ግንባታው አይቆምም፤ ህዳሴያችን እውን ይሆናል!!

አባይን የሚገድበውም ሆነ ሀገሩን የሚጠብቀው ህዝቡ ነው፡፡ የድህነትና ተረጂነት ታሪካችንን ሙሉ በሙሉ ለመለወጥ ወሳኙን ሚና የሚጫወተውም እሱው ነው። የአባይ ውሀን ምስጢር ፈቺም ተርጓሚም እሱው፡፡ አባይ፣ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት፣ ቀሳውስት፣ ሼሆች፣ ደራስያንና ባጠቃላይ ህዝቡ ብዙ ብሎለታል፡፡ ከመነሻው የአባይን ወንዝ ለማጥናት ሀገርና ውቅያኖስ አቋርጠው የመጡ ቱሪስቶች፣ ጸሀፍትና ደራስያን፣ ጋዜጠኞችም ጭምር ብዙ ብለውለታል፡፡ የአልተደረሰበት፣ ያልተፈታ ያልተገለጠ፣ ረቂቅ ምስጢር ያለው ወንዝ ነው አባይ፡፡ ያም ሆኖ አባይን በጭልፋ ነው፡፡ 

አባይ ወንዝ ብቻ አይደለም፡፡ ታሪክም፣ ባህልም፣ ትውፊትም፣ ቅርስም፣ ስነፍጥረትም፣ ስነጽሁፍም፣ አርኪዮሎጂም፣ ቦታኒም  ወዘተ ወዘተ ነው፡፡ የአባይ ወንዝ የሀገር ሲሳይ ብቻ ሳይሆን የአለም ሲሳይም ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ምድር ተነስቶ ሱዳንና ግብጽን አብልቶና አጠጥቶ ሲያበቃ ረዥሙ የአለማችን ወንዝ ጉዞውን የሚቋጨው ሜዲትራኒያን ባህርን በመቀላቀል ነው፡፡ ሜዲትራኒያን ባህር ሲገባ ኢትዮጵያዊው አባይ፣ አፍሪካዊው አባይ፣ አለምአቀፋዊ አባይ ይሆናል፡፡ 

አባይ፣ ኢትዮጵያና ልጆችዋ በስሙ ሲኮሩ እንጂ ሳይጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ ቦ ግዜ ለኩሉ እንዲሉ አባቶች ግዜው ደረሰ ፈቀደና በራሱ ቤት የራሱን ህዝብ እንዲጠቅም፣ እንዲያገለግል፣ የሀገሩን ለም አፈር ይዞ ከመሰደድ እንዲታቀብ ግን ደግሞ ለሌሎችም መትረፉን እንዲቀጥል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ተጥሎ ስራው በከፍተኛ ፍጥነት ተራምዶ እነሆ ወደ መገባደጃው ተዳርሶአል፡፡

ከፍጥረተ አለም ጀምሮ በቅዱሳን መጻህፍት ጭምር ውስጥ ሳይቀር የሚገኘው አባይ ወንዝ ሀገሩን እያስራበ ጎረቤቶቹን የሚያጠግብ፣ የሚያስቦርቅ፣ እንደ አምላክ የሚቆጠር፣ “አባታችን” ተብሎ የሚወደስ አመታዊ ክብረ በአል የሚከበርለት፣ ታላቅ መንፈሳዊ ሀይል ተደርጎ የሚወሰድ፣ የሚዘፈንለትና ስራው ብዙ የሆነ ወንዝ ነው፡፡ በአባይ ወንዝ ውሀ ላይ ኢትዮጵያ ግድብ እንዳትሰራ አለም አቀፍ ጫና ሲደርስባት ብድር እንዳታገኝ ስትከለከል ኖራለች፡፡ ዛሬ ግን ከማንም ብድር ሳትጠይቅ በራስዋ ህዝብ አቅም፣ እውቀትና ጉልበት ለመገንባት በቃች፡፡ እነሆ የግድቡ ግንባታ የጉዞዉን ግማሽ አልፎ ለመጠቃለል ሩብ ጉዳይ ሊሆን ምንም ያህል ያልቀረው ለመሆን በቅቷል። 

የአባይ ወንዝ ሙላቱ በግርማ ሞገስ የታጀበ፣ አስፈሪ፣ አስጨናቂና ገምሻራ ሲሆን ሲጎድል ደግሞ ፍሰቱ በታላቅ ዝምታና አርምሞ የተዋጠ፣ አለምን መስማት እንጂ መናገር አያሻም የሚል አይነት አቋም ያለው ነው፡፡ በብርቱና ሀይለኛ፣ በመካከለኛና በአቅመ ደካማ ፍጡራን የሚመሰልበት ግዜም አለው የአባይ ወንዝ፤ ወቅት ነው የሚወስነው – “አባይ ጉደል ብለው አለኝ በትሳስ ….” እንዲል ዜማው፡፡  

ኢትዮጵያ ጠላቶችዋ በአባይ ወንዝ ውሀ ተጠቅማ ግድብ እንዳትሰራ ለዘመናት አሲረውባታል፡፡ ዘምተውባታል፡፡ ነገር ግን፣ ጉዳዩን የያዘው አበሻ ነውና አልተሳካላቸውም።

ኢትዮጵያ ከዘመነ ፍጥረት ጀምራ ራስዋም በገነት ተመስላ ከማህጸንዋ የሚፈልቀውን የአባይን ወንዝ ውሀ ለጎረቤቶችዋ እንደ ወተት በማጠጣት አሳድጋለች፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ ካለ አባይ ውሀ ሕይወትም፣ እስትንፋስም፣ ደስታም፣ ጠግቦ መብላትም፣ ሰርግም ሀዘንም ባልታሰባቸው ነበር፡፡ ካለአባይ ወንዝ ውሀ ሱዳኖችም ግብጾችም እንደአገር አገር ሆነው ባልቀጠሉም ነበር፡፡ በጥቅሉ፣ ኢትዮጵያዊው አባይ የህይወት ብቻ ሳይሆን የሀሴት፣ የተድላና የደስታ ምንጫቸው፤ የህልውናቸው መሰረት ነው፡፡

ግብጾችና ሱዳኖች ለአባይ ወንዝና ለውሀው ያላቸው ፍቅርና ውዴታ ወሰንና ድንበር የሌለው በመሆኑ አንዳንዴም ሳይሆን ሁልግዜም የራሳቸው የግል ብቻ አድርገው በመቁጠር ታሪካዊ ስህተት ይሳሳታሉ፡፡ ጭርሱንም የአባይ ማህጸንና መፍለቂያ የሆነችውንም ሀገር በጠላትነት ማየትን ይመርጣሉ፡፡ ውሀውን አትንኩብን፤ እኛ ብቻ እንጠጣው፣ እኛ ብቻ እንስራበት፣ እኛ ብቻ እንረስበት፣ እኛ ብቻ እንክበርበት ወደሚል ከስግብግብነት ያለፈ ራስ ወዳድነት ውስጥ ይነከራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለመልካም ጉርብትናም ሆነ ለአብሮነት አይበጅም፡፡

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝና ውሀ ለሁላችንም ይበቃል፡፡ የተፈጥሮ በረከት ነው፡፡ በሰላምና በፍቅር እንጠቀምበት ብላ ማሰብዋ ትልቅነት ነው፡፡ አባይ ወንዝ በፍጥረተ አለም ኢትዮጵያ ውስጥ  ቢፈጠርም ኢትዮጵያ ብቻ እንዲቀር ተደርጎ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ለአለም እንዲተርፍም ጭምር ነው ፍጥረቱ፡፡ እናስቀረው ብንልም አይቻልም፡፡ አባይ፣ በስርአቱ ካልተመራ ሊያጠፋና ሊያወድም የሚያችል አቅምና ጉልበት ያለው፤ አሻፈረኝ፣ አልገዛም ባይ ሞገደኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አቅምና ጉልበት አግኝታ ይህን ታላቅና በአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራን የሚይዝ፣ በአለም ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሆነውን ግድብ ለዛውም 6000 ሜጋ ዋት ሀይል የማመኝጨት አቅም ያለው፣ ትሰራለች ቀርቶ ታስባለች ብሎ የገመተ ማንም አልነበረም፤ ማድረግም ተቻለ፡፡ 

ከውጭ እርዳታና የገንዘብ ድጋፍ አግኝተን ግድብ እንዳንሰራ በግብጽና በተባባሪዎችዋ  አማካኝነት ብዙ ቢሴርብን አልሆነም፤ ያንን ሁሉ  ሰባብረን ተፈጥሮ በጋራ የሰጠችንን ስጦታ በጋራ መጠቀም እንችላለን በሚለው የኢትዮጵያ ቋሚ መርህ ከሱዳንም ከግብጽም ጋር በጋራ (የተጠበቀውን ያህልም ባይሆን) በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡ ግድቡ የውሀ ድርሻችንን ይቀንሳል የሚለውም ስጋት የውሀ ፍሰቱ ሳይዛባ እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ ተገልጾላቸዋል፤ እየተግባባንም እንገኛለን፡፡ 

ግብጾች የውሃ አወሳሰዳቸውንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻሉ ከ1896 ጀምረው የውሃ መቀልበሻና የውሃ ማጠራቀሚያ ግድቦችን በተለያየ ጊዜያት ሰርተዋል፡፡ የመጀመሪያው የአስዋን የውሃ ማጠራቀሚያ ግድብ የተጠናቀቀው በ1881 ነው፡፡ ለራሳቸው ይህን ሲያደርጉ ለኛ ግን እርስ በርስ መጋጨትን ነበር ሲደግሱልንና ሲመኙልን የኖሩት።

ከእርስ በእርስ ንትርክና መባላት አልፈን ሩቅ ለማሰብና ለማለም እንዳንችል ይሄው እርስ በርስ እንጋጭ ዘንድ የቤት ስራ እየተቀመመ የሚሰጠንም በእነዚሁ ወገኖች ሲሆን ሰላምና መረጋጋት ያላት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ጭርሱንም አይፈቅዱም፤ አይሹምም ነበር፡፡ ሰላም ልማትና እድገት ካለ አሁን እየሰራን ያለውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ አንድ ቀን ኢትዮጵያ ትገነባለች ብለው ለዘመናት ሲፈሩ ሲሸበሩ የኖሩትን ጉዳይ እውን እናደርጋለን ማለት ነው፤ እውን ይሆናል፡፡ ራእያችን እውን ትሆናል!!!!

ይሄ ሁሉ ስጋት፣ አባታችን ብቻ ሳይሆን ህይወታችንም ነው ብለው የሚያምኑበትንና የሚያመልኩበትን የአባይ ውሀ መጠኑ ይቀንሳል ብለው ስለሚያምኑ ብቻ ሳይሆን ብቻችንን መጠቀም አለብን ከሚለው ስግብግብነትም የመነጨ ነው፡፡ የተሳሳተው አረዳዳቸው ዛሬ ላይ  እውነቱን የተረዳና የተገነዘበ ይመስላል፤ ልብ እየገዙ ስለመሆናቸው ብልጭታዎች አሉና፡፡ 

ከእኛ ወደ ግብጽ የሚሄደው የደለል አፈር ክምችት በዝቶ መጠራቀም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ግድቡን ለመጥረግና ለማጽዳትም ራሱን የቻለ ከባድ ስራ መሆኑን በውሀው ዳርቻ ያለው መሬት በማእበል ከመበላቱም አልፎ አደገኛ በሽታ እያመጣባቸው ይገኛል፡፡ ለግብጾች ሌላ የቤት ስራና ፈተና መሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግን ይህን ሁሉ  ችግር ያስወግዱ ዘንድ ይተባበራቸዋል።

ተፈጥሮአዊ ህግ ነውና የሰው ልጅ ሰፋ ያሉ የልማት ዕቅዶች በሚያከናውንበት ወቅት በአካባቢው ላይ ለውጥ ያመጣል፡፡ ከዚህም የተነሳ ቀድሞ ያልነበሩ አሉታዊ ተጽእኖዎችን የሚያሳድሩ ሁኔታዎችም ይፈጠራሉ፡፡ ዋናው ቁም ነገር አሉታዊ ተጽእኖዎቹን ከሚገኘው ሁለንተናዊ ጥቅም ጋር በማነጻጸር ጥቅሙ ከጉዳቱ በብዙ እጅ መብለጡን ማረጋገጥ ተገቢና ወሳኝም ነው፤ ኢትዮጵያም ይህን አድርጋለች፡፡

ባጠቃላይ፣ ማንም ምንም አለ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለፍጻሜው በሚያበቃው ደረጃ  ተጠናክሮ ቀጥሎአል፤ ይቀጥላልም። ቀሪውንም እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን፡፡ ስራውም ሳይደናቀፍ ሌት ከቀን እየቀጠለ ይገኛል፡፡ ስራው ቆሞአል የሚለው የሀሰት ፕሮፓጋንዳም የሀገሪቱና የህዝቡ ጠላቶች ባዶ፣ ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ወሬ ነው፡፡