስላማዊ ሀይሎች እጅ ስር ወደቀች፡፡ዛሬም የአልቃይዳና የአይሲስ መናሀሪያ ለመሆን በቃች፡፡እንዲያውም ከጋዳፊ መንግሰት መውደቅ በኃላ በቀጠናው አክራሪው እስላማዊ ሀይል አልቃይዳና አይሲስ ከዚህ በፊት ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ትልቅ ጉልበትና አቅም ለማግኘት በቁ፡፡
ዛሬ ላይ ጋዳፊን ከስልጣን ለማውረድ በቀለም አብዮት ቀመራቸው ያደረጉትን ስህተት ምእራባውያኑ አምነው ቢቀበሉም ነገሩ መመለሻ አጥቶ እዳው በገዘፈ መልኩ ለእነሱው ተረፈ፡፡ከሊቢያ የተዘረፈው የጦር መሳሪያ ከሰሜን አፍሪካ እስከ ምእራብና ምስራቅ አፍሪካ እስከ ባብል መንዴብ ላለው አክራሪ ሀይል በስፋት መታጠቅ በሽብር ስራ መሰማራት አለምን በአሸባሪዎች ስጋት ስር እንድትወድቅ የበለጠ ምክንያት ሆነ፡፡
ኒዮ ሊበራሉ ሀይል በጋዳፊ ላይ የቀለም አብዮት ለማስነሳት የተነሳበት ዋኛ ምክንያት ጋደፊ የሊቢያን የተፈጥሮ ሀብት ጋዝና የነዳጅ ዘይት አላስመዘብርም በማለቱ ከዚያም ባለፍ በአፍሪካ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ሊኖራቸው አይገባም በሚል የአፍሪካን መሪዎች አስተባብሮ እቅዳቸውን በማክሸፉ ነበር፡፡ ጋዳፊ የቱንም ያህል አምባገነን ቢሆንም ለህዝቡ በእጅጉ የጠቀመ መሪ ነበር፡፡ እስከወደቀበት ግዜ ድረስ ሊቢያውያን መብራት ውህ የቤት ኪራይ የህክምና የትምህርት ወዘተ ነጻ በመሆኑ አይከፍሉም ነበር፡፡ውጭ ሄደው በፈለጉበት ሀገር የመማር መብታቸው የተከበረ ሲሆን ወጪው የሚሸፈነው የኪስ ገንዘብ በወር 1200 ዶላር የሚከፈላቸው ከሊቢያ መንግስት ነበር፡፡ሲያገቡ ወይም የግል ስራ እርሻ የመሳሰለውን እንጀምራለን ሲሉ ግማሽ ወጪው የሚሸፈንላቸው በጋዳፊ መንግስት ነበር፡፡
ለሁሉም ብዙ ማለት ቢቻልም ሊቢያውያን ከእንግዲህ ያንን ዘመን በ200 አመታት ውስጥም ተመልሰው አያገኙትም፡፡
ኒዮ ሊበራሉ ሀይል በሶርያ የቀለም አብዮት በማካሄድ አሳድ አልበሽርን ከስልጣን እናስወግዳለን ብለው በወኪሎቻቸው አክራሪ ተቃዋሚዎች አማካኝነት የቀሰቀሱት የህዝብ አመጽ ሶርያን እንደ ሀገር አወደማት፡፡ህዝብዋም አለቀ፡፡ከተሞችዋም ታሪካዊ ቅርሶችዋም ወደሙ፡፡ፈራረሱ፡፡በህይወት የተረፈውም ህዝብ ሀገር ለቆ ተሰደደ፡፡
አጋጣሚው የተመቸው አልቃይዳና አይሲስ በሶሪያ ምድር ላይ እንደልቡ ፈነጨበት፡፡ዛሬም ሶርያ የጦር አውድማ ሁና ቀጥላለች፡፡ያችን ሀገር መልሶ ለመገንባት ስንት ዘመንና ስንት ትውልድ እንደሚጠይቅ ለመናገር ይከብዳል፡፡ይህ ሁሉ የሆነው አስተዋይነት በሌለው የሶርያ አክራሪ ተቃዋሚ ሀይልና በመንግስቱም በኩል በነበረው ግትር አቓም ተናንቀው እነሱም ያለቁትን ያህል አልቀው የገደሉትን ያህል ገድለው ዛሬም እየተጋደሉ ቀጠሉ፡፡
ሶርያ ጥንታዊትዋ ሀገር የልጆችዋ የመቃብር ስፍራ ሆነች፡፡ምንም ነገር የሌለባት ሙትና በድን ከተማ፡፡ በድን ሀገር፡፡ነጋ ጠባ የመድፍና የመትረየስ የአውሮፕላን ድብደባ በምድርና በሰማይዋ ላይ የሚያጉዋራባት የሚያፉዋጭባት የሚሰማባት ሀገር፡፡የቀለም አብዮቱ ትሩፋት ይሀው ነው፡፡ የቀለም አብዮቶች ብርቱካናማ ቡልዶዘር ቀስተደመና አረንጉዋዴ የሚባል ወዘተ ስሞች እየወጣላቸው በየሀገራቱ እንዲካሄዱ ከመደረጉ በፊት በዚያ ሀገር በተቃዋሚነት ያሉ የፖለቲካ መሪዎችና የፓርው አባላት ወደተለያዩ ሀገራት እንዲሄዱና እንዲማሩ ወጪያቸው የሚሸፈነው በምእራባውያኑ መንግስታት እንዲሸፈን ይደረጋል፡፡
ስልጠናው የሚሰጠው በደህንነትና መረጃ ተቓማቱ አማካኝነት ሲሆን እንዴት ህዝቡ በመንግስት ላይ አምጾ እንዲነሳ ለማድረግ እንደሚቻል፤አመጾቹን የማቀጣጠልና በተለያዩ አካባቢዎች የማስፋፋት ጥበቦች፤ህዝቡን ከጸጥታ ሀይሎች ጋር ማጋጨትና ደም ማቃባት፤ ህዝቡን በምሬትና በበቀል ሆ ብሎ እንዲነሳ ማድረግ፤ የመንግስት ንብረቶችን ለመንግስት ቅርበት አላቸው የሚባሉ የግለሰብና የባለስልጣናት ናቸው ተብለው የሚታመኑ ንብረትና ድርጅቶችን ማውደም መሪዎችን ማጥፋት፤የሀሰት ፈጠራ የሽብር ፕሮፓጋንዳዎችን ማዛመት መንዛት፤የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖር ውጥረትና ጭንቀት በህዝቡ ውስጥ እንዲሰፍን ማድረግ የኢኮኖሚ ተቓማትን ማሽመድመድ ተቃውሞው እያየለ ይበልጥ እየገነፈለ እንዲሄድ ማድረግ የሚደርሰውን ጥፋትና ውድመት በአለም አቀፍ ሚዲያዎች በሶሻል(ማህበራዊ ሚዲያዎች) በሰፊው እንዲሸፈን ማድረግ ወዘተ ስራዎችን በሰፊው በተቀነባበረ ሁኔታ ይሰራሉ፡፡
በሀገር በውስጥ ያሉት የቀለም አብዮቱ መሪዎች(አክራሪው ተቃዋሚ) እለት በእለት ለውጭ ሀይሎቹ ሪፖርት በማድረግ ተለዋጭ አመራር ይቀበላሉ፡፡ያስፈጽማሉ፡፡ይህን የሚያደርጉት የተቃውሞው ፖለቲካ መሪዎች በታቀደው መሰረት ከተሳካላቸው መንግስታዊ ስልጣኑን ይይዛሉ፡፡ሁኔታው ከተለወጠ ደግሞ አስቀድሞ በተገባላቸው ቃል መሰረት በስደት እንዲወጡ እዛው ሀገር ያሉት ኤምባሲዎች አስቸኩዋይ ቪዛ እንዲያገኙ በማድረግ ከሀገር ያወጡዋቸዋል፡፡
እንግዲህ በዚህ መልኩ ነው ለህዝብ ዲሞክራሲ ሰብአዊ መብት ለፕሬስና ለመናገር ለመደራጀት ነጻነት ለነጻ ገበያ መርህ ወዘተ በሚል የህዝብን መከፋትና ብሶት በመጠቀም ግን ደግሞ በውስጡ እጅግ የተሸፈነ የዜጎችን መሰረታዊ መብትና ትቅም ሳይሆን የኒዮ ሊበራል ሀይሎች ከዚያች ሀገር የተፈጥሮ ሀብት ያለተቀናቃኝ ለማጋበስ እንዲችሉ ስልጣን ላይ ሊያወጡዋቸው የፈለጉትን ሀይሎች በመጠቀም በአንድ ሀገር ላይ ታላቅ ትርምስ ሁከት ግርግር ውድመትና ጥፋት እንዲከሰት የሚያደርጉት፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ ያለ መንግስት የሀገሬን የተፈጥሮ ሀብት ነዳጅ ጋዝ ዘይት ወርቅ መዳብ አልማዝ ፖታሺየም ኡራኒየም ኮባልት ታንታለም ፋብሪካ መሬት ድርጅቶች ወዘተ ለውጭ ሀይሎች አሳልፌ አልሰጥም አልሸጥም ሀገሬን አለማለሁ ህዝቡ ይጠቀምበታል የሚል የጸና አቓም ያለው ሀገሬን አላስመዘብርም የሚል ከሆነ ያለምንም ጥርጥር ያንን መንግስት በተገኘው አጋጣሚ ያገኙትን ሀይል አደራጅተው አሰልጥነው አስታጥቀውም ጭምር ከስልጣን እንዲወርድ አድርገው የራሳቸውን ተላላኪና ቡችላ ወይም ሳተላይት የሆነ መንግስት እንዲመሰረት ያደርጋሉ፡፡
ድሮ ድሮ መፈንቅለ መንግስት በስውር በማዘጋጀት ጥቅማቸውን የሚያስከብር ቡድን ወይም ታዋቂ ግለሰብ ከሰራዊቱም ሆነ ከሲቪሉ መልምለው የሀገር መሪነቱን ያስረክቡዋቸው ነበር፡፡አካሄድ እየታወቀ ሲመጣ አዲስ ያመጡት ስልት መሆኑ ነው የቀለም አብዮት፡፡ያው በህዝብ አመጽና ቁጣ አስደግፈው ትርምስ ፈጥረው የሞያካሂዱት መፈንቅለ መንግስት ማለት ነው፡፡ የቀለም አብዮቱ ሙከራ በተለያዩ የአለም ሀገራት ተደጋጋሚ ውድቀትና ክሽፈት ነው የገጠመው፡፡ ሀገራቱንና ህዝቡን ለከፋ አደጋና የኢኮኖሚ ውድቀት ለሀገር መፈራረስና መበታተን በማብቃት ጭራሹንም ሀገሩን ለቆ የሚሄደው ስደተኛ ቁጥሩ በብዙ መቶሺዎች በማሻቀቡ ተሰዶም አውሮፓን በማጥለቅለቁ እዳው ተመልሶ ለራሳቸው ተረፈ፡፡የቀለም አብዮት የውድመት አብዮት ነው፡፡ ሀገርና ህዝብን ለከፋ ጥፋት አጋልጦ የሚሰጥ የሚያወድም፡፡