ህገ-መንግስቱን ማክበር ራስን ማክበር ነው!

 

                                 

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትናንት በሀገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ መቆጠር ግድ ሆኖባቸው ነበር። አካባቢያቸው ለእድገትና ብልፅግና ጀርባውን ሰጥቶ የሚኖሩበት ቀዬ በግዞትና በፀባይ ማረሚያነት ተፈርጆ የልማቱ ተቋዳሽ መሆንም አልቻሉም። እርግጥም የትናንቷ ኢትዮጵያ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦቿ የሰቆቃ ምድር ነበረች፡፡ ዜጎች ኑሯቸውን በቅጡ እንዳይገፉ የተቸገሩበት፣ ተስፋቸው ተሟጥጦ ግራ የተጋቡበት፣ መቋጫ በሌለው ጦርነት፣ ረሃብና ስደት የሚንገላቱበት ያ ሰቅጣጭ ወቅት ዳግም ላይመለስ ተሰናብቷል፡፡

ዛሬ ህገ-መንግስቱን ማክበር ራስን እንደ ማክበር የሚቆጠርበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ዜጎች ለአዲስ ህይወት ማበብ ተስፋ ሰንቀው፣ በፀና ህብረት ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኑሮን ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ንፁህ አየር መማግ፣ በሠላም ገብቶ መውጣት፣ በነፃነት መንቀሳቀስን ችለውበታል፡፡ ለዚህ መብቃት የተቻለው ደግሞ ሺህዎች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ነው፡፡ በውጤቱም በመላ አገሪቱ ሠላም ተገኝቷል፤ የልማት መስመር ተይዟል፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በፅኑ መሠረት ላይ ቆሟል፡፡

እነዚያ አስከፊ የህይወት ጉዞዎች ተገትተዋል፤ ጨቋኙ አምባገነናዊ ሥርዓት ምሱን አግኝቶ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፤ በሕዝብ ጫንቃ ላይ ተፈናጥጦ መንገስ አብቅቷል፤ የመንግሥት ሥልጣን በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ የሚረከቡባት ሀገር መፍጠር ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተጎናፀፉትን ሠላምና ዴሞክራሲ መሠረት በማድረግ ከልማቱ በፍትሃዊነትና እኩልነት ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የፀና እምነት ተይዟል፡፡ ፍሬውንም መቋደስ፣ ፅዋውንም ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ታዲያ የዚህ ሁሉ መነሻ መሠረቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በደም ቀለም በተጻፈ ቃል ኪዳን ያፀደቁት የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ነው፡፡

እርግጥ ላለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ጥቅሞቻቸውን በማጎልበት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአንድነት ተነሳስተዋል፡፡ በብዝኃነት ላይ መሠረቱን የጣለው አንድነት ለህዳሴውም ስኬት መገለጫ ነውና የዜጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ህገ መንግሥት ጠብቆ ለማቆየት ሁሉም በፅናት ቆሟል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበት፤ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት መሠረት የተጣለበት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፤ ውበትና ህብረት የታየበት ብሎም የሥልጣን ባለቤት የተረጋገጠበት፤ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ የተጀመረበት መሠረቱ ይኸው ህገ መንግሥት ነው፡፡

የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መርጠው በላኳቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ህገ መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ሁለት አሥርት ዓመታትን ተሻግሯል፡፡

በእነዚህ ጊዜያት የክልሎችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተለይም በልማትና ዕድገት አፈጻፀም ረገድ በጎ እርምጃዎች ተወስደው መልካም ውጤቶች ታይተዋል፡፡ በህገ መንግሥት በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓት ከአገሪቱ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታ በመነሳት በህገ መንግሥቱ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ሕብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ያለፉት አፋኝ መንግሥታት የቀበሩትን የማንነትና የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ጥያቄን በአስተማማኝ ደረጃ መመለስ ችሏል፡፡

በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

በዚህም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፏቸውና በየደረጃው ተጠቃሚነታቸው ጎልብቷል፡፡ አካባቢያቸውንም በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አኳያ ደግሞ የልማትና ዕድገት አፈጻፀም በክልሎች እኩል ተጠቃሚነት እየተፈፀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ልማታዊው መንግሥት ግልፅ የሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም እየተቀመሩ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎችና ለምልዓተ ሕዝቡ የሚደርስበት ስልቶች ተቀይሰዋል፡፡

የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች የሚለዩበትን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፉት ልምዶች በመነሳት እንዲፈተሹና እንዲስተካከሉ በማድረግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡

ክልሎች በገጠርና ከተማ የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶችን በመንደፍና ሕዝቦቻቸውን ዋናው ፈፃሚ አካል በማድረግ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአማካይ ለተመዘገበው ከሁለት አኃዝ በላይ እድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አግዟል፡፡

የፌዴራል መንግሥትም ክልሎችን ከክልሎች ብሎም ከአዋሳኝ አገሮች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን በመስራትና ፈጣን የቴሌኮም አገልግሎቶችን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማፋጠን፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትንና የአገር ውስጥና የውጭ አገር የገበያ ትስስርን በመፍጠርና በማጎልበት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱ ግብ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተተገበረ  ይገኛል፡፡

የሚቀሩ ስራዎች ቢኖሩም የመጀመሪያው አምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ህዝቡን  በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል። አጥጋቢ ውጤትም ተገኝቶበታል። እየተተገበረ ያለው ሁለተኛው የልማት ትልምም ይህንኑ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ተሳታፊነትንና ተጠቃሚነትን ወደ ላቀ ደረጃ በሚያሸጋግር መልኩ ተቀይሶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። የላቀ ውጤትም ይገኝበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በአገሪቱ ያሉ ክልሎች እርስ በርስ በመደጋገፍና ልምዶችን በመለዋወጥ የሚያደርጉት የጎንዮሽ ይሁን የተዋረድ ግንኙነት ለእኩል ተጠቃሚነትና በተመጣጣኝ ልማትና እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ይህም የልማትና የመልካም አስተዳደር ማነቆዎችን በመፍታትና በጎ ልምዶችን በማስፋፋት ሂደቱን ማስቀጠል ከተቻለ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ አገሪቱ መካከለኛ ገቢዎች ካላቸው አገራት ተርታ የማትሰለፍበት አንዳች ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም፡፡

በሀገሪቱ ያሉ ክልሎች እርስ በርስ በመደጋገፍና ልምዶችን በመለዋወጥ የሚያደርጉት የጎንዮሽ ይሁን የተዋረድ ግንኙነት ለእኩል ተጠቃሚነትና በተመጣጣኝ ልማትና እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ይህም የልማትና የመልካም አስተዳደር ማነቆዎችን በመፍታትና በጎ ልምዶችን በማስፋፋት ሂደቱን ማስቀጠል ከተቻለ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ አገሪቱ መካከለኛ ገቢዎች ካላቸው አገራት ተርታ የማትሰለፍበት አንዳች ምክንያት የሌለ መሆኑን የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡

የሀገሪቱ ክልሎቹ መንግሥታትና ህዝቡ ከሚያደርጋቸው ልማታዊ ርብርብ ጎን ለጎን በፌዴራል መንግሥት በኩል የተለያዩ ተገቢነት ያላቸው ሚኒስትሮች የሚገኙበት የልዩ እገዛ ቦርድ ተቋቁሟል፡፡ የአጎራባች ክልሎች የልማት ትብብር ፕሮግራም በመንደፍና የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች የሚያሳኩ የበጀት አመዳደብና ድጋፍ ሥርዓቶችን የመዘርጋት ዘላቂ አቅም የመገንባት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡ እስካሁን የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆናቸው እንደተጠበቁ ሆነው፤ ለቀጣዩም መሠረት ስለሚጥሉ የፌዴራልና የክልሎች መንግሥታት የጋራ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

እዚህ ላይ ልዩ እንደ ሶማሌ፣ጋምቤላ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝን በመሳሰሉ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ስላለው በመንደር የማሰባሰብ ፕሮግራም ጥቂት ማለት ተገቢነት የሚኖረው ይመስለኛል—አንዳንድ የሀገራችንን ማደግና መበልፀግ የማይሹ ሃይሎች ይህን ሁኔታ እየደጋገሙ ያነሱታልና፡፡ ታዲያ በቅድሚያ መታወቅ ያለበት በመንደር የማሰባሰብ ፕሮግራም ዓላማው ዜጎች ከሀገራቸው ልማትና ዕድገት በላቀ ደረጃ የሚጠቀሙበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አካል እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፕሮግራሙ በአገሪቱ የመልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲና የልማት መብቶችን ለማስጠበቅ የሚከናወን ነው፡፡

ፕሮግራሙ በዴሞክራሲያዊ መብት ረገድ ዜጎች ተበታትነው በሚኖሩበት ሁኔታ የተደራጀ ትግል ሲያካሂዱም ይሁን ድምፃቸውን ሊያሰሙ አዳጋች እንዳይሆንባቸውም ያደርጋል፡፡ እናም ፕሮግራሙ ዜጎች በመብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸው ዙሪያ እንደ ህዝብ ድርሻቸውን ሊወጡም ይሁን ከመንግሥት መዋቅር ጋር በቅርበት ለመወያየትና መፍትሄ ለማፈላለግም ያስችላቸዋል፡፡ ይህ ፕሮግራም ከሀገሪቱ አቅም ተነስተን የማህበራዊ፣ የምጣኔ ሃብታዊና የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ያስቻለ ነው፡፡ በውጤቱም የዜጎችን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ ከወዲሁ ከፍተኛ ለውጥ መታየት ጀምሯል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ከሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥና ከሚያስከትለው አደጋ ዜጎችን የመታደግ ዓላማንም ያነገበ ነው፡፡

ህዝቡ በሚሰባሰብበት ወቅት ከሁሉም በላይ ከዴሞክራሲያዊ መርሆች በመነሳት በሙሉ ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የሚፈፀም ፕሮግራም ነው፡፡ በቅድሚያም በየአካባቢዎቹ በቂ የጓሮ፣ የእርሻ፣ የግጦሽ መሬትና የውኃ አቅርቦት መኖሩን በማረጋገጥ ጭምር፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ሕዝቡ የተረጂነትና የጠባቂነት አስተሳሰብ ሳይሸከም ወደ ምርት ተግባር እንዲሸጋገር የሚያስችሉ የአመለካከት፣ የክህሎትና የግብዓት አቅርቦት ሥራዎች ጎን ለጎን ተከናውነዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ማህበራዊ የመሠረተ ልማት ተቋማት እየተገነቡ በአገልግሎት ላይ የዋሉበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡ ይህ በመንደር የማሰባሰብ ፕሮግራም በሌላ በኩል በልዩ ድጋፍ ክልሎች ያሉ ሕዝቦች በሠላም፣ በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በዚህም ሂደት በክልሎች መካከል ያለውን የተመጣጠነ ልማትና እድገት ዓላማ እያሳካ የሚገኝ ፕሮግራም ነው፡፡ በተነፃፃሪ እጅግ ባጠረ ጊዜ የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤና የኑሮ ደረጃ ከመሠረቱ የሚቀይር መሆኑም ፍሬው እየታየ ነው፡፡ ተመጣጣኝ ገቢ ያለውን አንድ የጋራ ማህበረሰብ በመገንባት ረገድም የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ ነው።

በዚህ አጭር ፅሑፍ ህገ-መንግስቱ ያስገኘውን ጥቅም ዘርዝሮ ማየት አይቻልም። ይሁንን ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዚህ ሰነድ ተጠቃሚዎች ሆነዋል—ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ። በእኔ እምነት በቅርቡ ህገ-መንግስቱን የሚቃወሙ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችን በመቃወም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉት ከዚሁ ተጠቃሚነታቸው በመነሳትና ያለፉት ስርዓቶች ተመልሰው እንዳይመጡ ካላቸው ፍላጎት በመነጨ ነው። ይህ ዕውነታም ህገ-መንግስቱን ማክበር ራስን ማክበር ነው ወደሚል ትክክለኛ መደምደሚ የሚወስደን ይመስለኛል።