እነ ጃዋር እስከ መቼ በድሃው የኦሮሞ ህዝብ ይነግዳሉ?

(ክፍል አንድ)

መግቢያ

ዕለተ ሰንበት—መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም። ቢሾፍቱ፣ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ላይ ይከበር በነበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የተከሰተውና በዓሉም እንዲቋረጥ ያደረገው አሳዛኝ ድርጊት የማንንም ሀገር ወዳድ ዜጋ ልብ ክፉኛ የሰበረ ክስተት ነው። የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ የሰላም፤ የፍቅርና የምስጋና ቀን በዓል ነው። ሆኖም ፀረ-ሰላምና ለመላው ኦሮሞ ህዝብ ኃይሎች በዚህ የኦሮሞ ህዝብ የሰላም፣ የአብሮነትና አምላክን የማመስገን መገለጫ በሆነው ታላቅ ስነ ስርዓት ላይ በፈጠሩት ሁከት ሳቢያ በተከሰተው ግርግርና መረጋገጥ፤ ዕለቱ ጥቁር ደመና አጥልቶበት አልፏል። እናም በሁከት ፈጣሪዎች በተፈጠረው ግርግር የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ አካልም ሊጎድል ችሏል። ይህን ፅሑፍ እያጠናቀርኩ እስከነበርኩበት ጊዜ ድረስ የሟች ወገኖቻችን ብዛት ወደ 100 መጠጋቱን መንግስት አስታውቋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዕለቱ በተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ በዜጎች ላይ ለደረሰው ሞትና የአካል ጉዳት ጥልቅ ሃዘናቸውን ገልፀዋል። መንግስትም ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የሶስት ቀናት ሃዘን አውጇል። እወጃውን ተከትሎ በመዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ እንደ አሜሪካና እንግሊዝን የመሳሰሉ የሀገራችን መንግስትና ህዝብ ወዳጅ ሀገራት ኤምባሲዎች የየሀገራቸውን ባንዴራ ዝቅ አድርገው በማውለብለብ የሃዘናችን ተካፋይ ሆነዋል። እናም ይህ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው አሳዛኝ ክስተት፤ ከማንኛውም የሀገር ውስጥ ዜጋ እስከ ለኢትዮጵያ ህዝቦችና መንግስት በጎ የሚመኙ የውጭ ሀገራትና ህዝቦች ድረስ ዘልቆ መቆርቆርንና ሃዘኔታን የፈጠረ ነው።

በአንፃሩ ደግሞ ሁሌም በድሃው የኦሮሞ ህዝብ ለሚነግዱት ለኦነጋዊዎቹ እነ ጃዋር መሐመድና መሰል የውጭ ሃይሎች ተላላኪዎች ሐሴትን ፈጥሯል። ከአሳዛኙ ድርጊት በስተጀርባ በሰው ልጅ ደምና ፍላፃ አጥንት በመነገድ ሲራራ ነጋዴ ለመሆን ለሚሹት ለእነ ጃዋርና የሃሳብ ተጣማሪዎቻቸው ኢሬቻም ሆነ ሌሎች የኦሮሞ ህዝብ ታላላቅ በዓላት ምንም ዓይነት ትርጉም እንደሌላቸው በገሃድ አሳይተውናል። እናም በማንኛውም ኦሮሞ ዘንድ በከፍተኛ አክብሮት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ለእነ ጃዋር የገንዘብ መሰብሰቢያ ኮሮጆ ሆኖ በቁማር መጫወቻ ካርድነት እያገለገለ ነው። የቁማር ካርዱን “ጆከር” አሜሪካና አውሮፓ ሆነው የሚመዙትና በመጫወቻነት በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ እንደ ዋዛ የሚጥሉት እነ ጃዋር፤ የኦሮሞን ህዝብ ክቡር ህይወት መነገጃ አድርገውታል። በእኔ እምነት በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በከፍተኛ አክብሮትና ስነ ስርዓት በየዓመቱ ባለፈው እሁድ መስከረም 22 ቀን ሳይከበር የተቋረጠው “የፀደይ ኢሬቻ” (Irreecha Birraa) እና መጪው በልግ ሲገባ የሚከበረው “የበልግ ኢሬቻ” (Irreecha Afraasa) በዓልም የዚሁ ቁማር ካርዳቸው መጫወቻ የሆኑና የሚሆኑ ይመስለኛል።

በኦሮሞ ህዝብ የሚከበረው ኢሬቻ—የእነ ጃዋር መጫወቻ?

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው የኦሮሞ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ከሚያከብረው በዓላት ውስጥ አንዱ ኢሬቻ ነው። ይህ የሰላም በዓል ማንኛውም የኦሮሞ ተወላጅ በላቀ ሁኔታ አምላኩን ያመሰግንበታል። አምላኩ ለስህተት፣ ለደባ፣ ለተንኮልና ለውሸት ትዕግስት የሌለው መሆኑን ያስባል። ይህ አምላክ በሰማይና በምድር ያለውን ማናቸውንም ነገር ፈጥሮ የሰው ልጅ እንዲጠቀምበትና እንዲያዝበት ስልጣን ስለሰጠው፤ ለዚህ ሁሉ የማይነጥፍ አምላካዊ ስጦታውና ለተደረገለት ሁሉ የኦሮሞ ህዝብ ምስጋና የሚያቀርብበት ቀን ነው—የኢሬቻ በዓል። ስሙንም እየጠራ ‘እንኳን ከክረምት ወደ ፀደይ በሰላም አደረስከን’ እያለ ተዓምራቱን ከፍ…ከፍ የሚያደርግበትም ታላቅ ዕለት ነው፤ በቅርቡ እንዳይከበር በሁከት ፈጣሪዎች የተስተጓጎለው በዓል።

ከእነዚህ ዕውነታዎች በመነሳት የኢሬቻ በዓል በማንኛውም ኦሮሞ ህዝብ ልብ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ስፍራ ለመገንዘብ የሚከብድ አይመስለኝም። አዎ! በዓሉ በሁሉም የኦሮሞ ተወላጅ ልብ ውስጥ ሰፊ ስፍራ አለው። ከክረምት ወደ ፀደይ በሚደረገው ሽግግር፤ ክረምት በፀደይ ተተክቷልና ደስታ ይገለፃል። የክረምቱ የጨለማ ጉም ተገፎ በብርሃን ተተክቷልና ደማቅ ብርሃን ይታያል። የፀደይ ፀሐይ ያለ ምንም ስስት በሙሉ አቅሟ ልግስናዋን ትቸራለችና ህይወት የደመቀች ትሆናለች። የኦሮሞ አርሶ አደር የዘራው እህል ፍሬ ሊያፈራ በአበባ ደምቆ ሌላው ደግሞ እያሸተ ነውና በተስፋነት ይመሰላል። በክረምቱ ዝናብ ሳቢያ የጨቀየው መሬት በፀደዩ መግባት እየደረቀ ነውና ሁሉም ከየቀየው ብቅ…ብቅ ብሎ የሰላም ቄጤማን የሚያነጥፍበት ወቅት ይሆናል። እናም ይህ ሰንሰለታዊ ክንውን በሁሉም የኦሮሞ ተወላጅና ባህሉን በሚያከብሩ የሀገራችን ወንድሞቹ ዘንድ በየዓመቱ ፀደይ ትውስታው ከታላቅነቱ ጋር አብሮ ውልብ ይላል፤ የኢሬቻ በዓል።

እንግዲህ ይህን አይረሴና ታላቅ ክብር የሚሰጠውን የኦሮሞን ህዝብ በዓል ነው— ፅንፈኞቹ እነ ጃዋር ለንግድ ካርድ መጫወቻነት የመረጡት። በኢሬቻ ላይ ሁከት ፈጣሪዎችን በማደራጀት የበርካታ ንፁሃን ወገኖቻችን ህይወት እንዲጠፋና አካላቸውም እንዲጎድል ያደረጉት። አዎ! እነ ጃዋር በኦሮሞ ህዝብ ደስታ የማይደሰቱ ነጋዴዎች ናቸው። ህዝቡ ባለፈው ክረምት ውስጥ ሰጥሞ ፀደይን እንዳያይ የሚሹ፣ የፀደይ ፀሐይን ሳይጠግብ በዚያው እንዲያሸልብ የሚያደርግ አጀንዳን የሰነቁ፣ አርሶ አደሩ የዘራውን እሸት ማፍራቱን እንዳያይ የፈረዱበትና የነገ ተስፋው እንዲጨልምበት የሚያሴሩ ስብስቦች ናቸው። እናም እኔ በበኩሌ እነዚህን ለባዕዳን በተላላኪነት ተሰልፈው ከኦሮሞ ባህላዊ ትውፊቶች ጋር የሚጋጩና የገዛ ወገናቸውን የሚያባሉ ግለሰቦችንና ቡድኖችን “ኦሮሞዎች ናቸው” ብዬ ለማሰብ አልፈልግም። ምክንያቱም ከኦሮሞ ባህላዊ እሴቶችና እምነቶች ጋር በገሃድ የሚጋጩ ከሆነ፤ የእነዚህ አካላት ኦሮሞነት በምንም ዓይነት ስሌት ቁጥር ውስጥ ሊገባ ስለማይችል ነው—ኦሮሞ ሆኖ ራሱ ከሚያምንበት ትውፊቱ ጋር ሊጋጭ አይችልምና።

ያም ሆኖ ማንኛውም የኦሮሞ ተወላጅም ይሁን ኢትዮጵያዊ የኢሬቻ ክብረ-በዓል የእነ ጃዋር ቁማር መጫወቻ እንዲሆን በፍፁም መፍቀድ ያለበት አይመስለኝም። ምክንያቱም እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች ዛሬ ኢሬቻን በመበጥበጥ የንፁሃን ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ ካደረጉ፣ ነገ ደግሞ እያንዳንዱ የኦሮሞ ተወላጅ በግልም ይሁን በቡድን የሚያምንበትን እምነት ተፃርሮ እንዲቆምና እርስ በእርሱ እንዲናከስ ከማድረግ ስለማይመለሱ ነው። ይህም የእነ ጃዋር ልብና አመለካከት ከኦሮሞ ህዝብ ጋር አለመሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል። እሳቤያቸው ‘ገንዘብ እስካስገኘ ድረስ ማንኛውም የሁከት መንገድ ትክክል ነው’ የሚል በመሆኑም ባህላዊም ይሁን ሃይማኖታዊ ቀኖናዎችን ከመጋፋት ወደ ኋላ አይሉም። ለዚህም ነው—የኦሮሞ ህዝብ በታላቅ አክብሮት የሚያከብረውን ዕለተ-ኢሬቻን ያደናቀፉት። ለዚህም ነው—ኦሮሞ ለአምላኩ ‘እንኳን በሰላም አደረስከኝ’ ብሎ በነቂስ ሲወጣ ሰላሙን ነስተውት የሐይቅና የናዳ ሰለባ ሆኖ ህይወቱን እንዲያጣ ያደረጉት። ለዚህም ነው— ለአምላኩ የሚያቀርበውን ምስጋና ሳይጀምር በተቧደኑ ጥቂት ጀሌዎቻቸው አማካኝነት ምስጋናውን ወደ ሐዘን የለወጡበት።

ይህ ሃቅም እነ ጃዋር አምላክ የሌላቸው ወይም ባህላዊ ትውፊቶችን የሚፃረሩ አክራሪዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድም ከኦሮሞ ባህል ባፈነገጠ ሁኔታ አባገዳዎች በበዓሉ ላይ ንግግር ሲያደርጉ፤ የእነ ጃዋር ጀሌዎች መነጋገሪያውን (ማይክራፎኑን) ከአባገዳዎች እጅ ላይ በኃይል በመንጠቅ መድረኩ ላይ ወጥተው ከበዓሉ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው የፖለቲካ ቅስቀሳዎች ማድረጋቸውን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። ይህም የእነ ጃዋር ቡድን ከጥንት ጀምሮ የኖረውንና በአባገዳዎች የሚመራውን ብሎም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ህዝብ በዩኔስኮ የባህል ቅርፅነት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ተግባራትን እያከናወኑለት ያለውን የገዳ ስርዓት በመቃወም የራሳቸውን የተለየ ስርዓት ህዝቡ ውስጥ ለማስረፅ እየተጫወቱ መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ይመስለኛል። ይህ ጨዋታቸው የአንድን ብሔር የአምልኮ መብት በጠራራ ፀሐይ የሚገፍ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባር በመሆኑ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል።

አባገዳዎችን የማያዳምጥና የማያከብር ተቃውሞ—ለምን?

ሁከት ፈጣሪዎቹ የእነ ጃዋር ጀሌዎች በክብረ-በዓሉ ላይ በደንቡ መሰረት በበዓሉ ላይ አምላክን በማመስገን ምርቃት ለመስጠት የተገኙ አባገዳዎችን ከመድረኩ ላይ በማውረድ እንደማያዳምጧቸውና እንደማያከብሯቸው በገሃድ አሳይተዋል። ግና እዚህ ላይ ‘ለምን አባገዳዎችን የማያዳምጥና የማያከብር ተቃውሞ ተፈጠረ?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። እርግጥ ጥያቄውን ለመመለስ ዙሪያ ጥምጥም መጓዝ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ሃቁ ግልፅ ነው። ይኸውም እነ ጃዋርና ጀሌዎቻቸው ለየትኛውም የኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ ትሩፋቶች ቦታ የማይሰጡ መሆናቸው ነው።

በእኔ እምነት የኦሮሞ ህዝብ የገዳ ስርዓት የዴሞክራሲ መሰረትና ሁነኛ ማሳያ ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ ስርዓት በ1424 ዓ.ም መጀመሩ ይነገርለታል። እንደ ማንኛውም ዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፤ የገዳ ስርዓትም ህግ አውጪ፣ ህግ አስፈፃሚና ህግ ተርጓሚ አካላት አሉት። በዚህ የስልጣን ክፍፍል መሰረትም ስርዓቱ ህዝቡን በባህላዊ መንገድ ያስተዳድራል። በስልጣን ክፍፍሉ ቦታ ውስጥ አባገዳዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይወስዳሉ። የላይኛው የስልጣን እርከን የአባገዳው ነው። እናም በየስምንት ዓመቱ አንዴ የሚመረጠው አባገዳ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ መናቻውን ተግዳሮቶችን ይፈታል፤ የሚፈቱበትን መንገዶችንም ያመላክታል።

በስርዓቱ ውስጥ የቤተሰብ፣ የጎረቤት፣ የአካባቢ ወይም የደን ጥበቃ እንዲሁም የግጭት አፈታት ስርዓት እስከ አሁን የተረጋገጡና እየተሰራባቸው የመጡ ህግጋት ናቸው። የዚህ ስርዓት ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት አባገዳ በህብረተሰቡ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸውና ክብር የሚቸራቸው ናቸው። ህብረተሰቡ እርሳቸው ያሉትን በባህሉና በደንቡ መሰረት ይፈፅማል። በአጭር አነጋገር አባገዳው የኦሮሞ ህዝብ ዘውግ ናቸው ማለት ይቻላል። ሁሉም የኦሮሞ ተወላጅ አክብሮትን በመቸር ለአባገዳው ውሳኔ ተገዥ ይሆናል።

ይሁንና በኢሬቻ በዓል ላይ የተገኘውና እነ ጃዋር ያደራጁት ጀሌ ከዚህ የኦሮሞ ህዝብ ወግና ባህል ባፈነገጠ መልኩ በቅርቡ ከተመረጡት አባገዳ እጅ ላይ መነጋገሪውን በመንጠቅና መድረኩን በመቆጣጠር ያሻውን ሲፈፅም ታይቷል። ይህም እነ ጃዋር ቀደም ብለው ላደራጁት ጀሌ የሰጡት ቀጥተኛ ትዕዛዝ መኖሩን የሚያሳይ ይመስለኛል። እርግጥም እነ ጃዋር ከተቻለ የኢሬቻ በዓሉን መቆጣጠርና ከህዝቡ ፍላጎት ውጪ በሆነ ሁኔታ በራሳቸው መንገድ ለመምራት፣ ይህ ካልተሳካ ደግሞ ኢሬቻውን ማደናቀፍ የሚያስችል የሁከት መንገድን እንዲከተሉ አስቀድመው ለጀሌዎቻቸው መመሪያ የሰጧቸው መሆኑ ጥርጥር ያለው አይመስለኝም። በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም የተመለከትኩት ይህንኑ መሰል ‘የመተግበሪያ መንገድ’ ነው። እናም ጀሌዎቹም አብዛኛው ህዝብ የእነርሱን ፍላጎት የሚከተል ባለመሆኑ በዓሉን ሙሉ ለሙሉ ሊቆጣጠሩት ባለመቻላቸው በዓሉን ለማወክ ችለዋል። በዚህም ሳቢያ የተፈጠረውን ዘግናኝ ነገር ተመልክተናል።

ዳሩ ግን ይህ የሁከት ፈጣሪዎቹ አባገዳዎችን የሚያዋርድና የማያዳምጥ የንቀት መንገድ ዓላማው ግልፅ ይመስለኛል። እርሱም የኦሮሞን ህዝብ ሰላም በመንሳት በክልሉ ውስጥ አለመረጋጋት ተፈጥሮ ህዝቡ የጀመራቸው የልማት ዕቅዶች ዕውን እንዳይሆኑ በተላላኪነት የሁከት ተግባርን መፍጠር ነው። እየሆነ ያለውም ይኸው ነው። ሆኖም ይህን መሰሉ የትርምስ አጀንዳ ለየትኛውም ህዝብ የሚጠቅም አይደለም።

ለእነ ጃዋር በኦሮሞ ህዝብ ስም የመነገድ ተግባር ሀገር ቤት ያለው የብሔራችን ተወላጅ ተቀጣጣይ ጧፍ መሆን የለበትም። የፅንፈኞቹን የእነ ጃዋርን “የምኞት ዓለም” ዲስኩርን በመስማት ነባሩን የገዳ ስርዓት ለመሻር መሞከር ባህሉንና ትውፊቱን ከሚያከብረው ከአብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ጋር ከመጋጨት በስተቀር የሚያስገኘው አንዳችም ፋይዳ ያለ አይመስለኝም። በኢሬቻው ዕለት አባገዳዎችን በወቅቱ ባለማዳመጥና ባለማክበር የተፈጠረው ክስተት ያስከፈለው መስዋዕትነት ጥሩ መልዕክት ሰጥቶን ያለፈ ይመስለኛል።

አባገዳዎች ከስድስት በላይ ለሚሆኑ ክፍለ-ዘመናት የኦሮሞን ህዝብ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ችግሩን ሲፈቱለት የመጡ እንደመሆናቸው መጠን፤ ችግሮች ካሉም መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉት እነርሱ እንጂ በሰው ልጅ ደም የተላላኪነት ንግድ የሚያካሂዱት እነ ጃዋር አለመሆናቸውን ክስተቱ የማይዘነጋ ዕውነታን አሳይቶናል ማለት ይቻላል። እናም አባገዳዎችንና ሽማግሌዎችን አለማዳመጥ አለማክበር ለኦሮሞ ህዝብ በጎ የማያስቡ ኃይሎች እንጂ የየትኛውም ኦሮሞ መገለጫ አለመሆኑን መገንዘብና ለዚህም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መስራት የሚገባ ይመስለኛል።

ከሁከት ፈጣሪዎቹ በስተጀርባ የእነማን እጆች አሉ?

ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ‘እነ ጃዋር ተላላኪዎች ናቸው’ የሚል ሃሳብ ሳነሳ፤ በውድ አንባቢዎቼ አዕምሮ ዘንድ ‘የእነማን?’ የሚል ጥያቄ መመላለሱ የሚቀር አይመስለኝም። እናም ጊዜው አሁን በመሆኑ የላኪዎቹን ማንነት ከራሴ ድምዳሜ በመነሳት እንዲህ እገልፃቸዋለሁ። ሃሳቤን በማስረጃ ማስደገፍ እችል ዘንድም ውድ አንባቢዎቼን በእግረ-ህሊና የዛሬ አራት ዓመት ተኩል ገደማ ልውሰዳችሁ።…

ነገሩ እንዲህ ነበር። በሀገር ቤት ወቅቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተመርቆ ስራ የጀመረበት ነበር። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ: በዕውቀቱና በገንዘቡ ለግድቡ ግንባታ ርብርብ ያደርጋል። “የነገ ሰውነቱን” በማሰብ ሁሉም በየፊናው ያቅሙን ያደርጋል። ከዕለት ጉርሱ እየቀነሰ ያለውን ነገር ሁሉ ለግድቡ ግንባታ ያውላል። በአራቱም የሀገራችን ማዕዘን የሚገኘው ኢትዮጵያዊ የራሱን የማይደበዝዝ ደማቅ ታሪክ ለመፃፍ እጁን ይሰነዝራል።…”ያለውን የሰጠ፣ ንፉግ አይባልም” እያለ።

በግብፅ በኩል ግን ሀገራችን በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም መብት የሌላት ይመስል፤ ‘ሁሉም ነገር ወደ ኢትዮጵያ ግንባር’ የተባለ ይመስል ነበር። የሀገሩንና የህዝቡን ልፋት መና ለማስቀረት የባዕዳን ተላላኪ ሆኖ የተሰለፈውና ራሱን “ኦነግ” እያለ የሚጠራው የሽብር ቡድን ካይሮ ከተማ ላይ የግብፅን ሰንደቅ ዓላማ አንግቦ “አኛ ኦሮሞዎች እንጂ ኢትዮጵያዊያኖች ስላልሆንን የዓባይ ግድብ አይመለከተንም” በማለት የተላላኪነት ሚናውን ሲወጣ አይተነዋል። ይህ ባንዳ ቡድን እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው የኦሮሞ ተወላጅ ለግድቡ ግንባታ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያለውን ጥሪት በመስጠት ሀገራዊ አሻራውን ለማኖር ከዳር እስከ ዳር መነቃነቁ ምኑም አይደለም። “ውሻ በበላበት ይጮሃል” እንዲሉ አበው፤ “ኦነግ” የተሰኘው የግብፆች ጀሌም፤ በወቅቱ ተላልኮ የሚጣልለትን ፍርፋሪ እንጂ የህዝቦችን ዘለቄታዊ ጥቅም የማይመለከት በመሆኑ በባንዳነት ተሰልፎ የገዛ ሀገሩን ለመቃወም የበቃ አሳፋሪ ባንዳ መሆኑንም ተግባሩ ፊት ለፊት አፍ አውጥቶ ተናግሯል።

ዛሬስ?…አዎ! ዛሬም ያው ነው። ከዚህ ቀደም ከአስመራ ተነስቶ ካይሮ ድረስ በመሄድ ሰላማዊ ሰልፍ ቢያደርግም በአሁኑ ወቅት ግን እዚያው ግብፅ ውስጥ ሆኖ በግብፆች ሲሽሞነሞን እየተመለከትነው ነው። ሰሞኑን በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና በአንዳንድ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ እንደተመለከትኩት፤ በአንድ አዳራሽ ውስጥ ግብፆች የኦነግን ባንዴራ አንገታቸው ላይ አድርገው የግብፅ ባለስልጣን ድምፀት ያለው በሚመስል ሰው አማካኝነት ከሶስት ደቂቃ በላይ በሚዘልቀው የቪዲዮ ምስል ላይ የግብፅና የኦሮሞ ህዝብ ጉርብትና በየት በኩል ኩታ ገጠም እንደሆነ ባይገባኝም፤ “ጎረቤቶቻችን እናንተ ኦሮሞዎች…” በማለት ይጀምርና “…ሀገር ቤት ውስጥ እያካሄዳችሁ ያለውን ትግል እናውቃለን። ራሳችሁን ነፃ እስከምታወጡ ድረስ የምናደግላችሁን ድጋፍ አናቋርጥም።…” የሚል መልዕክት እያስተላለፈ ይቀጥላል። ሌላ ሌላም “የአብረናችሁ ነን” ዲስኩርን ያሰማል። እርግጥ ይህ በአሁኑ ወቅት የግብፅ አንዳንድ አካላት የሚያስተላልፉት መልዕክት በሙባረክ ዘመን ተሞክሮ የከሸፈ በመሆኑ ዛሬ ላይ ይሰራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል።

ውድ አንባቢያን ‘ከሁከት ፈጣሪዎቹ በስተጀርባ ያሉትን እጆች’ የሚዳስሰው ምልከታዬ በዚህ አልተቋጨም። ገና ቀሪ ሃቆች ይንሸራሸሩበታል። እናም በክፍል ሁለት ፅሑፌ ላይ ይህን ምልከታዬን እንዲሁም በእነ ጃዋር ትዕዛዝ ሰጪነት ከተቋረጠውና በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ ካለው የኢሬቻ በዓል ጋር የተያያዙ ሁነቶችን ላስነብባችሁ እሞክራለሁ።