የሀገር ሀብትና ንብረት ሲወድም የሚስቅ እሰይ የሚል የሀገርን ምንነት ያልተረዳ ወይንም ደግሞ የሀገርና ወገን ጥላቻ ያለው ሰው ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ሀገር የህዝብ እንደመሆንዋ መጠን ሰላምና ደህንነትዋን ነቅቶ ሊጠብቃት የሚችለው ህዝብ ነው፡፡ ዘመንም፣ መንግስታትም ሊቀያየሩ ይችላሉ፡፡ ሀገርና ህዝብ በየትውልዱ ፈረቃ ያለማቋረጥ ይቀጥላሉ፡፡ በሀገር ንብረት መውደም የሚስቅና የሚሳለቅ ሰው ነገ ምን ሊመጣ ይችላል ብሎ ለመገመት የተሳነው ጅል ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
የሀገሪቱ ሀብት ተጠብቆ ሊቀጥል እንጂ ሊወድም አይገባውም፤ ነገም ከነገ ወዲም የሚጠቅመው ህዝቡን ነውና፡፡ በአንድ ከድህነት ለመውጣት ሰፊ ትግል በያዘች ሀገር ላይ መሰረተ ልማት በአብዛኛው ባልተስፋፋበት ይሄንኑም ለማሳካት ሌት ከቀን በሚሰራበት ሀገር ተቃውሞን በመንተራስ የሚካሄዱት ስንትና ስንት የተለፋባቸውን መሰረተ ልማቶች ንብረቶች በእሳት ማጋየትና ወደ አመድነት መለወጥ እጅግ በጣም አሳዛኝ ድርጊት ነው፤ ሕብረተሰቡንም ለከፋ ችግር መዳረግ ነው፡፡ በስክነት ሲታሰብም በስፋት የሚጎዳው የአካባቢው ህብረተሰብ ነው፡፡ ህዝቡ በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ከመልካም አስተዳደርና ከፍትህ፣ ከመሬት ቅርምትና ሽያጭ ከሙስና ጋር በተያያዘ በስፋት ያሰማቸው ተቃውሞዎችና የመብቴ ይክበርልኝ ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን መንግሰት ተቀብሎ ጥልቀታዊ ተሀድሶ ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡
ይህንን ስር የሰደደ ችግር መንግስትና ህዝብ በጋራ ውይይት እንደሚፈቱት ይታመናል፡፡ ሆኖም ግን በህዝቡ ውስጥ የሚሰማው ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ ወደከፋ ደረጃ እንዲለወጥ የተፈጠረውን አጋጣሚ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመለወጥ በተለይም ግብጽና ኦነግ ሀገር ውስጥ ያሉ ወኪሎቻቸውን በመጠቀም ከፍተኛ የገንዘብ በጀት በመመደብ በከፍተኛ ደረጃ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በየአካባቢው ያሉ ወጣቶችን በስፋት በመመልመልና በማሰማራት በሀብትና ንብረት ማውደም ስራ ላይ እንዲሰማሩ አድርገዋል፡፡ ለዚህም በውጭ ሚዲያ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ሽፋን እንዲያገኙ ከማድረግም አልፈው ሁኔታውን ለማቀጣጠል ሶሻል ሚዲያዎችን በስፋት በመጠቀም በህዝቡ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሽብር ውስጥ እንዲገባ በፍርሀት እንዲዋጥና ነገን በፍርሀት እንዲመለከት እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያይ ግጭት ወስጥም እንዲገባ የማድረግ ሰፊ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡
ግብጽና ኦነግ እንዲሁም ያሰማሩዋቸው ወኪሎቻቸው የህዝቡን የመብቴ ይከበርልኝ ተቃውሞና ጥያቄ ቀዳዳውን በመጠቀም ርቀው በመሄድ በውጭ የሚገኙት አለቆቻቸው በሚያስተላልፉላቸው ትእዛዝ መሰረት የመንግስትና የህዝብን እንዲሁም የልማታዊ ተቋማትን ንብረቶች ማንደድና ማጋየቱን ተያያዘውታል፡፡
የታቀደው የንብረት ማውደሙ ድርጊት አንዱ ግብ የውጭ ኢንቨስተሮች ሀገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት የለም በሚል እንዳይመጡ፣ ገብተው በስራ ላይ ያሉትም ድርጅቶቻቸውን ዘግተው ሰላም የለም በሚል እንዲወጡ የማድረግ በአጠቃላይ የሀገሪቱን ልማትና እድገት የማሰናከል የተጀመሩ ታላላቅ ሀገራዊ እድገትና ለውጥ የሚያመጡ ፕሮጀክቶች የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ እንዲቆሙና እንዲስተጓጎሉ የማድረግ መሰሪ ሴራ ሲሆን ይሄንንም አድርገውት አይተናል፡፡ ይሄንን ደግሞ በምንም መልኩ ተቀብለን መቀጠል አንችልም፡፡ ከጀርባው የጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች እጅ እንዳለበት ግልጽ ነውና፡፡
ንብረት ማውደም ለምን የሚለው ጥያቄም የሚነሳውም እዚሁ ላይ ነው፡፡ ድርጊቱ ከህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄና ተቃውሞ ጋር እንደማይገናኝ ማሳያው ይሀው የተለየ ሀገርና ንብረት የማውደም ድርጊት ነው፡፡ ህዝቡ የመብቴ ይከበርልኝ ጠንካራ ተቃውሞ ማሰማቱ ቅሬታውን በተለያየ መንገድ መግለጹ በመንግስትም በኩል ችግሩን ተቀብሎ ጥልቀት ያለው ተሀድሶ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑ እየተገለጸ ባለበት ሁኔታ ለውጦቹን መጠበቁ ተገቢ ሁኖ ሳለ ህዝብ የራሱ መጠቀሚያ በሆኑ ንብረቶች በመንግስትና በህዝብ ሀብቶች ላይ የማውደም እርምጃ እንደማይወስድ ይታወቃል፡፡
ፋብሪካዎች ሲቃጠሉ ግዙፍ ንብረቶች ተሸከርካሪዎች በእሳት እንዲጋዩ ሆን ተብሎ ሲደረግ ሲወድሙ በአካባቢው በነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥሮ እየሰራ የሚኖረው ህዝብ ብዙ ቤተሰብ የሚያስተዳድረው ልጆቹን የሚያኖርበት የገቢ ምንጩ እንደሚዘጋ ስለሚያውቅ ይሄንን ድርጊት በፍጹም አያደርገውም ማለት ይቻላል፡፡ በራሱና በቤተሰቡ በልጆቹ ጉሮሮ የመፍረድ ያህል የአላዋቂነት ስራ መሆኑን ያውቃልና፡፡
የዚህ እኩይ ተግባር መሪዎችና ተባባሪዎች ለረዥም ግዜ አድፍጠው ጥናት ሲያካሂዱ የነበሩና አጠቃላይ ሀገራዊ ቀውስና ስራ አጥነት እንዲሰፍን፣ ስራ ያጡትም በተቃውሞው ጎራ በስፋት እንዲቀላቀሉ፣ መንግስትን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በመክተት የጸጥታ አስከባሪውንም ሀይል አቅም በየቦታው እንዲበታተን በማድረግ በዚህ አጋጣሚ ያቀድነውን እናሳካለን፣ እናወድማለን፣ እናቃጥላለን ብለው የሚንቀሳቀሱ የቀለም አብዮት ናፋቂዎችና አክራሪ እስላማዊ ሀይሎች በጥምረት የሚመሩት ሀገር የማጥፋት ድርጊት ነው፡፡ በሌሎች አገራት በተግባር የታየው ቀመርም ይሀው ነው፡፡
ይህንን ሀገር የማውደም ድርጊት የውጭ መንግስታት እንዲያውቁት በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንደሌለ ማሳያ አድርገን እንጠቀምበታለን በሚል ስሌት የተቀናበረ የተጠና የቀለም አብዮተኞችና የአክራሪዎች ኤክስፐርቶች ምክርና አመራር ያለበት መሆኑን በገሀድ ያሳያል፡፡ የዚህ ድርጊት አቀናባሪዎችና መሪዎች ለዚሁ የጥፋት ተግባር የሚውል በተለያየ ግዜያት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በስውር ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተው ወይንም በሽፋን በሚንቀሳቀሱ ወኪሎቻቸው አማካኝነት ገንዘቡ ወደክልሎቹ እንዲገባ በመደረጉ የተወሰኑ ወጣቶችንም በገንዘብ ሀይል በመግዛት ለዚህ የጥፋትና ውድመት ድርጊት እንዳሰማሯቸው ለመገመት አያስቸግርም፡፡
የነጃዋር መሀመድ አክራሪ እስላማዊ ፖለቲካና ኦነግ ሙሉ በሙሉ በግብጽ መንግስት በመደገፍ የግብጽ ሹሞችም ይፋ ድጋፍ ለኦነግ እንደሚሰጡ በገለጹበት ድርጊትና ሁኔታ ውስጥ ሲታይ በአሁኑ ሰአት ኢትዮጵያን ከውስጥ የማተራመሱና በየቦታው ንብረትና ሀብት የማውደሙ ሴራና ድርጊት የተመራውና የተቀናበረው በእነዚሁ ሀይሎች ለመሆኑ ቅንጣት ጥርጣሬ የለም፡፡
ግብጽ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ምንም ችግር የለም ተግባብተን እየሰራን ነው ስትል የሰጠችው መግለጫ ማዘናጊያና አቅጣጫ ማስቀየሪያ እንደነበር አሁን ላይ በይፋ ማየት ችለናል፡፡ የግብጽ ሹሞች ካይሮ ውስጥ በተደረገ ስብሳባ የኦነግን ባንዲራ ለብሰው ከኦነግ መሪዎች ጋር በመሆን ኦነግን እንረዳለን በሙሉ አቅማችን እንደግፋለን ሲሉ የሰጡት በቪዲዮ የተቀረጸ ይፋ ማረጋገጫ ይሄንኑ ያላቸውን ቁርኝትና በጋራ ሁነው በውስጥ በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የተቀናጀ ሀገር አውዳሚ ሴራ በአደባባይ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የአባይ ግድብን ግንባታ ለማስቆም የተገባቡት ቃል ኪዳን ባለቤቱን የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከዳር ያስቆጣና ያስነሳ ድርጊትም ሆኖአል፡፡ የአባይ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት 100 ሚሊዮን ህዝብ በባለቤትነት የሚመራው በህዝቡ ገንዘብ እየተገነባ ያለ ነው፡፡ በዚህ መሰረታዊ ምክንያት ኦነግም ሆነ ግብጽ የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ የገቡት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መሆኑን በግልጽ ሊያውቁት ይገባል፡፡
ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትሰራ ምንም አይነት አለምአቀፍ እርዳታም ሆነ ብድር እንዳታገኝ ግብጽ ከወዳጆችዋ ጋር በመሆን ከፍተኛ ጫና ስታሳድር ያለማሰለስ ኖራለች፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳከም ማንኛውንም ቀዳዳ በመጠቀም ስትሰራ እንደኖረች የኢትዮጵያ መንግስትም ህዝብም በሚገባ ያውቃሉ፡፡
ኢትዮጵያ የአባይ ውሀ 90በመቶ ባለቤት ሁና ለብዙ ዘመናት ሳትጠቀምበት በድህነት፣ በድርቅና በረሀብ ህዝብዋ እየተጎዳ የኖረች ሲሆን ግብጽ ደግሞ በአባይ ውሀ ከመጠቀምም አልፋ ከብራበታለች፤ በድህነታችንም ሲሳለቁ ኖረዋል፡፡ በቅርቡም የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ለመሆኑ ኢትዮጵያ ድሀ ሀገር ናት አቅም አግኝታ እንዴት የአባይን ወንዝ ግድብ ለመስራት ትበቃለች በሚል በጋዜጦቻቸው ሲሳለቁ ነበር፡፡
የአባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያም የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ ተፈጥሮ ወንዙን በጋራ እንድንጠቀም ያደለችን በመሆኑ በጋራና በፍቅር ልንጠቀምበት ይገባል እኛ እየተጠቀምን የግብጽ ህዝብ ይጎዳ አላልንም፡፡ የግድቡ ግንባታ ግብጽ ልታገኝ የሚገባትን የውሀ ድርሻ አይቀንስም በሚል ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ሁኔታ አቋሟን ለግብጽም ለአለም አቀፉ ህብረተሰብም ገልጻለች፡፡
ግብጽ በዲፕሎማሲው መስክ ፍጹም ሰላማዊ መስላ ብትታይም ከጀርባ በተለያየ መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፣ ሁከት እንዲከሰት፣ በህዝቡ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር፣ በዚህም የአባይ ግድብ ግንባታ እንዲቋረጥ፣ እንዲቆም ስትሰራ ቆይታ ዛሬ ላይ ከኦነግ ጋር የሰራቸው ደባ በአደባባይ ወጥቶአል፡፡
ቀደም ሲል የተለያዩ እርምጃዎችን እንዴት በኢትዮጵያ ላይ እንውሰድ በሚል ሲመክርና አማራጮችን ሲያነሳና ሲጥል የነበረው የግብጽ መንግስት የተሻለ አማራጭ ብሎ ያስቀመጠው የተለያዩ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሀይሎችን ገንዘብ መድቦ በመርዳት በህዝቡ ውስጥ ቁጣና የከረረ ተቃውሞ እንዲነሳ በማድረግ ሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ ውስጥ እንድትገባ በዚህም የግድቡ ግንባታ እንዲቆም ማድረግ ይቻላል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡ አሁን በስራ ላይ እያዋሉት ያለውም ይሄንኑ ነው፡፡
ለዚህ ጉዳይ አስፈጻሚነት በዋነኛነት የግብጽ መንግስት ከጎኑ ካሰለፋቸው ውስጥ ኦነግ፣ ግንቦት ሰባትና ኦብነግ በቀዳሚነት ይገኙበታል፡፡ ኢሳት የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ ሙሉ ወጪው የሚሸፈነው በግብጽ፣ በኩዌትና በኳታር መንግስት እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ግብጽ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ የማሰናከል አላማ ይዛ የምትሰራ ሲሆን ኩዌትና ኳታር ደግሞ የዋሀቢዝምንና የሰለፊን አክራሪ እስላማዊ እምነት በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው ሰርጎ እንዲገባ ለማድረግ በተለያዩ ሽፋኖች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በሽፋን በመጠቀምና በማሰማራት በህዝቡ ውስጥም በመግባት ይህ ቀረው የማይባል ስራ ለመስራት ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህን ስራ ሲሰሩ የነበሩትን ድርጅቶች መንግስት ቀደም ባሉ አመታት ከሀገር ለቀው እንዲወጡ አድርጎአል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ እያቆጠቆጠ ካለው አክራሪ እስላማዊነት ጀርባ ሳኡዲ አረቢያን ጨምሮ የእነዚህ ሀገራት ስውር እጅ እንዳለበት አከራካሪ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ አክራሪው የእስላማዊ እምነት አራማጅና መሪ በቀጥታም በእነሱ የሚረዳው ጃዋር መሀመድ ኦሮሚያ ለሙስሊም ኦሮሞዎች ብቻ በሚል ሲቀሰቅስ እንደነበረና ከእነሱ ውጪ ያለውን በሜንጫ እንደሚቀሉ በአደባባይ ሲናገር እንደነበረም ይታወቃል፡፡
ይህ ለአመታት ውስጥ ውስጡን በስውር ሲሰሩበት የቆዩት በሀገር ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ የማስነሳት ሴራ ከጀርባው የተለያዩ ተዋናዮች ያሉበት ሲሆን ዛሬ በህዝቡ በኩል የተነሱትን የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ፣ የሙስና ወዘተ ችግሮች ተቃውሞና የመብታችን ይከበርልን ጥያቄን መስመሩን በማሳት የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳካት ሲሉ ጠልፈውት ይገኛሉ፡፡ ህዝብ በሀገሩ ህልውናና ደህንነት ጉዳይ ከማንም ጋር አይደራደርም፡፡ በህዝቡ የተነሳውን ተገቢ ጥያቄ ህዝብና መንግስት የሚፈቱት የውስጥ ጉዳይ ነው፡፡ ለውጪ ሀይሎች ስውር አላማ በርና ቀዳዳ መክፈት እንደሌለበት አሁን ህዝቡ በሚገባ ተገንዝቦታል፡፡
ይልቁንም በኢንቨስትመንትና በተለያዩ ስራዎች ስም ኢትዮጵያ ውስጥ ህጋዊ ፈቃድ አግኝተው በመግባት በሽፋን የስለላ ስራ እየሰሩ፣ ሰዎችም እየመለመሉ፣ ገንዘብም እየረጩ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ምክንያት በሆኑት የተለያዩ የግብጽ መንግስት ድርጅቶች ካምፓኒዎች ወዘተ የሌሎቹንም ጭምር የመፈተሽ፣ የማጣራትና የመመርመር ብሎም ህጋዊ ፈቃዳቸውን የማምከኑ ስራ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ በዚህ በኩል ሰፊ ከፍተት አግኝተው ሰፊ ስራ ለመስራት ችለዋል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡
ዜጎችን በቅርብ የማግኘቱ፣ በድርጅታቸው ውስጥ ቀጥሮ የማሰራቱ ለተለያየ ስራ የመጠቀሙ ነገር በይደርና በቸልታ የሚታለፍ አይሆንም፡፡ በኢንቨስትመንት ስም በተያዙ እርሻዎች በገነቡዋቸው ፋብሪካዎች ውስጥ በቀጠሩዋቸው ዜጎቻችን ውስጥስ ምን ሲሰሩ ነበር የኖሩት? ብሎ መፈተሽ የጉዳዩን ስር ለመጨበጥ ያስችላል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰው የመንግስትና የህዝብን ሀብትና ንብረት የማውደም፣ ብዙ ሺህ ዜጎችን ከስራ የማፈናቀል ሴራ ባለቤቶች እነዚሁ ከጀርባ ያሉ ጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች የመሩት መሆኑ ዛሬ ላይ እውነቱ ገሀድ ወጥቶአል፡፡
ህዝቡ ተቃውሞ ቢያሰማም ለራሱና ለቤተሰቡ የሚጠቅመውን ሰርቶ እንጀራ የሚያገኝበትን ድርጅት ተቋም አያቃጥልም፡፡ ተጎጂው ከነቤተሰቡ እራሱ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በየቦታው ከከተማ ከተማ በመለስተኛ ጭነት መኪናዎች ተጭነው በመዘዋወር ንብረት የማውደም ወንጀል የሚፈጽሙት ሰዎች ድርጊቱን በሚፈጽሙበት ከተማ ባሉ ነዋሪዎች የማይታወቁ ናቸው፡፡ ይሄ ስልታቸው መሆኑ ነው፡፡
ከአንዱ ወደሌላው ቦታና ስፍራ በማይታወቁበት ከተማ በመሄድ ቀድሞ በጥናት በደረሳቸው መረጃ መሰረት ጥፋቱን እንደሚፈጽሙ የሚሳፈሩበትን መኪና እንዳይለይ ሙሉ በሙሉ ከከተማውና ከፍተሻ ኬላዎች ውጭ አርቀው በማቆም ድርጊቱን ከፈጸሙ በኃላ በእግራቸው ርቀው በመጓዝ ተሳፍረው ወደሌላ ከተማ እንደሚሄዱ ከአስር እስከ አስራ አምስት በሚደርስ አነስተኛ ቡድን የተደራጁ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ንብረቱን፣ ሀብቱን፣ የሚሰራበትን ድርጅት ነቅቶ የመጠበቅና ከውድመት የመከላከል ሀላፊነት የሀዝቡና የህዝቡ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ መልኩ የመከላከል፣ አስቀድሞ የመጠበቅ ስራ መሰራት ያለበትም በህዝቡ ነው፡፡ ሁሉም ቦታ ፖሊስ ላይኖር ይችላል፡፡ ከተፈጠሩት ክስተቶች የተቀሰሙ ልምዶችና የተገኙ በርካታ ትምህርቶችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው።
የአደጋ ዝግጁነትና የመከላከል ትምህርት በድርጅቶች፣ በፋብሪካዎች፣ በእርሻ ቦታዎች ወዘተ በሰፊው ማስተማር፣ በቋሚነት በፈረቃ የራሳቸውን 24 ሰአት ጥበቃ በየድርጅታቸው እንዲያደርጉ ማድረግ፣ በገበያ ላይ በብዛት ስለሚገኙ ከሌሉም ከአስመጪ ካምፓኒዎች ጋር በመነጋገርና በመስመጣት የጥበቃ ካሜራዎችን በማይገመቱ ቦታዎች ላይ መትከል ችግሩን ለመቅረፍ አማራጭ መንገዶች ናቸው፡፡
በኢኮኖሚ ሳቦታጅ ስሌት የየአካባቢውንም ሆነ በአጠቃላይ የሐገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሽመድመድ የውጭ ሀይሎች የሀገር ውስጥ ወኪሎቻቸውን በመጠቀም የሚያደርጉት ሴራ ሊመክን የሚችለው በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ የውስጥን ችግር በውስጥ በመፍታት ለውጭ ሀይሎች ምንም ቀዳዳና ክፍተት ባለመፍጠር ሀገርን የመጠበቅና የመከላከሉ የጋራ ሀላፊነት የመንግስትም የህዝብም ነው፡፡
ባጠቃላይ በሀገርና በህዝብ ሀብት መውደም ህዝብም ሀገርም ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ ከውድቀት ውጪ የሚመጣም የሚገኝም ለውጥ የለም፡፡ በሀገር ንብረትና ሀብት መውደምና መቃጠል የሚስቀው የሀገርን ምንነት ያልተረዳ ጅል ሰው ብቻ ነው፡፡ ይስቃል ጅሉ ሰው እንዲሉ፡፡