በንጹሃን ወገኖች ደም ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ

በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በከፍተኛ ድምቀት ሲከበር በነበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የደረሰው አደጋ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ በጣም አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ይህ ከልብ የማይወጣ አደጋና ጥልቅ ሃዘን አገራቸውን የሚወዱ ዜጎች ሁሉ ቆም ብለው ማሰብ የሚገባቸው ሰአት ላይ መድረሳቸውን ያመላከተ ነው፡፡ ንፁሃን ወገኖቻችን እንደወጡ ቀርተው አገሪቱ ማቅ በለበሰችበት በዚህ ጊዜ አሁንም በክልሉ የዜጎችን እና የመንግስትን ንብረት የማውደም ተግባሮች አለመቆማቸው የሚያሳስብ እና ሃገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ ሊመክርበት የሚገባ አቢይ ጉዳይ ነው። ኢሬቻ ማለት የተጣላው የሚታረቅበት፣ ለተጋደለው ጉማ (ካሣ) ተከፍሎ ለዕርቅ ‹‹መልካ›› የሚወጣበት ቀን ሲሆን፣ ‹‹መልካ ማለት የፍቅር፣ የመታረቂያ፣ የወደፊት ሰላማችንን መለመኛ ቀን ነው፡፡”

 ስለሆነም በአገራችን ኢትዮጵያ ለዓመት ያህል አልበርድ ያለው አለመረጋጋት ምን ዓይነት መፍትሔ ያስፈልገዋል? ለመነጋገርና ለመደማመጥ አሻፈረኝ ብለውና ከአገሪቱ የተቃውሞ ፖለቲካ በስተጀርባ ሆነው የሚጨፍሩብን እነማንስ ናቸው? በህዝብና በመንግሥት መካከል የተፈጠረውን ቅራኔ የኢሬቻ በአልን በማወክ አልያም ደግሞ የህዝብ ንብረቶችን በማቃጠል የሚፈታ ነወይ? ሥልጡንና ዴሞክራሲያዊ አካሄዶች እየተገፉ በዚህ ሁኔታ የት ድረስ መጓዝ ይቻላል? ህዝቡስ  እስከ መቼ በሥጋት ውስጥ ይኖራል? ወዘተ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አንስቶ ለመፍትሔው መረባረብ  የግድ ይሆናል፡፡

ሞት የነጠቃቸውን ወገኖች እያሰብን ባለንበት ሰአት እንኳ የሟቾች ቁጥርና አሟሟት ለዜሮ ድምር ፖለቲካ ገበያ ቀርቦ ስንመለከተው በእርግጥም ያሳስባል። ይህ ብቻ አይደለም፤ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች ለተጨማሪ ሕይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ገፊ ምክንያት እንዲሆን ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑም በተመሳሳይ የሚያሳስብ ነው፡፡  የጥፋት ኃይሎች ከግብጽና ከኦነግ ጋር ባቀነባበሩት ሴራ ምክንያት አደጋው ስለመድረሱ አረጋጋጭ የሆኑ በርካታ ማሳያዎች ባሉበት ሁኔታ ተቃውሞውን በማኅበራዊ ሚዲያ በመምራት ላይ ያሉት የሌባ አይነ ደረቅ እንዲሉ ዛሬም ጣታቸውን መንግስት ላይ እየቀሰሩ መሆናቸው ግና የቤት ስራቸውን ያልጨረሱ ስለመሆናቸው ያመላክተናል፡፡

ግብጽ ከራሷ የወሰደችውን ተሞክሮ ጨምሮ በብዙ አገሮች እንደታየው ተቃውሞዎችና ግጭቶችን  ወደ እርስ በርስ ጦርነት በመቀየር ሃገራችንን የማተራመስ ፍላጎቷን ለማሳካት ከኦነግ ጋር ውል ስለመፈጸሟ በገሃድ እየታየ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደገና እያገረሸ ካለው አመጻ በስተጀርባ ያለችበት መሆኑንም በገዛ መገናኛ ብዙሃኗ ጮቤ እየረገጠች አረጋግጣልናለች።

በአሁኑ ሰአት የሕዝቡን ጥያቄዎች በአግባቡ የሚመልሱ ተግባራዊ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡ በሕግ ዋስትና ያገኙ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በተግባር እንዲረጋገጡም መንግስት እራሱን እየፈተሸና በጥልቀት እያደሰ ነው፡፡ ሕዝብን ለምሬት የሚዳርጉ አሠራሮች በአስቸኳይ ይወገዱ የህዝብ ተሳትፎ እየተጠየቀ ነው። ይህ በሚደረግበት በዚህ ሰአት ምላሹ ቃጠሎ ከሆነ በእርግጥም ከበስተጀርባ ስውር እጆች ስለመኖራቸው እርገጠኛ መሆን አይቻልም ይሆን?

ጥያቄያችን ስራ አጥነትና ነጻነት ነው ከሚል ወጣት የዜጎችን ነፃነት የሚጋፉ ድርጊቶችን ማየትና ስራአጦችን በሚያበራክት አውዳሚ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ማየት ግራ አጋቢ ነው ብለን የምናልፈው ሳይሆን ከበስተጀርባቸው ያለውን እንድናይ የሚጋብዘን ነው። የኦነግን ባንዲራና መፈክር እያውለበለቡ እና እያነበነቡ ጥያቄያችን ይደመጥ ብሎ ነገር የማይመችና የህግ የበላይነትን መጻረር ነው። የኦነግን ባንዲራ እያውለበለቡ ህዝብን ለመለብለብ የተሰነናዱትን እና መሰናዶውንም ወደተግባር የቀየሩ ሃይሎችን በግልጽ እየተመለከትን በቦታው ላይ ከነበሩት ይልቅ ቤታቸው ተቀምጠው የነበረ መሆኑን የሚናገሩትን መራራ ጉዲና ምንጭ አድርጎ 600 ሰው ሞቷል የሚል ዜና መስራት የግብጽን የረዘመና ስውር እጅ ያሳየናል።  

መንግሥት የደረሱት የሕይወት ሕልፈቶችን በተመለከተ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ለማቋቋም መዘጋጀቱ ተመልክቷል፡፡ በዜጎቻችን ሕልፈት ሳቢያ የተፈጠረው ቅራኔ ረገብ ብሎ በምክንያታዊነት መነጋገር ካልተቻለ፣ ሰላም ማስፈን አዳጋች ከመሆኑም በላይ የዜጎች ጉዳት ተባብሶ የሚቀጥል መሆኑን የተገነዘበችው ግብጽ ደግሞ የኦነግን ባንዲራ ተከናንባ ጉሮወሸባዬ እያለች ነው፡፡

የወገኖቻችን ህይወት ባለፈበትና ከዚሁም ጋር ተያይዞ የበርካቶች ንብረት እየወደመና ህዝቡ በስጋት ውስጥ ባለበት ሰአት ላይ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የግብጽን ቡራኬ ከወዲሁ ሊቋደሱ መቋመጣቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ ማሳወቃቸውም በእርግጥም ከግብጽ ጋር የተፈጠረውን የማይመስል ጋብቻ የሚያጠይቅ ነው፡፡

የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር (ኦአነግ)፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር (ኦነአግ)፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ብሔር ፓርቲ (ኦነብፓ) ሰኞ መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ ባለፈው እሑድ የኢሬቻን በዓል ለማክበር የተሰበሰበው ሕዝብ በሰላም ተቃውሞ እያሰማ እያለ በተፈጠረ ግጭት ከ600 በላይ ሰዎች ሕይወት አልፏል ብለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ በተገቢ መንገድ ለመምራት የሞራልም ሆነ የፖለቲካ ብቃት ያጣ በመሆኑ ሥልጣን እንዲለቅ ፓርቲዎቹ መጠየቃቸውም ከጉዳዩ ጋር የሚያያይዘው ነገር የቱ እንደሆነ ግራ ቢያጋባም የአቋራጭ ስልጣን ፍላጎታቸውን ጥግጋት የሚያመላክት ነው፡፡

የኦነግ አባላት መሆናቸውን  የሚገልጽ ‹‹ባነር›› የያዙ ሁለት ወጣቶች በእሬቻው መድረክ ወጥተው ሲመለሱም የልዩ ኃይሉ ፖሊሶች በትህትና በኦሮሚኛ በማነጋገር እንዳይደግሙት ከማሳሰብ ውጪ፣ ነገሮችን በጣም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲመሩ የነበረ መሆኑን በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች እየመሰከሩም የግብጽ ጀሌዎች የስልጣን መወጣጫ ለማድረግ እየሞከሩ መሆኑ ለወገኖቻቸው ያላቸውን ንቀት ያመላክተናል፡፡

በእነዚህ ዘገባዎች በባህላዊው እና ሃይማኖታዊው መድረክ ‹‹Down Down Weyane›› (ውድቀት ለወያኔ) ‹‹Down Down TPLF›› (ውድቀት ለሕወሓት) የሚል መፈክሮችን በማይክራፎን ሲያሰሙ የነበሩ የፖለቲካ ተላላኪዎችን ተመልክተናል፤ አንዳንዶቹም የሻቢያ ቅጥረኞች መሆናቸው እየተወሳ ነው።

በነዚህ ዘገባዎች እንደተስተዋለው ከወጣቶቹ ላይ ማይክራፎኑን ለመንጠቅ አስተናባሪዎችና ፖሊሶች ቢረባረቡም አንዳንድ ወጣቶች ይህንን ድርጊት የውኃ ላስቲክ በመወርወር ለመቃወም ሲሞክሩ ሌሎቹ የሚወረውሩትን ሲገስጹ ነው፡፡

በወቅቱ የተከሰተው የሰዎች ሕልፈትም በመረጋገጥና በመተፋፈግ መሆኑን አስከሬኖቹን የተመለከቱ መገናኛ ብዙሃኖችና የሆስፒታሎቹ ሜዲካል ዳይሬክተሮች ቢያረጋግጡም  በፖሊሶች የተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ  ከፍተኛ ፍንዳታ የሚያሰማና በመጀመሪያም ከጭሱ ይልቅ ድንጋጤን የሚፈጥረው ድምፁ መሆኑን በዚህ የተነሳ ምን ይከሰታል የሚለውን በአግባቡ ኃላፊዎቹ ሊገነዘቡት የሚገባ የነበረ መሆኑ አያከራክርም፡፡  በዚህም ተባለ በዚያ ይህንን አደጋ ለግጽ አጀንዳ አሳልፎ መስጠትና ለአቋራጭ ስልጣን መንጠላጠያ ማድረግ ክስረት ነው። በዚህ በኩል ሮሮ እያሰሙ በዚያ በኩል ህዝብን ማስመረርም ተቀባይነት የለውም። ከግብጽ ጋር የተደነሰውም ጉሮ ወሸባዬ ታንጎ እንጂ የኦሮሚያን ህዝብ እንደማይወክል ሊታወቅ ይገባል።