በጥልቀት የመታደስ ማለት  ሹም ሽረት ማለት አይደለም!!

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከነሃሴ 10-15/2008 ዓ.ም ድረስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ያለፉትን አስራ አምስት ዓመታት የለውጥ ጉዞ በመገምገም በአንድ በኩል በእስካሁኑ ትግል የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚፈታተኑ ችግሮችን በመቅረፍ የህዝብ መብትና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፉና ጥቅል የሆኑትን የውሳኔ ሃሳቦች ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡  
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዚሁ ግምገማ የተረጋገጠውና ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት፤ ይልቁንም የውሳኔ ሃሳቦቹን ተግባር ላይ ለማዋል ይቻል ዘንድ ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ  አገራችን ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት በሁሉም መስኮች ከፍተኛ ለውጥ እያመጣች የተጓዘች መሆኑን የተመለከተው ነው፡፡ ህዝብና መንግስት መሪ ድርጅቱ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ተግባር ላይ ማዋል ይችሉ ዘንድ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በህገ-መንግስት የተደገፈ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ግልፅ ነው፡፡ ለቀጣዩ ተሃድሶ በዚህ የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት የዜጎችና የልዩ ልዩ ማህበረሰቦች የፖለቲካ መብቶች ህጋዊ እውቅናና ዋስትና አግኝተው መከበራቸውንም ይብዛም ይነስ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት ያስከበረ አዲስ ዓይነት ፌደራላዊ የእኩልነት ስርዓት የተገነባና የሃይማኖት እኩልነት ተከብሮ መንግስትና ሃይማኖት መነጣጠላቸውንም በተመሳሳይ አምኖ መቀበል ግድ ይላል፡፡ የተጀመረውን እንዳልነበረ ወስዶ እና ከጉድለቱ ተምሮ መቀጠልን መሰረት ያላደረገ ለውጥን መሻት ትርጉም የለሽ ነው። በጥቅሉ  የዜጎችና የመላ ህዝባችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ቅድሚያ ሰጥቶ የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ህዝብ የሚጠቀምበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት በመገንባት ረገድ ረጅም ርቀት የተጓዘ መሆኑን መቀበል ለቀጣዩ ተሃድሶ ሁነኛ መደላድል ነው፡፡
የዚህ ተረክ መነሻም ይህን የተቀበለና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይህንኑ መነሻ በማድረግ ባካሄደው ግምገማ በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የሆነውን የመንግስት ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ ማረጋገጡን መነሻ በማድረግ በተወሰደው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ያለውን እና እየታየ ያለውን ብዥታ ማጥራት ነው፡፡ 
ከላይ በተመለከተው አግባብ አገራዊ ለውጡ በስኬት ሲጓዝ የቆየው መንግስታዊ ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ ማድረግ በመቻሉ የሆነውን ያህል፣ ይህ ስልጣን ያለአግባብ ለመጠቀም ለሚሹ ግለሰቦች በመሳሪያነት ማገልገል ሲጀምር የተጀመረው ልማት የተደነቃቀፈ መሆኑና መልካም አስተዳደርም አደጋ ላይ መውደቁ ይታወቃል፡፡ 
በአሁኑ ጊዜ ህዝብን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ ይኸው እንደሆነ በማስመር ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግስት ስልጣንን ያለአግባብ ለግል ኑሮ መሰረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌና ስህተት መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ እርምጃም መውሰድ እንዳለበት ወስኗል፡፡ ዝንባሌው በሚታይባቸው ቦታዎች ሁሉ በአግባቡ እየተፈተሸ እንዲስተካከልና የድርጅቱ ጥራትና ጥንካሬ ተጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆነው ርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ መወሰኑም ይታወቃል፡፡  
ችግሩና የውሳኔው አፈጻጸም አካል የሚሆነው ህዝብና መላው የድርጅቱ አባላት እርምጃውን ወይም የተሃድሶውን እንደምታ ከሹም ሽረት ጋር ብቻ ያያያዙት መሆኑ በተለያዩ መልኮች መስተዋሉ ነው። ስለሆነም ከላይ ከተመለከተውና ድርጅቱም ካረጋገጣቸው ዋነኛ ችግሮች በመነሳት በጥልቀት የመታደስ ምንነትን፤ አዳሽና ታዳሽ የሆነውን ወገንና ዘርፎች እንዲሁም  የተገቢነቱን እንደምታ በዝርዝር መመልከት ስኬታማ ለሆነ ተሃድሶ እና ሃገራዊ ህዳሴ ተገቢ ይሆናል። 
በጥልቀት የመታደስ  ትርጉም ከሹም ሽረት እጅግ የራቀና ይልቁንም ከአመለካከት ጋር የተያያዘ ነው። መሪ ድርጅቱ ከላይ በተመለከተው አግባብ ስለተሃድሶና መወሰድ ስለሚገባቸው የእርምጃ ውሳኔዎች ሲያወራ የመጀመሪያው እና ቁልፉ ጉዳይ ጎጂ ነገሮችን በድፍረት የመጋፈጥ ልምድና ተሞክሮ ያለውና በችግር ፈቺነቱ የሚታወቁት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አባላቶቻቸው ማንኛውንም ህብረተሰባዊ ፈተና ተደብቀው ማለፍ የማይችሉ የመሆኑን  እውነታ በጥብቅ የመቀበል የአመለካከት ተሃድሶ ማድረግን በተመለከተ እየተናገረ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በጥልቀት የመታደስ የመጀመሪያው ሚስጥር በዚህ ረገድ ያለው ችግር በተሟላ ደረጃ እስኪወገድ ድረስ ድርጅቱ እና አባላቱ ለአፍታም ቸል ሳይሉ  ጉዳዩን እያነሱ ሊጥሉና ሊፋጩበት የሚገባ መሆኑን የተመለከተ ነው፡፡
ድርጅቱ በተደጋጋሚ እንደሚገልጸውም ሆነ በተጨባጭ እንደሚስተዋለው ስርአቱ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ የተጋረጠበት እንደሆነ በመገንዘብ ከተሃድሶ ሂደቱ ጀምሮ ለአስራ አራት አመታት ያህል በፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል መፋለሙ እሙን ነው፡፡ በዚሁም ልክ ነባራዊውን ሁኔታ ቀላል በማይባል ደረጃ ለልማታዊነት የተመቸ እንዲሆን ማደረጉም እሙን እና ሰሞንኛ የነበረው ግምገማም ከላይ በተመለከተው መልኩ ያረጋገጠው ነው፡፡ ይህ መሰረታዊ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬም ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያመቹ አረንቋዎች ጨርሶ አልተወገዱም፡፡ በተጨማሪም በነባራዊው ሂደትና ራሳቸው ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች በሚፈጥሯቸው ቀዳዳዎች የተነሳ ዛሬም ለኪራይ ሰብሳቢ አዝማሚያና ተግባራት መበራከት ለም አፈር ሆነው የሚያገለግሉ ችግሮች ትንሽ አይደሉም፡፡ ሁለተኛው እና በጥልቀት የመታደስ ሚስጥር የድርጅቱና አባላቱ ድክመቶች ለዚህ አፍራሽ አዝማሚያ መከሰትና መስፋፋት ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ማመንና ከዚህ የመውጫውን መንገድ ማበጃጀትን የተመለከተ እንጂ አንዱ አዳሽ ሌላኛው ታዳሽ ሆኖ የሚደረግ ሹም ሽር ነው ብሎ መውሰድ ከባድ ችግር ነው፡፡ ስለሆነም ትላንት ከትላንት ወዲያ ከነበረውም በላይ በፋይናንስ አቅሙና በጥገኛ መረቡ የጠነከረ ኪራይ ሰብሳቢነት አሁንም የስርዓቱ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን እና ይህ በየትኛውም ዓይነት የድርጅቱ መልካም ስራ ሊሸፈን የማይችልና የማይገባው እውነታ መሆኑን ድርጅቱ እና አባላቱ ሊቀበሉ የሚገባ መሆኑን የተመለከተው ነጥብ በጥልቀት የመታደስ ምንነትን ፍንትው አድርጎ የሚገልጥ ነው፡፡ 
ስርዓታችንን የሚፈታተነው ኪራይ ሰብሳቢነት እንደአመቺነቱ በልዩ ልዩ መልኮች የሚከሰት ነው፡፡ አንዳንዴ በግብር ስወራ፣ ሌላ ጊዜ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ የሞኖፖል አቅጣጫን ተከትሎ ሸማቹን በመዝረፍ፣ ሌላ ጊዜ መሬት በማግበስበስ ይከሰታል፡፡ ወይም ደግሞ የመንግስትን ፕሮጀክቶች ባልተገባ የጥገኛ መረብ ታግዞ ማግኘትና ጥራቱ የተጓደለ የፕሮጀክት አፈፃፀም በማሳየት ከህጋዊው በጀት በላይ ከመንግስት ገንዘብ በመውሰድና በመሳሰሉት መልክም ይገለፃል፡፡ 
አንዳንዴ ህብረተሰብ ውስጥ በተለይ በግሉ ሴክተር የተሰማራው ባለሃብት ዋናው የኪራይ ሰብሳቢ ኃይል ሆኖ በሚወጣበት፣ ሌላ ጊዜ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተመሳሳይ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች በሚበራከቱበት ሁኔታም ሊገለፅ የመቻሉ ምክንያት የድርጅቱ እና አባላቱ የመታገል እና የማታገል ጥንካሬና ድክመት መሆኑንም አምኖ መቀበልን የተመለከተው ጉዳይ በጥልቀት የመታደስ ምንነትን የሚያጠይቅ ነው፡፡ በአንድ አካባቢ የሚካሄደው ትግል አይሎ ኪራይ ሰብሳቢነት እየተጠራቀመ ሲሄድ፣ ሌላ ቀዳዳ ፈልጎ በሆነ ሴክተርና መልክ የመገለፁ ምክንያት ከመታገልና ከማታገል ድክመትና ጥንካሬ የሚመነጭ እንጂ ሌላ መነሻ ስለሌለው ነው በጥልቀት መታደስ ማለት ከሹም ሽር የቀደሙ በርካታ እንደምታዎች አሉት የምንለው ፡፡ 
አንድ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል በትግሉ አስገዳጅነት ልማታዊ አቅጣጫ ሲይዝ፣ ሌላ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል በሌላ መልክና አጋጣሚ ብቅ የሚልበት ሂደት እንደነበር ድርጅቱ ባደረገው ግምገማ ያረጋገጠ መሆኑን ገልጦልናል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ ትግሉ ሲዳከም ዝንባሌው እየሰፋ፣ ትግሉ ሲጠናከር ደግሞ ዝንባሌው እየቀነሰ በሚታይበት ሁኔታ ውስጥ ድርጅቱ ማለፉንም ግምገማውን ተከትሎ የወጣው መግለጫ አረጋግጧል፡፡ ስለሆነም ጥልቅ ተሃድሶ ማለት ይህን በመገንዘብ ህዝቡ፣ ድርጅቱ እና መንግስት በሚያካሂዱት የተቀናጀ ትግል ዝንባሌው እንደገና በቁጥጥር ስር የሚውልበትን ሁኔታ መፍጠር ማለት እንደሆነም መገንዘብ ያስፈልጋል ፡፡ 
ኪራይ ሰብሳቢነት በተንሰራፋ ቁጥር ልማታዊ ዴሞክራሲያዊነት መዳከሙ፣ በአንፃሩ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊነት በተጠናከረ ቁጥር ኪራይ ሰብሳቢነት መዳከሙ የታወቀ ነው፡፡ ይህ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የታየ ክስተት ነው፡፡ በብዙ ልማታዊ አገሮች ኪራይ ሰብሳቢነት ከቁጥጥር ውጭ እንዲሄድ ሲፈቀድለት ጅምር ልማታዊ ጥረቶችን ሁሉ በማጨናገፍ አገሮች ካሰቡት ሳይደርሱ እንዲቀሩ አድርጓል፡፡ በአንፃሩ የተዋጣለት ፀረ ኪራይ ሰብሳቢ ትግል ያካሄዱ አገሮች ሁሉ በአንድ ወይ በሌላ መልክ የተከሰተ ኪራይ ሰብሳቢነት ሳይደፍቃቸው ካሰቡበት ደርሰዋል፡፡ በጥልቀት መታደስ ማለት በእኛ ሁኔታም ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደማይችል የህዳሴው እና የተሃድሶው አካላት በሙሉ በየደረጃቸው ሊገነዘቡ እና የአመለካከት ለውጥ ሊያመጡ ይገባል ማለትንም የሚጨምር እንጂ ድፍን ያለ ሹም ሽረት አድርጎ መውሰድን ብቻ የተመለከተ አይደለም፤ ሹም ሽረት የመጨረሻው አማራጭ ነው።

በጥልቀት መታደስን በተመለከተ ስናወራ ከሌላው ባለድርሻ በላቀ ደረጃ የድርጅቱ አባላትን ጨምሮ የመንግስት ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት  ከላይ የተመለከቱ እና ከአመለካከት ጋር የተያያዙትን ጉዳዮች በሚገባ ሊያስታውሱና ሊያጤኑት ይገባል። ይህ ከሆነ ደግሞ በአገራችን የተጀመረውን ፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል  ዳር ማድረስ ይቻላል። ይህ ከሆነ ደግሞ  ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተመዘገቡት ውጤቶች ተጠብቀው ይበልጥ በአዳዲስ ድሎች ይጎለብታሉ፡፡ ኢኮኖሚያችን አሁንም ፈጣንና ህዝብ የሚጠቀምበት እድገት እያሳየ ሊጓዝ ይችላል፡፡ አገራችን ገና በቅጡ ያልተነካ ድልብ የልማት አቅም ያላት አገር ነች፡፡ የህዝብ ብዛቷ፣ መሬቷ፣ ውኃዋ፣ ኢነርጅ የማምረት አቅሟ፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የማስፋፋትና በእነዚህ ሁሉ መስኮች ተወዳዳሪ የመሆን ብቃቷ እጅግ የሚያስጎመጅና በተነፃፃሪ ጠንካራ ትግል ወደውጤትነት ሊቀየር ይችላል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ መታደስን ከሹም ሽረት ጋር ብቻ አያይዘን የምንመለከት ከሆነ ኪራይ ሰብሳቢነት ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ የበለጠ እድል ስለሚያገኝ የዚህ ተፃራሪ ውጤት ይመጣል፡፡ መጀመሪያ ላይ የእድገት መገታት፣ በሂደት ደግሞ እንደማንኛውም በጥገኝነት አቅሙ የተሰለበ አገር ያደርገናል፡፡ ከዚህም አልፎ በቅርቡ አንዳንድ አካባቢዎች የአገራችን ክፍል እንደተከሰተው ዓይነት ግጭትና አለመረጋጋት የሚያስከትል የመልካም አስተዳደር እጦትና ትርምስ ሊያስከትል ይችላል። ስለሆነም ስለውድቀታችንም ሆነ ትንሳኤያችን በጥልቀት የመታደስ ዋነኛና መሰረታዊ የሆነው ሚስጥር ከላይ ከተመለከቱ የአመለካከት ጉዳዮች ጋር የተያያዘው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ፡፡