ሥርዓቱ ውጣ ውረዶችን አልፏል፤ ዛሬም ተግዳሮቶችን ይሻገራል!

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመስረት ውድ የህዝብ ልጆች ህይወታቸውን የሰጡትንና አካላቸውን ያጎደሉትን ብሎም ንብረታቸውን ያጡትን ያህል እንኳን ባይሆንም፤ ከሥርዓቱ ምስረታ በኋላ በርካታ ውጣ ውረዶች ታልፈዋል፡፡ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊው ሥርዓትን ዕውን ለማድረግ ከተከፈለው መስዕዋትነት አንፃር ሲታይ አሁን የተፈጠሩት ተግዳሮች የማይፈቱ አይደሉም፡፡ ሥርዓቱ ተግዳሮቶቹን ለመፍታት ልምድ ያለው ብቻ ሳይሆን አቅምም ያለው ነው፡፡

ያለፈውን ታሪካችንን መለስ ብለን ስንመለከት ያለፉት ሥርዓቶች ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ገዥዎችን ተጠቃሚ ያደረጉት ብቻ ሳይሆኑ፤ ሀገራችንን በሁለንተናዊ መልኩ ጎድተዋታል፡፡ ምጣኔ ሀብቷን አድቅቀዋል፤ ዜጎቿን የበይ ተመልካች በማድረግ ለችጋርና ለስደት ዳርገዋል፡፡ ይህ የታሪካችን አንድ አካል መሆኑ ጨርሶ የሚካድ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ በተለይ የጥቂት መኮንኖች ስብስብ የነበረው ወታደራዊው አምባገነናዊ የደርግ ሥርዓት የህዝቡን የትግል ውጤት በመቀማትና አጋጣሚውን በመጠቀም ድሉን ወደ የራሱ አስመስሎ በሀገሪቱ ላይ ተጨማሪ ጣጣ ፈጥሮ ማለፉ የትናንት ትውስታችን መሆኑ አይረሴ ነው፡፡

ይሁንና ሕዝቦቿ ከደርግ ውድቀት በኋላ የተረጋጋች እና ዜጎቿም ተፈቃቅደውና አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት መስርተው እርስ በርስ እየተከባበሩ በፈጠሩት ፌዴራላዊ ሥርዓት የፈጣንና ተከታታይ ልማት ተቋዳሽ የሚሆኑበት ሀገር ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ታዲያ ይህን እየጎለበተ የመጣውንና የዴሞክራሲ ባህል እየተገነባባት ያለች ሀገርን ለመመስረት እልህ አስጨራሽ ትግልንና የህይወት መስዋዕትነትን ጭምር ጠይቋል፡፡ ይህ በታሪክ ሁሌም የሚወሳ ሃቅ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ወታደራዊው አምባገነን የደርግ ሥርዓት በተደመሰሰበት ማግስት ለሌላ ትግል የሚጋብዙ ፈታኝ የአስተሳሰብ ተግዳሮቶች በሀገሪቱ ተፈጥረው ነበር፡፡ በወቅቱ ተራማጅ አስተሳሰብን የያዙ ፌዴራሊዝም ለዘመናት ደም አፍሳሽ የሆነውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ቀውስ ለመፍታት ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ያመኑ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በአንድ ጎራ፤ በሌላ ወገን ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ሁለት ፅንፎች ጫፍ ላይ የወጡ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ወገኖች ነበሩ፡፡

ከእነዚህወገኖች ውስጥ አንደኛው፣ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታን ባላገናዘበ መልኩ የችግሮቹ መፍትሄ መገነጣጠል ነው ብሎ የሚያምን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የሀገሪቱ መፍትሔ የሆነውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንደ መበታተን አደጋ በመቁጠር ባረጀ እና ባፈጀ የአንድነት ስም የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ መብት ብሎም መፈቃቀድን “በእኛ እናውቅልሃለን” የፖለቲካ እሽክርክሪት በማጦዝ ሀገሪቱን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት አልመው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ነበሩ፡፡ ታዲያ በወቅቱ እነዚህን ተግዳሮቶች በሰከነ ብስለት በመፍታት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊት ሀገርን ለመመስረት ከፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር ከባድ ትግል ማካሄድ ግድ ብሎ ነበር። ውጤቱም በተራማጅ ኃይሎች አሸናፊነት እልባት ሊሰጠው ችሏል፡፡

ከዚህ በኋላም ቢሆን ሁሉም ነገር ደልዳላ አልነበረም፡፡ መግለፅ በሚያስቸግር መልኩ ሀገሪቱ ከባድ ፈተናዎች እንደገና ከፊት ለፊቷ ተደቀነባት፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች የላቀ ስፍራ የያዘው እና የሀገሪቱ ዋነኛ ጠላት የሆነው ድህነትን የመዋጋት ዘመቻና ገፅታን የመቀየር ስራ ነበር፡፡ ታዲያ ይህ የጋራ ጠላት መፍትሔ የሚያገኘው በመንግሥትና በመላ ሀገሪቱ ዜጎች  የተባበረ ክንድ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡

እናም ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት በቅድሚያ የመሪነት ሚናውን በመውሰድ ህዝቡን በአስተሳሰብ ደረጃ በድህነት ላይ ድል እንዲቀዳጅ የማድረግ ኃላፊነትን በሚገባ ለመወጣት ቆርጦ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡ በወቅቱም ‘ድህነትን የመታገል ታላቅ ጉዞ እንዴት ሊከናወን ይቸላል? ይህን የጋራ ጠላት ተዋግቶ ለማሸነፍ መሠረታዊ የሚባሉ ቁልፍ ጉዳዮችስ ምንድናቸው?’ የሚሉ ዐብይ ተግባራትን መለየት ወሳኝ ጉዳይ ነበር፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሆነውን ህገ መንግሥት ማፅደቅ ቁልፉ ተግባር ሆኖ ብቅ አለ፡፡

እርግጥ ህገ መንግሥቱን ለማፅደቅ መንግሥት መድረኩን ቢያመቻችም አንዳንድ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎችና የህዝቡን የሥልጣን ባለቤትነቱን በአቋራጭ ለመንጠቅ ያሰፈሰፉ ፀረ ሠላም ኃይሎች ሁኔታውን በቀላሉ ሊቀበሉት አልፈቀዱም፡፡ ሆኖም በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግሥት ሥልጣን ከህዝብ የሚመነጭ እንደሆነ እነዚህ ወገኖች በግልፅ እንዲያውቁ የተለያዩ ጥረቶችን ከማድረግ አልቦዘነም፡፡ እናም ሥልጣን የሚገኘው ከኢትዮጵያ ህዝብ በሚሰጥ የይሁንታ ድምፅ እንደሆነም የማረጋገጥ ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህ ወቅት ‘ሀገሪቱ ህገ መንግሥት ሊኖራት አይገባም እንዲሁም ብሔርን መሠረት ያደረገ ፈዴራላዊ ሥርዓት የምትገነባ ሀገር በምንም መልኩ ተጠቃሚ ልትሆን አትችልም’ የሚሉ ተቃራኒ አመለካከቶች ዋነኛ ፈተናዎች ሆነው ብቅ ቢሉም ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡

እናም እነዚህ ውጣ ውረዶች ዴሞክራሲያዊ ምላሽ እየተሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈቅደውና ተማምነው ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የኢፌዴሪ ህገ መንግሥትን ማፅደቅ ችለዋል፡፡ ህገ መንግሥቱም የቃል ኪዳናቸው ሰነድ በመሆን የኢትዮጵያ ህዝቦችን የዘመናት ጥያቄዎችን ሊመልስ በቃ፡፡ ህዝቦቿም ሀገርን አዋርዶና ህዝብን አሸማቅቆ ዜጎችን ለተመፅዋችነት የዳረገው ብሎም ለዘመናት ከጫንቃቸው ላይ አልወርድ ብሎ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ክፉ ጠላት ጋር ግልፅ ውጊያ መግጠም ጀመሩ፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከድህነት በላይ ጠላት እንደሌላቸውም አረጋገጡ፡፡ ይህን በጽናት ለመዋጋትም እጅ ለእጅ ተያያዙ፡፡

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመንግሥት በተነደፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ማስመዝገብ ጀመሩ፡፡ ከድህነት አዙሪት ተላቀው ወደ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት መሸጋገርን ተያያዙ፡፡ ውጤቱንም ማጣጣም ጀመሩ፡፡ ህገ መንግሥቱ ፀድቆ በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት እውን ከሆነ ወዲህ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ምላሽ እያገኙ መጡ፡፡ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸን ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ አረጋገጠላቸው፡፡ በእነዚህ መብቶቻቸውም ተጠቃሚ ሆኑ። በእርግጥም የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ትግል መንስዔም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ነበርና ይህም ሆነ፡፡

እርግጥ ህዝቦች የዘመናት ጥያቄዎቻቸውን በመለሰው ህገ መንግስት መብቶቻቸውን ቢያጣጥሙም ውጣ ውረዶቹ ግን አልቀሩም፡፡ በተለይም ጨለምተኞችና ፅንፈኞች  ‘የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ከሆነ ሀገሪቱ ወደማያባራ ጦርነት ውስጥ ትገባለች፤ ሀገሪቱም የመበታተን አደጋ ይገጥማታል፣ ህዝቦቿም በየጎራው ተከፋፍለው እርስ በርሳቸው ይጨራረሳሉ’ የሚል ልቦለድ ድርሰት በመከተብ ማርታቸውን እንዳጧጧፉት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በወቅቱ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ብዙ ደሰኮሩ፤ የፖለቲካ ተንታኞች ተብዬዎችም ብዙ ቀበጣጠሩ፤ ፅንፈኞችም ‘ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለሀገሪቱ አይበጅም’ ሲሉ ብዙ አራገቡ፡፡

እርግጥ በወቅቱ ጨለምተኞቹና ፅንፈኞቹ በሀገሪቱ የተዘረጋው ፌዴራላዊ ሥርዓት ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠፍቷቸው አልነበረም— የቀድሞው ሥርዓት ናፋቂ ከሆኑት ኃይሎች ጋር በመሰለፍ ማቀንቀኑን መርጠው እንጂ፡፡ ግና ጨለምተኞቹና ፅንፈኞቹ ያሻቸውን ቢሉም መንግሥትና ህዝቡ በውዠንብራቸው ሳይዘናጉ ብዝኃነታቸውን ውበታቸው በማድረግ አንድነታቸውን አጠናክረው ለጋራ ዕድገት መረባረቡን መረጡ፡፡ በዚህም በሀገራችን ዕውን እየሆነ ያለው ሥርዓት በማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝና የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን አስመስክረዋል፡፡ ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወት እምነትን አስይዞ በአዲስ የአስተሳሰብ መንፈስ ወደ ልማት ጎዳና መትመም ችለዋል፡፡

እናም ሥርዓቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት የቻለ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ሥርዓቱ እነዚህን ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ ሀገራችንንና ህዝቦቿን ዛሬ ላይ ላሉበት አስተማማኝ ቁመና ቢያበቃትም ቅሉ፤ አሁንም ተግዳሮቶችን እያስተናገደ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱት እነዚህ ተግዳሮቶች መሰረት ያደረጉት የህዝቡን ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዩችን ቢሆኑም፤ ሀገራችን እየተከተለችው ባለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አማካኝነት የተመዘገበው ድል በማይዋጥላቸው የውስጥና የውጭ ፅንፈኛና ፀረ-ሰላም ኃይሎች መጠለፉ እውነት ነው፡፡ የህዝቦች ጥያቄዎች በፅንፈኞችና ሀገራችንን ሁሌም በሚያስደነግጣቸው አንዳንድ የውጭ ሃይሎች መጠለፉም በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ውስጥ ሁከትና ግጭት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህም ሳቢያ ህይወት እያለፈ ነው፤ ንብረት እየወደመ ነው፡፡ አሁን ሥርዓቱን ያገጠሙት ተግዳሮቶች እነዚህ ይመስሉኛል፡፡

እናም በእኔ እምነት ተግዳሮቶቹን መፍታት የሚቻለው በሥርዓቱ ብቻ ነው። እርግጥ ሀገራችን ውስጥ እየተተገበረ ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትናንት ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ውጣ ውረዶችን እየፈታና ችግሮችን እያረመ የመጣ በመሆኑ እነዚህ ተግዳሮቶች ይፈታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ዛሬ ሥርዓቱን ተግዳሮቶቹ እየፈተኑት ቢሆኑም፤ የችግሮቹ አራማጅ ኃይሎች የዘመናት ጥያቄያቸውን በህገ መንገስቱ ያረጋገጡት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለመሆናቸው፤ ከመንግስት ጋር ሆነው በሥርዓቱ አማካኝነት ተግዳሮቶቹን እንደሚፈቷቸው በእርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ ሌሎች ተግዳሮቶች ቢያጋጥማቸውም ዋስትናቸው ዴሞክራሲያዊና ፌደራላዊ ሥርዓቱ በመሆኑ በህግ አግባብ መሻገራቸው አይቀሬ ነው፡፡