ታከለ አለሙ
በአንድ ሀገር ወይንም በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ወይንም ቅርብና ሩቅ ተበሎ ከሚመደቡ በጠላትነት በሚፈረጁ ሀገራት ውስጥ ግዜውን ተከትሎ የሚከሰት የሀይል ሰላለፍ ሁሌም ይኖራል፡፡ አለ፡፡ በሀገራችን በዚህ ዘመን ባሉት ሰዎች ውስጥ ይታወቅ እንደሁ ባይታወቅም የቅራኔ ህግጋት የራሳቸው ቅደም ተከተል አላቸው፡፡ የጎራው አሰላለፍ፡፡
በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው አለም ቓሚ ወዳጅና ቋሚ ጠላት የለም እንዲል መጽሀፉ የሀገሪቱን ጂኦ ፖለቲክስ ተከትሎ በአጎራባች ሀገራት በቅርብና ሩቅ ያሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንቅስቃሴ እየተመዘነ እየተሰፈረ እንቅስቃሴአቸው እየተለካ በቅርብ ያለ ጠላት አስጊ ጠላት ምናልባታዊ ጠላት የሩቅ ጠላት በሚል ስትራቴጂካዊ ጥናት ውስጥ ተለይቶ ይቀመጣል፡፡
ይሄም ለሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ብሄራዊ ጥቅምም መከበር የሀገሪትዋን ጠላቶች በውል ለይቶ ማስቀመጡ ለሁልግዜውም የማያቁዋርጥ ዝግጁነትና መሰናዶ ይረዳል፡፡ የሐገሪቱ ስትራቴጂክ ጠላቶች በቀድሞ መንግስታት ዘመንም ሆነ አሁን በውል ተለይተው የሚታወቁ ናቸው፡፡
እነዚህ ሀይሎች የትኛውም መንግስት መጣ ሄደ ከሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት መሬት ውሀ መጠቀም አለብን ማግኘት ይገባናል ብለው የመብት ጥያቄ የሚያነሱ በመሆኑ መንግስት ቢለዋወጥም ቓሚና ስትራቴጂክ ጠላት ሆነው ይቀጥላሉ፡፡
ሀገሪቱን ለማዳከም አቅመቢስ ለማድረግ በመብትዋ ተጠቃሚ እንዳትሆን የውስጥ ተላላኪዎችን በመግዛት በማደራጀት በማሰልጠን በማስታጠቅ በገንዘብ ሀይል በመርዳት መቼም ሆነ መቼ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖራት በተፈጥሮ ሀብትዋ እንዳትጠቀም ለማድረግ ይሰራሉ፡፡
በዚህ ትርምስ መሀልም ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማቀድ ይሰራሉ፡፡ በሀገር ውስጥ የሚነሱትን ማንኛውንም አይነት በመንግስት ላይ የሚነሳ ተቃውሞ በመጠቀም አድማሱን ለማስፋት ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠቀሙት በሀገር ተወላጆች በስርአቱ ተከፍተናል የሚሉ ቡድኖችን በማደራጀትና በማሰባሰብ ነው፡፡
በዲፕሎማሲው መስክ ከአንገት በላይ በሚደረገው ጨዋታ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እንዲሉ እየተዋወቅን አንተናነቅ ማለትም ይቻላል ከሀገሪቱ ጋር ፈርጀ ብዙ ትብብር በብዙ መስኮች አለን እናደርጋለን በሚል የኢኮኖሚ የባህል የትምህርት የቴክኒዮሎጂ ትብብር የንግድ ልውውጥ ወዘተ ይፈጥራሉ፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ዋነኛው ስራቸው ወዳጅ መስለው በመቅረብ ሀገሪቱን መሰለል አቅምዋን ማጥናት ቦታዎችን ማወቅ የሀገር ተወላጅ የሆኑ ዜጎችን በገንዘብ በመግዛት መልሰው ሀገራቸውን እንዲሰልሉ ማድረግና የእነሱን ብሄራዊ ጥቅም የሚነካውንና የማይነካውን በውል ለይቶ ማወቅ ለዚህም ምላሽ በሚሆን መልኩ መዘጋጀት ነው፡፡ ጥቅማችን ይነካል ብለው ካመኑ እስከ ወታደራዊ እርምጃ ድረስ የሚራመድ ነው፡፡
ይህ የማይቻል መሆኑን ሲያውቁ ደግሞ እሾህን በእሾህ እንዲሉ የሀገሬውን ተወላጅ በገንዘብ ገዝተው በመጠቀም በራሱ ሀገር ላይ ጠላት ሁኖ እንዲዘምት ያሰማሩታል፡፡ ይሄ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ በተደጋጋሚ ታይቶአል፡፡ አሁንም እየሰሩበት ይገኛሉ፡፡
በዚህ ረገድ ግብጽ በአባይ ውሀ ምክንያት ጥንትም ዛሬም ለኢትዮጵያ ያልተኛች ልትተኛም የማትችል ስትራቴጂካዊ ጠላት የሆነች ሀገር ናት፡፡ ይህንንም ተጨባጭ እውነት ለብዙ መቶ አመታት አስመስክራለች፡፡የአባይን ወንዝ ውሀ ከምንጩ ለመቆጣጠር እጅግ በጣም ብዙ የጠላትነት ሴራዎችን በኢትዮጵያ ላይ አሲራለች፡፡ ሰራዊት አዝምታ በግብጽ የጦር መሪዎች አማካኝነት ኢትዮጵያን ወግታለች፡፡ ጉራና ጉንደት ላይ በኢትዮጵያ ሰራዊት ተሸንፋ ተመልሳለች፡፡
ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትሰራ አለም አቀፍ እርዳታም እንዳታገኝ ሰፊ ዘመቻ አድርጋለች፡፡
በኤርትራ ይንቀሳቀስ የነበረውን እስላማዊ አክራሪ ድርጅት ጀብህን እንዲመሰረት ያደረገችው ግብጽ ነች፡፡የያኔው የግብጹ ፕሬዚደንት ጀማል አብደል ናስር ነው ያቓቓመው፡፡ግቡም ኤርትራ አረባዊት ናት በሚል ፓርቲውን ለስልጣን ማብቃትና በኤርትራ በኩል አድርጎ የአባይን ወንዝ ውሀ ለመቆጣጠር ይቻላል ከሚለው የተሳሳተ ስሌት የመነጨ ነበር፡፡
ሌላው በኤርትራ ውስጥ ጀብህ በሚከፍተው ጦርነት የኢትዮጵያን መንግስት ትኩረት መሳብ እረፍት ማሳጣትና የአባይን ወንዝ እገድባለሁ ብሎ እንዳያስብ የማድረግ ስልት ነበር፡፡አድርጎታልም፡፡ለእነዚሁ ሀይሎች ወታደራዊ ስልጠና ድርጅት ትጥቅ ማረፊያ ሰፈር ቢሮ በመስጠት ሁሉን የምታሟላው ግብጽ ነበረች፡፡
በ1953 አም በኢትዮጵያ ታቅዶ ከከሸፈው የጀነራል መንግስቱ ንጉሱን ከሰልጣን የማስወገድ መፈንቅለ መንግስት ሴራ ጀርባ የግብጽ ደህንነት በበላይነት እንደመራው ውሎ አድሮ ምስጢሩ ይፋ ወጥቶአል፡፡መጽሀፍም ታትሞ ለንባብ በቅቶአል፡፡
የሶማሊያውን ጀነራል ዚያድ ባሬ ሰራዊት በዘመናዊ መሳሪያ በማስታጠቅ በንጉሱም ሆነ በደርግ መንግስት ዘመን በግዛት ይገባኛል ጥያቄ ከኦጋዴን እስከ አዋሽ ወንዝ ድረስ የሶማሊያ ነው በሚል ቅዠት ኢትዮጵያን እንዲወር ያደረገችው የወረራ እቅዱንም በማውጣት ጀነራሎችዋም በአማካሪነት በመሰለፍ ኢትዮጵያ እንድትወረር ያደረገችው ግብጽ ነበረች፡፡
ወረራው ተመክቶ በታላቅ ተጋድሎና መስዋእትነት ተመልሶአል፡፡ወራሪው ሰራዊትም ኢትዮጵያ መሬት ውስጥ እንደገባ ሳይወጣ ተደምስሶ ቀርቶአል፡፡ኦጋዴንን እገነጥላለሁ ብሎ የሚዋጋው አክራሪው እስላማዊ ሀይል የኦጋዴን ነጻ አውጪ ድርጅት ሙሉ በሙሉ የሚረዳው በግብጽ ነው፡፡ኦነግ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ብሎ ራሱን የሚጠራው ድርጅት የሚረዳው የሚታገዘው በግብጽ ነው፡፡
ከ1997 አም ምርጫ በኃላ ከእስር ተፈቶ ወደስደት የሄደው ቡድን በስደት ያቓቓመው ግንቦት ሰባት ሙሉ በሙሉ የሚረዳው በግብጽ መንግስት ሁኖ እርዳታውና ዶላሩን የሚቀበለው በቀጥታ ከኤርትራው መንግስት ከሻእቢያ ነው፡፡ከድሮ እስከ ዘንድሮ የዘለቀው የግብጽ ጸረ ኢትዮጵያ አቓምና ፖሊሲ የግብጽ መንግስታት ቢቀያየሩም አይቀየርም፡፡
ይህ ሁሉ ኢትዮጵያ ተሻግራ ሂዳ ግብጽን ተተናኩላ ሳይሆን የአባይ ውሀ ምንጭና ባለቤት ኢትዮጵያ በመሆንዋ ምክንያት ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ በአባይ ውሀ ላይ ግድብ እንዳትሰራ ከሰራች ከወንዙ የሚገኘው የውሀ መጠን ይቀንሳል ከሚል ስጋትና ፍራቻ የመነጨ ነው፡፡ግድብ ከተሰራ በአየር ድብደባ አፈራርሰዋለሁ ሰራዊትም አዘምታለሁ እስከማለትም ትደነፋ ነበር፡፡
እነሆ ኢትዮጵያም ግዜ ፈቀደና በራስዋ አቅም ካለውጭ ሀይሎች እርዳታና ብድር በራስዋ ህዝብ አቅም ገንዘብና ጉልበት የአባይን ወንዝ ውሀ ለራስዋ ጥቅም ለማዋል ስትል ለመገንባት በቃች፡፡ስራው እየተገባደደ ይገኛል፡፡
ግብጽ ታላቁን የአስዋን ግድብ የአባይን ወንዝ መሰረት አድርጋ በሩሲያ መንግስት እርዳታ ስትገነባ አርቲፊሺያል ሀይቅ ስትሰራበት በአባይ ወንዝ ውሀ መስኖ ዘርግታ በአለም ተወዳጅ የሆነ አትክልትና ፍራፍሬ ብርቱካን እያመረተች ለአለም ስትሸጥ ኢትዮጵያና ልጆችዋ በረሀብና በድርቅ እየተመቱ ምጽዋት እርዳታ ጠባቂ ተረጂ ሁነው ነበር፡፡ዛሬ ሁኔታው ተለውጦአል፡፡
ግብጽ ማግኘት ያለባትን የውሀ መጠን ታገኛለች፡፡በተረፈ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለአፍታ አይቆምም፡፡ዛሬ ላይ በህዝቡ ውስጥ ከመልካም አስተዳደርና ከፍትህ እጦት ከሙስና ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ተቃውሞ መንገዱን በማስቀየስ ወደራሳችን ጠቀሜታ እናውለዋለን የሚለው የግብጽና ሻእቢያ ሴራ እንዳሰቡት ሳይሆን መክኖአል፡፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ አባላቱ የፈጠሩትነ የውስጥ ችግር በጥልቀታዊው ተሀድሶ ይፈታል፡፡ በውስጥ ያለ ቅራኔ ሁልግዜም በአግባቡ ሲፈታ የተሻለ እድገትን እንደሚያመጣ የቅራኔ አፈታት ህግጋት ያስረዳሉ፡፡ስለዚህም በቅራኔ አያያዝና አፈታት ህግ መሰረት በመጀመሪያ ደረጃ ሊፈታ የሚገባው በውስጥ ያለው ችግር ነው፡፡በመቀጠል የህዝቡን ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ የመመለስ ስራ ሲሰራና ህዝቡ እርካታውን ሲገልጽ ሁኔታውን ለመጠቀም ሲራወጡ የነበሩት የግብጽና የሻእቢያ ቅጥረኞች ሰንቀውት የነበረው ባዶ ተስፋ ሲመክን በአይናቸው ያዩታል፡፡የጎራ አሰላለፉም በግልጽና በገሀድ ነጥሮ ወጣ ማለት ይሀው ነው፡፡