የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት

                              

የኢፌዴሪ መንግስት ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን (State of Emergency) በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 93 ላይ በተጠቀሱት ድንጋጌዎች መሰረት አውጇል። የዚህ አዋጅ አነሳሽ ምክንያት የኢትዮጵያን ዕድገት ማየት የማይሹና ሀገራችንና ህዝቦቿ ወደ ነበሩበት የድህነት ታሪክ ተመለስው እንዲገቡ ፍላጎት ያላቸው ሀገራትና ኃይሎች ከሀገራችን አሸባሪዎችና አንዳንድ ፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ጋር ለጥፋት ተቀናጅተው በመስራት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በፈጠሩት ሁከት ሳቢያ የዜጎች ህይወት በመጥፋቱ፣ አካል በመጉደሉና ንብረት በመውደሙ ብሎም ሀገራችን ወደ ትርምስ እንዳትገባና የጀመርነው ፈጣን ልማትና ፍትሐዊ የህዝብ ተጠቃሚነት ደብዛው እንዳይጠፋ ነው። ችግሩን በመደበኛው የህግ አግባብ መፍታትና መከላከል ስላልተቻለም ነው—አዋጁ እንዲወጣ የተደረገው። እናም ሀገሪቱ ወደ ለየለት ብጥብጥና ዝርፊያ ከመግቧቷ በፊት፣ እኛም ሀገር አልባ ዜጎች እንዳንሆን የአዋጁ መተግበር የግድ ብሏል።

እርግጥ በማንኛውም ሀገር ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው፤ ሀገሪቱ የሚያጋጥማትን በወቅቱ የሚያጋጥማትን ችግሮች ፈጣን መፍትሔ ለመስጠት እንዲቻል በማሰብ ነው። በስራ ላይ ያሉት መደበኛ አሰራሮች የተፈጠረውን ችግር መቋቋም ሲያቅታቸው አዋጁ እውን እንዲሆን ይደረጋል። በዚህም የተፈጠረውን ችግር ተቆጣጥሮ  ሀገሪቱ ከተደቀነባት ግልፅና ወቅታዊ አደጋ (Clear and present danger) ለማውጣትና ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀልበስ እንዲቻል የአዋጁ እውን መሆን አስፈላጊ ይሆናል።

ታዲያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሀገራችን ውስጥ ብቻ የተደረገ አሊያም ከመንግስት መዳከም ጋር የሚታወጅ ተደርጎ መታየት ያለበት አይመስለኝም። ምዕራባዊያኑም ቢሆኑ ሀገራቸው ውስጥ አስቸጋሪ ክስተት በሚፈጠርበት ወቅት ይህን አዋጅ ያወጣሉ። እዚህ ላይ ሁለት አብነቶችን ማንሳት ይቻላል— የፈረንሳይንና የአሜሪካን ሁኔታ። እ.ኤ.አ በ1958 የተረቀቀው የፈረንሳይ ሪፐብሊክ ህገ-መንግስት አንቀፅ 16 ለሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የተለየ ስልጣን ይሰጠዋል። ይህ ስልጣንም ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሁለቱ ምክር ቤቶችና ከህገ-መንግስት ካውንስል ጋር በመመካከር፤ የሪፐብሊኩ ተቋማት፣ የህዝቡ ነፃነት፣ ሉዓላዊ የግዛት አንድነት አነደጋ ላይ በሚወድቁበት ጊዜ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን ለመወጣት አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥምና ህገ-መንግስታዊው የመንግስት የስልጣን ተዋረዶች ተግባራቸውን በትክክለኛ መንገድ እንዳያከናውኑ ሲደናቀፉ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው አካላት ጋር በመመካከር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የማወጅ ስልጣን ይሰጠዋል።

ይህ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌም በሪፐብሊኩ ህገ-መንግስት አንቀፅ 36 ላይ በግልፅ ተመልክቷል። በመሆኑም አዋጁ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወታደራዊ ተቋማት የፖሊስን የፀጥታ አጠባበቅ ስራ የመረከብ፣ እንደ መሰብሰብና የማንኛውንም ግለሰብ ግላዊ ይዞታ በቀንም ይሁን በማታ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የመበርበር፣ የፕሬስ ቅድመ-ምርመራ የማድረግንና የተለያዩ ትዕይንቶችንና ምልክቶችን የማገድ…ወዘተ. የመሳሰሉ መሰረታዊ የነፃነት መብቶችን የመገደብ፣ ለመደበኛው የሀገሪቱ ህግ ተገዥ የማይሆኑ ግለሰቦችን የማባረር ወይም በሪፐብሊኩ የግዛት ወሰን ውስጥ የመኖር መብት የሌላቸውን ሰዎችን ከሀገሪቱ የማስወጣት ስልጣንን የሚያካትት ነው።

እንደሚታወቀው ፈረንሳይ በዋነኛነት ለሚታወቁ ለሶስት ጊዜያት በግብረ-ሽበራ ተግባር ተመትታለች። ሀገሪቱ በመጀመሪያው የተቃጣባትን የሽብር ተግባር ለመከላከል የፀረ-ሽብርተኝነት ህግን በማሻሻል ጉዳዩን ለመቀልበስ ሞክራለች። ለጥቆም ለሁለተኛ ጊዜ በሀገሪቱ ርዕሰ መዲና ፓሪስ ውስጥ በጂዎች ሆቴል ላይ የደረሰውና ለ137 ሰዎች ህይወት መጥፋትና ለበርካታ ንብረት መውደም ምክንያት በሆነው የሽብር ጥቃትን ለመቀልበስ ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ገቢራዊ አድርጋለች።

በዚህ አዋጅ ቀደም ሲል በሪፐብሊኩ ህገ መንግስት በአንቀፅ 16 እና 36 ላይ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመተግበር የሽብር ተግባሩን ለመቀልበስ ሞክረዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስከ ቅርብ ለአንድ ዓመት ፀንቶ ከቆየ በኋላ፤ በቅርቡ ተነስቶ ነበር።

ሆኖም ልክ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በሶስተኛው ቀን ሶስተኛው የሽብር ተግባር በባህር ዳርቻ አካባቢ እየተዝናኑ በነበሩ የሀገሪቱ ዜጎች ላይ በመፈፀሙ፤ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ወደ ቦታው መልሰውታል። በዚህም ሳቢያ የፈረንሳይ ሪፐብሊክና ህዝቦቿ በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ይገኛሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካም በፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብልዩ ቡሽ የስልጣን ዘመን ወቅት በተፈፀመው የመስከረም 9/11 የሽብር ጥቃት ተከትሎ፤ ሀገሪቱ “7463” የተሰኘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አውጥታለች— ከዛሬ 16  ዓመታት በፊት። ይህ አዋጅም ከትኝሽዬው ቡሽ የስልጣን ዘመን ወቅት በየዓመቱ እየታደሰ መጥቶ እስከ ዛሬው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ የመጨረሻው የስልጣን ዘመን ድረስ ዘልቋል። እናም ኦባማ ከአንድ ወር በፊት ለ16ኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አራዝመውታል።

ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሀገራቸው የአሸባሪነት ስጋት ተጋርጦባታል በሚሉት ሀገር ውስጥ በራሳቸው ውሳኔ ጦራቸውን የማዝመት፣ በማንኛውም ጊዜ የሀገሪቱን ብሔራዊ ዘብ (National Guard) የመጥራት፣ የአዋጁን ማንኛውንም ክፍል የሚቃረኑ ህጎችን የማገድ፣ ያለ ፈቃደኝነት ጡረታ የመውጣት ወይም ከፍተኛ መኮንኖችን ከጦሩ እንዳይለቁ የማድረግ እንዲሁም ያለተገደበ ቁጥር ያላቸውን አዳዲስ ባለ አንድና ባለ ሁለት ኮከብ ጄኔራሎችን (ብርጋዲየር ጄኔራልና ሜጄር ጄኔራሎችን) የመሾምና የከፍተኛና የመስመራዊ መኮንኖችን የማዕረግ ዕድገትና ቁጥር የሚገድብ ህጋዊ አካሄዶችን የማንሳት ስልጣንን የሚሰጥ ነው። እናም ልክ እንደ ፈረንሳይ ሁሉ፤ አሜሪካም የብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ትገኛለች።

እንግዲህ ከእነዚህ የፈረንሳይና የአሜሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር፤ ሁለቱም ሀገራት የህዝቦቻቸውን ህይወትና ንብረት ለመታደግ ብሎም የሀገራቸውን ህልውና ከጥቃት አድራሾች ለመከላከልና ያጋጠማቸውን ወቅታዊ አደጋ ለመቀልበስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ገቢራዊ እንደሚያደርጉ ነው። በሀገራችን ውስጥም የተደረገው ይኸው ነው። ምንም ዓይነት አዲስ ነገር የለውም። እናም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት፤ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከት ምክንያት የሰው ህይወት ማለፉ፣ አካል መጉደሉና ንብረት መውደሙ ለአዋጁ መውጣት አስፈላጊነት ምክንያት ሆኗል።

እርግጥ ያለፈውን አንድ ዓመት የሀገራችንን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ስንመለከት፤ ዓመቱ የፖለቲካ ችግሮች የተስተዋሉበት መሆኑ አይካድም። በአማራና በኦሮሚያ አካባቢዎች ውስጥ የሀገራችንን ዕድገት የማይፈልጉ እንደ ግብፅ ተቋማት ያሉ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያ በአሸባሪነት ከሰየመቻቸው ቡድኖችና ከጥቂት የዲያስፖራ ፅንፈኞች ጋር በማበር ሰላማችንን በማወክ ልማታችንን እንዳናከናውን የተፈፀመው ተግባር ሁነኛ ማሳየ ነው።

በእነዚህ ኃይሎች የውጭና የውስጥ ቅንጅታዊ ተግባር ምክንያት በኢሬቻ በዓልና እርሱን ተከትሎ በተከናወኑ የሁከት ተግባሮች የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል፣ አካልም ጎድሏል። በኦሮሚያ ክልል የተፈፀመውን ውድመት ብቻ ብንመለከት እንኳን ከ50 በላይ የሚሆኑ ፋብሪካዎች ወድመዋል። እንዲህ ዓይነቱ የሰዎችን ህይወት የመቅጠፍና የሀገሪቱን ሃብቶች በኃይል የማውደም ተግባር፤ የሽብርተኞችና ሀገራችን እያስመዘገበች ባለችው ልማት ደስተኛ ያልሆኑ ኃይሎች እንጂ የጤነኛ ተቃውሞ ፍላጎቶች ሊሆኑ አይችሉም።

እነዚህ ሽብርተኞችና የውጭ ሃይሎች ይህን ፀረ-ኢትዮጵያ ተግባራቸውን እንደሚቀጥሉ ስለሚታወቅም፤ ድርጊታቸው የሀገሪቱንና የህዝቦቿን ደህንነት ብሎም የመንቀሳቀስና ሃብት የማፍራት ህገ-መንግስታዊ መብትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ከዚህ ባለፈም ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንገስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አሸባሪዎቹና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ፈፃሚዎቻቸው በእስካሁኑ የውድመት ተግባራቸው ካስመዘገቧቸው ሪከርዶች ለመገንዘብ የሚከብድ አይመስለኝም።  

በዚህም ሳቢያ ህገ-መንግስቱ አንቀፅ 93 መሰረት ሀገሪቱ ላጋጠማት ችግር ፈጣንና ወቅታዊ መፍትሔ ለመስጠት እንዲቻል በማሰብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማወጅ አስፈልጓል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ኮማንድ ፖስት የአዋጁን አፈፃፀም ይመራል። እርግጥ በአንድ ሀገር ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት በርካታ ጉዳዩች ከግምት ውስጥ ይገባሉ። ሁሉም መብቶች ሊከለከሉ አይችሉም። ሁሉም መብቶችም አይፈቀዱም። አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ አንዳንድ መብቶች ላይ ገደብ ሊጣል ይችላል። ውጭ በሚገኙ የሀገራችን አሸባሪዎችና የሀገር ውስጥ መልዕክት ተቀባዩቻቸው አማካኝነት የተፈጠረውን ሁከትና ብጥብጥ ያባብሳሉ ወይም የሀገሪቱን ህገ-መንግስታዊ አንድነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ በሚባሉ መብቶች ላይ ገደብ መጣሉ አይቀርም። 

እናም ከዚህ አኳያ ምንም እንኳን የአዋጁን ሙሉ ይዘት በዚህ አጭር ፅሑፍ ለማብራራት ባይቻልም፤ ሰሞኑን በመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከተሰጡ መግለጫዎች በመነሳት ገደብ የተደረገባቸውን ዋና ዋና ጉዳዩችን ለአንባቢዎቼ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። አንድ አዋጅ የሚወጣው ተፈፃሚ እንዲሆን በመሆኑ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተለያዩ አካባቢዎች በይፋም ሆነ በድብቅ በህዝቦች መካከል መቃቃር፣ ጥርጣሬንና ግጭትን የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን ይከለክላል። እንዲሁም በህዝቦችና ሃይማኖቶች መካከል ግጭትና መቃቃር የሚፈጥሩ ፅሑፎችን ማዘጋጀትና ማሰራጨት ብሎም ትዕይንቶችንና ምልክቶችን ማሳየትና መተግበርንም ያግዳል። የህዝብንና የሀገርን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ እንደሚጥሉ በኮማንድ ፖስቱ የታመነባቸው ማናቸውም የመገናኛ ዘዴዎች ሊዘጉ ይችላሉ።

እርግጥ አዋጁ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተፈፃሚነት ያለው ቢሆንም፤ እንደየአስፈላጊነቱ በልዩ ሁኔታ አዋጁ እንዲተገበርባቸው የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የመሰብሰብ፣ የመሰለፍና፣ የመደራጀት መብቶችም ሊታገዱ ይችላሉ። በሁከት ብጥብጥ ተግባር መሳተፉ የተጠረጠረና የተሳተፈ ማንኛውም ግለሰብ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር እንዲውል ይደረጋል። እነዚህ ግለሰቦች ትምህርት ይሰጣቸዋል፤ በህግ አግባብ መጠየቅ ያለባቸውም እንዲጠየቁ ይደረጋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዕውን እንዲሆንባቸው በኮማንድ ፖስቱ የወሰኑት አካባቢዎች የግለሰቦችን መኖሪያ ቤትና መኪና ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ መበርበርና መፈተሽ ይቻላል። ግለሰቦችን አስቁሞ ስለማንነታቸው መረጃ መጠየቅም ይቻላል። ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የሰዓት እላፊ ባይታወጅም፤ በኮማንድ ፖስቱ ወደፊት ለህዝብ በሚገለፁ አካባቢዎችም የሰዓት እላፊ ሊታወጅ ይችላል።

በአዋጁ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል አደጋ የተጋረጠባቸውንና አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ መንገዶችንና ተቋማትን የመዝጋት እንዲሁም ሰዎች በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡና ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ የማዘዝ ተግባር ሊከናወን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም አወጁ ገቢራዊ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ዜጎች ህጋዊ ፈቃድ ቢኖራቸውም የጦር መሳሪያ ይዘው እንዳይነቀሳቀሱ፣ ተቀጣጣይ ነገርና ስለት ወይም እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ሊከለከሉ ይችላል። 

እዚህ ላይ ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ የተመጣጣኝ ርምጃ አፈፃፀም ይመስለኛል። ተመጣጣኝ ርምጃ ማለት ለአንድ ለተከሰተ ወቅታዊ ሁነት እንደ ጉዳዩ ስፋትና ጥልቀት የሚሰጥ ምላሽ ነው። ከዚህ አኳያ አዋጁ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስራ መከላከል ላልተቻለ ጉዳይ ተመጣጣኝ ርምጃ እንደሚኖር ይገልፃል። በመሆኑም በአዋጁ አፈፃፀም ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ሊፈጠሩ የሚችሉና በመደበኛው አሰራር ህግን ማስከበር ካልተቻለ ተመጣጣኝ ርምጃው ከሁኔታው ስፋትና ጥልቀት አኳያ እየተመዘነ ገቢራዊ ይሆናል።

እንደሚታወቀው የአዋጁ አስፈፃሚዎች የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌዴራልና የክልል ፖሊስ አካላት እንዲሁም ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ናቸው። እዚህ ላይ ከ“ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች” በስተቀር፣ የተጠቀሱት የፀጥታ አካላት በግልፅ ስለሚታወቁ፤ “ሌሎቹን የፀጥታ ኃይሎች” ማወቁ ተገቢነት ይኖረዋል። ለአንዳንድ ወገኖች የተሳሳተ ትርጓሜ ከመዳረግም የሚያድን ይመስለኛል።

በመሆኑም “ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች” ማለት በየአካባቢው የሚገኝ የሚኒሻ ኃይል፣ ከመደበኛው የግብርናም ይሁን ሌላ ስራቸው ሳይነጠሉ በየገጠሩ የፀጥታ ተግባርን የሚያከናውኑ እንዲሁም ሀገሪቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስትሆን እንድትጠራቸው ትችል ዘንድ በተለያዩ ወቅቶች ያሰለጠነቻቸው የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል (National Reserve Force) አባላትና በመንግስታዊም ይሁን መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የጥበቃ አባላት ናቸው። እነዚህን የፀጥታ ኃይሎች በአንድ የዕዝ ሰንሰለት ውስጥ በማስገባትና ቀጥተኛ ትዕዛዝ እንዲያገኙ በማድረግ ለአዋጁ አፈፃፀም ተግባራዊነት እንዲሰሩ ይደረጋል።     

እርግጥ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአዋጁ አፈፃፀም ወቅት ዜጎች በህገ-መንግስተ የተጎናፀፏቸው ሰብዓዊ መብቶችና በቪየና ኮንቬንሽን ላይ የሰፈሩት የዲፕሎማቲክ መብቶች እንደማይጣሱ አረጋግጠዋል። ለዚህም የአዋጁን አፈፃፀም የሚከታተል አካል እንደሚቋቋም አስታውቀዋል። ይህ ዕውነታ የሚያሳየን ሀገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ብትሆንም በተቻለ መጠን የዜጎቿን ሰብዓዊ መብት ለመጠበቅና ለዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የምትገዛ መሆኑን ነው። እናም ሀገራችን በአዋጁ የስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ነበረችበትና በዓላም አቀፉ ማህበረሰብ ወደምትታወቅበት የሰላም ተምሳሌትነት እንድትመለስ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ትብብር ማድረግ ይኖርበታል።

በመሆኑም በቅድሚያ ሁሉም ዜጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበር አለበት። ለጥቆም ለአዋጁ ተፈፃሚነት ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል። አዋጁን የማያከበርና ለተፈፃሚነቱም ከኮማንድ ፖስቱ አባላት ለሚቀርብለት የድጋፍ ጥያቄ የማይተባበር ማንኛውም ግለሰብ በአዋጁ መሰረት ቅጣት ይጣልበታል። ያም ሆኖ ግን ጉዳዩ ሀገርን ከውጭና ከውስጥ አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎች የጥፋት ተልዕኮ የመታደግ ብሎም ዕድገታችን ያስኮረፋቸውን አንዳንድ የውጭ ሀገራትን የእጅ አዙር ሴራ መከላከል በመሆኑ ሁሉም ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት የሚኖርበት ይመስለኛል።

መቼም የትኛውም ሀገር ወዳድ ዜጋ  በእነዚህ ኃይሎች ሰላሙ እንዲደፈርስ፣ ማናቸውም ህገ-መንግስታዊ መብቶቹ ተነጥቀው የስርዓት አልበኞች መፈንጫ ሆኖ ህይወቱን፣ ሃብቱንና ንብረቱን እንዲያጣ ብሎም ሀገር አልባ ሆኖ በትርምስ ውስጥ እንዲኖር አሊያም በጎረቤት ሀገር ውስጥ የጥገኝነት ህይወትን እንዲገፋ የሚፈልግ አይመስለኝም።

እናም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበርና ተፈፃሚነቱን መተባበር ማለት እነዚህን መጥፎ ክስተቶች በስድስት ወራት ውስጥ ገትቶ በተለመደው ሰላማዊ የህይወት መስመር ውስጥ መግባት ነው። ይህን ዕውን ለማድረግም ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውንና በቀጣይ በኮማንድ ፖስቱ የሚሰጡ ተከታታይ ማብራሪያዎችን በአንክሮ በመከታተል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል እላለሁ።