ይነበብ ይግለጡ
ጥልቀታዊው ተሀድሶ በአዲስ ተስፋ በአዲስ የጅማሬ ጉዞ ከቀድሞዎቹም በበለጠ ከስህተቶች በመማር መሰረታዊ የተባሉትን ችግሮች በመፍታት የተጀመረውን ሀገራዊ ልማትና እድገት እንደሚያስቀጥል ኢህአዴግ ደጋግሞ ገልጾአል፡፡ የተሀድሶው ጥልቀት ቀመሮች ምን ምን ላይ እንደሚያተኩሩ በተግባር የሚታይ ቢሆንም ከፍተኛ ስር ነቀል ለውጦችን እንደሚያካትት ይታመናል፡፡ ጥልቀታዊው ተሀድሶ፡፡
ኢህአዴግ ሀገርን በአዲስ መሰረት ላይ በመለወጥና በመገንባት ረገድ ከቀድሞዎቹ ሁሉ በተለየ ግዙፍ ስራዎችን ሰርቶአል፡፡በዚህ ክርክር የሚገጥም ወገን አይኖርም፡፡በመሰረት ልማት ግንባታ ከተሞችን በማዘመን ግድቦችን በመላ ሀገሪቱ በመስራት የጥራቱ ደረጃ ችግር ያለበት ቢሆንም ትምህርትን ከአንደኛ ሁለተኛ ደረጃ እስከ ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ ድረስ በመላው ሀገሪቱ በማስፋፋት ከ35 በላይ ዩኒቨርስቲዎችን የጤና ተቓማትን ሆስፒታሎችንና የጤና ጣቢያዎችን ክሊኒኮች በሰፊው በመስራት ረገድ ብዙ ተራምዶአል፡፡
የከተማ ቀላል የባቡር አገልግሎትን እንዲሁም ከጅቡቲ አዲስ አበባ የሚደርሰውን ቀድሞ የነበረውን መስመር በአዲስና ዘመናዊ መልኩ በመገንባት ሰፈ አቅም እንዲኖረው ተደርጎአል፡፡ የኢትዮጵያን ንግድ መርከብ አቅም በማሳደግና በማስፋፋት በርካታ ዘመናዊ የንግድ መርከቦች እንዲኖሩት በማድረግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀድሞ ከነበረው አቅም በላይ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ቦይንግ ጀቶች ድሪም ላይነሮች ባለቤት ለመሆን በቅቶአል፡፡
የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የዘመነ አየር ማረፊያ ለመሆን መቻሉ በአፍሪካ በአለምም ተመራጭ ተሸላሚ አየር መንገድ ለመሆን መብቃቱ የግል ባንኮች ኢንሹራንሶች ሆስፒታሎችና ከፍተኛ ክሊኒኮች የግል የትምሀርት ተቓማት ኮሌጆች ዩኒቨርስቲዎች መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መስፋፋታቸው በአዲስ አበባ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ታላላቅ ሆቴሎች መከፈታቸው የሀገሪትዋን እድገት ከማሳየቱም አልፎ ተመራጭ አድርጎአታል፡፡
ሀገሪቱ የአፍሪካ ህብረት ዋና ጵ/ቤት መቀመጫ ከመሆንዋም በላይ ታላላቅ አለም አቀፍ ድርጅቶች ቢሮ ከፍተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡የአለም አቀፉ ዲፕሎማሲ ከኒውዮርክና ቤልጂየም ቀጥላ ሶስተኛ መቀመጫና መናሀሪያ ሀገርና ከተማ ለመሆን መብቃትዋ ተመራጭነትዋን አሳድጎታል፡፡በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ተሰሚ ተደማጭ ተጵእኖ ፈጣሪ ሀገር ለመሆንም በቅታለች፡፡
በሀገሪትዋ ውስጥ የተጀመሩት ሜጋ ፕሮጀክቶች በአንደኛው ጂቲፒ ያልተጠናቀቁት በሁለተኛው ውስጥ የሚካተቱ ሁኖ እንደገናም ሀገሪቱን መካከለኛ ደረጃ ላይ ካሉ ያደጉ ሀገራት ተርታ የሚያሰልፋት ሁለተኛው ጂቲፒ ተጀምሮ በስራ ላይ ውሎአል፡፡ እየተሰራበትም ነው፡፡የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራው ሲጠናቀቅ በአፍሪካ አንደኛ በአለም ሰባተኛ ደረጃ የያዘ ነው የሚሆነው፡፡ ለሀገሪቱ የሚያስገኘው የውጭ ገቢ እንዲሁም በሀገር ውስጥ የሚከፍተው እጅግ መጠነ ሰፊ የስራ እድል የዜጎችን የነገ ተስፋ የሚታደግና የሚያለመልም ነው፡፡በዚህ ረገድ ብዙ ተሰርቶአል፡፡
በሌሎቹም የኢንዱስትሪ መስኮች ለሀገሪትዋና ለዜጎችዋ በዘላቂነት የሚበጁ ታላላቅ ተስፋዎች ያላቸው ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ከድህነት ጋር የተጀመረው ትግል በታላቅ የህዝብ ተሳትፎ በሁሉም መስክ ወደፊት እየተራመደ ይገኛል፡፡ እነዚህ ለአብነት የተነሱ እንጂ ከተነገረውም ከተዘረዘረውም በላይ ታላላቅ ለሀገርና ለህዝብ የሚበጁ ሀገራዊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡እየተሰሩም ይገኛሉ፡፡
በቅርቡ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ በአባልነት መመረጥዋ ራሱን ችሎ ትልቅ ሀገራዊና አለማአቀፋዊ ድል ነው፡፡ሀገሪትዋ የጨበጠቻቸው የተጎናጸፈቻቸው በመሰረተ ልማት በኢኮኖሚ ግንባታውና በልማቱ በግብርናው በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው መስኩ በአለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ግዳጅ ወዘተ የተመዘገቡ እጅግ አመርቂ ብሄራዊ ኩራትና ክብርን ከፍ ያደረጉ ከድህነትና ከተመጽዋችነት ታሪክ ለመውጣት በተደረገው አድካሚና መራራ ትግል ውስጥ የተገኙ ድሎች ናቸው፡፡
አጅግ አመርቂ ሀገራዊ የልማትና የእድገት ውጤቶች የመገኘታቸውን ያህል በተለይ በአሁኑ ሰአት በሀገራችን ላይ የተጋረጡ ስጋትና አደጋዎችም አሉ፡፡የእነዚህ ችግሮች አስኩዋል መነሻዎች በራሱ በገዢው ግንባር ውስጥ በአጭሩ ሳይቀጩ ቆይተው ግዜአቸውን ጠብቀው እያደጉ በመሄድ በህብረተሰቡ ውስጥ የመረረ መከፋትና ቁጣን የቀሰቀሱት መጠነ ሰፊ የመልካም አስተዳደር የፍትህ እጦት ችግሮች የሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት አደጋዎች እያደር እየገዘፈ መምጣታቸው ነው፡፡
የመንግስትን ሀላፊነትና ወንበር ለግል መጠቀሚያ ማድረግ በሰፊው ከመከሰቱም ባሻገር ህብረተሰቡን ለከፍተኛ ብሶትና ምሬት መዳረጉ ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ ክልሎች የተከሰተው ተቃውሞ ወደ ግጭት ማምራቱ አሳሳቢ ሀገራዊ አደጋዎች ናቸው፡፡ኢህአዴግ እነዚህ ችግሮች በየደረጃው እያደጉና እየሰፉ መምጣታቸውን ከአመታት በፊት ማለት በሚቻል መልኩ በዝርዝር አጥንቶ ለይቶ አስቀምጦአቸዋል፡፡የችግሮቹ የብሶቶቹ የህዝብ ምሬቶቹ ዋነኛ ፈጣሪዎች ከውጭ ያለ ሀይል አይደለም፡፡ተቃዋሚውም አይደለም፡፡ በውስጥ ያለው ኪራይ ሰብሳቢና ሙሰኛው በመልካም አስተዳደርና በፍትህ ላይ ህዝቡን ሲያስመርር የነበረው ሀይል ነው፡፡
አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል እንደሚባለው በመሬት ቅርምትና ዘረፋ በኢንቨስትመንት በፕሮጀክቶች በኮንዶሚኒየም በመንገድ ስራ በኮንስትራክሽን በጉምሩክ በግድብና ሀይል ግንባታ በየመንግስት ተቓማትና መስሪያቤቶች በሀላፊነት ተቀምጠው የራሳቸውን መረብ (ኔት ወርክ) በመዘርጋት የውስጥ ሌቦች ከውጭ አቀባባይ ሌቦችና ደላላዎች ጋር በመመሳጠር ህዝብ የሰጣቸውን አደራና ሀላፊነት በመዘንጋት ለግል ክብረትና ሀብት ክምችት በሰፊው በመንቀሳቀሳቸው ምክንያት ህዝቡ ተቃውሞውን በሰፊው አሰምቶአል፡፡
ይህ ደግሞ በበርካታ ሀገራት ሲፈጠር የኖረ ዛሬም ያለ ወደፊትም ሊከሰት ሊፈጠር የሚችል ችግር ነው፡፡የሚፈታው ቁርጠኛ በሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ውሳኔና አመራር ብቻ ነው፡፡ፖለቲካ ድርጅቱ ሁሌም እራሱን እያጠራና እየፈተሸ በውስጡ ከህዝብ ጋር ሆድና ጀርባ እያደረገው የሄደውን በጉያው ተሸጉጦ በመንግስት ወንበር ላይ ተቀምጦ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ሲመዘብር የኖረውን ከመንግስት ግምጃ ቤት ሳይቀር እያወጣ ያለአንዳች ሀፍረት ሲሸጥና ሲለውጥ ሲከብርበት የኖረውን የህዝብ ተመራጭነትና ሀላፊነት የሚባለውን አሽቀንጥሮ የጣለውን ስብስብ ኢህአዴግ ፈልፍሎ በማውጣት በህግ ተጠያቂ ማድረግ የግድ ይጠበቅበታል፡፡ዋነኛው ጥልቀታዊ ተሀድሶ ከዚህ ይጀምራል፡፡
ጥልቀታዊው ተሀድሶ በፈርጀ ብዙ መስኮች የሚካሄድ ቢሆንም የትኩረት አቅጣጫው በመዋቅራዊ ለውጦች በአሰራርና በአደረጃጀት ላይም በማተኮር ሁሉንም ዜጎች አሳታፊ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ህዝብ ለምን ተማረረ ? ለምን ተከፋ? ለምንስ አዘነ ችግሩ ምንድነው መፍትሄውስ ? ብሎ መጠየቅ ችግሩንም ለመፍታት መስራት የነገ ሳይሆን የዛሬ የኢህአዴግ የቤት ስራ ነው፡፡ይወጣዋል ተብሎም ይታመናል፡፡ተደጋጋሚ ተግባራዊ ተሞክሮዎችም አሉት፡፡
ሁልግዜም የህዝብ ተቃውሞዎች ሲነሱ ለመብቱ ድምጹን ሲያሰማ ይሄ ጥያቄ ጥቂት ሰዎች ያነሳሱት የሚለው የህዝብን መብት የተጋፋና የሚጋፋ አባባል ዛሬ ላይ የትም አያደርስም፡፡ሀገር የህዝብ ነች፡፡ሀገር የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የግል ንብረት ወይንም መገልገያ አይደለችም፡፡በሀላፊነታቸው የሚኩራሩ የሚመጻደቁም ካሉ ስልጣን ዘለአለማዊ አይደለም፡፡በጡረታም በህመምም ሊለቁት ይችላሉ፡፡ቓሚ አይደለምና፡፡ቋሚዎቹ ህዝብና ሀገር ብቻ ናቸው፡፡ ግዜ የማይሽረው እውነት ይሄ ነው፡፡
በዘረፋና በምዝበራ የተሰማሩት ግለሰቦችም ቢሆኑ ነገ በህግ መጠየቅ ይመጣል ብለው ሳይሆን ስልጣኑ በእጃችን እስካለ ድረስ ማን ይነካናል ብለው የሚያስቡ ከሆነ መሰረታዊ ስህተት ተሳስተዋል፡፡ስልጣን የህዝብ ነው፡፡ወንበሩም የህዝብ ነው;፡፡የተዘረፈውም ሀብት ከሀገር ወጥቶ የትም አይሄድም፡፡ይህንንም ማሰብ አለመቻላቸው አስገራሚ ነው፡፡ካለፉት መንግስታት አነሳስና ውድቀት አለመማርም ታላቅ ስህተት ነው፡፡የታሪክ አጋጣሚ በምን መልኩ ሊለወጥ እንደሚችል ማንም መተንበይ አይችልም፡፡
ተለዋዋጩና ወቅታዊው ሁኔታ ወደየት ያመራል በምን መልኩስ ይቛጫል ብሎ ሀገርንና ህዝብን በማይጎዳ መልኩ ማሰብ ትልቅነት ነው፡፡በተለይም ከሀገርና ከህዝብ ሰላም በላይ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም፡፡በንጉሱ ግዜ ህዝቡን ምንድነው ለለውጥ ያስነሳው? ደርግን በሆታ የተቀበለው ህዝብ ኃላ ላይ ለምንድነው ፊቱን ያዞረበት?እኛስ እየሄድንበት ያለው መንገድ የህዝብን አደራና ሀላፊነት ከመወጣት አንጻር ትክክል ነወይ? ብለው የሚጠይቁ ግለሰቦችም ሆኑ መሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በሀሳብና በእይታ የበሰሉ አርቀው የሚያስተውሉ ሁኔታዎችን በአግባቡ የሚተነትኑ ለችግሮቹም መፍትሄ የሚያስገኙ ሰዎች ከምንግዜውም የበለጠ ዛሬ ለሀገሪቱ ይጠቅማሉ፡፡ያስፈልጋሉ፡፡
ከመንግስት ከፍተኛ የፖለቲካ ሹሞችና ሀላፊዎች ጋር በመመሳጠር የመንግስትና የህዝብን ሀብት በሚሊዮኖች በመዝረፍ በተገኘ ገንዘብ በሽፋን የሚሰሩትን የግለሰቦች ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን እንደገና የመንግስት ድርጅቶች የራሳቸውን ቢሮና ጽህፈት ቤት በሚሊዮኖች አውጥተው መስራት ሲችሉ ከጀርባ በሚደረግ ድርድርና ትእዛዝ በወር ሚሊዮኖች እየከፈሉ እንዲከራዩ በብዙ ቦታዎች ተደርጎአል፡፡የግፍ ግፍ ነው፡፡መንግስት ለራሱ ተቓማት የሚሆን ምን አጣ ? አስቂኙም ነገር ይሀው ነው፡፡
መንግስት ማንም ወሮበላ እየተሞዳሞደ በፎርጅድ ካርታ እየሰራና ከመሬት ይዞታ ሀላፊዎች ጋር እየተመሳጠረ የሀገርና የህዝብ መሬት እየዘረፈ እየቸበቸበ ሲሸጥ ሲለውጥ ሲከብር መንግስትና ህግ የለም እስኪባል ትዝብት ላይ እስኪወድቅ ድረስ ኢህአዴግም ሆነ የሚመራው መንግስት የት ነበሩ የሚሉ ጥያቄዎች በሰፊው ይነሳሉ፡፡
መሬቱም ሰማዩም በእጁ የሆነው መንግስት ለራሱ ተቓማት ድርጅቶች መስሪያቤቶች ለነባሮቹም ሆኑ አዲስ ለተመሰረቱት ሰፊ ቦታ ሰጥቶ በራሳቸው በጀት ለዛሬውም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ የሐገርና የህዝብ ሀብት ሁኖ የሚቀጥል ዘመናዊ ፎቆች እንዲሰሩ ማድረግ አቅቶት ለዛውም መሬት ሰጪው ራሱ መንግስት ሁኖ ባለበት ሀገር ይሄ ይደረጋል ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡ሙስናው ከዚህም ያልፋል፡፡
ብዙ የመንግስት መስሪያቤቶች በቅርብ አመታት የተሰሩ የግለሰቦችን ህንጻዎች እንዲከራዩ የሚያደርገው በራሱ በመንግስት ውስጥ ያለው ኪራይ ሰብሳቢውና ሙሰኛው ሀይል ነው፡፡ከመንግስት በሚከፈለው የኪራይ ገንዘብ ያለገደብ ስለሚከብርበት ነው፡፡
ከአንድ የግለሰብ ፎቆችን ከተከራየ የመንግስት መስሪያ ቤት በትንሹ በወር አንድና ሁለት ሚሊዮን አከራዩ ይወስዳል፡፡በአመት 12 ወይም 24 ሚሊዮን መሆኑ ነው፡፡ በዚህ የሀገር ገንዘብ አንድ የመንግስት መስሪያ ቤት አጅግ ዘመናዊ የሆነ የተንጣለለ ፎቅ ሊሰራ አይችልም ይሆን ? ምዝበራው ከዚህም በላይ የከፋ ነው፡፡ይሄ በአንድ ዘርፍ ያለ ሲሆን ወደ ውስጥ ሲገባ ሲፈተሸ ሲመረመር ጉዱ ገና ነው የሚያስብል ነው፡፡
የሆነውን ሁሉ የሚያውቀው ህዝብ በአደባባይ በህጋዊነት ስም ስለሚሰራው ሙሰኛነት ኪራይ ሰብሳቢነት የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ችግር ከዚህም በላይ ሰፊውን ህብረተሰብ በከተማ ልማት እድገት ስም ከጀርባ ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር ከመኖሪያው እያፈናቀሉ የሚጫወቱበት ሰብአዊ መብትንና ህዝብን የናቀ የደፈረ ተግባር በዚህ ሁሉ ግፍና በደል ህዝብ አምርሮ በቃኝ እንዲል ያደረጉት የራሱ የኢህአዴግ አባላትና በየደረጃው የነበሩ ያሉ አመራሮች ናቸው፡፡ሌላ ህዝቡን ያንገፈገፈ ያስመረረ በቁጣ እንዲነሳ ያደረገው ሀይል የለም፡፡ጥልቀታዊው ተሀድሶ ይሄን ሁሉ ይፈትሻል ተብሎ ይታመናል፡፡
በእርግጥ የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም የራሳቸውን የፖለቲካ አላማና አጀንዳ ለማሳካት የሚራወጡ አስሩን የሚቀባዥሩ የውስጥና የውጭ ሀይሎችን ከሻእቢያ እስከ ግብጽ ድረስ አይተናል፡፡ እነሱ ትላንትም ዛሬም የሚመኙት በምንም ይሁን በምን ይህቺ ሀገር ፈራርሳ ጠፍታ ባዶ አውድማ ሁና ማየትን ነው፡፡
ዛሬም ሀሳባቸው የተሳካ መስሎአቸው ጮቤ እየረገጡ ይገኛሉ፡፡ ምኞታቸው ከህልም የዘለለ አይሆንም፡፡በከፍተኛ ደረጃ በሚሊዮኖች ዶላር እየረጩ ግዜው ዛሬ ነው በማለት እየተክለፈለፉ እየተራወጡ ይገኛሉ፡፡
የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ እናስቆማለን በማለት ግብጽ እየደነፋች ነው፡፡ሻእቢያም አብሮ ያጋፍራል፡፡የትም ደግሞ አይደርሱም፡፡አሳዛኙ ነገር በኢትዮጵያዊነት ስም የሚነግዱ ክፍሎች ከእነሱው ጋር በአጫፋሪነት ቆመው ሲደልቁ መታየታቸው ነው፡፡የሀገራቸውንና የህዛባቸውን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፈው የሸጡ ከሀዲና ግብረ በላዎች ናቸው፡፡መንግስት ዘላለማዊ አይደለም፡፡ይመጣል፡፡ይሄዳል፡፡ሰዎችም ያልፋሉ፡፡እናት ሀገር ግን አታልፍም፡፡
ከሀገራቸው ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተሰልፈው ጭርሱንም ሀገሪቱን ለመበታተን ለመከፋፈል የጀመረችውን የታላቅ ህዳሴ ትንሳኤ ለማጨናገፍ ህዝቡንም እርስ በእርሱ በማጋጨት ለመበታተን መሰለፋቸው መቼም ሆነ መቼ ታሪክም ትውልድም ይቅር የማይለው ስህተት ነው፡፡የውስጥን ችግር በውስጥ በጋራ በወይይት በመነጋገር በመደማመጥ ሀገርና ህዝብ አደጋ ላይ ሳይወድቅ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለችግሮቹ እልባት ማበጀት ይቻላል፡፡
ዙሪያ ገባዋን በጠላቶችዋ በተከበበች ሀገር ላይ ከጠላቶችዋ ጋር ተሰልፎ ሀገር ለማጥፋት መሰለፍ የከፋው የወንጀል አይነት ነው፡፡ኢትዮጵያ ታላቅ በሆነ ሀገራዊ የልማትና የእድገት አመርቂ ግስጋሴ ላይ በመራመድ አለምን ያስደመመ ኢኮኖሚያዊ እመርታ ያስመዘገበች ሀገር ነች፡፡ችግሮች አሉ፡፡አዎን እልፍ ችግሮች አሉ፡፡
ችግሮችን የምንፈታው እየተባላንና እየተፋጀን ሀገራችንን ለውጭ ጠላቶችዋ አሳልፈን ለመስጠት እየተዘጋጀን አይደለም፡፡ አባቶቻችን በባዶ እግራቸው እየሄዱ አጥንትና ደማቸውን ከፍለው የጠበቁዋትን ሀገር ዛሬ ሰለጠነ ተማረ አወቀ የተባለው ትውልድ ሊበትናት ሊያጠፋት አይገባም፡፡
ኢትዮጵያ አስጎምጂ የነገ ታላቅ ተስፋዎችን ሰንቃ ወደፊት እየተራመደች ያለች ሀገር ነች፡፡የዛኑም ያህል ኪራይ ሰብሳቢውና ሙሰኛው ሀይል በራሱ በመንግስት ጉያ ውስጥ ተሸጉጦ በመንግስትና በኢህአዴግ ስም እየነገደ እያስፈራራ ያሻውን እየሰራ አይነኬ ነኝ እስከሚል ድረስ ወጥ የረገጠበት ሁኔታ ህዝብን ክፉኛ አስመርሮ ቁጣ እንዲነሳ መሰረታዊ ምክንያት ሆኖአል፡፡የተሀድሶ ጥልቀቱ ይህንን ካንሰር የሆነ ችግር ነቅሎ በመጣል ይፈታዋል፡፡ በጥልቀታዊው ተሀድሶ ድሉ የህዝብና የሀገር ይሆናል፡፡